“ዲሲፕሊን ሳታከብርና አንደበትህን ሳትቆጣጠር ለሰው ተምሳሌት መሆን አይቻልም” ስዩም ተሰፋዬ /ኢት.ቡና/

በከፍተኛ ሊግ የእግርኳስ ህይወቱን ጀምሯል…በተጨዋችነት ዘመኑ በታችኛው ሊግ የተጫወተው ለሁለት ክለቦች ለደብረብርሃን ብርድልብስና መተሃራ ስኳር ብቻ ነው… ከዚያም ወደ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች አቅንቶ ለኒያላ፣ ለመብራት ሃይል፣ ለደደቢትና ለመቀለ 70 እንደርታ ከተጫወተ በኋላ አሁን ለኢትዮጵያ ቡና ፊርማውን አኑሯል የረጅም አመት ልምዱን ለመጠቀም አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ከ31 አመት ለአፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ የቡድኑ አባል የነበረውንና ከዲሲፕሊን ጋር ራሱን ጠብቆ አሁን ድረስ እየተጫወተ ያለውን ስዩም ተስፋዬን አስፈርሞታል…. ከሃትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝጋር ቆይታ ያደረገው ስዩም ተስፋዬ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሹን ሰጥቷል

ሀትሪክ:- ለረጅም አመታት በተጨዋችነት የመቀጠልህን ምስጢር እስቲ አውጋን…?

ስዩም:- የተለየ ምንም ምስጢር የለም የተለየ ልምድም የለኝም ግን በብዙ መንገድ ራሴን እቆጣጠራለሁ ስፖርቱ የሚፈልገውን ዲሲፕሊን አከብራለሁ ማረፍ ያለብኝ ጊዜ አርፋለሁ አመጋገቤን አስተካክላለሁ ለጨዋታዎች ትኩረት እሰጣለሁ ልምምዴን በአግባቡ እሰራለሁ..የሚያስፈልገውን አደርጋለሁ ዋናው ምክንያት ይሄ ይመስለኛል

ሀትሪክ:- አሸነፍኩ የምትላቸውን ዋንጫዎች እስቲ ዘርዘር አድርግልን..?

ስዩም:- ከታች ከከፍተኛ ሊግ መተሃራ ስኳር ወደ ፕሪሚየር ሊግ ሲገባ ዋናው ተጨዋች ነበርኩ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ስንገባ ዋንጫውን ወስጃለሁ የውድድር አመቱ ኮከብ ተጨዋች ሆኜ ተመርጫለሁ ሌላው ከደደቢትና ከመቀለ 70 እንደርታ ጋር የሊጉን ዋንጫ አንስቻለሁ እነኚህ ናቸው ሌሎች የሲቲ ካፑ ዋንጫዎች ሳይቆጠሩ ማለቴ ነው…

ሀትሪክ:- በተጨዋችነት ዘመንህ ምርጡ ጊዜህ መቼ ነው..?

ስዩም:- የመቀለ 70 እንደርታ ምርጡ ጊዜዬ ነው በቆይታዬም ደስተኛ ነኝ በርግጥ ለደደቢት ረጅም ጊዜ ተጫውቼ የሊጉን ዋንጫ ማንሳቴ ቢያስደስተኝም በርካታ ደጋፊ ከመኖሩ አንጻር በመቀለ 70 እንደርታ ያሳካሁት ዋንጫና ቆይታዬን እወደዋለሁ መቀለ በገባሁበት አመት ነው ዋንጫ ያነሳሁት ከበርካታ ደጋፊም ጋር ደስታዬን እንደመግለጼ ምርጫዬ የመቀለ 70 እንደርታ ድሌ ነው

ሀትሪክ:- አንተ ለመቀለ 70 በፈረምክበት አመት ዋንጫ በማንሳታችሁ ራስህን እንደ ዕድል ጠሪ ታያለህ..?

ስዩም:- /ሳቅ/ እንደዛ አላስብም በዋናነትም በስራ እንጂ በእድልም አላምንም

ሀትሪክ:- ዕድል የለም እያልክ ይሆን…?

ስዩም:-/ሳቅ/ አላልኩም ዕድልማ አለ ወሳኝነትም እንዳለሁም አምናለሁ ግን ከስራ በፊት እድል አላስቀድምም ምንም ነገር ሳይሰራ እድልን መጠበቅ ይከብዳል ሰርቼ እድሌን እጠቀማለሁ ብዬ ነው የማምነው

ሀትሪክ:- ከ31 አመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ያለፈው የአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቡድን አባል ነህና …እስቲ ጊዜውን ስታስብ ትዝ የሚልህ ምንድነው..?

ስዩም:- ከ31 አመት በኋላ ማለፋችን ህዝቡ ላይ የፈጠረው ደስታ የዚህ ቡድን አባል መሆን የፈጠረው ኩራት አይረሳኝም ምክንያቱም ያን ታሪክ ድጋሚ ልስራው ብትል አይቻልም በዚሁ ጎን ያለፍን ጊዜ ህዝቡ ቤተሰቦቼ ጋር ሄዶ በጋራ ጨፍረው ያሳለፉት ደስታ አይረሳም የሚገርም ጊዜ ነበር

ሀትሪክ:- ከአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቡድን ስብስብ ውስጥ አሁን ለዋሊያዎቹ እየተጫወቱ ያሉት ስንት ናቸው..?

ስዩም:- ከእኔ ውጪ ሽመልስ በቀለ፣ ጀማል ጣሰውና ጌታነህ ከበደ ይመስሉኛል

ሀትሪክ:- በዚያ ቡድን ውስጥ ከነበሩ ምርጥ ነገሮች መሃል በአሁኑ ስብስብ ውስጥ የለምና ቢጨመር የምትለው ነገር አለ..?

ስዩም:- የቡድኑ አባል ባለመሆኔ ይሄ ነገር ቢኖር ለማለት ይቸግረኛል በቲቪ መስኮት እንደ ህዝቡ እያየሁ ብዙ
መናገር ይከብደኛል ቡድኑ ውስጥ ብኖር መናገር ይቀለኝ ነበር ለማንኛውም ሌላ ሚዲያ ላይ ገልጬዋለሁ ከ8 አመት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ሳያልፉ በፊት ተጨዋቾቹ አቅም አላቸው ወጣቶች የበዙበት ቡድን ነው ግን ጊዜ ያስፈልጋቸዋል ጊዜ ከተሰጣቸው ብዙ ነገር ማሳካት ይችላሉ ብዬ ተናግሬ ነበር ያሰብኩትም መሳካቱ አስደስቶኛል ያላቸው አቅም ጥሩ ነው በግሌ ማለት የምፈልገው አሁን ለአፍሪካ ዋንጫ አልፈዋል በእኛ ጊዜ ማሳካት ያልቻልነውን እንዲያሳኩ እመኛለሁ አንድ ደረጃ እንዲጨምሩ እግዚአብሄር ይርዳቸው በቅርብ ጊዜም ከደቡብ አፍሪካ ጋር ባላቸው ጨዋታ ድል እንዲቀናቸው እመኛለሁ

ሀትሪክ:- በዋሊያ አባልነት ያጣጣምከው ደስታ እንደመኖሩ የአሁኑ ብሄራዊ ቡድን አባል ብሆን ብለህ አልጓጓህም..?

ስዩም:-/ሳቅ በሳቅ/ አይ መስፈርቱ ብቃት ብቻ ነው ብለህ ነው..? አይመስለኝም አሁን ካለህ አቅምና ልትሰጥ ከምትችለው ጥቅም በላይ ያሳለፍከውን አመት ነው የሚያሰሉት ለብሄራዊ ቡድን ለመጫወት መለኪያው መች ብቃት ሆነ? የኮታ ምደባ ነው የሚመስለው.. ምርጫውና ጥሪው አቅም ላይ ብቻ አልመሠለኝም

ሀትሪክ:- ረጅም አመት መጫወት ሽማግሌ ነው ለማለት በቂ ነው..?

ስዩም:- እኔ የሚገርመኝ እሱ ነው.. አንድ ነገር ላስታውስ.. ብሄራዊ ሊግ መጫወት የጀመርኩት ዘጠነኛ ክፍል ላይ ሆኜ ነው አጀማመሬን ማንም አያውቅም የሆነ ጊዜ ለብሄራዊ ቡድን ተጫውተሃል ስምህ የሆነ ጊዜ ይታወቃል ይሄን አመት ለብሄራዊ ቡድን ተጫውቷል ይባልና ያንተ ነገር ያበቃል ከዚያ ውጪ ምን እያሳየ ነው አቅሙ አሁንም አለ ወይ ብሎ የሚገመግምህ አታገኝም ይሄ መታረም አለበት

ሀትሪክ:- አንተ ግን አቅሙ አለኝ ብለህ ታስባለህ..? ውስጥህ የሚነግርህ ይህን ነው?

ስዩም:- ምንም ጥያቄ የለውም ለዋሊያዎቹ ለመጫወት አቅም አለኝ …አሁን ሳልደብቅ መናገር የምፈልገው አንድ ነገር አለ አገሬን በደንብ በማገልገሌ ለዋሊያዎቹ የመመረጥ አቅም ቢኖረኝም የመጫወት ፍላጎቱ ግን የለኝም በቃ ሌሎች ተጨዋቾች ደግሞ ቦታውን ይዘው ሌላ ታሪክ ለመስራት ይጣሩ ….

ሀትሪክ:- አሰልጣኝ ካሳዬ አንተን ማስፈረሙ ታዲያ የተለየ አይን እንዳለው ያሳያል ማለት ይቻላል..?

ስዩም:- አዎ ምን ጥያቄ አለው..? ሌላ ቦታ ያልኩትን ነው የምደግመው…ብዙዎቹ አሰልጣኞች አቅምህን አይተው ሳይሆን በሚዲያና በፌስቡክ አይተው ስለሆነ የሚመርጡት ክፍተት አለባቸው ካሳዬ ግን ይለያል..ስልጠናውን አይቻለሁ በጣም የተለየ መሆኑ ገርሞኛል እስካሁን ያላገኘሁትን ነው ከርሱ ያገኘሁት… በተጨዋችነት ዘመኔ ለምጄ የመጣሁት ስልጠና ስላለ የአሁኑ አዲስ ልምምድ ሲመጣ ለመልመድ ጊዜ ይወስዳል ለወጣቶቹ ለታዳጊዎቹ ግን ከስር ቢሰራባቸው ከፍተኛ ለውጥ ያመጣሉ ብዬ አስባለሁ የማልዋሸው ግን በካሳዬ ልምድ ተገርሜያለሁ

ሀትሪክ:- ለኢትዮጵያ ቡና ለመፈረም የካሳዬ መኖር ተጽዕኖ አሳድሯል ማለት ይቻላል..?

ስዩም:- አዎ ለቡና ለመፈረም የርሱ መኖር ትልቅ ድጋፍ ሆኖኛል…. ከዚህ በፊትኮ ለኢትዮጵያ ቡና እንድፈርም ሁለቴ ተጠይቄ አልተስማማሁም ነበር አሁን ግን ለካሳዬና ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት በመቻሌ ደስ ብሎኛል

ሀትሪክ:- ከኮንፌዴሬሽን ካፕ በመጀመሪያ ዙር መሠናበት አያበሳጭም….? ለሽንፈቱስ ዋነኛ ምክንያት ምን ይመስልሃል..?

ስዩም:- ኡጋንዳ በነበረው ጨዋታ ላይ ተጠባባቂ ነበርኩና በደንብ የታዘብኩት ነገር ነበር…. በተለይ ከዕረፍት በኋላ ሙሉ በሙሉ የጨዋታ ብልጫ ወስደንባቸው በርካታ የግብ ሙከራ አድርገናል እንደዛ ሆኖ 2 ለ 1 አለቀ ያን ስታይ በአሪፍ ሁኔታ እንደምታሸንፍና ውጤቱን እንደምትቀለብሰው ትረዳለህ ጥሩ መሆናችን በሀገራችን በምናደርገው የመልስ ጨዋታ እንደምናሸንፍ ርግጠኛ ነበርን ግን አልተሳካም ያበሳጫል….ጫና ፈጥረን እንደምንጫወት ስለገባቸው በመልሱ ጨዋታ ጥቅጥቅ ብለው ነበር ሲከላከሉ የነበረው….የእነሱን ለማስከፈት ሙሉ በሙሉ ወደ ማጥቃት ስንገባ ነው እነሱ አጋጣሚውን ተጠቅመው ያስቆጠሩትና ያሸነፉን..በዚያ ሁሉ ብልጫ አለማሸነፋችን ቅር ያሰኛል

ሀትሪክ:- የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች እንዴት ተቀበሉህ…?

ስዩም:- ሁለት አይነት ዕይታ አለው.. በተወሰነ መልኩ በጥሩ ሁኔታ የተቀበሉኝም አሉ በተቃራኒውም የሆኑ አሉ ስሜቱ ይለያያል … አሁን ያለኝን አቅምና ልሰጥ የምችለውን ጥቅም እያሰቡ በጥሩ ጎኑ የተቀበሉኝ እንዳሉ ሁሉ የተጫወትኩባቸውን ጊዜያት እያሰቡ የተቃወሙም አሉ ….እናም አቀባበሉ ሁለት ስሜቶች አሏቸው/ሳቅ/ ይሄ ለኔ አዲስ ባለመሆኑና ሲኒየር ተጨዋች እንደመሆኔ አልደነገጥኩም አልተረበሽኩም

ሀትሪክ:- ኢትዮጵያ ቡና በወጣቶች የተሞላ እንደመሆኑ ከልምድህ እያካፈልካቸው ነው..?

ስዩም:- አዎ….ግን በደንብ ላግዝ ልናገር ሳትልም ታወራዋለህኮ..ልምዱ ውስጤ አለ… ልናገር ብዬ ሳይሆን ሁኔታው እንድታወራ ያደርግሃል ፎርማል በሆነ መንገድ ሳይሆን እኔ ያሳለፍኩትን እነሱ ያልደረሱበትን እየተነጋገርን የጎዳኝንም ሆነ የጠቀመኝን እየነገርኳቸው እየተማማርን ነው በዚህም ደስተኛ ነኝ

ሀትሪክ:- የዲ ኤስ ቲቪ ጅማሮንስ እንዴት አየኸው..?

ስዩም:- በጣም ትልቅ ትርጉምማ አለው…እይታው ራሱ ይሰፋል.. ለአሰልጣኞች፣ለጋዜጠኞች፣ ለተመልካቹ ሳይቀር ትልቅ ጥቅም አለው። በተለይ ለናንተ ለሚዲያዎች ለመፍረድ ይሁን ለመተቸት ለማድነቅም ይጠቅማል። ተጨዋቹም ከዚህ አገር ወጥቶ በፕሮፌሽናልነት ለመጫወትም ቪዲዮዎችን ለማግኘትም ይቀላል።

ሀትሪክ:- ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ ተገቢ ጥንቃቄ አላደረገም የሚሉ ወገኖች አሉ… አንተስ ምን ትመክራለህ…?

ስዩም:- የሚገርመኝ ይሄ ነው….ኮቪድን ከመከላከል አንጻር ሰው እንዴት ለራሱ ህይወት ምክር ይፈልጋል..? ተነግሮናል አደጋውና ስርጭቱ መጨመሩን ተረድተናል እንዴት አንጠነቀቅም? ይሄ ጉዳይ ምክር አይጠይቅም ምናልባት ለማስታወስ ያህል ሊነገር ይችል ይሆናል በአጠቃላይ ለመላው ህብረተሰቡ የምለው ነገን ለማለም ዛሬ ላይ ተገቢውን የመከላከል ርምጃ ልንወሰድ ይገባል

ሀትሪክ:- ስዩም ተስፋዬ…መዝናኛው ምንድነው..?

ስዩም:- እንዲህ ነው ብዬ መናገር ይከብደኛል አላውቀውማ..በኳስ ፣ ከቤተሰቦቼ ጋር ስሆን፣የሆነ ቦታ ከጓደኞቼ ጋር ስንበላ ስንጠጣ ሊሆን ይችላል የተፈጠረው ሁኔታ ላይ በጣም ልዝናና እችል ይሆናል እንጂ ይሄ ነው የምለው የለም ጥሩ መጽሃፍም ሊያዝናናኝኮ ይችላል ፌስቡክ ላይ ባየሁት ልዝናና እችልም ይሆናል ከዚያ ውጪ የሚያዝናናኝ ይሄ ነው ማለት አልችልም።

ሀትሪክ:- ባለትዳርና የሁለት ልጆችአባት….አስተዋውቀና..?

ስዩም:- /ሳቅ/ ባለትዳር ነኝ ባለቤቴ መታሰቢያ ተገኔ ትባላለች ልጆቼ ራፋኤል ስዩምና ላምሮት ስዩም ይባላሉ በጣም እወዳቸዋለሁ….በነሱም ደስተኛ ነኝ

ሀትሪክ:- ራፋኤል….አዲሱ የማን.ዩናይትድ ተከላካይ ራፋኤል ቫራን አድናቂ ስለሆንክ ወይስ ለሀገሩ ተከላካይነት እንደ እሱ እንዲሆን ፈልገህ..?

ስዩም:- /ሳቅ በሳቅ/ አይደለም አይደለም ብዙ ታሪክ አለው አሁን የምናገረው አይደለም /ሳቅ/

ሀትሪክ:- ከመልካም ስነምግባር ጋር ትዳርህን በሰላም መምራትህ ሲታይ ሞዴል ነህ መባሉ ያንስብሃል..?

ስዩም:- /ሳቅ/ አዎ አያንስብኝም እንደ ዜጋ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን አገልግያለሁ በክለብ ደረጃ ረጅም ጊዜ ተጫውቻለሁ…ቤተሰቤን በጥሩ መንገድ እየመራሁ ነው…የስፖርቱን ዲሲፕሊን አክብሬያለሁ ይሄ ሞዴል ለመባል ያስችላል…ግን ይሄ ብቻ በቂ አይደለም ዲሲፕሊን ማክበር አኗኗር ላይ መልካም ሰው መሆንም የግድ ነው ዲሲፕሊን ሳታከብርና አንደበትህን ሳትቆጣጠር ለሰው ተምሳሌት መሆን አይቻልም ከስፖርቱ ውጪም በብዙ መንገድ በአኗኗር ጭምር ሞዴል መሆን ይቻላልና ይሄ ላይ ቢተኮር ደስ ይለኛል

ሀትሪክ:- ባለቤትህን አመስግናት መልዕክት እንድታስላልፍላት ዕድሉን ልስጥህ..?

ስዩም:- ባለቤቴ መታሰቢያን በጣም ነው የምወዳት የሁለት ልጆች አባት አድርጋኛለች ህይወቴን እንድደሰት በተጣጣመ ሁኔታ እንድመራ አድርጋለችና በጣም ነው የማመሰግነው እርሷ እናት ጭምር ናት ከዚያ ውጪ ቤተሰቦቼ ሁሉ ሰላም እንዲሆኑ ሀገር ሰላም እንድትሆን እግዚአብሄር ልጆቼንም ኢትዮጵያንና ህዝቧን እንዲጠብቅም እጸልያለሁ።

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport