“በመጀመሪያው ተሳትፏችን በኮከብ ግብ አግቢነት በመሸለሜ፣ የራሴንና የሀገሬን ስም በታሪክ መዝገብ በማስፈሬ ተደስቻለሁ” ሎዛ አበራ (የኢት.ንግድ ባንክ)

ደምቃ ማንፀባረቋን የቀጠለችው ሎዛ አበራ

“በመጀመሪያው ተሳትፏችን በኮከብ ግብ አግቢነት በመሸለሜ፣ የራሴንና የሀገሬን ስም በታሪክ መዝገብ በማስፈሬ ተደስቻለሁ”
ሎዛ አበራ (የኢት.ንግድ ባንክ)

ኢትዮጵያ ከንግስት ዘውዲቱ በኋላ የመጀመሪያዋን ሴት ርዕሰ ብሔር አግኝታለች…ክብርት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን፤የኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ከተወለደበት ከ20 አመታት በኋላ ያገኛት የእግር ኳሱ ርዕስ ብሔርና ንግስት ሎዛ አበራ ናት ብል ተሳስተሃል ወይም አጋነሃል ብሎ የሚሟገተኝ ይኖር ይሆን?ለዚህ አባባሌ ማስረጃ አይኖረውም ብላችሁ የምትሰጉ ካላችሁ ምላሼ ምንም አትስጉ ነው…ከዱራሜ አቧራማና ገጠራማ መንደር የተገኘችው ሎዛ አበራ በኢትዮጵያ የሴቶች እግር ኳስ ስሟን በወርቅ ቀለም ያፃፈች፣በወንዶች እንኳን ማሳካት ያልቻልነውን የሙሉ ፕሮፌሽናል ተጨዋችነትን እድልን በአውሮፓ (በማልታ) ማሳካት የቻለች፣በርካታ ጎሎችን በማስቆጠር በሀገር ውስጥ ሪከርድን የጨበጠች፣በሀገር ውስጥ ተገድባ ሳትቀር በኬንያ በተካሄደው የሴካፋ ዞን የሴቶች እግር ኳስ ሻምፒዮና በ13 ጎል በኮከብ ግብ አግቢነት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ስሟን በደማቁ በታሪክ መዝገብ ላይ ያስፈረች ከመሆንዋ አንፃር ስያሜዋ ይበዛበታል የሚል እምነት የለኝም፤ንግስናዋ ሁሉንም የሚያስማማው፣የማይሞሞቀንም የማይበርደንም በትክክል የሚመጥናት በመሆኑ ነው፡፡

በሜዳ ውስጥ ብቻ ሣይሆን ከሜዳ ውጪ ባለው ህይወቷም ፍፁም የተረጋጋች፣አንደበተ ርቱዕ የሆነችው ሎዛ አበራ በሃይማኖት ተኮትኩታ ስለማደጓ ስነ-ምግባርዋ ብቻ ሣይሆን በንግግሮቿ መሀል የፈጠራት አምላክዋን ስም ደጋግማ ማንሣትዋና የመፅሀፍ ቅዱስ ቃልን መጠቀምዋ በእግር ኳስ ብቻ ሳይሆን በሃይማኖትዋም ያላትን የጠነከረ የእምነት ያሳብቃል፡፡

የዚህችን ጀግና ታሪክ ሰሪነት በተደጋጋሚ ለመዘገብ የማይሰንፈውና ብዕሩ አልታዘዝ የማይለው የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስክዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ከኬንያ ሌላ አዲስ ስኬት በወርቅ ቀለም አፅፋ በመመለስ ለብ ባለ ደስታ ግን ደግሞ በበዓልና በአዲስ አመት የሞቀ ስሜት ውስጥ ያለችውን የእግር ኳሱን አንፀባራቂ ኮከብ ሎዛ አበራን ከኬንያ መልስ አግኝቶ አውርቷታል፡፡

ጋዜጠኛው ከሎዛ ጋር የነበረውን ቆይታ መክፈቺያ ወይም መባረኪያ ጥያቄ ያደረገው “…እንዴ…?…ሎዛ ወደ ትዳር አለም ጎራ ካልሽ ቀናቶችና ወራቶች እየነጎዱ ነው…ምን ቤት ነህ…?…ብለሽ ካላሳፈርሽኝ …ቤታችሁ ውስጥ ድክ ድክ የሚል ህፃን ልጅ ስለመውለድ አላሰባችሁም…?…”በማለት የግል ህይወቷንና ምስጢርዋን የሚበረብር ጥያቄ በመወርወር ስለ በዓልና ስለ ኬንያ ቆይታዋ፣ስላገኘችው ክብር እንዲሁም የግል ህይወቷን በወፍ በረር በመፈተሽ የአዲስ ዓመት የመጀመሪያ እንግዳ በማድረግ ከዚህ በታች ባለው መልኩ አቀናብሮታል፤እንደተለመደው አብሮነታችሁን አውሱን ትህትና የተሞላበት የዘወትር ልመናችን ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …ሎዛዬ…እንኳን አደረሰሽ…?…

ሎዛ፡- …እንኳ አብሮ አደረሰን…በዚህ አጋጣሚ ለእናንተም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብም መልካም አዲስ አመት ማለት እፈልጋለሁ…

ሀትሪክ፡- …ሎዛ ባል ካገባሽ…ይቅርታ ትዳር ከመሠረትሽ በኋላ…የመጀመሪያ በዓልሽ ነው ልበል…?…

ሎዛ፡- …(በምጥን ፈገግታ ታጅባ)…በአዲስ አመት ደረጃ አዎን…!…አዲስ አመትን በዚህ መልኩ ሳከብር የመጀመሪያዬ ነው…

ሀትሪክ፡- …የተለየ ነገር አየሽበት…?…

ሎዛ፡- …የተለየ ነገር ሣይሆን…ሁለቱም የየራሳቸው ደስ የሚል ከለር አላቸው…በፊት በዓልን የማከብረው ከቤተሰቦቼ ጋር በእነሱ ጫንቃ ስር ሆኜ ነበር…አሁን ግን…(እየሳቀች)…በራሴ ቤት የምትለው ነገር አለ አይደል…ከባለቤቴ ጋር ሆኜ ያከበርነው አዲስ አመት ነበር…በእውነት ነው የምልህ አዲስ አመትን በዚህ መልኩ መቀበሌ በጣም ደስ ብሎኛል… ከእስከዛሬው አዲስ አመትም የተለየ ስሜትና ትውስታ ጥሎብኝ ያለፈ ነበር ማለት እችላለሁ…

ሀትሪክ፡-.. ከዚህ አንፃር ሎዛ አበራ ከ23 አመታት በኋላ ዶሮ ሠርታ ያከበረችው ታሪካዊ በዓል ነበር በይኛ…?…

ሎዛ፡-… (በጣም ሣቅ)…አዎን ትክክል ነህ…!…በፊት የተሠራ የተዘጋጀ ነበር የምበላው…አሁን ወጉ ደርሶኝ እኔ ነኝ ባለቤቴንም ቤተሰቦቼንም ሠርቼ ያበላሁት…(አሁንም ሳቅ)…በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ…

ሀትሪክ፡- …እንደ ድፍረት እንዳታይብኝ እንጂ…ዶሮውን መስራት ቻልሽበት ብልሽ ትቀየሚኛለሽ…?… ምን አይነት አስተያየትስ ተሰጠሽ…?…

ሎዛ፡- … (አሁንም በጣም ሳቅ)…ሳላጋንና ሳልዋሽ ነው የምነግርህ…ሁሉም ሰው ነው የወደደልኝና ያደነቀኝ…(ሣቅ)…ምን አለ መሰለህ አንተ በጥያቄህ እንደሰጋኸው ብዙ ሰውጋ ሴት ስፖርተኞችን በተመለከተ የተሳሳተ አመለካከት አለ…እኛ ሴት ስፖርትኞች ከሙያ ጋር የተጣለን ወይም ምንም አይነት ነገር መስራት እንደማንችል አድርጎ የማሰብ ነገር አለ…ግን ይሄ ሥህተት ነው…ስፖርተኞች ብንሆንም ምንም የማይወጣልን ባለሙያዎችንም ነን…እንደዚህ ያለ አስተሳሰብ ስህተት መሆኑን በተግባር ያሳየሁም ይምስለኛል…ስፖርትኞች ሙያ የላቸውም የሚለውን አባባል አንቀበለውም…በደንብ መስራትም እንችላለን…

ሀትሪክ፡- …ካገባሽ ቀናቶችና ወራቶች እየተቆጠሩ ነው…ከማግባትሽ በፊትና ካገባሽ በኋላ በሙያሽ ላይ ልዩነት አየሽ…?…ወይም በአጭር አማርኛ…ትዳርና ሰፖርት ይስማማሉ…?…ወይስ ይጣላሉ…?…

ሎዛ፡- …ይበልጥ ይፋቀራሉ…(ሣቅ)…ሁለቱም የየራሳቸውን የሚጠይቁት ኃላፊነት አላቸው…ያንን ማወቁ ነው ቁም ነገሩ…ትዳር ራሱን የቻለ ህይወት ነው…የራሱ አያያዝ (ማኔጅማንት) አለው…እግር ኳስም ሥራ ነው…የራሱ አየያዝና የሚጠየቀው ነገር አለ…ይሄንን ካወክ የሚያጋጭም የሚያጣላም ነገር የለውም…ከመጣላትና ከመጋጨት ይልቅ ተመጋጋቢነታቸውና ተደጋጋፊነታቸው ነው ይበልጥ የሚታየው…በትዳር ስትወስን በፕሮግራም ትመራለህ…የበለጠ ኃላፊነት እንዲሰማህም ያደርጋል… ከምንም በላይ በሙያህ የሚረዳህና የሚያስብልህም ሰው ታገኛለህ…በትዳር አለም ውስጥ ስትሆን ከብዙ ነገርም ትቆጠባለህ…ይበልጥ ስኬታማ እንድትሆን የሚሰጠው ጥቅም ይልቃል…ከዚህ የበለጠም ሌሎች ኃላፊነቶች ሊመጡ ይችላሉ…ራስን አዕምሮን ማዘጋጀት ከተቻለ የሚመጣውን ቻሌንጅ (ፈተና) መቋቋም ይቻላል…

ሀትሪክ፡- …በወንዶችም በሴቶቹም እግር ኳስ…ተጫዋቾች ትምህርታቸውን ሲያቋርጡ ማየት አዲስ ነገር አይደለም…ሎዛ አበራ ግን በዚህ ሁሉ እውቅናና ዝና ሳትዘናጋ ደብተር ይዛ ትምህርት ቤት ትሄዳለች የሚለውን ስሰማ በጣም ተገረምኩ…?…

ሎዛ፡- …ለምን ይገርምሃል…ትምህርትና እውቀት ማንም የማይዘርፈው ሀብት ነው ሲባል አልሠማህም…?…(ሣቅ)…እኔ ለትምህርት ትልቅ ዋጋና ቦታ እሰጣለሁ…ማንኛውንም ስራ በእውቀት፣ በትምህርት ስትመራው የበለጠ ስኬታማ ትሆናለህ የሚል የጠነከረ እምነት ስላለኝ…ትክክል ነህ እየተማርኩ ነው…

ሀትሪክ፡- …የሚገርም ነው…!… ለመሆኑ የት ነው የምትማሪው…ምንድነው የምታጠኚው…?…

ሎዛ፡- …የምማረው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማታው የትምህር ክፍለ ጊዜ ነው…የማጠናው ደግሞ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ኤንድ ኢንፎርሜሽን ሲስተም ነው…የሚገርምህ ነገር ከሁለት አመት በፊት ወደ ማልታ ስሄድ ትምህርቴን አቋርጬ (With draw) አድርጌ ነበር የሄድኩት…ስመጣ ያንን ያቋረጥኩትን ትምህርቴን ነው የቀጠልኩት…እግዚአብሔር ከፈቀደ በሚቀጥለው አመት ጋዋን ለብሼ ስመረቅ ልታየኝ ትችላለህ…(ሣቅ)…

 

ሀትሪክ፡- ..ቢዝነሱንም እንደምታስቆጥሪው እንደምታዘንቢው ጎል ልታዘንቢው ነው…?…ይሄንን ፊልድ የመረጥሽው…?…

ሎዛ፡- …(ሣቅ)…እሱን የሚያውቀው የፈጠረኝ አምላክ ነው…ከላይ ለመግለፅ ሞክሬያለሁ የምትሠሪው ስራ በትምህርት ሲታገዝ የበለጠ ፍሬያማ ይሆናል የሚል እምነቱ አለኝ…በመማር የማሳድጋቸው ነገሮችም አሉ…በቀሰምኩት እውቀት በቢዝነስ ውስጥ ለመስራት ሃሣቡ አለኝ አምላኬ ከረዳኝ…አሁን የያዝኩትን ትምህርት ፈጣሪ ብሎ ከጨረስኩና ድግሬዬን ከያዝኩ በኋላም መማሬን እቀጥላለሁ…የተጫዋችነት ዘመን የተገደበ ነው…እድሜህን በሙሉ እየተጫወትክ አትኖርም… ስለዚህ ለነገ ዛሬ ማሰብ አለብኝ…አሁን እየተማርኩት ባለው ትምህርት ስፖርት ውስጥ የምሠራቸው ነገሮች ካሉ እነዛን ሥራዎች በልምድ ብቻ ሣይሀን በእውቀትም መስራትን ነው የማስበው…

ሀትሪክ፡- …ብዙ የወንድም የሴትም ተጨዋቾች የፓስፖርትና የእግዜሩ የሚባል ሁለት አይነት እድሜ አላቸው በሚል ይቀለዳል…ሎዛ ግን ከዚህ በተቃራኒ እድሜዋን አትደብቅም…ትክክለኛውን ትናገራለች… በእድሜዋ የሠራችውንም የመመዝገብ ባህሪም አላት የሚለውን ስሰማ ተገርሜያለሁ…እውነት ነው…?…

ሎዛ፡- …(ፈገግ እንደማለት እያለች)…እድሜን የሚሰጠው እግዚአብሔር ነው…መጨመርም መቀነስም የሚችለው አሱ ነው…ከዚህ ውጪ ብንቀንስም ብንጨምርም የሚሆነው ውሸት ነው…ውሸት ደግሞ ኃጢአት ነው…እኔ እድሜዬን ከመሸራረፍ ወይም እድሜዬን ከማሳነስና ከመደበቅ ይልቅ ምን ሠራሁበ ት የሚለው ነው የሚያስጨንቅኝ…በፍፁም አምላክ በሰጠኝ እድሜዬ መቀለድ አልፈልግም..ስጠየቅም አምላክ የሰጠኝን እድሜዬን በትክክል ነው የምናገረው…በእድሜዬ፣በዘመኔ የሠራኋቸውን በሙሉ የመመዝገብ የተለየ ልምዱ አለኝ…በዚህ አመት…በዚህ እድሜዬ ይሄን ይሄን ሠርቻለሁ…ወይም በዚህ እድሜዬ ይሄን አደርጋለሁ…ከዚህ እድሜዬ በኃላ ደግሞ ይሄንን አድርጌ ከዚህ ተነስቼ እዚህ ጋር እደርሳለሁ ወይም መድረስ አለብኝ ብዬ አቅዳለሁ…መዝግቤም እይዛለሁ…እኔ ያለኝ እድሜ አንድ ነው…እሱም በእግዚአብሔርና በቤተሰቦቼ የሚታወቀው…የፓስፖርት የምናምን የሚባል እድሜ የለኝም…አምላክ በሰጠኝ ነገር ተደስቼ አመስግኜ ነው የምኖረው…

ሀትሪክ፡- …በእርግጥ በኃይማኖታቸው የጠነከሩ ብዙ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ…ከዛ ውስጥ አንዷ አንቺ ነሽ…አንዳንዶች ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ የመፅሀፍ ቅዱስ ቃልን በመጥቀስ ኃይማኖተኛ ለመባል እንቅልፍ ሲያጡ ይታያል…በዚህ ዙሪያ ምን ትያለሽ…?…

ሎዛ፡- …ይሄንን ለመፍረድ እኔ አቅሙ የለኝም…እኔ ግን አንድ የማምነው ነገር አለ…በእምነት ውስጥ መኖር እንጂ ለታይታ መሆን አለበት አልልም…እንግዲህ እንደምናውቀው በእምነታቸው ጠንካራ የሆኑ ሰዎች በየትኛውም ዓለም ዲሲፒሊንድ ናቸው…ከሰው ጋር ያላቸው መግባባትም ጥሩ ነው…በዚያ ላይ ትሁትቶች ናቸው…ሥራ ላይ አይቀልዱም…ስራቸውን ያከብራሉ…በዚህም ምድር የሚኖሩት በጥበብ ነው…ለዚህም ይመስለኛል…እኔም እንደዚህ ለማድረግ ነው የምሞክረው…ከህፃንነቴ ጀምሮ ያደኩት ዱራሜ ውስጥ ነው…ሰንበት ት/ቤት እየተማርኩ ነው ያደኩት…ቤተሰቦቼ ያሳደጉኝ እግዚአብሔርን እንዳከብር እንድፈራ አድርገው ነው…ይሄንን መሠረት ከልጅነቴ ጀምሮ ይዤ መምጣቴ ለዛሬው ማንነቴ ጠቅሞኛል ብዬ አስባለሁ…በዚህ ባደኩበት መንፈሳዊ ህይወት ብዙ የተሻሻልኩበትና ያደኩበት ነገር አለ…መንፈሳዊ ሰው መሆን ከብዙ ነገር ያርቅሃል…እግዚአብሔርን እንድትፈራ…በእግዚአብሔር ትዕዛዝ እንድትኖር ያደርግሃል…የሰውን አትፈልግም፣አትመኝም…ይልቁንም ሰዎች የተሻለ ነገር እንዲያገኙ፣ እንዲኖሩ ታስባለህ…

ሀትሪክ፡- …በትየኛውም መመዘኛ ሽንፈት እንደማይወደድ ግልፅ ነው…የሎዛ ሽንፈት መጥላት ግን የተለየ ነው…በፍፁም ሽንፈትን አትወድም አሉኝ…የነገሩኝ ዋሹ…?…

ሎዛ፡- …(ሣቅ)…አልዋሹም…የሽንፈት ጠላት ነኝ…አንድ እውነት ምንድነው…?…በእግር ኳስ ሁሉም ነገር አለበት…ማሸነፍም መሸነፍም…ፀቤና ጥላቻዬ ከዚህኛው ሀቅ ጋር አይደለም…አምርሬ የምጠላው እየቻልክ መሸነፍን ነው…እየቻልን ስንሸነፍ ሽንፈቱ በጣም መራራ ይሆንብኛል…የእግር ኳሱ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት መሸነፍ የስፖርቱ ባህሪ ነው…ማሸነፍ የምትችልበት አቅም እያለህ…እየቻልክ መሸነፍ ግን አምርሬ እጠላለሁ…እስከ ዛሬ ኳስ ስጫወት ወደ ሜዳ የምገባው ለማሸነፍ ነው…አንድም ቀን ከማንም ጋር እንጫወት ማንም በቡድኑ ውስጥ ይኑር ስለ ሽንፈት ለአዕምሮዬ ነግሬው ወደ ሜዳ ገብቼ አላውቅም…በተፈጥሮዬ እየቻሉ አቅሙ እያለ መሸነፍን አልወድም…አምርሬም እጣላለሁ…

ሀትሪክ፡- …ብዙዎች ላለመሳሳት ሲጥሩ በመሳሳታቸውም ሲቆጩ…ሎዛ ግን መሳሳትን እንደመልካም አጋጣሚ የምታይበት የተለየ ነገር አላት ተባልኩ…ይሄስ ምንድነው…እስቲ አብራሪልኝ…?…

ሎዛ፡- …አንድ እምነት አለኝ ስህተት ከተማርክበት ጥሩ አጋጣሚ ነው የሚል…ማንም እንደሚያውቀው የሚሠራ ሰው ከስህተት አይፀዳም…መጥፎው ነገር መሳሳቱ አይደለም…ከስህተትም አለመማሩ እንጂ… ስህተት አለመስራት ጥሩ ነው…ካልተሳሳትክስ እንዴት ትማራለህ…?…እግር ኳስ በባህሪው በስህተት የተሞላ ነው…የእግር ኳስን ተፈጥሮ ስታይ አንድ ቡድን ጎል የሚያገባው ወይም የሚያሸንፈው ተጋጣሚው ቡድን የፈጠረውን ስህተት ተጠቅሞ ነው…እግር ኳስ ሁሉ ነገሩ ስህተት ነው…እኔ መሳሳቴን እንደ ትልቅ አጋጣሚ ወይም ሲሳይ ነው የማየው…ምክንያቱም ከዛ ስህተት ተምሬ ነገ የተሻልኩ እሆንበታለሁ…ስህተትህን ስታውቅ በዚህ በኩል መሻሻል አለብኝ ትላለህ…ካልተሳሳትክ ግን የምትማርበት የምትለወጥበት እድል አይኖርም…ስታሳሳት አጠገብህ ካሉ ከሰዎች፣ከአሰልጣኞች፣ ከተጨዋቾች ትማራለህ…ተማሪ በትክክል ከመለሰው ሣይሆን ኤክስ ከሆነው ከተሳሳተው ነው የሚማረው…የተሳሳተውን መቼም አይረሣውም…ትክክል የሆነውንማ ቀድሞም ያውቀዋል…ስለዚህ መሳሳት መልካም ነው ባልልም መሳሳት ግን ጥሩ መማሪያም መሻሻያም ነው የሚል እምነት ስላለኝ መሳሳቴን በክፋት ሳይሆን እንደ መልካም አጋጣሚ ነው የምወስደው…

ሀትሪክ፡- …በእግርግጥ ይሄ ጥያቄ ያለ ጊዜው የተወለደ ጥያቄ ሆኖብሽ ልትደነግጪ ትችይ ይሆናል… ግን ሎዛዬ…ከዚህ በኋላ ስንት አመት የመጫወት እቅድ አለሽ…?…ብዬ ብጠይቅሽ ትመልሺልኛለሽ…?…

ሎዛ፡-… (እየሳቀች)…ይሄ ሁሉ ዳር ዳርታ ጫማሽን መቼ ትሰቅያለሽ…?…ለማለት ከሆነ አይሳካልህም… ምክንያቱም እድሜዬ በጣም ገና ነው…እግር ኳስን በአግባቡ እንኳን ጠግቤ ስላልተጫወትኩ ስለዚህ ነገር ላስብ አልችልም…ከዚህ በኋላ ሶስት አራት ወይም አስር አመት እጫወታለሁ ብዬ ላስቀምጥልህ አልችልም…እግዚአብሔር ከፈቀደልኝ…ከዚህ በኋላ ራሱ ረዥም አመታት መጫወትን ነው የምፈልገው…ራሴን ከጠበኩ ብዙ አመታት መጫወት እችላለሁ…ለዚህ ደግሞ አንድ የቅርብ ጊዜ ምሣሌ ልስጥህ…

ሀትሪክ፡- …በጣም ደስ ይለኛል…?

ሎዛ፡- …ክርስቲያኖ ሮናልዶ በ37 አመቱ እንኳን ምን አይነት ብቃትን እያሳየን…እግር ኳስን በትልቅ ክለብ ደረጃ እንዴት እየተጫወተ እንደሆነ እያየን እየታዘብን ነው…ራስን ጠብቆ በብቃት መጫወት እንደሚቻል እሱ ትልቅ ምሣሌ ነው…እግር ኳስ የጊዜ ገደብ ያለው ሙያ እንደሆነ ባውቅም ራሴን በመጠበቅ ረዥም አመት በመጫወት ለተተኪ ቦታዬን ስለመልቀቅ ነው የማስበው…

ሀትሪክ፡- …የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም፣የኢትዮጵያ ብ/ቡድን አምበል የሆንሽው በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ነው…አምበል መሆንሽን ወደሽዋል…?…እንዴትስ ተቀበልሽው…?…

ሎዛ፡- …አምበል በመሆኔ በጣም ተደስቻለሁ…ሀገሬንም የምጫወትበትን ክለብም በአምበልነት ስለማገልገል ብዙ ጊዜ አስብ ነበር…ያም ዘመን ካሰብኩበት ጊዜ ፈጥኖ ስለመጣ በጣም ደስ ብሎኛል… አምበል ሆኜ በመሾሜ ሌላ ተጨማሪ ኃላፊነት ነው የተሰጠኝ…እምነትም ነው የተጣለብኝ…አምበል ስትሆን በተጫዋችና በአሰልጣኝ መሀል ነው የምትሆነው…

ሀትሪክ፡- …ምግብ ላይና ትሬይኒግ ላይ መቆጣጠር ብቻ ስራ የሚመስላቸው አምበሎች አሉ…ሎዛስ ምን አይነት አምበል ናት ብልሽ መልስሽ ምንድነው…?…

ሎዛ፡- …እንዳልኩህ ነው…አምበል መሆን ማለት በአሰልጣኝና በተጨዋቾች መሀል መሆን ማለት ነው…የአምበልነት ሚና ልምምድ፣ስብሰባ ወይም በምግብ ቁጥጥር ላይ ብቻ የተወሰነ እንዳልሆነ ነው የምረዳው…አምበል ስትሆን የቡድኑ ውጤት፣የተጨዋቹ ሁኔተ ያሳስብሃል…ለተጨዋቾችም ለአሰልጣኙም ይበልጥ ቅርብ እንድትሆን ያደርግሀል…በሁለቱም ሳይድ (ወገን) ያለውን ባላንስ አድርገህ (አመዛዝነህ) ለቡድኑ የሚጠቅም ነገር እንድታደርግ ይረዳሃል…የቡድኑን የጨዋታና የአሸናፊነት መንፈስ ለማስፈን ጥረት ማድረግ፣በሜዳ ውስጥም ከሜዳ ውጪም ጥሩ በሆንበትም ባልሆንበትም ሰዓት ከተጨዋቹ ጎን በመሆን የምታነሣሣ የምታነቃ አምበል መሆኔን ማሳየት ነው የምፈልገው…እኔ አምበል በመሆኔ ፊት ለፊት ስለሆንኩ ሁሉም ሰው ከእኔ የተለየ ነገር ይጠብቃል…ያንን መወጣትና የተሻለ ነገር በቡድኑ ውስጥ እንዲኖር የቡድኑን ስሜት ለማምጣት ጥረት አደርጋለሁ…እነዚህ ኃላፊነቶች አሉብኝ ብዬ በግሌ እነዛን ነገሮች ለማድረግ እየጣርኩ ነው…ልምዱን እያገኘሁ ስሄድ ከዚህ የበለጠ ነገር የምታደርግ አምበል ለመሆን እጥራለሁ…

ሀትሪክ፡- …በአምበልነትሽ የምትሰሪውን የተመለከቱ በርካታ ሰዎች ሎዛ የአሰልጣኝነት ፍንጭ ይታይባታል…ወደፊት አሰልጣኝ ብትሆን ሊያዋጣት ይችላል እያሉ ከወዲሁ ምስክርነታቸውን መስጠት ጀምረዋል…ወደፊት አሰልጣኝ የመሆን ሃሣቡ አለሽ…?…

ሎዛ፡- ..ሙሉ በሙሉ አሰልጣኝ እሆናለሁ ብዬ አላስብም..በዋናነነት ቴክኒካል ነገሮች ውስጥ የምገባ ነው የሚመስለኝ…ከእግር ኳስ ስገለል ከስፖርቱ ሣልርቅ የማገልገል ፍላጎቱ አለኝ…በተጨዋችነት ስላሳለፍኩ…
….እግር ኳስ ውስጥ ያሉትን ድክመቶች በተወሰነ መልኩ እረዳለሁ እነዛን ነገሮች መቀረፍና ተጨዋቾችን ማገዝ ስለሚቻልበት ነገር ነው የማስበው… አሰልጣኝ እሆናለሁ ብዬ ሙሉ በሙሉ ባልደመድምም ከሙያው የመራቅ ሃሣቡ ግን የለኝም… ልጆች የሚያድጉበት፣ ተጨዋቾች በየትኛውም አለም ወጥተው የሚጫወቱበት በአለም እግር ኳስ ላይ ሴት ተጨዋቾቹ ጎልተው እንዲወጡ በሚያደርግ ስራ ላይ የምጠመድ ይመስለኛል…

ሀትሪክ፡- እስቲ አሁን ደግሞ አንፀባራቂ ውጤትና በግልሽ አዲስ ስኬት አግኝተሽ ስለተመለሽበት የኬንያው የሴካፋ ዞን ውድድር እናውራ… እንዴት ነበር ውድድራችሁ…?…

ሎዛ፡-… ውድድሩ በጣም አሪፍ ነበር… የሴካፋ ዞን የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ሲካሄድ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው…. ወደ ኬንያ የተጓዝነው በጥሩ የቡድን መንፈስና የአሸናፊነት ስሜት ነበር… መጨረሻው በምንፈልገው መልኩ ባይጠናቀቅም እስከ ውድድሩ ፍፃሜ በመድረስ የተሻለ ነገር ለማድረግና ለማሳየት ሞክረናል…. አጨራረሱ በዋንጫ ቢደመደም ለእኛ በጣም አሪፍና ትልቅ ታሪክ ነበር… በእርግጥ እስከ ፍፃሜ መድረሳችንም በሴቶች እግር ኳስ ሌላው አዲስ ታሪክ ነው…. ዋንጫውን ይዘን ወደ ሀገራችን በመምጣት ለህዝባችን በአዲስ አመት ስጦታነት ብናበረክት የተለየ ስሜት ይሰማን ነበር…. ያም ባይሆ እንደዚህ አይነት ውድድር ማድረጋችን ትልቅ ጠቀሜታ አለው… በኢንተርናሽና የውድድር መድረክ ልምድ እንድናገኝና አቅማችንን እንድናሳድግ ይረዳል በራስ መተማመናችንም ይጨምራል… በአጠቃላይ ጥሩ ቆይታ ነበር…

ሀትሪክ፡-… በውድድሩ የግብ ዝናብ አወረዳችኋል… አንቺ በግልሽ ከተቆጠሩት ከ25 በላይ ግቦች 13ቱን አስቆጥረሸል ይሄ ሁሉ የጎል ዝናብ ከእናንተ ጥንካሬ ወይስ ከተጋጣሚዎቻችሁ ድክመት….?….

ሎዛ፡- … እውነት ለመናገር በርካታ ጎል የተቆጠረው ቡድኖቹ ደካማ ስለነበሩ አይደለም… ጎሉ ስለገባና ስለበዛ በዚህ ደረጃ እንዲታሰብም አልፈልግም…. ጎሉ መብዛቱ የበላይነታችንን ወይም ልዩነታችንን አስፍቶት ይሆናል እንጂ ፉክክሩ ቀላል የሚባል አልነበረም… ለምሣሌ በመጀመሪያ ጨዋታችን አሁን ዋንጫውን ከወሰደው ቡድን ጋር ስንጫወት በብዙ ግብ ነበር ያሸነፍነው…. በምን ያህል የበላይነት እንዳሸነፍነው የታየ ነው .. የኡጋንዳውን ክለብ ብትወስድ ከእኛ ጋር በግማሽ ፍፃሜ እስከተገናኘንበት ድረስ አንድም ግብ አላስተናገደም… እኛ ግን ግብ አስቆጥረንበታል… በመለያ ምትም አሸንፈን ነው ለዋንጫ ያለፍነው… በሁለቱም ምድብ የነበረው ፉክክር ቀላል የሚባል አልነበረም. … የጎሉን ብዛት ማየት ብቻ ፉክክሩን ማሳነስ ተገቢ አይመስለኝም… በትክክል የነበረውን ውድድር መከታተል የቻለ ሰው ምስክርነቱን ይሰጣል….

ሀትሪክ፡- … አንቺና መዲና አወል በጋራ 21 ጎል አካባቢ አስቆጥራችኋል…. እስቲ ስለበራችሁ ጥምረትና ስለመዲና አውሪኝ….?..

ሎዛ፡-… ከመዲ ጋር ጥሩ የመግባባትና የመናበብ ነገር አለን… ሁለታችንም በተቀራረቢ የእድሜ ክልል ውስጥ ነው ያለነው… ከዚህ በፊት ከ20 አመት በታች ብ/ቡድን ውስጥ አብረን መጫወታችን በጣም እንድንተዋወቅና እንድንግባባ ረድቶናል… መዲና የራሷ የሆነ ብዙ ችሎታዎች አሏት… እኔም የራሴ የሆነ ነገር አለኝ… ያንን አቀናጅተን በኬንያ ጥሩ የሚባል ጥምረትን ፈጥረናል…. መዲና በተፈጥሮዋ ኳስን አቅልላ የምትጫወት ልጅ ናት… ያ ደግሞ እግር ኳስን ከፍ ያደርገዋል….

 

ሀትሪክ፡-… በኢትዮጵያ እግር ኳስም፣ ማልታ ድረስ ተጉዘሽም በኮከብ ግብ አግቢነትና ተጨዋችነት ትልቅ ክብርን አግኝተሻል… አሁን ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄው የሴካፋ ዞን የሻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ኮከብ ግብ አግቢ በመሆን አዲስ ታሪክ አፅፈሻል…. ምን ስሜት ፈጠረብሽ?

ሎዛ፡- … በእርግጥ በጣም የተለየ ደስታ ተሰምቶኛል.. ክለቤ ሻምፒዮን ሆኖ ቢሆን ኖሮ ደስታዬ የበለጠ ሙሉ ይሆን ነበር… በጣም የሚገርምህ ነገር ኮከብ ግብ አግቢ ሆኜ እንደምመለስ ከአዲስ አበባ ከመነሳቴ በፊት በእርጠኝነት ተናግሬ ነበር… ለዚህ ደግሞ የነገርኳቸው ሰዎችና ተጨዋቾች ምስክር መሆን ይችላሉ… በኬንያ የገጠመኝ ቀድሜ የገመትኩት በመሆኑ በጣም ደስ ብሎኛል…. በዚህ ሲካሄድ በታሪኩ የመጀመሪያ በሆነው ውድድር ላይ አዲስ ታሪክ በመስራቴ የራሴንም፣ የክለቤንም፣ የሀገሬንም ስም በታሪክ መዝገብ ላይ አፅፌ በመመለሴ በቃላት የማግልገልፀው ደስታ እንዲሰማኝ አድርጓል… ይሄ ሁሉ እንዲሆን ትልቁን ሚና የተጫወቱት የቡድን ጓደኞቼ ናቸውና እነሱን ላመሰግናቸው እወዳለሁ … ይሄንን ስኬት ብቻዬን አላመጣሁት የእነሱ ሚና ከፍተኛ ነውና ሊመሰገኑ ይገባል….

ሀትሪክ፡-.. እስከ ፍፃሜ ደርሳችሁ ዋንጫውን አለማግኘት ምን አይነት የህመም ስሜት አለው….?…

ሎዛ፡- ቀላል ነው ትለኛለች ብለህ እንዳትጠብቅ ከፍተኛ የህልምም ስሜት አለው… ግን እግር ኳስ ነው… በመጨረሻ የሚያሸንፈውና ዋንጫውን የሚወስደው አንድ ቡድን በመሆኑ የሆነውን በፀጋ ከመቀበል ውጪ አማራጭ የለም… በእርግጠኝነት እስከ ፍፃሜ እንደምንደርስ ውስጤ እምነት ነበረው… ዋንጫውን በመውሰድ ታሪክ እንደምንሰራም ከራሴ ጋር አወራ ነበር… ግን አልሆነም… በቀኑ ጥሩ የነበረው፣ የተሻለው ቡድን ዋንጫውን አንስቷል… እንደግልም እንደ ቡድንም ዋንጫውን አለመውሰዳችን ያስቆጫል… ግን አሁን ይሄ አልፏል… ማሰብ ስለቀጣይ ነው… ከዚህ አጋጣሚ ብዙ እንማርበታለን.. እንደዚህ አይነት ጨዋታዎችም ጠንካራም ይሁን ደካማ ጎናችንን ታይበታለህ ሁለተኛ ወጥተን መምጣታችን …. ትልቅ ስኬት በመሆኑ እግዚአብሔር የፈቀደውን ተቀብለናል….

ሀትሪክ፡-… ቡድኑን ለፍፃሜ ያደረሰውን አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛውን ግለጪልኝ ብልሽ እንዴት ትገልጪዋለሽ….?…

ሎዛ፡- ኮች እንደሚታወቀው የስራ ሰው ነው… ላለፉት 22 አመታት የሴቶች እግር ኳስ ላይ ሠርቷል… በጣም ብዙ እግር ኳስ ተጨዋቾችን አፍርቷል… ሽታዬን፣ ራሂማንና ሌሎችንም ያሰለጠነ ስኬታማ ያደረገ አሰልጣኝ ነው… ብዙ ታሪኮች ሰርቷል… ብዙ ስኬቶችንም አሳክቷል… በዚህ አመት ነው ከብ/ቡድን ውጪ በክለብ ደረጃ አብሮ የመስራት እድል ያጋጣመኝ… በስራ አይደራደርም… ሁሉም ሰው ዲሲፕሊን ኖሮት ሥራውን አክብሮ እንዲሠራ ነው የሚፈልገው… ስርዓት ያለውን ተጨዋች ያከብራል… ሁሉም ቢሆን ቡድኑ የተሻለ እንዲሆንና ሠርተን እንለወጥ ነው የሚለው… የእግር ኳስ ባህሪያቶችን ያውቃል.. ልጆች እንዲሻሻሉና እንዲለወጡ እንዲጠቀሙ ያደርጋል…. አድርጓል…. ትልቅ አሰልጣኝ ነው…. ለሴቶች እግር ኳስ ይሄንን ያህል ዘመን ራሱን አሳልፎ የሰጠ የለም… ስለ እሱ ከእኔ በላይ የእሱ ታሪኮችም ራሳቸው ይናገራሉ… እኔ ግን በግሌ በዚህ ደረጃ ነው የምገልፀው፡፡

ሀትሪክ፡- … አውሮፓን አቋርጦ ማልታ የደረሰው የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ህይወትሽ ያልቀጠለው ለምንድነው? በሎዛ ክለብ ማጣት ወይስ በሌላ ችግር ብዬ ብጠይቅሽ ትመልሼልኛለሽ…?…

ሎዛ፡-… የመጀመሪያው ኮቪድ-19 የፈጠረው ክፍተት ነው…. ነገሮች በዛው እንዳይቀጥሉ ኮቪድ በአለም ላይ የፈጠረው ችግር እንቅፋት ሆኖብኛል… በዚህ መሀል ሰው የራሱ የሆኑ ፕላኖችና እቅዶች ይኖሩታል… እነዚህ ነገሮች ትንሽ ያዝ አድርገውታል… በዚህ ዙሪያ የተቋረጡ ነገሮች የሉም… ወጥቶ መጫወቱ እንዳለ ሆኖ በእግር ኳስ ውስጥ በአገር ውስጥም በውጭም የተሻለ ክለብና ጥቅም የትኛው ነው የሚለው ነው የሚወስነው….

ሀትሪክ፡- ሎዛዬ የቆይታችንን ማሳረጊያና መዝጊያ የማደርገው በግል ህይወትሽ በመግባት ነው… ሎዛ ትዳር ከመሰረትሽ ቀናቶችና ወራቶች ተቆጥረዋል… ከዚህ አንፃር ቤታችሁን የሚያሞቅ… ቤታችሁ ውስጥ ድክ… ድክ… የሚል ሕፃን ስለማፍራት አላሰባችሁም…? ብለሽ ትመልሺልኛለሽ ….ወይስ በግል ህይወቴ ምን አገባህ ትይኛለሽ…?….

ሎዛ፡-… (በጣም ሳቅ)… ሆ! … ትገርማለህ… ማሰቡ አይቀርም ልጅ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው… ደግሞም አስፈላጊም ነው.. እቅዶችም አሉኝ.. እኔ አንድ የማምነው ነገር አለ… ስለወለድኩ እግር ኳሱን አላቆምም… ወልጄም ቢሆን እግር ኳስን በብቃት እንደምጫወት ይሰማኛል… አለማችን ላይ የትኛውም ሴት እግር ኳስ ተጨዋቾች ልጅ ወልደው ተመልሰው በብቃታቸው ሲጫወቱ አይተናል.. የእኔም ከዚህ የሚርቅ አይመስለኝም….በእኛም ሀገር ልጅ ወልደው የሚጫወቱ አሉ… ለዚህ ምሣሌ እኛ ክለብ ቅርባችን ያለችው ትዝታ አለች… እሷን እንደምሳሌ መውሰድ እንችላለን… በዛ መንገድ ነው የማስበው…

ሀትሪክ፡-… ሎዛ በድጋሚ አመሰግለሁ.. እንግዳዬ ስለሆንሽ…. ?…

ሎዛ፡- እኔም አንተንም የሀትሪክ ዝግጅት ክፍሉን በጣም አመሰግናለሁ… በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም እያለሁ አስበህ እንግዳ ስለምታደርገኝ እኔም ከልቤ አመሰግናለሁ….

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.