በአቤኔዘር አበበ
ተጠባቂው 53ኛው የአዲስ አበባ ደርቢ በኢትዮጵያ ቡና 2–1 አሸናፊነት ተጠናቋል። በደማቅ የደጋፊዎች ድባብ የታጀበው ጨዋታ በሦስት ግቦችና በሦስት ቀይ ካርዶች ተደምድሟል።

በመጀመሪያው አጋማሽ እስከ 30ኛው ደቂቃ ድረስ ጎል የሚያስቆጥሩ ሙከራዎች በብዛት አልታዩም። ከዚያ በኋላ ግን ኢትዮጵያ ቡና ጫናውን በማሳደግ የተሻለ ብልጫ ወስዷል። በ36ኛው ደቂቃ ተመስገን ያደረገው ሙከራ እና ፀጋዓብ የበረከትን አደገኛ ኳስ በግሩም ሁኔታ ማዳኑ ከተጠቀሱት ክስተቶች መካከል ነበሩ። አጋማሹም ያለ ግብ ተጠናቋል።ከዕረፍት መልስ ግን የኢትዮጵያ ቡና የግብ ድልድዩን ከፍቷል።የቅዱስ ጊዮርጊስን ተከላካዮች ድክመት በመጠቀም በ56ኛው ደቂቃ የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች በፍቃዱ ዓለማየሁ ቡናን መሪ ሲያደርግ፣ በ74ኛው ደቂቃ አቢዱሉ የሱፍ ከማኢዘን ምት ያሻማትን ኳስ ኦካይ ጁል የቡድኑን ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል።ቅዱስ ጊዮርጊስ በ83ኛው ደቂቃ አማኑኤል ኤርቦ ባስቆጠረው ግብ ወደ ጨዋታው ቢመለስም፣ አቻ ለመሆን አልቻለም።በጨዋታው መጨረሻ ደቂቃዎች ውጥረቱ ከፍ ብሎ ሦስት ቀይ ካርዶች ታይተዋል። በ90+3ኛው ደቂቃ በፍቃዱ ዓለማየሁ ቀጥተኛ ቀይ ካርድ ሲያይ፣ በረከት ወልደዮሐንስ በሁለት ቢጫ ካርዶች ከሜዳ ተሰናብቷል። በ90+4ኛው ደቂቃም ያሬድ የማነ ቀይ ካርድ ተመልክቶ ከሜዳ ወጥቷል።በመጨረሻም ኢትዮጵያ ቡና በደማቅ የሸገር ደርቢ ፉክክር ቅዱስ ጊዮርጊስን 2–1 በማሸነፍ ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል።
አስተያየት ይስጡ