“ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ አብዛኞቹ አሰልጣኞች ይልቅ 100 ፐርሰንት ጨዋ ነኝ ብዬ አምናለሁ”

ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ አብዛኞቹ አሰልጣኞች ይልቅ 100 ፐርሰንት ጨዋ ነኝ ብዬ አምናለሁ”

“ከእግር ኳስ የምሰናበተው ወይ አይበላ ወይ አያስበላ ተብዬ ነው”
አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር /አዲስ አበባ ከተማ/

በስልጠና ህይወት 7 አመታትን አሳልፏል…ጓደኛዬን ለመርዳት ገብቼበት ህይወቴ ሆኗል ሲል ይናገራል..2007 አካባቢ ልደታ በተለምዶ ቢርሞ በሚሰኘው ሜዳ ላይ ፈይሰል አብዱልአዚዝ /ጩኒ/ ከሚያቃቸው ሰዎች ገንዘብ እያሰባሰበ ለታዳጊዎች ሲለፋ አየሁትና ልረዳው ብዬ ተቀላቀልኩት… ከዚያ አንድ አመት ከ8 ወር ካባቢ ለሃረር ሲቲ
ሰራሁና በ2009 መጨረሻ ከአስራት አባተ ጋር ለአዲስ አበባ ምክትል ሆኜ ሰራሁ …ከዚያ 2013 ላይ ዋና አሰልጣኝ ሆኜ እንድሰራ ስራ አስኪያጁ ነጻነት ታከለ ሃላፊነቱን ሰጠኝ … ዋና አሰልጣኝ ሆኜ በሰራሁበት አመት ቡድኑን ወደ ፕሪሚየር ሊግ አሳደኩት ሲል ይናገራል…በርግጠኝነት ይሄ ስኬታማ ሰው ማነው ትሉኛላችሁ ብዬ አልጠብቅም ምክንያቱ የታሪኩ ባለቤት እንግዳችን አሰልጣኝ እስማኤል አቡበከር መሆኑ ግልጽ ነውና… ከዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ያወጋው እስማኤል ለበርካታ ጉዳዮች ምላሹን ሰጥቷል።

ሀትሪክ:- ዋና አሰልጣኝ በሆንክህበት አመት ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማደግ ያለህን ብቃት ከመነሻው አያሳይም..?

እስማኤል:- /ሳቅ/ አዎ ያለኝን አቅም ማሳየት ይችላል ስልጠና ሳሰለጥን የያዝኳቸውን ልጆች ነው አዲስ አበባ ያመጣኋቸው..ጥሩ ጊዜ እንዳሳልፍም ረድተውኛል በማለፋችንም ደስ ብሎናል።

ሀትሪክ:- እስቲ ወደስልጠናው ሳንገባ የተጨዋችነት ዘመንህን አስታውሰን..?

እስማኤል:- ወደ 13 አመት ተጫውቻለሁ…የመጀመሪያው ለሙገር ቢ የተጫወትኩበት ነው ያኔ ለቢ ቡድኑ የተጫወትኩት ለአንድ አመት ከ6 ወር ብቻ ተጫውቼ ወደ ዋናው ቡድን አደግኩ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የተጨዋችነት ዘመኔ ለዋና ቡድን ብቻ የተጫወትኩት ነው ከሙገር ዋናው ቡድን ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተዛወርኩ ነገር ግን ተጎዳሁ ታክሜ ከጉዳት መልክ ለኪራይ ቤት ፈረምኩ

ሀትሪክ:- ኪራይ ቤት እያለህ ለታዳጊና ብሄራዊ ቡድን ተጠራህ..?

እስማኤል:- አዎ ኪራይ ቤት እያለሁ የካቲት ወር ላይ ለተዳጊ ብሄራዊ ቡድን ተመረጥኩ ነሀሴ ደግሞ ለብሄራዊ ቡድን ተመረጥኩ ደስ አለኝ ከኪራይ ቤት ወደ መድን ገባሁ ከመድን በኋላ ወደ ኦማን ሀገር ለሙከራ አቀናሁ እዚያም ብሽሽቴን ተጎዳሁና 6 ወር ይረፍ ተብሎ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሼ ለቅ/ጊዮርጊስ ፈረምኩ ከዚያ ከቅ/ጊዮርጊስ ለአለም ወጣቶች ሻምፒዮና ወደ አርጀንቲና የተጓዘው የጋርዚያቶ ቡድን ላይ ተካትቼ ተጓዝኩ

ሀትሪክ :- ከዚያስ ከአርጀንቲና መልስስ..?

እስማኤል:- አርጀንቲና አንድ አመት ቆየሁ ልመለስ ስፈልግ አቶ አብነት ገ/መስቀል የቲኬቱን ችለውኝ ተመለስኩና ለአንድ አመት በድጋሚ ለቅ/ጊዮርጊስ ተጫውቻለሁ ከጊዮርጊስ መልስ ለመከላከያ፣ለሀዋሳ ከተማ፣ ለጥቁር አባይ ተጫውቻለሁ.. የጨዋታ ዘመኔ የተጠናቀቀው ግን ለኤልፓ ተጫውቼ ነው… 13ቱ አመት ይህን ይመስላል/ሳቅ/

ሀትሪክ:- በ13 አመቱ የተጨዋችነት ዘመን ምርጡ ጊዜህ መቼ ነበር..?

እስማኤል:- የኔ ምርጥ ጊዜ ከመንግሰቱ ወርቁና ንጉሴ ገብሬ ጋር በ1992 የነበረኝ ጊዜ ለኔ ወሳኝና ምርጡ ጊዜ ነበር… ብዙ ሰው ዋንጫ የወሰደበትን ዘመን ምርጡ ጊዜ ነው ሊል ይችላል ለኔ ግን እንደሱ አይደለም ዋንጫ ከወሰድኩባቸው ጊዮርጊስና ሀዋሳ ይልቅ በመንግስቱ ጊዜ የነበረኝ ቆይታን አስበልጣለሁ ምርጥ ስራ እንሰራ ነበር አስገራሚ አቋም ላይ ነበርኩ ወደላይ ወጣሁ የምለው ያኔ ነው ሰውነቴ ፈርጣማ ቁመቴም ረጅም ፈጣንም ነበርኩ በቴስታ ግብ ማስቆጠር ላይ ጎበዝ ነበርኩ አሪፍ አብዶኛ ከመሆኔም በተጨማሪ ኳስ እየገፋሁ ስሮጥ ያለኳስ የሚሮጠውን እቀድም ሁሉ ነበር ያ ጊዜ ነው ለኔ ምርጡ….

ሀትሪክ:- አዲስ አበባ ገና ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ሳያልፍ ለማለፉ ወሳኝ የተባለው ድላችሁ የትኛው ነው..?

እስማኤል:- በዋናነት ማለፋችን የተረጋገጠው ውድድሩ ሊጠናቀቅ አራት ጨዋታ እየቀረው ኢኮስኮን 2 ለ 0 ስንረታ ነው ነገር ግን ከማለፋችን በፊት ወሳኙ ድል በሰባት ነጥብ እየመራነው የነበረውን ዋነኛ ተፎካካሪያችንን አምበሪቾን በ2ኛ ዙር አምስተኛ ጨዋታ ላይ አሸንፈን ልዩነታችንን ወደ 10 ነጥብ ስናሰፋ ነው

ሀትሪክ:- በፕሪሚየር ሊጉና በከፍተኛ ሊጉ መሃል የተጋነነ
ልዩነት የለም የሚሉ አሉ…አንተስ..?

እስማኤል:- እኔም የሰፋ ልዩነት አላየሁም እንደሁም ከፍተኛ ሊጉ ላይ ያሉ ተጨዋቾች ተሯሩጦ በመጫወት በጣም የተሻሉ ናቸው ብዬ አስባለሁ የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ ቀርፈፍ ይላል ተጨዋቾቹ ደግሞ የአዕምሮ አጠቃቀማቸው ከከፍተኛ ሊግ ተጨዋቾች የተሻሉ መሆናቸውን ታዝቤያለሁ

ሀትሪክ:- የከፍተኛ ሊግ ክለቦች ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ሲያድጉ ተጨዋቾቹን አሰናብተው ሌሎች በፕሪሚየር ሊጉ ልምድ ያላቸውን ተጨዋቾች ያስፈርማሉ ለሊጉ አይመጥኑም ማለት ነው…?

እስማኤል:- እኔ ብዙም አይመቸኝም እኛ ቡድን ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ የከፍተኛ ሊግ ተጨዋቾች አሉ በኛ ደረጃ ያለብንን ክፍተት እንዲሞሉ ብለን ያመጣናቸው የፕሪሚየር ሊግ ተጨዋቾች መሃል ደግሞ ብቃታቸው ወርዶ ያልተጫወቱ አሉ የከፍተኛ ሊግን እንቅስቃሴ መቋቋም አልቻሉም ሶስት አመት የለፉም እንዳሉ ምንም ሳያደርጉ ሽልማት የወሰዱ አሉ ለፍተውም የቀነስናቸው አሉ ምክንያቱም መሃልና አጥቂ መስመራችን ላይ ክፍተት ነበረና ይህን ለማስተካከል ቀንሰናል ምንም ማድረግ አልቻልንም እንደ አሰልጣኝ ያለ ተጨማሪ መመዘኛ የተሻለው ይጫወት የምል ነኝ የመጡበትን ሊግ አወዳድሬ አላስገባም ምርጥ ከሆኑ ብቻ ነው የሚገቡት… አንድ ምሳሌ ላሳይ የአዳማው አብዲሳ ፕሪሚየር ሊጉ ላይ 10 ግብ አለው የመጣው ግን ከአርሲ ነገሌ ከዚያ ለገጣፎ ገብቶ አሁን ለአዳማ እየተጫወተ ነው መታየት ያለበት አቅም ነው ተጨዋች ከከፍተኛም ሆነ ከአንደኛ ሊጎች ሊገኝ ይችላል ችግሩ አሰልጣኙም ሆነ ተጨዋቹ እዚያው እዚያው የሚሽከረከር መሆኑ ነው ይሄ መሰበር አለበት የፌስ ቡክ ጎራ ያላቸውን ተጨዋቾች ማየታችን ሊቆም ይገባል ለሀገር አይጠቅምምና መታረም ያለበት ይሄ ነው ብቃት ላይ ያለው ተጨዋች ይሰለፍ ካልክ ዮሀንስ ሳህሌ ከታች መርጦት አሁን ለሀገር ወሳኝ እንደሆነው አስቻለሁ ታመነ በርካቶች ሊገኙ ይችላሉ ከዚህ አንጻር በሊጎቹ ተጨዋቾች መሃልም የሰፋ ልዩነት አለ ብዬ አላምንም።

ሀትሪክ:- እንደ አሰልጣኝ ለተጨዋቾችህ ቅርብ ነህ..?

እስማኤል:- እኔ ስራ ላይ ኮስታራ ነኝ ከዚያ ውጪ ግን ወንድም ነኝ በእድሜ ደረጃ ብዙ ስለማንራራቅ ለመቀራረብ አይቸግረንም ግን የኔና የተጫዋቹ ሚና መታወቅ አለበት ተጨዋቹ ሃላፊነቱ የመጫወት የኔ ደግሞ ተጨዋቹን መርዳት ነው ብዙ ጊዜ ተጨዋቾች ችግራቸውን ለአሰልጣኝ አይናገሩም ይሄ ባህላችን ወደፊት እየተቀረፈ ሲሄድ ለውጥ ይኖራል ብዬ አምናለሁ ስራ ላይና ዲሲፕሊን ላይ ግን ኮስታራ ነኝ/ሳቅ/ ለሙያቸው ክብር ከሰጡ ለህብረተሰቡም ጠቃሚ ይሆናሉ እግር ኳስ የልማት አካል እንደመሆኑ ተጨዋቹ ህብረተሰቡን የሚጥቀም ተደርጎ ለመቀረጽ ዲሲፕሊን ማክበር ይኖርበታል ብዬ አስባለሁ።

ሀትሪክ:- በባህሪይ ቁጥብ ነው የሚል መረጃ አግኝቻለሁና ትስማማለህ…?

እስማኤል:- /ሳቅ/ እግር ኳሱ ላይ ብዙ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች አሉ የኔ ፕርሰናሊቲ እንዲነካ አልፈልግም ፐርሰናሊቲ ያለውና የሚከበርለት ሰው መሆን እፈልጋለሁ ተምሳሌት መሆን አለብኝ ብዬ አስባለሁና ከብዙ ሰው ጋር መነካካት አልሻም መብትና ግዴታዬን አውቄ መንቀሳቀስ እፈልጋለሁ እኛ ሀገር ውስጥ ግሩፕ እያለ ትክክለኛ ነገር ይፈጠራል ብዬ አላምንም በግሩፕ በቲቮዞም አላምንም የፌስቡክ አርበኛና የታይታ ሰው መሆን አልፈልግም በግሌ ግን ብዙ የምረዳቸው ምስኪኖች አሉ የነሱ ዱአና ጸሎት ነው ለዚህ ያደረሰኝ ብዬ አምናለሁ እንዲህ አደረኩ ብዬ መፎከር ግን አልሻም የአደባባይና የፌስቡክ ስራ መስራትም አልፈልግም በዚህ ደግሞ ርካታ ይሰማኛል።

ሀትሪክ:- በአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ እጅ የተቀበላችሁትን ማበረታቻ እንዴት ተቀበልከው..?

እስማኤል:- አዎ በጣም ተደስቻለሁ… የተመዘገበው ድል አስደሰቷቸው የከተማ አስተዳደሩ ሽልማት ማዘጋጀቱ ከክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ እጅም ሽልማት መቀበሌ ትልቅ ደስታ ፈጥሮብኛል ትልቅ ማበረታቻ ሆኖኛል ከሁሉ የተደሰትኩት ከብሩ በላይ የተሰጠኝ እውቅናና ክብር ነው ለከንቲባችንንና ለቦርድ አባላት፣ ለክለባችን ዋና ስራ አስኪያጅ ምስጋናዬን አቀርባለሁ

ሀትሪክ:- ወደ አዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እንለፍና በውድድሩ ላይ መሳተፋችሁ ተጠቃሚ አድርጓችኋል..?

እስማኤል:- የራሳችን ግብ አለን ገና ከተሰባሰብን 11 ቀናችን ቢሆን ነው ሲቲ ካፕ ላይ ላለመሳተፍ ሞክረን ባለመቻሉ ተሳትፈናል ብዙ ክፍተቶች ነበሩ አሁን ነው እየተቀረፉ የመጡት… ኢትዮጵያ ሆቴል የገባነው ገና በቅርቡ ነው ማቴሪያሎች የተሟሉት ተጨዋቾች ፈርመው የጨረሱት ገና አሁን ነው የሜዳ ችግር ነበረብን አበበ ቢቂላ ደግሞ ደጋግሞ ለመስራት ጉዳት ያመጣል በአጠቃላይ ግባችን አዲስ አበባን ማስጠራትና በፕሪሚየር ሊጉ መቆየት ነው… የኔ መለኪያዬ ይሄ ነው በርግጠኝነት አሳካዋለሁ አዲስ አበባ በሊጉ ይቆያል ኢንሽ አላህ…

ሀትሪክ:- በመንፈሳዊ ህይወት ጠንካራ ነህ..? ለአሁኑ ህይወቴ ሚና አለው ትላለህ..?

እስማኤል:- መንፈሳዊ ህይወቴማ ትልቅ አስተዋጽዎ አለው ከሰዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት ውስን የሚሆነውማም ለዚህ ነው በእኔ ዕምነት “የሰጪ እጅ ከላይ ነው” ብዬ አምናለሁ በእግርኳስ ውስጥ ደግሞ በራስ መተማመን እንዳይኖርህ የሚያደርገው ሙሰኛ መሆን ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ አብዛኞቹ አሰልጣኞች 100 ፐርሰንት ጨዋ ነኝ ብዬ አምናለሁ ደግሜ ልናገረው 100 ፐርሰንት…
ያን ያደረገው ደግሞ መንፈሳዊ ህይወቴ ነው ሰዎችን አከብራለሁ ታላላቆቼን ማክበር ተምሬያለሁ መጥፎ ነገር ሲሰራ እቃወማለሁ …

ሀትሪክ:- ከተጨዋቾች ጋር የሚሞዳሞዱ በእገሌ ኤጀንት በኩል መምጣት አለብህ የሚሉ አሰልጣኞች አሉ…አንተስ ንጹህ ነህ..?

እስማኤል:- በፍጹም የለሁበትም 100 ፐርሰንት ከገንዘብና ከሙስና ጋር አልተነካካሁም

ሀትሪክ:- እስማኤል በሙስና ባይታማም ሰዎች ሲጠቀሙ ሲያይ ህገወጥም ቢሆንም ዝም ይላል ይባላል ይሄስ ስህተት ነው..?

እስማኤል:- የሰውን መብት በሚነካ ነገር ላይ አልሳተፍም አንድ ኤጀንት በህጉ መሠረት የሚከፈለው ብር አለ ያንን መክፈል የተጨዋቾች መብት ነው ከዚያ ውጪ የሆነ ተገቢ ያልሆነ ክፍያ ኤጀንቱ ሲጠይቅ ከሰማሁ እቃወማለሁ ተጨዋቹ ግን መብቱን አያስከብርም እኔ ያለሁበት የተጨዋቾች ማህበር መስራች ነኝ ከአስሩ አንዱ ነኝ ለተጨዋቾች መብት እከራከራለሁ ነገር ግን ተጨዋቾች ለመብታቸው አይከራከሩም ማህበሩ ተቋቁሞ መርዳት ማጠናከር ሲኖርባቸው ሲቸገሩ ብቻ ነው የሚመጡት ይሄ ልክ አይደለም ይሄ መታረም አለበት ማህበሩን በሚገባ ደግፈው መጠናከር አለበት ለጥያቄህ መልስ ለመስጠት ያህል ከእግርኳስ የምሰናበተው ወይ አይበላ ወይ አያስበላ ተብዬ ነው እንጂ ከዚያ ውጪ የምሰናበትበት ምክንያት የለም

ሀትሪክ:- አንተ ብለህ ይሁን አይሁን ባይታወቅም ጋዜጠኛም ይሁን ኤጀንት ተጨዋቾች ጋር እየደወሉ ብር አምጣ አሰልጣኙም አለበት የሚሉ አሉ ተብያለሁ…መረጃ አልነበረህም..?

እስማኤል:- ዘንድሮ የሰማሁት ነገር የለም በ2013 ላይ ግን አሁን ለመከላከያ የሚጫወተው ገዛኸኝ በልጉዳ ያኔ ነቀምት ሲጫወት አውቀዋለሁ ልጁ ፈጣንና ጉልበተኛ ጨዋም ነው ቡድን መሪው እሱን ጨምሮ ሌሎች አጥቂዎችን በቴሌግራም ሲልክልኝ ገዛኸኝን መረጥኩና ይፈርም ተባለ ሲፈርም ኤጀንቱና የቡድን መሪው ግንኙነት ነበራቸው ይህን አላውቅም ነበር..ስሰማ ኤጀንቱ ኮቹም ይፈልጋል ብሎ ሊበላ መሞከሩን ስሰማ ምንም የማውቀው ነገር አልነበረም እንዲህ የሚያደርጉ ሊኖሩ ልታማ እችላለሁ እንጂ ያደረኩት ነገር የለም…ይህንን ራሱ ያወኩት ተጨዋቾቹ ሀዋሳ ላይ ኳስ ሲመለከት አግኝቼው ነው…ያኔ ምናለ ቢነግረኝ በወቅቱ ዝም ብሎ ካለፈ በኋላ አወራኝ ይሄን አስታውሳለሁ ከዚያ ውጪ የማንንም ሂሳብ አልነካሁም..። የተባሉትም ጋዜጠኛው ይሁኑ ኤጀንት አላውቅም ተጨዋቾቹም መብታቸውን ማወቅ አለባቸው በእገሌ ኑ ሲባሉ መቃወም አለባቸው እኔ አላልኩም አንድ ትልቅ ተጨዋች ልግባ የሚከፈለውን እከፍላለሁ ብሎኝ ተበሳጭቼ ስልኩን ዘጋሁ ከዚያ በኋላ አንስቼለትም አላውቅም አዲስ አበባ ላይ እንዲህ አይነት ነገር የለም …

ሀትሪክ:- እስቲ ስለ አቡበከር ናስር እናውራ… ምን ያህል እጅህ አለበት..?

እስማኤል:- ሀረር ሲቲ ላይ እያለሁ ክለቡ ታኬታ ሲገዛ ጎድሏቸው ያላገኙ ተጨዋቾች ነበሩ ጫማው ጥራትም አልነበረውም ታዲያ አንድ የቀድሞ ተጨዋች ግርማ ሳህሌን ነግረነው አምስት ታኬታዎች ሰጥቶን ነበረና ሁለቱን የወሰዱት አቡበከር ናስርና ሚኪያስ መኮንን ነበሩ ለግርማ ሰሞኑን እያወራሁት ነበር ያኔ ጫማ የሰጠኸው ታዳጊ ነው የብሄራዊ ቡድን ወሳኝ ተጨዋች የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢ የሆነው እያልኩት ነበር… ልጅ ይወለዳል ሁሉም አሰልጣኝ ደግሞ የራሱን አስተዋጽዎ የሚያደርገው… ያ ኘው ትልቁ ጉዳይ… አሰልጣኝ አጥናፉ አለሙ ጥሩ ቡድን ነው የገነባው..እንደዚኛው ቡድን ግብጽን የረታ ቡድን የለም በደርሶ መልስ 5ለ2 ረቷል…በዚህ ቡድን ውስጥ አቡበከር አልተመረጠም ነበርና ለአሰልጣኝ አጥናፉ አንድ ያላየኸው ምርጥ ልጅ አለ ስለው አምጣው ልየው አለኝ በፖዘቲቭ ስሜት ነው ያለኝና ተደሰትኩ.. አቡበከርን እንዲያየው አደረኩ…ቀጭን ነበር በብዛት ኤም አር አይ የጣለውን ጣለና እነ አቡበከር አለፉ በአንድ ልምምድ ላይ ምርጥ ግብ አስቆጠረ ከዚያ ግብጽን 3ለ1 ሲረቱ ሁለት ግቦችን ማስቆጠር በመቻሉ እድገቱ እየጨመረ መጣ… ድሬዳዋ እያሉ ኢትዮጵያ ቡናዎች ማናገር ጀመሩበዚያ ላይ አቡበከር የቡና ደጋፊ በመሆኑ ሁሉም ነገር ተሰካ የነርሱን ወጪ ለመተካት አቡኪና ሚኪን ለመውሰድ 60ሺህ ብር ከፈሉ..አሁን ኮከብ ባለሪከርድ የሆነ አጥቂ ሆኗል በርሱ ደስተኛ ነኝ።

ሀትሪክ:- አሁንስ ትገናኛላችሁ..?ይደውልልሃል..?

እስማኤል:- እንገናኛለን አዎ /ሳቅ/

ሀትሪክ:- የመጨረሻ ጥያቄ እስቲ ስለትዳርህ አውራኝ..?

እስማኤል:- ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ነኝ። ባለቤቴ ዚያዳ ሻሚል ትባላለች ከጠንካራ ስኬታማ ባል ጀርባ ጠንካራ ሚስት አለች ይባላልና ሚስቴ እንደርሱ ናት
ልጆቼ አቡበከር ፣አብዱልሃኪም፣ ኢስራና መሬም ይባላሉ

ሀትሪክ:- የበኩር ልጅህ አቡበከር የተባለው አቡኪን አስበህ ነው..?

እስማኤል:- /ሳቅ/ ብዙ ጊዜ በኛ ከልጆችህ አንዱን የአባትህ ስም እንዲይዝ ታደርጋለህ አሁን ስሜ እስማኤል አቡበከር ይባላል ከልጆቼ አንዱ አቡበከር ይባላል በዚህ ነው የመጀመሪያ ልጄን አቡበከር ያልኩት እንጂ በተረፈ አቡኪን አይመለከትም
በነገራችን ላይ በእስልምና ውስጥ አቡበከር ታማኝ፣ አዛዥና አማኝ እንደማለት ነው ቤተሰብ ልጆቹ እንዲህ እንዲሆኑ ስለሚፈልግ ስሙን ስለሚያወጣ ነው ስሙ የወጣው…

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport