መነሻ ገጽ መከላከያ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ተካሂደው በዕሁዱ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ የሚፋለሙትን ክለቦች አሳውቋል ።
መከላከያቅዱስ ጊዮርጊስዜናዎች

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ተካሂደው በዕሁዱ የፍፃሜ ጨዋታ ላይ የሚፋለሙትን ክለቦች አሳውቋል ።

አጋራ
አጋራ

በመጀመሪያው ጨዋታ 7 ሰአት ላይ በምድብ 2 አንደኛ ሆኖ ያጠናቀቀውን ጅማ አባጅፋርን በምድብ 1 ሁለተኛ ሆኖ ካጠናቀቀው ባህርዳር ከተማ ያገናኘ ነበር ። የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎችን ጅማ አባጅፋሮች ጫን ብለው በመጫወት የባህርዳር ከተማን ግብ ለመድፈር ጥረት አድርገዋል ።

በአንፃሩ ባህርዳር ከተማዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመመለስ እና ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት ግብ ለማስቆጠር ቢጥሩም በፊት መስመር ላይ የነበረባቸው ክፍተት ግብ ከማስቆጠር አግዷቸው ነበር ።

ባህርዳሮች ኳሱን ተቆጣጥረው ጫና ለመፍጠር ሲሞክሩ ጅማ አባጅፋሮች የሚያገኟቸውን ኳሶች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል በመድረስ ግብ ለማስቆጠር የሞከሩ ሲሆን በዚህም 37ኛ ደቂቃ ላይ በባህርዳር የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ዱላ ሙላቱ ላይ ጥፋት ተሰርቶበት ጅማ አባጅፋሮች የፍፁም ቅጣት ምት አገኙ ። 17 ቁጥሩ ዳዊት ፍቃዱም ፍፁም ቅጣት ምቱን አስቆጠረ ። የመጀመሪያው አጋማሽም በጅማ አባጅፋር መሪነት ተጠናቀቀ ።

የሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚመሩት ባህርዳር ከተማዎች ውጤቱን ለመቀየር ፍፁም አለሙን እና ኒኪማን ቀይረው ወደ ሜዳ አስገቡ ። ሁለቱ ቅያሪዎች በሁለቱም የባህርዳርን የማጥቃት እንቅስቃሴ ቀድሞ ከነበረው የፈጠነ እንዲሆን አድርጎታል ።

በዚህም 68ኛ ደቂቃ ላይ የባህርዳሩ 9 ቁጥር ተመስገን ደረሰ ባስቆጠረው ግብ ጨዋታው 1 ለ 1 ሆነ ። ጅማ አባጅፋሮች በተለይም የሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ የባህርዳር ከተማ ተከላካይ መስመር አለመረጋጋት ተከትሎ ያገኟቸውን የግብ ዕድሎች ሊጠቀሙባቸው አልቻሉም ።

አቻ ከሆኑ በኋላ ተመጣጣኝ ሊባል የሚችል ጨዋታን ያሳዩን ሲሆን ነገር ግን ሌላ ግብ ያስቆጠረ ክለብ አለመኖሩን ተከትሎ አላፊውን ክለብ ለመለየት ጨዋታው ወደ መለያ ምት አመራ ።

አዝናኝ በነበረው የመለያ ምት እስከ 7ኛው ምት ድረስ ሁለቱም ክለቦች ምንም ሳይስቱ ሁሉንም አስቆጥረው የነበረ ቢሆንም 8ኛውን የጅማ አባጅፋር መለያ ምት ዱላ ሙላቱ መቶት በባህርዳሩ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑሪ ተመለሰበት ። በዚህም ባህርዳር ከተማ በመለያ ምት 8 – 7 በማሸነፍ የፍፃሜ ተፋላሚ መሆኑን አረጋገጠ ።

በጨዋታውም ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያሳይ የነበረው የባህርዳሩ ፉአድ ፈረጃ የጨዋታው ኮከብ በመባል የዋንጫ እና የ12,000 ብር ተሸላሚ መሆን ችሏል ።

በዕለቱ ሁለተኛውን የፍፃሜ አላፊ ቡድን ለመለየት የተደረገው ጨዋታ ምድብ 1 አንደኛ ሆኖ ያጠናቀቀውን ቅዱስ ጊዮርጊስን ምድብ 2 ሁለተኛ ሆኖ ካጠናቀቀው መከላከያ ያገናኘ ነበር ። ጨዋታው ቀዝቀዝ ያለ እና ኳሶች ብዙም ወደ ግብ ያልደረሱበት ነበር ።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች ኳሱን ከተከላካይ መስርተው ለመውጣት ሲያደርጉ የነበረው ሙከራ መሀል ሜዳው ላይ ጥቅጥቅ ብሎ እየተጫወተ በነበረው የመከላከያ ቡድን በተደጋጋሚ ይከሽፍ የነበረ ሲሆን ይህም የቅዱስ ጊዮርጊስ ኳሶች በብዛት በተከላካዮቹ መካከል በሚደረግ ቅበብል ብቻ እንዲቆዩ አስገድዷል ።

የግብ ሙከራ ያን ያህል ባላስመከተን ጨዋታ 8ኛ ደቂቃ ላይ ፀጋዬ መላኩ እንዱም 19ኛ ደቂቃ ላይ ሀይደር ሸረፋ ያደረጓቸው ሙከራዎች እና በመከላከያው ግብ ጠባቂ ክሌሞንት ቦዬ የተመለሱባቸው ኳሶች ተጠቃሽ ነበሩ ።

በአንፃሩ መከላከያ የቅዱስ ጊዮርጊስን የጨዋታ ፍሰት በማቋረጥ በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ለማድረስ ቢሞክሩም ይህ ነው የሚባል የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም ። የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽም 0 ለ 0 በሆነ ውጤት ተጠናቀቀ ።

የጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽም ከመጀመሪያው አጋማሽ እምብዛም የተለየ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ባያስመለክተንም በሁለቱም ክለቦች በኩል ወደ ግብ በመድረስ ደረጃ ከመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ነበር ። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ለአጥቂ መስመር ተጨዋቾች የሚላኩ ኳሶች በመከላከያ ተከላካዮች በመመለስ እና ከጨዋታ ውጪ በመሆን ሲበላሹ ነበር ።

በመከላከያ በኩል ከመጀመሪያው አጋማሽ ከነበረው በተሻለ ወደ ግብ ለመድረስ ጥረት ያደረጉ ሲሆን ግብ ማስቆጠር ግን አልቻሉም ነበር ።

በ80ኛ ደቂቃ ላይ የመከላከያው 13 ገናናው ረጋሳ ከራሱ የግብ የሜዳ ክፍል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ያሻገረው ኳስ የቅዱስ ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ባህሩ ጥላሁን ስህተት ሰርቶ ግብ ሊቆጠር የነበረበት አጋጣሚ ተጠቃሽ ነው ። መደበኛው የጨዋታ ጊዜም ከተጨማሪ ደቂቃዎች ጋር ምንም ግብ ሳያስተናግድ እንደ መጀመሪያው ጨዋታ ሁሉ ወደ መለያ ምት አመራ ።

በመለያ ምቱም ከተመቱት አምስት አምስት ምቶች ውስጥ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በረከት ወልዴ ሲስት በመከላከያ በኩል ግን አምስቱንም በማስቆጠር የዕሁዱን የፍፃሜ ጨዋታ ቲኬት መቁረጥ ችለዋል

። በጨዋታውም የቅዱስ ጊዮርጊሱ ተከላካይ ፍሪምፖንግ ሜንሱ የጨዋታው ኮከብ በመባል የዋንጫ እና የ12,000 ብር ሽልማት ተሸላሚ ሆኗል ። ይህም በውድድሩ የጨዋታው ኮከብ ከተሸናፊ ቡድን ሲመረጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሆኗል ።

በሁለቱ ጨዋታዎች ውጤት መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ጅማ አባጅፋር ለደረጃ እንዲሁም ባህርዳር ከተማ እና መከላከያ ለሻምፕዮንነት በመጪው ዕሁድ በአበበ ቢቂላ ስታድየም ይፋለማሉ ።

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ሽረ ምድረገነትዜናዎችየኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ

ምድረ ገነት ሽረ ከኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ውድድር ውጭ ሆነ!

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሲሳተፍ የነበረው እና በተጠናቀቀው የውድድር አመት ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ...

መቻልኢትዮጵያ ቡናዜናዎችየዝውውር ዜናዎች

ሁለቱን ተጫዋቾች ሁለቱ ክለቦች ተካፈሉ

ለሁለት ክለብ በመፈረማቸው ቅጣት ላይ የነበሩት ተጫዋቾች ለመቻል እና ለኢትዮጲያ ቡና እንዲጫወቱ...

ካፍዜናዎች

የኒጀር እና ሞሮኮ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ሊመራ ነው

ራቫት ላይ የሚደረገው ወሳኙ የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በኢትዮዽያዊያን ዳኞች ይመራል። ኬኒያ...