የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከካፍ እና ፊፋ ከሚያገኘው አመታዊ የገንዘብ ድጎማ ውጭ ከተለያዩ ተቋማት ጋር የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት በመፈጸም የገቢ አቅሙን ለማሳደግ ከፍተኛ ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።
በዛሬው እለት ደግሞ በኢሊሌ ሆቴል የኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድንን ስፖንሰር ለማድረግ በሚያስችል መልኩ ከኤልኔት ግሩፕ ድርጅቶች ጋር (Taxiye፣ Elauto engineering፣Elnet Technologies) ጋር በገንዘብ እንዲሁም በአይነት የሚደረግ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ለቀጣዮቹ አራት አመታት የሚቆይ የኮንትራት ጊዜ ተፈራርመዋል።

በየዓመቱ 7 ሚሊዮን ብር በገንዘብ የሚያስገኝ ስምምነት የፈፀሙ ሲሆን በተጨማሪም በየዓመቱ ሁለት ሁለት 1.8 ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የTaxiye መኪኖችን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በስጦታ መልክ የሚሰጥ ሲሆን፤ እንዲሁም በየዓመቱ ውጤታማ እንቅስቃሴ ለሚያሳዩ አሰልጣኞችም ሆነ ተጫዋቾች (በተመልካቾች ለሚመረጥ) የመኪና ሽልማት የሚሰጡ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪም ብሔራዊ ቡድኑ አንድ ጨዋታ ባሸነፈ ቁጥር ደግሞ 500,000 ብር ማበረታቻ ገንዘብ እንደሚሰጡ ተገልጿል።

ደረጃዉን የጠበቀ ብሔራዊ ቡድን ሆኖ እንዲታይ አጠቃላይ ድርጅቱ ለመደገፍ እና አብሮ ለመስራት ፍላጎቱ አለን ያሉት የኢልኔት ግሩፕ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ ናኦል ስለ ድርጅቶቹም አጠር ያለ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በማብራሪያቸውም:-
ኢልኔት ግሩፕ ድርጅቶች በዉስጡ ዘጠኝ የሚደርሱ ድርጅቶች ያሉት ስለመሆኑ ለጊዜዉ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ የገቡት አምስት ሲሆኑ ከሚሰሯቸዉ ስራዎች መካከልም Taxiyeን ወደ ኢትዮጵያ አምጥቶ ለሽያጭ ያቀርባል ፣ ሪል ስቴት ግንባታ ላይ ይሰራል ፣ በቅርቡም ከ10,500 በላይ ያረጁ መኪኖችን መቀየር ላይ እየሰሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል። በተጨማሪም ኢልኔት ፋዉንዴሽን የሚባል በየአመቱ ከድርጅቶቹ አመታዊ ገቢ በሚሰበሰብ ገቢ የሚደገፍ የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን የተለያዩ የድጋፍ ስራዎችንም እየሰራ አንደሚገኝ ገልፀዋል።
በመጨረሻም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በምን መልኩ የኢልኔት ድርጅቶችን እንደሚያስተዋዉቁ የገለፁ ሲሆን በልምምድ መለያዎች ላይ ፣ አዲስአበባ ስታዲየም ላይ በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ ባነሮችን በመለጠፍ እንዲሁም በተዛማች መንገዶች የኢልኔት ግሩፕ ድርጅቶችን እንደሚያስተዋዉቁ ተናግረዋል።

አጠቃላይ የስፖንሰርሽፕ ስምምምነቱም ለአራት አመታት የሚቆይ ይሆናል።
አስተያየት ይስጡ