“ጓደኞቼ መኪና ወይም ቤት ገዝተዋል ይሄ አያዝናናኝም፤ የኔ ደስታ ብዙዎችን ረድቶ ማቆም መቻል ነው” ሳሙኤል ዮሃንስ /ፋሲል ከነማ/ የበጎ ሰው ተሸላሚ

ሀረር ተወልዶ ባህርዳር ከተማ ማደጉን ይናገራል እንግዳችን …ባህርዳር በሚገኘውና በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በሚሰለጥነው ጣና ባህርዳር የታዳጊ ፕሮጀክት ላይ ሀ ብሎ እግርኳስን ጀምሯል…በተጨዋችነት ዘመኑ ንግድ ባንክ ተስፋ ቡድን፣ የአማራ ውሃ ስራዎች፣ ከዚያ ድሬዳዋ ከተማ፣ ወልዋሎ አዲግራት ተጉዞ አሁን ለፋሲል ከነማ እየተጫወተ ይገኛል የሻምፒዮኑ ፋሲል ከነማ ወሳኝ ተጨዋችም ነው…በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ስር የነበረው ከ23 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ስር የመመረጥ እድልም አግኝቷል…ከተጨዋችነቱ በዘለለ ባህርዳር ህጻናት ማሳደጊያ 50 ህጻናትን እየረዳ በመገኘቱ የመጀመርያው የስፖርት ዞን የአመቱ ምርጥ በጎ ሰው ተብሎ ተሸልሟል ፋሲል ከነማው ሁሉገብ ተጫዋች ሳሙኤል ዮሃንስ…..

…የአመቱ በጎ ሰው ሻምፒዮኑ ሳሙኤል ዮሀንስ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ለተነሱለት በርካታ ጥያቄዎች ምላሹን ሰጥቷል።

ሀትሪክ:- በቅድሚያ እንኳን ደስ አለህ… የስፖርት ዞን በጎ ሰው ተብለህ ስትጠራ የተሠማህን ስሜት እስቲ አጋራን?

ሳሙኤል:- የፈጣሪ ተአምር ነው የሆነብኝ..ልጅ ሆኜ መሆን የምፈልገውን ነው ሆኜ ያገኘሁት…ሰው መርዳት ለሰው መኖር ያስደስተኛል…ያደረኩት ነገር ለኔ ግዴታዬ ነው ለሌላው ከመደበኛ ስራው ጎን ለጎን የሚሰራው ሊሆን ይችል ይሆናል ለኔ ግን ግዴታ ነው በቃ ለኔ ቤተሰቦቼ ናቸው በሽልማቱ መድረክ በትልልቅ ሰዎች ፊት በመቆሜ ተደስቻለሁ እግዚአብሄርን አመስግኜበታለሁ እርሱ ጤና ይስጠኝ እንጂ ወደፊት ብዙ እቅዶች አሉኝ ለሁሉም ሀገር ሰላም ይሁን…

ሀትሪክ:- ስለ በጎ ተግባርህ እናውራ….400 ህጻናት የነበሩበት ማሳደጊያ ውስጥ አሁን 50 ህጻናት ብቻ ቀርተዋል…ምክንያቱ ምንድነው?

ሳሙኤል:- የአቅም ችግር ነው የነበሩት ሰራተኞች ወጥተው አሁን በበጎ ፈቃደኞች ነው እየተሰራ ያለው .. አሁን ያሉት አስተዳዳሪ አቶ አሰግድ በረደድ ይባላሉ ከቤተሰባቸው ጋር እዚያው ግቢ ውስጥ ናቸው የሚኖሩት በርሳቸው ጥረት ነው የቆየው …በርካታ ቅርንጫፍ ማሳደጊያዎች በችግር ፈርሰው አሁን ያሉት የባህር ዳር የህጻናት መርጃና የደሴው ማእከል ናቸው የቀሩት የደሴውም እየፈረሰ ነው ማለት ይችላል…
ያሉት በቋሚነት የሚረዱበት ሌሎችም የሚገቡበትን ነው ማመቻቸት የምፈልገው…

ሀትሪክ:- እየረዳሃቸው ያሉ ሃምሳዎቹ ህጻናት ሁኔታ ምን ይመስላል?

ሳሙኤል:- በፊት የነበረው ስናይ ከጀርመን ነበር ድርጅቱ የሚረዳው… የሚገርምህ ውጪ ያሉ የሚረዱበት ሁኔታ ነበር ቤተሰብ ጋር የሚኖሩ ችግረኞችን ሳይቀር የሚረዳ መሆኑን ስታይ ምን ያህል አቅም እንደነበረው ያሳያል
የረጂዎቹ አቅም እያጠረ ሲመጣ የውስጦቹ እድሜ የጨመሩትን የማስወጣት ስራ ሊሰራም ችሏል አሁን ላይ 50 ህጻናት አሉ በትምህርታቸው ጎበዝ በመሆናቸው ስለምግብ ምናምን እንዲያስቡ እኔ ባለፍኩበት መንገድ እንዲጓዙ አልፈልግምና ከአስተዳዳሪው ጋር የምንችለውን እያደረግን ስፖንሰር እያፈላለግን እንገኛለን

ሀትሪክ:- የባህርዳር ህብረተሰብስ ድጋፍ ምን ይመስላል?

ሳሙኤል:- ኮቪድ ሲገባ ወደ ባህርዳር ተመለስኩ ታዲያ ድርጅቱን ሳየው ችግር ውስጥ ነበረና ብቻዬን ምንም ማድረግ እንደማልችል በማመኔ ሰዎችን ማሳየት ጀመርኩ በኮቪዱ ጊዜ ታዲያ የባህርዳር ወጣቶችና ባለሀብቶች ተረባርበዋል ሁላቸውም መጥተው ጎብኝተው እየተመለሱ ነው ርዳታውን ሲሰጡ የነበሩት…በወቅቱ ወጣቶቹ በጣም ሲረባረቡ ነበርና ላመሰግን እወዳለሁ

ሀትሪክ:- ለበጎ አድራጊዎች ለባለሃብቶች የድጋፍ ጥሪ እንድታደርግ እድሉን ልስጥህ?

ሳሙኤል:- አመሠግናለሁ…አንተንም ሀትሪክንም አመሰግናለሁ..መናገር የምፈልገው እነዚህ ህጻናት የኛው ልጆች የኛው ዜጋዎች ናቸው ..እኛም ነን ያለናቸው…. ቤተሰብ የለንም ብለው ቆዝመው ውጤታማ ይሆናሉ ብለን ስለማናስብ ቤተሰባዊ ፍቅር እንዲመሠርቱ አድርገናል እናም ሀላፊነት ተሰምቶን ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚችለውኝ ድጋፍ እንዲሰጠን እጠይቃለሁ ብቻዬን ምንም አላመጣምና ሁሉም ቢተባበር ደስ ይለኛልበተለይ አስተዳዳሪው አቶ በረደድ ብዙ ለፍቷልና ፍሬውን ቢያይ ደስ ይለኛል

ሀትሪክ:- የቡድን ጓደኞችህና የሌሎች ክለብ ተጨዋቾችስ ድጋፋቸው ምን ይመስላል?

ሳሙኤል:- በግሌ ርዳታ ከመጠየቄ በፊት ማእከሉን እንዲጎበኙ ነው ያደረኩት.. በዚህም ተሳክቶልኛል በተለይ 2013 በኮቪድ ምክንያት አንድ ቦታ የመሰባሰብና የመጫወት በጎ እድል ገጥሞናል… ከህጻናት ማሳደጊያው ብወጣም ተጨዋቾችን ወስጄ እያስጎበኘሁ ነበር የሊጉ ጨዋታ ባህርዳር በነበረበት ጊዜ ወደ ስድስት የሚጠጉ ክለብ ተጨዋቾችን አስጎብኝቼ እንዲረዷቸው አደርጌያለሁ አምና ወልዋሎ አዲግራትም እያለሁ ተጨዋቾቹ እንዲጎበኟቸው አድርጌ በየወሩ ተጨዋቹ በግሉ 500ብር ተቆራጭ አድርጎ በኔ በኩል ለልጆቹ እንዲደርስ ይደረግ ነበረና ጥሩ ረድተናል… እነሱንም አመሠግናለሁ

ሀትሪክ:- ልብህን ያሸነፈ በጎ አድራጊ ማነው?

ሳሙኤል:- እውነቱን ለመናገር ብዙ በጎ አድራጊዎች አሉ.. እነ መቅዶኒያ አበበች ጎበናን ምሳሌ ማድረግ ይቻላል… ስማቸውን ብዘነጋም አዛውንቶችን የሚረዱ ድሬዳዋ ውስጥም አሉ … የጠራሁልህ ድርጅቶች የቅርብ ጊዜ ናቸው የባህር ዳሩ ግን ረጅም አመት ቆይቷል ግን ብዙም አይታወቅምና እውቅና ተሰጥቶት ብዙዎች መጥተው ቢያዩት ደስ ይለኛል ድርጅቱ ሰፊ ነው 36ሺ ካሬ ላይ ነው ያረፈውና ተጨማሪ ችግረኛ ህጻናትን መያዝ ስለሚችል የሀገሬን ሰዎች ድጋፍ እጠብቃለሁ

ሀትሪክ :- ብድር በምድር ያልክ ይመስላልና እስቲ ስላደክበት የሃረሩ ህጻናት ማሳደጊያ አውራን?

ሳሙኤል:- እናትና አባቴን በልጅነቴ ነው ያጣኋቸው.. በተለይ አባቴን አላውቀውም ማለት ይቻላል ወታደር ስለነበር በግዳጅ ሄዶ ነው የቀረው ይሙት ይኑር አላውቅም ከእናቴም ጋር የኖርኩት አምስት አመቴ ድረስ ነበር ህመም ገጥሟት የጦር ሃይሎች ሆስፒታል ገባች ህክምና ብትወስድም ባለመዳኗ አረፈች ከርሷ ሞት በኋላ እዛው የወታደሮቹ ካምፕ ውስጥ ሁለት አመት ቆይቼ ወደ ሀረሩ ኾህተ ምስራቅ ህጻናት ማሳደጊያ ገባሁ.. .ወቅቱ በ1994 ማለት ነው..እስከ 2000 ድረስ አዚያው ህጻናት ማሳደጊያ ነበርኩ የቆየሁት.. የአቅም ችግር ሲመጣ ተረጂዎቹ ወደ ቤተሰባቸው እንዲቀላቀሉ ሲደረግ እኔና አምስት ልጆች ግን ቤተሰቦቻችን ሊመጡ ስላልቻሉ ወደ ባህርዳር እንድንሄድ ተደረገ..ከዚያ ወደ 2001 አካባቢ የአሰልጣኝ ደግ አደረግ ይግዛው ፕሮጀክት እንድገባ ተደርጌ ነው የእግር ኳስ ህይወቴን የጀመርኩት..

ሀትሪክ:- ተጨዋቾቻችን ቁምነገር የላቸውም ለሚሉ ወገኖች አለሁ እያልክ ነው?

ሳሙኤል:- /ሳቅ/ ተቃራኒ ተግባር ላይ ሰው ከተገኘ የመጣበትን ረስቷል ማለት ነው… ማንኛችም ትልቅ ደረጃ የደረስነውም ወይም የምንደርሰው ትልቅ ፈተናን አልፈን ይመስለኛል ይሄ የሚታወቅ ነው ለምን የመጣንበትን እንረሳለን? ሰውን የምትለየው በችግርህ ጊዜ ነው ካለህ ግን ሁሉ ጥሩ ሆኖ ይቀርብሃል ስታጣ ግን የሚቀርብህ የለምና ብሩ ምቾቱ ህይወት አጭር በመሆኗ የመጣንበትን ሳንረሳ እግዚአብሄር የሚወደውን መስራት ይጠበቅብናል..አንድ ነገር ልናገር ….ጓደኞቼ መኪና ወይም ቤት ገዝተዋል ይሄ አያዝናናኝም የኔ ደስታ ብዙዎችን ረድቶ ማቆም መቻል ነው
የወደፊቴን እግዚአብሄር ነው የሚያውቀው… እረፍት ሆኜ ስመጣ ከልጆቹ ጋር የምተኛው የምኖረው ትልቁ ፍላጎቴ ከነርሱ ጋር መኖር ነው ህጻናቶቹ አድገው ያለፉበትን ረስተው ጡት ነካሽ እንዲሆኑ አልፈልግምና በምችለው አጠገባቸው ለመሆን እሞክራለሁ በጥሩነት ተምሳሌታቸው ለመሆንም እፈልጋለሁ

ሀትሪክ:- እስቲ ስለ እግር ኳሱ እናውራ…ከአመታት በኋላ ለፋሲል ከነማ በፈረምክበት አመት ሻምፒዮን መሆንህ እድለኛ አያስብልህም?

ሳሙኤል:- በጣም እንጂ… ለፋሲል ከነማ ስፈርም ከትልቅነቱ የተነሳ ቻሌንጆች እንደሚገጥሙኝ አምኜ ነበር ከፋሲል በፊት የተጫወትኩባቸው ክለቦች ላለመውረድ የመጫወት ገጠመኞች ነበሩባቸውና የምችለውን ለማድረግ ስጥር ነው የቆየሁት… ፋሲል ከነማ ግን ጥራት ባላቸው ተጨዋቾች የተሞላ ነው አሰልጣኞቹም ጥሩ የሚባሉ ከመሆናቸው አንጻር የተሻለ ለመሆን እንድጥር አቅሜንም አሳያለሁ ብዬ ነበር የፈረምኩት እንደገባሁም እድለኛ ሆኜ የሊጉ ሻምፒዮን ሆኛለሁ ኮሮናም ገብቶ በአንድ ቦታ በመጫወት ጉልበት ሳይባክን አቅማችንን አውጥተን ሻምፒዮና ሆነናል።

ሀትሪክ:- በአፍሪካ መድረክ ተሳትፎ ምን ይጠበቅ?

ሳሙኤል:- የተሻለ ውጤት እጠብቃለሁ…. እርስ በርስ በደንብ መተዋወቃችን አሁን ደግሞ ቡድናችንን ያጠናከሩ ጥሩ ጥሩ ልጆች መፈረማቸው የበለጠ የተሻለ አድርጎናል ይሄም ለአፍሪካ ሻምፒየንስ ሊግም ይሁን ለሊጉ ፍልሚያ ጥሩ ጉልበትና ሃይል ይሆነናል ብዬ አስባለሁ ከአምናው ይልቅ ዘንድሮ የተሻለ ጥሩ እንሆናለን ብዬ አምናለሁ።

ሀትሪክ:- በቦታህ ከሀገርና ከሀገር ውጪ ያንተ ምርጥ ማነው?

ሳሙኤል:- በዋናነት የግራ መስመር ተሰላፊ ነኝ… ነገር ግን አሰልጣኛችን ሁለገብ አድርጎ ነው የሚጠቀምብኝ.. ያው አሰልጣኝ የሚልህን መስማት የግድ ነው በተፈጥሮ ቦታህ ካልአኝ ከሀገር ውስጥ አበባው ቡጣቆ ከውጪ ደግሞ የብራዚልና የሪያል ማድሪድ ተከላካይ ማርሴሎን እመርጣለሁ

ሀትሪክ:- በዋሊያዎቹ ቦታህ ያጣኸው ወይም ያልተመረጥከው ሁለገብ በመሆንህ ይሆን?

ሳሙኤል:- ይመስለኛል..የጊዜ ጉዳይ ነው የሚሆነው..ማንኛውም ተጨዋች ለሀገሩ መጫወት ይፈልጋልኮ እኔም ጋር ስሜቱ አለ…ዋናው ለሀገርህ የምትመረጠው በክለብህ በቦታህ ስኬታማ ስትሆን ነው እኔ ግን ሁለገብ ሆኜ በመሆኑ አሰልጣኞቹ ለማየት የተቸገሩ ይመስለኛል የራሴ ቋሚ ቦታ ኖሮኝ በረጅም ጊዜ ስህተቴን እያረምኩ ብሄድ ለመታየት ለመመረጥ እችል ነበር አሁን ግን ሁለገብነቴ ለቦታ ፉክክርና ለመመረጥ አላስቻለኝም ብዬ አስባለሁ በግራ መስመር ላይ ያለውም ጥሩ ተጨዋች በመሆኑ አሰልጣኜ አማራጩን ለማስፋትና እኔን ሌላ ቦታ ለመጠቀም መገደዱም ይገባኛል

ሀትሪክ:- የውጪ እድልስ አልተሞከረም ወይስ…?

ሳሙኤል:- ፍላጎቱማ አይቀርም ከሰው ጋር ቶሎ ለመግባባት ስለምቸገር ብዙ ሙከራ አላደረኩም ከዚያ ውጪ በፊት ተጨዋች የሚፈርመው ተጠይቆ ከሰው ምክር ተወስዶ ነው አሁን ግን በዲ ኤስ.ቲቪ መታየት መጀመሩ አሪፍ ነው አሰልጣኙ በራሱ ቪዲዮ አይቶ የመወሰን እድል አግኝቷል ሌሎቹም ክለቦች እኛን የማየት እድል ስላገኙ ተመልክተውኝ ወደፊት ፕሮፌሽናል የመሆን ዕድሉ ሊኖር ይችላል ብዬ እጠብቃለሁ።

ሀትሪክ:- አመቱን በስኬት ነው ያሳለፍኩት ማለት ትችላለህ?

ሳሙኤል:- አዎ በተሰማራሁበት ሁሉ ተሳክቶልኛል በፋሲል ከነማ ሁሉም ተጨዋች የሚመኘውን ሻምፒዮናነትን ሳሳካ በበጎ አድራጎት ተግባሬ መሸለሜ ደግሞ አስደስቶኛል በተለይ ሽልማቱ የበለጠ እንድሰራ ወደፊት ላሰብኳቸው ስራዎች ነዳጅ ሆኖኛል

ሀትሪክ:- ለዋሊያዎቹ ምን ትመኛለህ?

ሳሙኤል:- የህዝባችንን አስተሳሰብ መቀየር መቻል አለብን ተጨዋቹ ራሱ ብዙ ጫና አለበትኮ አንዳንዴ ለራሳችን የምንነግረው መጥፎ ልማድ አለ ያ መስተካከል አለበት እንደምንችል ተረድተን ሀገር እያሰብን መጫወት አለብን ያኔ ነው የሚሳካልን… ከ31 አመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ ያስቀየርነው ሃሳብ አለ አሁን ለካ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ እንችላለን አልን…እናም አሁንም ህዝቡ ከጎናቸው ሆኖ ሊያግዛቸው እነሱም እንደሚችሉ አምነው ሊተጉ ይገባል ለዋሊያዎቹ መልካም ውጤት እመኛለሁ

ሀትሪክ:- ለኢትዮጵያስ ምን ትመኛለህ..? /

ሳሙኤል:- ለውዷ ሀገሬማ ሰላም ነው የምመኘው… ማንም ወጥቶ የሚገባው ህልሙን ለማሳካት የሚጥረው ሰላም ካለ ነውና ለሀገሬ ሰላም እመኛለሁ እንደ ተጨዋች ሳልሳቀቅ እንድተጋ ሰላም ወሳኝ ነው…ሰላም ከሌለ ቡድንህን ይጎዳል ይከፋፍላልና ሰላም ወሳኝ ነው…ተጨዋቹ ከተለያየ ቦታና ብሄር የመጣ በመሆኑ መከባበርና መናበብ የሚኖረው ሰላም ካለ ብቻ ነውና አገሬን ሰላምሽ ይብዛ እላለሁ…

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport