THE BIG INTERVIEW WITH EDILU DEREJE
በማናጅመንት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተርስ ተመርቋል፡፡ አሁን ደግሞ በኮተቤ
ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ማኔጅመንት ማስተርሱን እየተማረ ነው፡፡ 1ኛ
ሴሚስተር ጨርሶ ወደ 2ኛው ሴሚሲተር የዞረው 4 የትምህርት አይነተቶች በሙሉ ኤ
በማምጣት አራት ነጥብ ይዞ ነው፡፡ በእግር ኳስ ሜዳዎች በሚወርዳቸው ስኬታማ
ሸርተቴዎቹ ይታወቃል ኢትዮጵያ ቡና በ2003 የሊጉን ዋንጫ ሲያነሣ አምበል ሆኖ
ዋንጫውን የተቀበለው እርሱ ነበር….እድሉ ደረጄ፡፡ በቅርቡ የአሰልጣኞች ስልጠና እድል
አግኝቶ ወደ ስፔን ባርሴሎና ያቀናል ከዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ሰፋ ያለ ቆይታ
ለቀረበለት ጥያቄ ከከፍተኛ የራስ መተማመን ጋር ሆኖ ምላሹን ሰጥቷል፡፡
ሀትሪክ፡- እግር ኳስ መጫወት የጀመ ርከው በገጠመኝ ወይስ በአላማ?
እድሉ፡- በጣም የማስታውሰው 7 አመት ሲሞላኝ እናቴ ትምህርት ቤት
ለማስመዝገብ ስትፈልገኝ ያገኘችኝ አዲስ ባንክ ሜዳ ላይ ነው፡፡ እዚያ ይገኛል ብለው
ነግረዋት አግኝታኝ ይዛኝ ወደ ት/ቤት ወሰደችኝ፡፡ ሁሌ የሚገርመኝ ሜዳ መገኘቴን ነው
የማውቀው፡፡ በክለብ ደረጃ መጫወት የጀመርኩት በ1990 ለመብራት ኃይል ሲ ቡድን
በመጫወት ነው፡፡ ለምርጫ ከመጣው 1000 ሰዉ መሀል ወደ 30 ሰው ለመያዝ
ችለናል፡፡ ምርጫው ላይ የዋናው ቡድን አሰልጣኝ ጋሼ ሀጎስ ደስታ መጥተው ያዩ ነበር፣
በመጨረሻም 30 ቀርተን ሳለ መልካዋከና ለዝግጅት የሚሄደው ታውቋል፡፡ እኔ
ዴልፒየሮና ገዙ ትምህርት ስለነበረን እንጂ ከዋናው ቡድን ጋር ልምምድ እንድንሰራ ተወስኖ
ነበር በወቅቱ የሲ ቡድን አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- ከዚያ በኋላ ያለው የእግር ኳስ ህይወትህ እንዴት ቀጠለ..?
እድሉ፡- በተጨዋችነት ዘመኔ የምጫወትበት ቦታን በተለምዶ 4 ቁጥር ይሉታል
የተከላካይ አማካይ ቦታን ከልጅነቴ ጀምሮ ስለምወደው እዚያ ነበር የምጫወተው
በመብራት ኃይል ተሰላፊነቴ ግን ተመላላሽ ቦታ ላይ ነበር የምጫወተው፡፡ በዚያ ወቅት
ቦታው ላይ ሙሴ ንፍታሌም፣ ሚጣ፣ ጩናና ሀብታሙ አይረን ፋታ የማይሰጡና እድሉን
የማታገኝበት ጊዜ ነበርና ተስፋ ቆረጥኩ… በ1992 መልካዋከና ክረምት ላይ ስሄድ
ለ3ኛ ተከታታይ አመት ነበርና እድል የማይሰጠኝ ከሆነ ምን አደርጋለው ብዬ አስቸግሬ
በእህል መኪና ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ ነገር ግን ማንም አያውቀኝም ነበርና ክለብ
አጣሁ… በኋላ ግን ታክሲ ማህበር፣ አየር መንገድ፣ ባንክ… እያልኩ ትልቅ ስም
ያገኘሁበትን ኢትዮጵያ ቡናን ተቀላቀልኩ፡፡ አየር መንገድና ባንክ ሁለት ሁለት አመት፣
መብራት 3 አመት፣ ታክሲ ማህበር 1 አመት ኢትዮጵያ ቡና 6 አመት፣ መድን 2 አመት
ከዚያ የካ ክፍለ ከተማ 6 ወር ተጫውቼ የእግር ኳስ ህይወቴ ተጠናቋል፡፡
ሀትሪክ ፡-ወርቃማ የተጫወትነት ዘመኔ የምትለው መቼ ነው?
እድሉ፡- በክለብ ደረጃ ኢትዮጵያ ቡና በ2003 ዋንጫ የወሰደበት ጊዜ ነበር ያኔ
የቡድኑ አምበል በመሆኔ ስኬታማ አመቴ ነበር፡፡ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ደግሞ በ1998
ሩዋንዳ ላይ የተዘጋጀውን የሴካፋ ዋንጫ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እየተመራን ባለድል
የሆንበትን አልረሳም በ1997 በአሰልጣኝ አስራት ኃይሌም ጊዜ ተመርጬ በጉዳት
ወጣው እንጂ ያኔም ባለድል እሆን ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- የማትረሣው ገጠመኝ አለህ?
እድሉ፡- (ሳቅ) ሁለት ገጠመኝ ልናገር… ትዳር እንዲያዝኩ 4 ኪሎ ግንፍሌ ነበር
የምኖረውና አምባሳደር ጋር ታክሲ ይዤ እየሄድኩ ታክሲው ውስጥ ሁለት የቡና ደጋፊዎች
እያወሩ ነው ወሬያቸው ስለቡና ነው እገሌ እንዲህ ነው እንትና ግን እንደዚህ ማድረግ
አለበት እያሉ ያወራሉ፡፡ አንደኛው ድንገት በርሱ እይታ ጥሩ አልነበርኩም መሰለኝ “ያ
እድሉ የሚባለው ነው እንጂ ለርሱ ሲባል አመቱን ሙሉ ሀምሌ እና ነሀሴ ይሁንለት እንዴ
ብሎ ሲናገር በሳቅ ሞትኩ ለካ ሸርተቴ አወራረዴን ለማውራት ነው መቼም አልረሳውም…
ደጋፊዎቹ ሳያዩኝ ወረድኩ አንዴ ደግሞ ቡራዩና ኒያላ ቡራዩ ላይ ሲጫወቱ እኔ የኒያላ
ተጨዋች ነበርኩ የኛ አሰልጣኝ ኮከቤ ነበር፡፡ ገና 20 ደቂቃ እንደተጫወትኩ ተመታሁና
ወጣሁ፡፡ ከተወሰነ ደቂቃ በኋላ ዳኛው መጥቶ ኮከቤን በቀይ ካርድ አስወጣው ቡራዩ ሰው
ከቦህ እየገፋህ በቅርብ ርቀት ሆኖ ነው የምንጫወተው፡፡ የት ልውጣ ይላል ኮከቤ… ዳኛው
ደግሞ የማውቀው ነገር የለም ውጣ ብያለው ውጣ ይለውና ኮከቤ ከሰው መሃል ሲቆም
በአጋጣሚ ኩርባ ነገር ላይ ነው የቆመው እንዲይውም እዚህ ላይ ነው የሚሻለው ብሎ
ሲናገር የሳኩትን አልረሳውም፡፡ ከህዝቡ ወጣ ሲል ከፍ ያለ ቦታ ስላገኘኮ ነው እዚህ
ይሻላል ያለው፡፡
ሀትሪክ፡- ከደጋፊ ጋር እየተጋፉ የደጋፊዎቹ ትንፋሽ እየተሰማህ መጫወት አይከብድም?
እድሉ፡- በዚህ አይነት መልኩ ከተነሣ ብዙ ነገር ማንሣት ይቻላል በጣም ከባድ ነው
ለእግር ኳስ የማይመች ብዙ ነገር አለ፡፡ ለአንድ ተጨዋች በሚሊዮን ብር እየከፈልክ
(ፕሪሚየር ሊግም፣ ሱፐር ሊግም ሆነ 1ኛ ሊግ) ብዙ ያወጣሉ፡፡ ያቺን ሜዳ
ለማስተካከልና አጥር ለመስራት ቢበዛ እንኳን 500 ሺህ ብር አይፈጅም ይህን
ለማስተካከል የኒውክለር ሳይንስ አይጠይቅም፡፡ ፈቃደኝነትና ለኳሱ ማሰብን ብቻ
ይጠይቃል እንጂ ከባድ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ የትኛውም ክልልና ቦታ ብትሄድ ተመልካች
አለ፡፡ ይሄ ትልቅ አቅም ነው ዳኛ መደብደብ ሜዳዎችን አለማጠር መስተካከልና
መታረም የሚችሉ ናቸው፡፡ ሜዳ ተዘጋጅቶ ህብረተሰቡም በነፃነት ኳስ መመልከት
እንዲችል፣ ዳኛውና ተጨዋቾቹ ትክክለኛ ከለላ አግኝተው ውድድርቹም በካሜራ
እየተቀረፁ ግጥሚያዋቹ ቢካሄዱ ትልቅ እድል ይፈጥራል፡፡ ኳሳችን እድለኛ ነው
የሚወደድና በዛ ያለ ተመልካች ያለው ስፖርት ነው፡፡ ደብረብርሃን ከነማን ይዤ አፋር
ሰመራ 11 ኪሜ ርቀት አፋር ዱብቲ የምትባል ከጅቡቲ 2 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ
- ማሰታውቂያ -
የምትገኝ ከተማ አለች፡፡ በ50 ሴንቲ ግሬድ ሙቀት ላይ ዳባ አፋርና ደብረብረሃን ሲጫወቱ
በጣም ብዙ ህዝብ ተገኝቷል፡፡ ከተጠቀምንበት ሰፊ እድል አለን፡፡
ሀትሪክ፡- በ2003 ኢትዮጵያ ቡና ሻምፒየን የሆንበትን ዘመን አስታውሰኝ?
እድሉ፡- እግር ኳስ የቡድን ውጤት ነው፡፡ አምበል መሆኔና 6 አመት እንደመቆየቴ
ዋንጫ ለመውሰድ ከጫፍ ደርሰን ያጣንባቸው አመታት ልምድ ነበረኝ በተቻለኝ መጠን
ቡድኑን ለማስተባበር ጥሪያለሁ፡፡ ተጨዋች እርሰ በርስና ከአሰልጣኝ ጋር አሰልጣኝ ደግሞ
ከአስተዳደር ክፍሉ ጋር በሚፈጠር ቅሬታና ግጭቶች እንዲሁም በሌሎች ውጫዊ
ምክንያቶች ዋንጫ ያጣንባቸው ጊዜያቶች ነበሩ፡፡ ያኔ ግን ሜዳ ላይ በነበረኝ አስተዋፅኦ
ከአመቱ 30 ጨዋታዎች ያልተሰለፍኩት 180 ደቂቃ ወይም 2 ጨዋታ ላይ ብቻ ነበር፡፡
አንዱን በፍቃደኝነት ሌላውን ደግሞ በህመም ነበር ያልተጫወትኩት…. ከፍተኛው
ሪከርድ የኔ ነበር፡፡ በወቅቱ ለኔ ክብር ሰጥተውኝ ስለነበር የነበሩት ተጨዋቾች በጋራ
ሁሉም ስታፍ በአንድ አላማ መቆም መቻላችን እኛና ደጋፊው ጋር የነበረው ስሜት ወደ
ሻምፒዮንነት ለመሄድ አስችሎናል ያ ጊዜ ለእኔም ሆነ ለኢትዮጵያ ቡና ልዩ ጊዜ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- ቡና ዋንጫ ባነሳ በወራቶች ውስጥ አንድ ደጋፊ መሞቱን ሰማው… ነበራችሁ
መረጃ?
እድሉ፡- አዎ በጣም የሚያሳዝን ገጠመኝ ነበር… ዶሮ ማነቂያ (ፒያሳ) ተወልዶ ያደገ
አንድ ደጋፊ ላይ የገጠመውን ነገር ምን እንደምለው አላውቅም፡፡ ቡና ዋንጫ ወስዶ
ብሞትም አይቆጨኝም ይል ነበር፡፡ ሰኔ 2003 ላይ ዋንጫ ወስደን የካቲት 2004 ላይ
የደጋፊው ህይወት አለፈ ምን እንደምል አላውቅም… በቤ/ክ አንድ የሚባል ነገር አለ…
ነፍስ ገዳይዋን ታውቃለች ይባላል.. የርሱ ነፍስ ትነግረው ነበር ብዬ አስባለው ይሄ ታሪክ
መቼም አይረሳኝም፡፡
ሀትሪክ፡- ላንተ በ2003 የኢትዮጵያ ቡና ኮከብ ማን ነበር?
እድሉ፡- እግር ኳስ የሁሉም አባላት የጋራ ድምር ውጤት ነው ባይ ነኝ፡፡ እንደ
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ኮከቡ ዳዊት እስጢፋኖስ ነበር፡፡ ለኔ ግን ምንያህል ተሾመ ልዩ
ነበር፡፡ 9 ጎል አግብቷል ብዙ ጎል የሆኑ ኳሶችን በማቀበል የበላይ ነበር፡፡ ኮከብ ተጨዋች
ተብለው ይመረጣሉ የሚል ግምት ካገኙት ተጨዋቾች አዳነ ግርማና ጌታነህ ከበደ ጋር
የተጠበቀው ምን ያህል ነበር በወቅቱ ኮከብ የተባለው አዳነ ግርማ መሆኑ ቅሬታ
አስነስቷል የቡና ደጋፊዎች ሳይቀሩ ኮከብ መባል ያለበት አሉላ ግርማ ነው ይሉ ነበር…
የምርጫውን ሂደት ለማስተካከል ሲስተሙን ማስተካከል ብቻ ይበቃል አሁንም
እውነተኛውን የአመቱ ኮከባችንን የምንመርጥበት ሲሲተም የለንም ሲስተሙ ላይ
ለውጥ ቢኖር ምርጫው ደስ የሚል ስሜት የሚፈጥርና ተቀባይነት የሚያገኝ ይሆናል ብዬ
አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ቡና በሊጉ ዋንጫ ካጣ 7 አመት ሞላው…የዋንጫ ድሉን
መድገም ያልቻለው ለምን ይመስልሃል?
እድሉ፡- የሜዳ ላይና ከሜዳ ውጪ ያሉ ነገሮች ይመስሉኛል… ሜዳ ላይ ያለው ስናይ
ጊዜያዊ ድል ይጠበቃል፡፡ ድል ደግሞ ሂደትን ይጠይቃል 7 አመት ቡና ዋንጫ አልበላም
ስለዚህ የአመራሮቹን ቆም ብሎ ማሰብ ይጠይቃል፡፡ ለችግሩ መፍትሔ ስትፈልግ ሜዳ ላይ
ካለው ችግር ይልቅ የቢሮን ችግር ለመፍታት ካስቀደምክ መፍትሔ አይመጣም…
መቅደም ያለበት የሜዳ ላይ ችግርን ቶሎ ማስወገድ ላይ ነው፡፡ የሜዳ ላይ ችግር
ከአስተዳደራዊ ችግር ቅድሚያ መሰጠት አለበት፡፡ መቶ አለቃ ፈቃደ ለምንድነው ሪዛይን
ያደረገው? የሜዳ ላይ ውጤት መጥፋቱ የፈጠረው ተፅዕኖ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ልቀቁ
የተባሉ አሰልጣኞችና አስተዳደሮች ነበሩ መነሻውኮ የሜዳ ላይ ውጤት መበላሸት ነው፡፡
አስተዳደራዊ ነገር ሁለተኛ ጉዳይ ነው… ሜዳ ላይ ቡና የሚታወቅበት የራሱ የሆነ ፍልስፍና
አለው እነ ጋምብሬ ቡቡ አሰግድ.. ከነርሱ በፊት የነበሩትን ተጨዋቾች ስታይ ቡና የራሱ
የሆነ ቀለም እንደነበረው ትረዳለህ፡፡ ደጋፊው የመጣውም ለዚህ ነው… ያ ማለት ግን አሁን
ያለው ደጋፊ ያንን ብቻ ይፈልጋል ማለት አይደለም ውጤታማና አዝናኝ ጨዋታ
የሚጫወተውን ኢትዮጵያ ቡናን መፍጠር ይቻላል ባይ ነኝ፡፡ በኔ ፍልስፍና ከተጫወትክ
ታሸንፋለህ ውጤት ታመጣለህ ብዬ አምናለው እየተጫወትክ ማሸነፍ በአንድ ድንጋይ ሁለት
ወፍ እንደማለት ነው… ይሄ ዋናው ነው ሁለተኛው እኔ የማኔጅመት ተማሪ ነኝ የስፖርት
ማኔጅመንትን እየተማርኩ ነው የቡና ስትራክቸር ብዙ አስተማማኝ አይደለም… 39 የቡና
የጠቅላላ ጉባኤ አባላት፣ መቶ አለቃ ፈቃደን ጨምሮ.. በቡና ላኪዎችና ባለ ድርሻ
አካላት ተወክለው መጥተው ነው ቡድኑ ባለቤት የሆኑት፡፡ የደጋፊው ሚና ደግሞ ዝቅተኛ
ነው በፊት በፊት በፋይናንስ ደረጃ ደጋፊው ዝቅተኛ ብር ነበር የሚያወጣው አሁን ግን
ከፍተኛ ገንዘብ እያወጣ ነው…የኢትዮጵያ ቡና አስቸጋሪ የሚባሉ ዘመናት ያለፉ
ይመስለኛል ይህን እድል ከተጠቀመበት ምርጥ የድል ዘመናት ይኖረዋል ባይ ነኝ፡፡
ስትራክቸሩ በአክሲዮን ደረጃ ደጋፊው ባለቤት የሚያሆንበት መንገድ መፈጠር አለበት…
አሁን ያለው ስትራክቸር ቢስተካከል ይመረጣል፡፡
ሀትሪክ፡- የቡና ደጋፊዎች ጫናን ተቋቁሞ ማሰልጠን ከበድ አይልም?
እድሉ፡- ፍላጎቱ ብዙ ነው፡፡ ቡና ውስጥ ያለው ፍላጎት ብዙ ቢሆንም ግን አንድ ነገር
ያስተሳስራቸዋል፡፡ ጥሩ አሰራርና ጥሩ ቡድን ካለ ሁሉንም ወደ አንድ መስመር ማምጣት
ይቻላል፡፡ ቡና ውስጥ ያለው ብዙው ፍላጎት በቡድኑና በአሰራሩ ላይ ድክመት ሲጨመርበት
ነገሮች ሰፋ ይላሉ ትርምስ ይፈጥራልና ጥሩ አስተዳደር ከጥሩ ቡድን ጋር ከተቀዳጀ
ጠንካራውን ቡናን መፍጠር ይቻላል፡፡ የስፖርት አስተዳደርም ከሌሎች አስተዳደራዊ
አካሄድ የሚለይበት መንገድ አለው፡፡ በተለያየ ምክንያት የሚሰባሰብ ግሩፕ የለውም፡፡
ከተለያዩ ቦታዎችና ሁኔታዎች የመጡ አባላትን በአንድነት ማስተዳደር ከሌላው
አስተዳደራዊ አካሄድ የተለየ ያደርገዋል፡፡ በተጨማሪም ለይተህ ሂድ የምትለው አካል
የለም፤ የመጣውን ሁሉንም ያቅፋል፡፡ በተጨማሪ ሌላው የሚለየው ስሜታዊነት
ይንፀባረቅበታል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሲጫወት አንዱ አሳምኖ
ቢያሸንፍም የተሸነፈው ቡድን መቀበል አይፈልግም አያምንም ስሜታዊነት ያጠቃዋል
ሽንፈቱንም ውጫዊ ያደርገዋል… ይሄ ደግሞ ከሌላው ማኔጅመንት የተለየ አካሄድ
እንደሚያስፈልገው ያሳያል፡፡ ለዚህም መፍትሔ የሚሆነው በእውቀት የተደገፈ አመራርና
ጠንካራ ቡድን መፍጠር ብቻ ነው፡፡ የክለቡ ደጋፊዎች ፍላጎቶች ጠንካራ ቡድንን ከተገነባና
ውጤት ከመጣ ይሸፈናል ብዬ አምናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-በተከላካይ አማካይ ቦታ ፋውለኛ ነው አይ አግሬሲቭ ነው የሚል ክርክር
ይነሳልና የቱነው አንተን የሚገልፅህ?
እድሉ፡- በተፈጥሮዬ ቦታውን እወደዋለሁ፡፡ ፋውለኛ ሳልሆን አግሬሲቭ የሚለው
ይገልፀኛል፤ በአመት ውስጥ ትልቁ ያየሁት ካርድ ብዛት 5 ቢጫ ያየሁበት ብቻ ነው፡፡
በታሪኬ ያየሁት 1 ቀይ ካርድ ያውም በ2 ቢጫ ያየሁት ነው፡፡ በ17 አመት ውስጥ 1 ቀይ
ብቻ ነው ያየሁት ይሄም ፋውለኛ አለመሆኔን ያሳያል፡፡ በኢንተርናሽናል ደረጃ በአምስት
አመት ውስጥ አንድም ቢጫ ካርድ ተመዞብኝ አያውቅም፡፡ እግር ኳስ የሚፈቅደውን
አጨዋወት እንጂ ሆን ብዬ ሰው አልጎዳም፡፡ በአጨዋወት ደረጃ የስቴቨን ጄራርድ አድናቂ
ነኝ፡፡ ሀገር ውስጥ ግን ተፅዕኖ የፈጠረብኝ አንዋር ያሲን (ትልቁ አንዋር) ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በተጨዋችነት ዘመንህ በተለይ በቡና ተሰላፊነት ፍትህ ተጓድሏል የምትልበት
ጊዜ ነበር?
እድሉ፡- በደንብ ነበር፡፡ በ1998 ጥር 21 ቀን ከጊዮርጊስ ጋር ስንጫወት 20ኛው
ደቂቃ ላይ ተቋርጠ፡፡ በነጋታው ፎርፌ ተብሎ 50ሺህ ብር እንድንከፍል ተደረገ፡፡ መነሻ
የቅጣቱ ሕግ ከየት መጣ? ካሜራ የለ አልተቀረፀ ምንም ምክንያት ሳይገለፅ በዶ/ር
አሸብር ወ/ጊዮርጊስ ዘመን በደል ደርሶብናል፡፡ የቡና ተጨዋች ዳንኤል ቀይ ካርድ አየ
ያለመግባባቱ መነሻው እርሱ ነው፡፡ ነገር ግን ለዋናው ቅጣት መነሻ መሆን አይችልም፡፡
ተጨዋቹ ቀይ ካርድ አይቶ ወጣ.. በቃ፡፡ ጨዋታው 0ለ0 ነው ደጋፊው መሃል በተነሣ
ግጭት ቡድናችንን ለመቅጣት ምክንያት መሆን ግን አልነበረበትም… የምርጫ 97 ግለት
በነበረበት ሰዓት ብዙ ነገሮች ወደ ረብሻ የሚያመሩበት ጊዜ ላይ ነበር…….. ሌላው
ደግሞ ወንጂ ላይ ከወንጂ ጋር ስንጫወት ከፍተኛ ብጥብጥ ነበር፡፡ በሲኦል ውስጥ
ተጫውቶ 3 ነጥብ እንደማምጣት ቁጠረው፡፡ ደጋፊ ረበሸ ርምጃ ግን አልተወሰደም ዳኞችና
ደጋፊዎች እኛን ጨምሮ በችግር ነው የወጣነው በኮሚሽነሩ ሪፖርት ታግዘው ሜዳውን
ማገድ ነበረባቸው ነገር ግን የተወሰደ ርምጃ አልነበረም በሳምንቱ ጊዮርጊስ ሄዶ ሲጫወት
45ኛ ደቂቃ ላይ ረብሻ ተነሣ፡፡ ቀሪው 45 ደቂቃ በገለልተኛ ሜዳ መካሄድ ነበረበት
አላለቀማ፡፡ ነገር ግን ቀጣይ ጨዋታዎችን አዳማ ላይ እንዲያካሄድ በጨዋታው ፎርፌ
እንዲቀጣ ተወሰነ፡፡ እኛ በትግል ያመጣነውን 3 ነጥብ ጊዮርጊስ በጎን አገኘ፡፡ በ1998
ላይ አመቱ ሲያልቅ በጊዮርጊስ የተበለጥነው በ1 ነጥብ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን
ከመከላከያ፣ ሙገርና ጊዮርጊስ ያደረግነው ጨዋታ ተሽሮ በ3ቱም ፎርፌ ተሰጥቶብናል፡፡
በትክክለኛ መንገድ ቀድመው ወንጂ ተቀጥቶ ተቃራኒ ሜዳ ላይ ከጊዮርጊስ ጋር
እንዲጫወት ቢደረግ ነጥብ ሊጥል ይችል ነበር.. እነዚህን ስታይ አድልዎ እንደተደረገ
ወይም አደረጉብን ብለን እንድንጠራጥር አድርገውናል፡፡
ሀትሪክ፡- በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ስንት አመት ተጫወክ? እነማን አሰለጠኑህ?
እድሉ፡- ከ17 አመት በታች፣ ከ20 አመት በታች ዋናው ብሔራዊ ቡድን 5 አመት
ያህል ተጫውቻለው… አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ፣ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፣ አሰልጣኝ
አብርሃም መብራቱ፣ አሰልጣኝ አብርሃም ተ/ሃይማኖት፣ አሰልጣኝ ከማል አህመድ፣
አሰልጣኝ ሀብቴ.. ኧረ ብዙ ናቸውኮ፡፡
ሀትሪክ፡- እነኚህ ሁሉ በ5 አመት ውስጥ ካሰለጠኑህ በኃላፊነት የሚቆዩት ለወራት ያህል
ነው በለኛ?
እድሉ፡- (ሳቅ በሳቅ) አንድ ገጠመኝ ላውራህ.. እኔና ደብሮም ከ20 አመት በታች
ዋና እና ምክትል አሰልጣኝ ሆነን ሰርተናል፡፡ እስቲ ያሰለጠኑን እንቁጠር ተባብለን
ስንቆጥር 10.. ስንቆጥር 20 ደረስን እያልን ስንሄድ 30 አሰልጣኞችን ቆጠርን
ሣንጨርሰው እርሱም ጀርመን ሄዶ.. ጠፋ.. ድጋሚ አልቆጠርናቸወም፤. እየጨመሩ
ሄዱኮ (ሳቅ በሳቅ)
ሀትሪክ፡- ስትገናኙ ከ30 ልትቀጥሉ ነው?
እድሉ፡- (ሳቅ በሳቅ).. በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ይገርማል አሠልጣኝ ንጉሴ ደስታ፣
አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ፣ አሰልጣኝ ጋርዚያቶ… ኧረ ይቀጥላል፡፡ 2 አመት የቆየና
ትልቁ ብዙ ጊዜ የሰራ በኖርማላይዜሽን ኮሚቴ ጊዜ የነበረው አሰልጣኝ አብርሃም
ተ/ሃይማኖት ይመስለኛል፡፡ በቅርብ ጊዜ ደግሞ በ2005 የአፍሪካ ዋንጫ የአሰልጣኝ
ሰውነት ቢሻው ቆይታ ረዘም ያለ ጊዜ እንዳስቆጠረ አውቃለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- በአሰልጣኝነት እነማንን አሰለጠንክ?
እድሉ፡- በስራው ሶስት አመት ሞልቶኛል ቡና ስገባ ቡድን መሪ ሆኜ ነው የገባሁት፡፡
በመቀጠል የዋናው ቡድን ም/ል አሰልጣኝ… ከ20 አመት በታች አሰልጣኝ፣ እንደገና
የዋናው ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ሆንኩ.. እንዲሁም ጊዜያዊ አሰልጣኝ ተብዬ ዋናውን
ቡድን 5 ወይም 6 ጨዋታዎችን መርቻለሁ፡፡ ደብረብርሃን ከነማን ሳሰለጥን ደግሞ
ውላችን በሊጉ ማቆየት ነበርና 7ኛ ደረጃ ይዘን ጨረስን… ከአዲስ አበባ ወጥቼ ማሰልጠኔ
ለኔ ጥሩ ልምድ ሆኖኛል፡፡ በነበረኝ ቆይታ አሁን ድረስ ስሜን የሚያስጠራ ስራ ሰርቼ
መጥቻለሁ፡፡ ብዙ ወጣቶችን አስፈርሜያለው፡፡ ወደ 4 የሚጠጉ የደብረ ብርሃን
ወጣቶችን፣ ከአዲስ አበባ ዋናው ቡድን መግባት ያልቻሉ በፕሪሚየር ሊጉም ሆነ በሱፐር
ሊጉ ያሉትን አስገብቻለው ውበት ያለው ኳስ እንደመውደዴ በሠራሁት ቡድን ተመልካቹ
ተደስቷል፡፡ ዋናው ቡድኑን ማቆየት የሚለውን አሳክቻለሁ የሲ ላይሰንስ አለኝ፡፡ አጫጭር
ኮርሶችን ወስጃለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- በሲ ላይሰንስ ፕሪሚየር ሊግን ማሰልጠን ይቻላል?
እድሉ፡- የሚከለክል የተቀመጠ ነገር የለም፡፡ ፌዴሬሽኑ ላይሰንስ ይኑርህ እንጂ
ማሰልጠን አይከለክልም፡፡ ቡናንኮ በሲ ላይሰንስ ነው ያሰለጠንኩት… እዚህ ላይ አንድ
መናገር የምፈልገው ጉዳይ አለኝ፡፡ በአሜሪካ ቢ ላይሰንስ መውሰድ ከፈለክና ኳስ
ተጨዋች ሆነህ ፊፋ በሚያውቀው ሊግ ውስጥ ከተሳተፍክ፣ 3 አመት ለብሔራዊ ቡድን
ከተጫወትክ ላይሰንስ መውሰድ ይቻላል፡፡ ሲ ላይሰንስ ለመውሰድ በፕሮፌሽናል ደረጃ
በክለብ 3 አመት መጫወት ከቻልክ ይፈቀድልሃል፡፡ እኛ አገር ግን የ17 አመት ልምድ
ክሬዲት አይሰጠውም፡፡ ንግድ ቤት ለመጀመር ላይሰንስ እንደምታወጣው፡፡ የእግር ኳስ
አሰልጣኝ ለመሆን ሳትቸገር ልምድህ ታይቶልህ ሊሰጥህ ይገባል ባለፈው ጊዜ
ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱና ኢንስትራክተር መኮንን ኩሩ ባሉበት በተጠራው
ስብሰባ ላይ ይህንን አመለካከቴን ገልጬ እነሱም ተቀብለውት በቀጣይ ህጎቹ ላይ
ለማካተት እንደሚሞክሩ ቃል ገብተዋል፡፡
ሀትሪክ፡-ከሀገር ውስጥ የአንተ ምርጡ አሰልጣኝ ማነው?
እድሉ፡- ከሀገር ውሰጥ አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ ቡድን ሲሰራ ልዩ ነው፡፡ ምርጥ
ብቃት አለው በባንክ ተሰላፊነቴ ኢንተርናሽናል ጨዋታ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወትነው
እኛ ነን የጥሎ ማለፍና የአሸናፊዎች አሸናፊን ዋንጫ ወስደን በ1997 ከግብፁ አረብ
ኮንትራክተር ጋር ተጫውተናል፡፡ በባንክም ምርጥ ታሪክ አለኝ ያ ታሪክ ደግሞ
የገ/መድህን ኃይሌ ነው… መድንም ከሱፐር ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ካደገ በኋላ 8ኛ ሆኖ
ጨርሶ በሊጉ መቆየቱን ካረጋገጠ በኋላ ነው ከክለቡ የተሰናበትኩት፡፡ እዚህ ላይ ለሁሉም
አሰልጣኞች ክብር አለኝ ከልጅነቴ ጀምሬ ካሳደገኝ ከጋሽ ሀጎስ ጀምሮ ለሁለም አሰልጣኞች
ክብር አለኝ፡፡ ወፍጮ ቤት ሄዶ ዱቄት ለምን ነካኝ አይባልም… እናም ካገኘኋቸው
አሰልጣኞች በሙሉ የወሰድኩት ነገር አለ፡፡
ሀትሪክ፡- በቀጣይ ግንቦት ወደ ስፔን ባርሴሎና ልትጓዝ ነው… እድሉ እንዴት ተገኘ?
እድሉ፡- ትምህርት ቤቱ ኤም ቢ ፒ ስኩል ይባላል በግል እዚያው ባርሴሎና የራሱ
ሜቶዶሎጂ ያለው በወጣቶች እድገት ላይ የሚሰራ ት/ቤት ለመማር እድሉን አግኝቻለው፡፡
በወጣቶች ላይ የኤክስፐርት ኮርስ ነው ስለ ጨዋታ ማንበብ፣ በየጊዜው የሚያድግ ሳይንስ
እና የወጣቶች ልማት ላይ ያተኮራል፡፡ 130 ክሬዲት ሀወር አለው፡፡ ሰአቱን ብታይ ዲግሪና
ማስተርስ በለው በዲግሪና በማስተርስ ደረጃ ይህን ያህልም አትወስድም በ3 ዓመት
ወይም በ4 አመት የሚያልቅ ኮርስ ቢሆንም በ1 ወር እንዲያልቅ ተደርጎ ጧት ማታና
በሳምንት ከ25 ሰዓት በላይ እናሳልፋለን፡፡ ትኩረታችንን እዚያው አድርገን የምንወስደው
ኮርስ ነው… በግሌ ተፃፅፌ ያገኘሁት እድል ነው፡፡ በተፈጥሮዬ በተለያዩ አልባሌ በሚባሉ
ቦታዎች ላይ አልገኝም በቀን ከ5-7 ሰዓት በኢንተርኔት ላይ አሳልፋለው… የተለያዩ
ሙከራዎችን አደርጋለው… ቡና እያለው ሳምሪ የምትባል የክለቡ ፀሐፊ ነበረች ለተለያየ
ኤምባሲ ደብዳቤ ስለማፅፋት ሴቭ ብቻ አድርጊው ሁሌ ስመጣ ከምትፅፊ የኤምባሲውን
ስም ብቻ ብንቀይረው ይሻላል እላት ነበር ሆላንድና ስፔን ሄዶ መማር ፍላጎት ነበረኝ፡፡
በእርግጥ ጉዳዩ ሪስክም ነበረው 500 ዩሮ ልኬያለው በተለየየ መንገድ ት/ቤቱ ትክክል
መሆኑን አረጋግጬ ብሩን ላኩላቸው ኤምባሲ ቪዛ ቢከለክለኝ ኖሮ ብሩ ይቀልጥ ነበር
በመጨረሻ ግን ተሳክቶልኝ ቪዛዬን አግኝቻለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-ወጪውንስ በተመለከተ የረዱህ ወገኖች አሉ?
እድሉ፡- ከቲኬት አንፃር ከተቻለ ስፖንሰር ቢያደርገኝ ወይም ዋጋውን ቢቀንስልኝ ብዬ
አየር መንገድን ሰሞኑን እጠይቃለው… ኢትዮጵያ ቡናን በጣም አመሰግናለሁ 80 ሺህ
ብር (ክለቡ 40 ሺህ ብር ደጋፊ ማህበሩ 40 ሺህ ብር) ሰጥተውኛል፡፡ የኢትዮጵያ እግር
ኳስ ፌዴሬሽንንም ጠይቄ 15 ሺህ ብር ሰጥተውኛል… የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ አባል
የሆነው አቶ ዮሴፍ ተስፋዬም በግል 10 ሺህ ብር ሰጥተውኛል ከዚህ ውጪ ኤፍሬም
(ባህሬን)፣ ኢንጂነር የሱፍ አቶ መንግሥቱ የኢትዮጵያ ቡና የመፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴም
ካላቸው ብር ላይ ቀንሰው ሰጥተውኛል እነሱንም አመሰግናለሁ ፈለቀ ሞሼና ወርቁ
ሺረጋን በተጨማሪም ትልቅ ድጋፍ እያረገልኝ ያለውን ሰይፈ ውብሸትን ከልብ
አመሰግናለሁ… በቀጣይ ሌሎች ወገኖችም ድጋፍ እንደሚ ያደርጉልኝ ተስፋ አደርጋለሁ
በሃሳብም በገንዘብም በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ ያደረጉልኝን በሙሉ አመሰግናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ወጣቶች ላይ መስራትህና ያልከውን መፈፀምህ አስደስቶሃል?
እድሉ፡- አዎ…. የአጭር ጊዜ የስልጠና ህይወ ት ነው ያለኝ፡፡ የተ ናገርኩትን ግን
ፈፅሜያለው ከቡና 8 ተጨዋቾች ይዤ ለደብረብርሃን እንዲጫወቱ አድርጊ ያለሁ….
ከ20 አመት በታች ሆነው ቡናን መቀላቀል ያልቻሉ ግን አቅም ያላቸውን ወስጄ ተጠቅ
ሜያለው አንዳንዱ ተስፋ ይቆርጣል ለምን አልተሳካም ብሎ በሊቢያ የሚጠፉምኮ አሉ፡፡
20 አመት ሙሉ ለፍቶ እድል ካጣ ተስፋ ይቆርጣል፡፡
እኔ ይህን ስሜት አውቀ ዋለው በ1992 ከመብራት ኃይል እምቢ ብዬ ስመጣና አዲስ
አበባ ስገባ ኳስ በማቆምና ባለማቆም ውስጥ ሆኜ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን
የንሰሃ አባቴ በአለም ላይ ብትታወቅስ ብለው አበር ታተው ተስፋ እንዳልቆርጥ ሆንኩ እንጂ
ግራ መጋባት ውስጥ የገባሁበት ጊዜ ነበር… በግራ መጋባት ውስጥ ገብተህ ራስህን ሱስ
ውስጥ ልታገኝ ትችላለህ… ከመብራት ከባንክ ተጨዋቾችን ወስ ጃው ደብረብርሃን
ዩኒቨርስቲ ይማር የነበረ ቢኒያም የሚባል ተጨዋች ወስጄ አጫውቻለው 1 አመት
ስለሚቀረው ቀረ እንጂ በብዙ ክለቦች የተፈለገ ተጨዋች ነው…. ወደፊት ምርጥ
እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ በተጨማሪም እዚያው ያሉ ወጣቶችን ይዤ ደብረብርሃንን
ጠንካራ አድረገነዋል፡፡ ለክለቡ ጠንካራ የቡድን ግንባታን ሰርቻለው የራሴን አስተዋፅኦ
አድርጌያለው ብዬ አምናለው፡፡ በአመራር ደረጃ “ወደ ተናገርከው ሂድ” የሚባል አባባል
አለ… በተግባር ወዳልኩት ሄጄ ሰርቻለው የክለብ ኃላፊዎች አሰልጣኞች ተጨዋቹ ሁሉም
ወደተናገረበት መሄድ አለበት ብዬ አምናለው፡፡ የኳሱ ችግር የሚመስለኝ ሁሉም ጋር
ትዕግስት የለም፡፡ ምናልባት የሚገመግመው የፖለቲካ ሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ
ተሿሚው ቴክኒካል ነገሮችን ማየት የማይቻል መሆኑን ያሳያልና መስተካከል አለበት፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ለባለሙያዎች ብዙ እድል መፍጠርም ሆነ መስጠት
አለመቻሉ ያ በሳጫል እነኚህ ሁሉ መስተካከል አለባቸው፡፡
ሀትሪክ፡-የፖለቲካና የዘር ኳስ እንዲጠፋ ምን ይደረግ ትላለህ?
እድሉ፡- የቡናንም ስናነሳ ያልነውን እዚሁ እንደግመዋለን፡፡ የሀገሪቱ ስትራክቸር
ካልተቀየረ ዋጋ የለውም፡፡ የፌዴሬሽኑ አደረጃጀት በ11 ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች
ውክልና ተመስርቶ ነው… የተላከውስ ሰው የማንን ፍላጎት ሊያረካ ነው የሚለውን ስታይ
ጥያቄው ከዚህ ይነሣል፡፡ ሰውየው ለሀገር አሰበም አላሰበም የሚያሰራው ሲሰተሙ
ይመስለኛል ባለሙያው ተሰባስቦ የአመራሩ ውክልና ከፖለቲከኞች እጅ ወጥቶ ከ5-7
ብቻ በሚሆኑ አመራሮች የሚመራ ፌዴሬሽን ቢሆን መልካም ነው ብዬ አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡-ክለቦቻችን በምን መልኩ መደራጀት አለባቸው ትላለህ?
እድሉ፡- ክለቦች የሚመሩት በቦርድ ነው ይላል የፊፋ መመሪያ… ከቦርድ ስር ስራ
አስኪያጅ መሰየሙ ደግሞ የግድ ነው፡፡ ምን አይነት ስራ አስኪያጅ መሆን አለበት
የሚለውም ተቀምጧል ሰፊ የሆነ የእግር ኳስ እውቀትና በትንሹ 10 አመት የሠራ
መሆን አለበት፤ የኮሚዩኒኬሽንና የተግባቦት አቅም ሊኖርው ይገባል፡፡ ከአሰልጣኝ፣
ከተጨዋቾች፣ ከቴክኒክ ዲፓርትመንት አባላት ጋር ሊገናኝ ይችላል ተብሎ ሊያሟላ
የሚገባው ሁሉ ተካቷል፡፡ በኛ ሀገር ግን ይሄ አይታሰብም፡፡ ፕላን አድርጎ ስትራቴጂ ነድፎ
ተግባራዊ የማድረግ አቅም ሊኖረው ይገባል ብሎ ያስቀምጣል… ይህን ስታይ ገና
መሆናችንን ትረዳለህ…የኮሚዩኒኬሽን ክፍሉ ኃላፊ የሚሆነው ባለሙያ ቢያንስ 5 አመት
በጋዜጠኝነት ሊሰራ ይገባል ይላል.. ይሄን የሚያሟላ ስንቱ ነው እነኚህን ሁሉ
መመዘኛዎች ክለቦቻችንን ሊያሟሉና ሊጠናከሩ ይገባል ብዬ አምናለው… አሠራሩ በዚህ
መልኩ ከተቀናጀ ብዙ ነገሮች ይቀየራሉ እነኚህ በሚገባ ካልተዋቀሩ ግን የብሔር ችግሮች
የተባሉ ሁሉ ሊፈቱ አይችሉም፡፡
ሀትሪክ፡- የኳሱ ወጪ በዛ ገቢ ግን የለም…ኳሱ አክሳሪ ነው ለሚሉ ያንተ ምላሽ
ምንድነው?
እድሉ፡- እግር ኳሱ ችግር የለበትም ወጪውም የሚያሰጋ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ አየር
መንገድ ለካፒቴን ከፍተኛ ገንዘብ ይከፍላል፡፡ ክፍያው ከሀገሪቱ ኑሮ አንፃር ካየነው ከፍተኛ
ነው ነገር ግን የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪው የሚያመጣው ገቢ ከፍተኛ መሆኑ
ለካፒቴኑ ለምን ተከፈለ አያስብልም፡፡ የእግር ኳስ ኢንዱስትሪው ግን በኳሱ የኃላፊነት ቦታ
ያሉ ሰዎች መስራት ያለባቸውን ስራ ባለመስራታቸው ከህብረተሰቡ በሚሰበሰብ ግብር
ወደ ኳሱ አምጥተው ህብረተሰቡ ቅሬታ ውስጥ እንዲገባ የሆነው አመራሮቹ በአግባብና
በአግባብ መስራት ባለመቻላቸው ብቻ ነው፡፡ በማርኬቲንግና በፋይናንስ ደረጃ ስራ
ባለመሰራቱ ኢንዱስትሪው ወጪ እንጂ ገቢ እንዳይኖረው መደረጉ ነው ችግር የፈጠረው፡፡
ኢንዱስትሪው ገቢ አምጪ እንዲሆን አመራሮቹ ማሰብ አለባቸው፡፡
ሀትሪክ፡-እስቲ ስለ ትዳርህ እናውራ…?
እድሉ፡- ባለትዳርና የ3 ልጆች አባት ነኝ፡፡ ባለቤቴ የኔነሽ ተስፋዬ ትባላለች
ሁለታችንም የፒያሳ ልጆች ነን፡፡ ሰንበት ት/ቤት ዘማሪ ነበረች ቤተክርስቲያን ነው
የተገናኘነው፡፡ ደብረሊባኖስ በስጋ ወደሙ ነው የተጋባነው፡፡ እግዚአብሔር በፍሬ ባርኮናል፡፡
አንደኛው ልጅ ዘሚካኤል ሁለተኛዋ ልጄ አርሴማ ትባላለች 3ኛው ልጄ ዘማርያም
ይባላል… ብዙ ጊዜ ቤቴን ቀጥ አድርጋ የመራችው ባለቤቴ ናት፡፡ እንዲያውም ዘንድሮ
ያላሰለጠንኩት ብቻዋን ሆና ልጆቼን በማሳደግ ልኖር ለምፈልገው ህልሜ ዋጋ በመክፈሏ
ትረፍ ብዬ ነው… በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናት እፈልጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-ጨረስኩ.. የምታመሰግነው ካለ እድሉን ልስጥህ?
እድሉ፡- ያሰለጠኑኝን አሰልጣኞች በሙሉ አመሰግናለሁ እንደ አባትና መምህር
ስለማያቸው አሰልጣኞቼን አመሰግናለሁ፡፡ ስጫወት ለደገፈኝ ፍቅር ለሰጠኝ የኢትዮጵያ
ቡና ደጋፊ ትልቅ አክብሮት አለኝ… ለመላው የስፖርት ቤተሰብም ምስጋናዬን ማቅረብ
እፈልጋለሁ፡፡