የምድብ ለ ሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ በሁለቱ የአማራ ክልል ክለቦች በባህርዳር እና ፋሲል ከተማ ከቀኑ በ8 ሰአት ጅማሬውን አደረገ ።
ጨዋታው ከጅማሬው ፈጣን እንቅስቃሴን ያስመለከተ ነበር ። ጨዋታው በተጀመረ ገና በ9ኛው ደቂቃ ላይ ኤርትራዊው የባህር ዳር ከተማ ተጫዋች አሊ ሱሌማን ግራ እጁ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ምክንያት በኪዳነ ማርያም ተስፋዬ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል ።

ፋሲል ከነማዎች ኳሶችን በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በማድረስ ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል ። በተለይም በኦኪኪ አፎላቢ በበረከት ደስታ እንዲሁም በሀብታሙ ተከስተ አማካይነት ጥሩ የሚባሉ የግብ ሙከራዎችን አድርገዋል ።
በባህርዳር ከተማ በኩል ኳሱን በመቆጣጠር በአንድ ሁለት ቅበብል ወደ ግብ ለመድረስ ቢሞክሩም ፍፁም አለሙ በቅጣት ምት ከሞከረው ውጪ ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ አላደረጉም ።
የጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ እንደተጀመረ በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚመራው ፋሲል ከነማ ሁለት ቅያሪዎችን አድርጎ ወደ ሜዳ ገብቷል ። በነዚህ ቅያሪዎችም ጫና ፈጥረው በመጫወት ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል ምንም እንኳን የባህርዳር የተከላካይ መስመርን እንዲሁም ግብ ጠባቂውን የፈተኑ ሙከራዎችን ባያደርጉም ።

በአንፃሩ ባህርዳር ከተማዎች በፍፁም አለሙ እንዲሁም በኪዳነማርያም ተስፋዬ አማካይነት አስቆጪ አጋጣሚዎች መፍጠር ችለው ነበር ። በተጨማሪም ተቀይሮ በገባው ኒኪማ አማካይነት ወደ ፋሲል ግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመድረስ ሲጥሩ ተስተውሏል ።
በአጠቃላይ ሁለቱም ክለቦች ከጨዋታው 3 ነጥብ ይዘው ለመውጣት ጥረት ቢያደርጉም ኳስን ከመረብ የሚያገናኝላቸው ተጫዋች ማግኘት አልቻሉም ። በመጨረሻም ጨዋታቸውን ያለምንም ግብ በማጠናቀቅ አንድ አንድ ነጥብ ይዘው ከሜዳ ወጥተዋል ።

በጨዋታው የባህር ዳር ከተማን ቡድን በአምበልነት ሲመራ የነበረው ተከላካዩ አህመድ ረሺድ የጨዋታው ኮከብ በመባል የተመረጠ ሲሆን የተዘጋጀለትን የዋንጫ እና የ12,000 ብር ሽልማት ተረክቧል ።

በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የነበረው በቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ ነበር ።
ጨዋታው በጅማሮው ቀዝቀዝ ያለ ቢሆንም ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር በሁለቱም ክለቦች በኩል ግብ ለማስቆጠር የተለያዩ ጥረቶች ተደርገዋል ።
ገና በጨዋታው 30ኛ ደቂቃ የነበረው ሀይልን የቀላቀለ ጨዋታ ምክንያት በማድረግ በሚመስል መልኩ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሁለት ቅያሪዎችን አድርገዋል ። በጨዋታው 38ኛ ደቂቃ ላይ በአዳማ ከተማ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በተሰራ ጥፋት ምክንያት ቅዱስ ጊዮርጊስ የፍፁም ቅጣት ምት አገኙ የተገኘዉን ፍፁም ቅጣት ምትም አምበሉ ሀይደር ሸረፋ አስቆጥሮ ፈረሰኞቹ መሪ እንዲሆኑ አስቻለ ።

ከግቧ መቆጠር በኋላ አዳማ ከተማዎች ብልጫ በመውሰድ ወደ ግብ ለመድረስ ቢሞክሩም ምንም ግብ ሳያስቆጥሩ የመጀመሪያው አጋማሽ በቅዱስ ጊዮርጊስ 1 ለ 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ መጀመር በኋላ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እንዲሁም በአዳማ ከተማ በኩል የአቻነቷን ግብ ለማስቆጠር እንቅስቃሴዎችን አድርገዋል ።
ነገር ግን በሁለቱም በኩል ወደ ግብ ለመድረስ የሚያደርጉት ሙከራ በተጋጣሚ ተከላካዮች ሲመክኑ ተስተውሏል ። አዳማ ከተማዎች ግብ ለማስቆጠር በተለይም በአምበሉ ዳዋ ሆቴሳ አማካይነት ሙከራዎችን አድርገዋል ።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል በ90+1 ደቂቃ ላይ አብርሀም ተስፋዬ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶት የግብ አግዳሚው የመለሰበት ኳስ አስደናቂ ነበር ።
በመጨረሻም የመደበኛው 90 ደቂቃ መጠናቀቅ በኋላ አራተኛው ዳኛ ተጨማሪ 5 ደቂቃዎችን ያሳዩ ሲሆን በነዚህ ደቂቃዎችም ምንም ግብ ሳይቆጠር ጨዋታው በፈረሰኞቹ 1 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቀቀ ።
የጨዋታውን ኮከብነት የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካይ ያብስራ ተስፋዬ ሆኖ የተመረጠ ሲሆን የዋንጫ እና የ12,000 ብር ሽልማት ተበርክቶለታል ።

በዚህም መሰረት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከምድብ ማለፉን ሲያረጋግጥ አዳማ ከተማ ደግሞ ከምድቡ መውደቁ ተረጋግጧል ። የምድብ ለ ቀጣይ ጨዋታዎች በመጪው እሁድ የሚካሄዱ ይሆናል ።

አስተያየት ይስጡ