መነሻ ገጽ The BiG Interview “ቀደም ሲል በእግር ኳስ አንድ ትውልድ ጠፍቷል፤አሁን ያለውን ትውልድ ለማጥፋት የሚንቀሳቀስ የተደራጀ ቡድን አለ” አቶ አስናቀ ደምሴ (የሕግ ባለሙያና የአዲስ አበባ አሰልጣኞች ማህበር ም/ ፕሬዝዳንት)
The BiG Interview

“ቀደም ሲል በእግር ኳስ አንድ ትውልድ ጠፍቷል፤አሁን ያለውን ትውልድ ለማጥፋት የሚንቀሳቀስ የተደራጀ ቡድን አለ” አቶ አስናቀ ደምሴ (የሕግ ባለሙያና የአዲስ አበባ አሰልጣኞች ማህበር ም/ ፕሬዝዳንት)

አጋራ
አጋራ

ይስሀቅ በላይ

“ኦኪኪ አፉላቢ የፕሬዝዳንቱን ፊርማ አጭበርብሮ በሕግ ሊጠየቅ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ ሊደረግ ሲገባ እሳቸው የሚመሩት ፌዴሬሽን ግን እንዲጫወት ጭራሽ ውሉን በማፅደቅ ወንጀሉን አበረታቷል”
→”አሰልጣኝ ነኝ” ብሎ መናገር በራሱ የሚያስፈራበት፤ የሚያሸማቅቅበት ደረጃ ላይ ደርሷል”

የአዲስ አበባ አሰልጣኞች ማህበርን በምክትል ፕሬዚዳንትነት የሚመራው የቀድመው የኪ.ቢ.አ.ድ አሰልጣኝ የነበረው አቶ አስናቀ
ደምሴ ክፉኛ ተቆጥቷል፤ በተለይ በቅርቡ ፌዴሬሽኑ 60 ለሚሆኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሰዎች የኢንስትራክተርነት ከርስ መስጠቱ
ከማስቆጣት አልፎ የሕግ ጥሰት ተፈፅመበታል በሚል ይቃወማል፤ በዚህ ሳያበቃ ኮርሱ የተሰጣቸው ብቻ ሳይሆኑ ኢንስትራክተር
ተብለው ኮርሱን የሰጡት ላይ የሚመዘዝባቸው የተገቢነት ጥያቄ አለ በማለት አምርሮ ይቃወማል፤
የተሰማውን ፊት ለፊት በመናገር ብቻ ሣይሆን ድፍረት በተሞላባቸው ጠንከር ያሉ አስተያየቶች የሚታወቀው የሕግ ባለሙያውና
የአዲስ አበባ አሰልጣኞች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አስናቀ ደምሴ የጅማ አባጅፋሩ ኦኪኪ አፉላቢ በአገርና በሕዝብ ላይ
የማጭበርበር ስራን ሰርቶ ወደ አገር ቤት እንዳይገባ መከልከል ከገባም በሕግ ሊጠየቅ ሲገባው የማጭበርበር ሙከራ የተደረገባቸው
ሰው የሚመሩትት ፌዴሬሽን በወንጀል ሳይጠይቅ እንዲጫወት በመፍቀድ አጭበርባሪነትን አበረታተዋል በማለት ይናገራል። በተለምዶ
መኢሠማ ህንፃ ተብሎ በሚጠራውና 3ተኛ ፎቅ በሚገኘው የአቶ አስናቀ ደምሴ ቢሮ የተገኘው የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር
ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ አነጋጋሪና ያልተደፈሩ ጉዳዮችን በድፍረት አንስቶ ያገኘውን ድፍረት የተሞላበት ምላሽ ከዚህ በታች ባለው መልኩ
አጠናክሮ አቅርቦታል፡፡

ሀትሪክ፡-የሀገሪቱ እግር ኳስ ከእኛ ሀገር ተጨዋቾች የተሻለ አቅም በሌላቸው ተጨዋቾች ተወሯል በማለት ብዙም ልዩነት የሌላቸው
የውጪ ሀገር ተጨዋቾች በሀገራችን ሊግ መበርከታቸውን የሚቃወሙ አሉ፤ አንተስ በዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ…?
አቶ አስናቀ፡- የውጪ ተጨዋቾች ወደ ሀገራችን ለምን መጡ…?… የሚል ጥሩ የሆነ አመለካከት የለኝም…፤ ጥያቄው ተጨዋቾች
መምጣታቸው ላይ ሳይሆን እንዴት ነው የሚመጡት…?… ከእኛ ሀገር ተጨዋቹ አንፃር… ያላቸው ልዩነት ምንድ ነው…? የሚለው ነው
በደንብ መፈተሽ ያለበት፡፡ አሁን ከምናየው አንፃር ይህ ነገር የተሰመረበት አይመስልም፤ ፍፁም ከእኛ ሀገር ተጨዋቾች የማይሻሉ
ናቸው ፕሮፌሽናል ተብለው የሚመጡት፡፡ ይሄ ለእኔ በሀገር እግር ኳስ በህዝብ ገንዘብ መቀለድ ነው፡፡ ከውጪ የሚመጡ ተጫዋቾችን
በተመለከተ አንድ በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነገር ልንገርህ…

ሀትሪክ፡-… ምን..?…

አቶ አስናቀ፡-…እዚህ ሀገር ምን እየተሠራ እንደሆነ ግራ ይገባሃል…!…ለጅማ አባጅፋር የሚጫወተውን አፎላቢ የሚባለውን ናይጄርያዊ
ተጨዋች ታውቀዋለህ…?

ሀትሪክ፡-…አዎን …ኦኪኪ አፎላቢ… ?…

አቶ አስናቀ፡- …ይህ ተጫዋች… ኢትዮጵያ ውስጥ መጫወት አይደለም… መግባት ነበረበት…?

ሀትሪክ፡- …ማለት አልገባኝም፤…?

አቶ አስናቀ፡- …አልገባኝም… የምትለው… ይሄ ተጨዋች… በሀገር ላይ ምን እንደሠራ…?…ምን አድርጎ… ወደ ግብፅ እንደሄደ ጠፍቶህ
ነው…? …የሚዲያ ሰው ሆነህ ይሄ ይጠፋሃል ብዬ አላስብም…፤…በጣም የሚገርመው ይሄ የጅማ አባጅፋር ተጨዋች የፌዴሬሽኑን
ፕሬዝዳንት ፊርማ አስመስሎ ማጭበርበሩ ታውቆ በሕግ ሊጠየቅ ወደ ሀገር ቤት እንዳይገባ ሊደረግ ሲገባው እሳቸው የሚመሩት
ፌዴሬሽን የተጨዋቹን ውል አፅድቆ እንዲጫወት ጭራሽ ፍቃድ ሰጥቶት ወንጀልን አበረታቷል፡፡ የፌዴሬሽኑን ፕሬዝዳንት ፊርማ
ለማጭበርበር ሞክሮ እንዴት ነው ፌዴሬሽኑ የተጨዋቹን ሕጋዊነትና ተገቢነት ተቀብሎ ውሉን የሚያፀድቅለት?ፊርማቸው

የተጭበረበረባቸው የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንትስ እንዴት ዝምታን ይመርጣሉ?ነው ወይስ ቀድመው ያውቃሉ?…ይሄ ተጨዋችስ ወደ ጨዋታ
ነበር መሄድ የነበረበት ወይስ ወደ ሕግ ፊት? የሆነው ግልፅ ነው… ተጨዋቹ ወደ ሜዳ እንዲመለስ ነው የተደረገው፡፡ ይሄን ማድረግ
ምን ማለት ነው? ምን አይነት መልዕክት ነው የሚያስተላልፈው? ተጨዋቹ የሀገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ፕሬዚዳንት ፊርማ
የማስመሰል፣ የማጭበርበር ሙከራ አድርጎ እንኳን ሊጠየቅ የገሰፀው ሠውእንኳን የለም፡፡ ይሄ ለእኔ የሚሰጠኝ ትርጉም በፌዴሬሽኑ
ስም በፕሬዚዳንቱ ስም ማጭበርበርና ለማጭበርበር መሞከር በወንጀል እንደማያስጠይቅና አስመስለህ ፊርማ ማጭበርበር መዝረፉ
ሁሉ የተፈቀደ ያህል አድርገህ እንድታስብ የሚያደርግ ነው የሚመስለው፡፡ ደግሞስ ለማጭበርበር ለማታለል የሞከረን ሰው እንዴት ነው
የተጭበረበረው ሰው በፕሬዚዳንት የሚመራው ፌዴሬሽን የመጫወት ፍቃድ የሚሰጠው ከዚህ ውጪ ደግሞ…

ሀትሪክ፡-…ከዚህ ውጪ ደግሞ ስትል…..?

አቶ አስናቀ፡-…ከዚህ ውጪ ደግሞ ከላይ ካነሣሁት የማጭበረበር ሙከራ በተጨማሪ በጉዳቱ ምክንያት የበርካታ ተጨዋቾችን እድል
ነጥቀን እንዲጫወት መፍቀድ አልነበረብንም፤ ምክንያቱም ይህ ተጨዋች ግብፅ ለሙከራ ሄዶ በጉዳት ምክንያት ነው የተቀነሰው፡፡
በዚህ ደረጃ ከግብፅ የተቀነሰን ተጨዋች ለሀገራችን ተጨዋቾች የሶስትና የአራት ወር ደሞዝ ሳትከፍል እሱ ግን ወንጀለኛና በጉዳት
ከግብፅ የተባረረ ተጨዋች ሆኖ በአካውንቱ ብሩ በዶላር ገብቶለት መጥቶ እንዲጫወት ነው የተደረገው፡፡ ይሄ ምን አይነት ሞራል
የጎደለው አሠራር ነው? የሀገራችንን ተጨዋቾች በዚያ ደረጀ አሳንሰህ ምን አይነት ሞራልስ ነው የሚኖራቸው? ደግሞስ ከግብፅ በሽተኛ
ነው ተብሎ የተባረረን ተጫዋች እኛ ዋናው የቡድናችን ተጨዋች አድርገን ነገ እንዴት ነው ግብፅን ገጥመን ውጤት የምንጠብቀው?
ይሄ ለእኔ የልጆች ጨዋታ ብቻ ሳይሆን በሀገር ሀብትና በሀገር ስፖርት ላይ መቀለድ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …የውጭ ተጨዋቾችን ገዳይ አንስተን የሀገሪቱ እግር ኳስ በውጭ ግብ ጠባቂያዎች መጥለቅለቁን ሳናነሳ ብናልፍ የሚወቅሰን
አይጠፋምና የሀገሪቱን እግር ኳስ ስለወረሩት የውጭ ዜግነት ያላቸው ግብ ጠባቂዎች ምን ትላለህ…?

አቶ አስናቀ፡- …እኛ በጣም ችላ ያልነው ግን የእግር ኳሱ በጣም አሳሳቢው ጉዳይ ሊጉ የውጪ ሀገር ዜግነት ባላቸው ግብ ጠባቂዎች
መጥለቅለቁ ነው፤ አሁንም መጀመሪያ ካልኩህ ጋር ተመሳሳይ ነው አቋሜ…፤ የውጪ ግብ ጠባቂ አይምጣ አይደለም…ልጓም ግን
ሊበጅለት ይገባል…፡፡…እግር ኳሳችን በከፍተኛ የግብ ጠባቂ ድርቅ ተጠቅቷል…፤ በክለብም በብ/ቡድን ደረጃም በረኛ አለን
የሚያስብል ደረጃ ላይ አይደለም ያለነው ብል አላጋነንኩም፡፡ ከሰውነት ቢሻው የአፍሪካ ዋንጫው ቡድን ጅምሮ ሌሎች ስህተቶች
እንዳሉ ሆነው ከፍተኛ የሆነ የግብ ጠባቂ ችግር እንዳለብን ታይቷል፤ ይሄ በጣም ያሳስበኛል…፤… ሌሎች ሀገሮች የእኛን ያህል የችግሩ
ሠለባ ሣይሆኑ የውጪ ግብ ጠባቂዎችን በተመለከተ ሕግ አውጥተው ወረራውን ተከላክለዋል፡፡ እኛ ሀገር ደግሞ የውጪ ግብ
ጠባቂዎች አጥለቅልቀውናል፡፡ ደግሞ እኮ በአፍሪካ የውድድር መድረክ የሚጫወቱ ክለቦች የውጪ በረኛ ቢይዙ በኢንተርናሽናል
የውድድር መድረክ ለመፎካከር ነው ብለህ ልትወስድ ትችላለህ፤ ላለመውረድ…፣ ታች ዲቪዚዮን የሚጫወት ቡድን የውጪ በረኛ
አምጥቶ ሲያጫውት ስታይ ታዝናለህ፤… ይሄ ለእኔ እብደት ነው፡፡ ወደዚህ ሁሉ ችግር የገፋን ልጓም አለማበጀታችን አለመስራታችን
ነው… ቀደም ባሉት አመታት ሀገሪቱ በምርጥ ምርጥ በረኞች መጥለቅለቅዋን እንጂ ችግር ውስጥ ወድቃ አልታየም፤ መምረጥ
እከሚያቅትህ የበረኞች ጎርፉ ነው የነበረው፡፡ ከእነ ተካበ እስከ እነ አሊ ረዲ ድረስ ቆጥረህ የማትጨርሳቸው በረኞች ናቸው የነበሩን፤
ዛሬ ይሄ የለም፡፡ ይሄን መስመር ከማስያዝ ይልቅ ዝምታን መምረጥ የፌዴሬሽኑ ሞራልና የሀገር ስሜት ጥያቄ ውስጥ ይከታል፡፡

ሀትሪክ፡-አንተ የአዲስ አበባ የእግር ኳስ አሰልጣኞች ማህበርን በምክትል ፕሬዚዳንት እየመራህ ነው፤ እሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ
ደግሞ የአዲስ አበባ ክለቦች እየተመናመኑ ወደ ሶስት የወረዱበት… ክለቦች ብቻ አይደለም የአዲስ አበባ አሰልጣኞች ቁጥርም በከፍተኛ
ሁኔታ እየተመናመነ የመጣበት ሁኔታ ነው ያለውና ይሄ ነገር አያስፈራህም… ምንስ መልዕክት ያስተላልፉልሃል…?

አቶ አስናቀ፡- …ይሄ መሆኑ ማስፈራት ብቻ አይደለም ውድቀቱም ምን ያህል እየተፋጠነ ነገ አዲስ አበባን የሚወክል ቡድን ጭራሽ
የሚጠፋበት ጊዜ እየደረሰ እንደመጣም የሚጠቁመኝ ነው፤ ለእኔ አዲስ አበባ ከሌሎች በተለየ ብዙ መሰረተ ልማቶች የተሟሉላት…
ታላላቅ ተቋማት ያሉባት ከተማ ናት፡፡ አዲስ አበባ የኢንተርናሽናል ተቋማት መቀመጫ… የኢትዮጵያ ብቻ ሣይሆን የአፍሪካም ዋና
ከተማ ተደርጋ ነው የምትወሰደው፡፡ ለምሣሌ የአሜሪካዋን ዋሽንግተን ዲሲን ብትወስድ ከሌሎች ስቴቶች ኋላ ቀር ብትመስልም ግን
የሀገሪቱ ልብ ናት፤ የመንግሥት መቀመጫ፣ ብዙ አቅም… ብዙ ጭንቅላት… ብዙ ሊሠሩ የሚችሉ ሰዎች… ያሉባት ከተማ ናት…፡፡
አዲስ አበባንም ስትወስድ ተመሳሳይ ነገር ነው የምናገኘው፡፡ አዲስ አበባ የሀገር እራስ ናት፡፡ ብዙ ጭንቅላት ብዙ ኃይልና መሠረተ

ልማት ያለባት የመንግሥትም መነሻ ከተማ ናት፡፡ ብቻ ግን ይሄ ሁሉ ኃይል ይሄ ሁሉ ጭንቅላትና መሠረተ ልማት ያለበት ከተማ ለእግር
ኳስ ሲሆን የት እንደሚገባ… ይሄን ሁሉ በተጨዋችነት፣ በክለብም ይሁን በአሰልጣኝነት ማሳደግ ያቃተን ለምንድነው? ከመብዛት
ይልቅ እየተመናመነ የሄደው ለምንድነው…? የሚለው በአግባቡ መፈተሽ ያለበት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ይመስለኛል፡፡ ድሮ አዲስ አበባ
በእግር ኳስ ገዝፎ ነበር የሚታየው… ዛሬ ወርዶ ሶስት ቀርቷል፤ ቅ/ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡናና መከላከያ፤መከላከያም የወታደር
ቡድን ነው፡፡ አዲስ አበባ ወኪል ለማጣት ተቃርባለች፤ ይሄ በጣም ያሳስባል ብቻ ሣይሆን ያስፈራል፡፡ ድሮ እኮ አዲስ አበባ 5ዐ
ክለቦችን የነበራት ከዚህ በፊት በዛ እንዳልተባለ አሁን ዋና ከተማዋን የሚወክል ቡድን የሚጠፋበት ጊዜ ላይ እየደረስን ነው፡፡
የሚታየው ሁሉ ኢትዮጵያ ውስጥ እግር ኳስ የለም እንዳይባል ለፖለቲካ ፍጆታ የሚሠራ ነው የሚመስለው፤ 7ዐ በመቶ ህዝብ
ኮንደሚኒየም ውስጥ ነዋሪ ነው፤ የትኛውም ኮንደሚኒየም ብትሄድ ታስቦ የተሠራለት የእግር ኳስ መጫወጫ የለም፡፡ ት/ቤት ድሮ
የተጨዋቾች መፍለቂያ ነው፤ አሁንስ? በጣም ተዳክሟል፡፡ በአጭሩ አዲስ አበባ ባለቤት ተቆርቋሪ አላት እንዴ…? የሚያስብል ነው፤
አዲስ አበባ ከስፖርቱ እየተገለለች ነው፡፡ የአዲስ አበባን አነሣን እንጂ ኦሮሚያም አለ የሚያስብል ነው ነገር ያለው? ለእኔ አይደለም…፤
ቡድኖች ቢኖሩም እኮ ከሌላ ቦታ በመጡ ተጨዋቾች የተጥለቀለቀ ነው፤ ስለ አዲስ አበባ ክለቦች ብዙ መታሰብ አለበት፡፡
ሀትሪክ፡- የአዲስ አበባ የእግር ኳስ አሰልጣኞች ማህበርን እየመራህ የአዲስ አበባ አሠልጣኞች ቁጥር መመናመን የማህበሩን ህልውና
ጥያቄ ውስጥ አይከተውም…?
አቶ አስናቀ፡- …ይሄም ሌላው ሊታይ የሚገባው ችግር ነው…፤… ብዙ መሥራትም እንዳለብን የሚጠቁም ቢሆንም የአሰልጣኞችን
ማህበር በተመለከተ ካነሣን ግን በጣም ጠንካራ

ሀትሪክ፡-ቀደም ሲል ኪራይ ቤቶችን አሰልጥንሃል… አሁን ደግሞ የአዲስ አበባ እግር ኳስ አሰልጣኞች ማህበርን በምክትል
ፕሬዝዳንትነት…የኢትዮጵያ አሰልጣኝ ማህበርን ደግሞ በአባልነት እያገለገልክ ነው፤ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አሰልጣኝ ተብሎ
መጠራት ያኮራል…? ሙያው ከመከበር ይልቅ ተንቋል…ተዋርዷል የሚሉ አሉ…አንተስ ምን ትላለህ….?
አቶ አስናቀ፡- …የአሰልጣኝነት ሙያ በውጪ በጣም የተከበረ ትልቅ ሙያ ነው…፤… አሰልጣኞች በሙያቸው ሁሉም
ያከብረዋል…፤…ለሥራቸው ትልቅ ክብርና ዋጋም ይሰጣል፡፡ በእኛም ሀገር በተለይ ቀደም ባሉት አመታት አሰልጣኝነት ትልቅ ክብር
ነበረው፤ ብዙዎች ለሙያው ከፍተኛ ክብር ነበራቸው፡፡ አሁን አሁን ግን ይሄ እየተሸረሸረ የመጣባቸው ሙያው እየተናቀ እየተዋረደ
የመጣበት ሁኔታ እንዳለ መካድ አይቻልም፡፡ በቃ በአጭሩ ሙያው ተዋርዷል፤ ተንቋል፡፡ "አሰልጣኝ ነኝ" ብሎ መናገር በራሱ
የሚያስፈራበት የሚያሸማቅቅበት ዘመን ላይ ነው የደረስነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ምናልባት አንዳንድ አሰልጣኞች ሥማቸው ከሙስና ጋር በመነሣቱ ከተጨዋቾች 40/60 ገንዘብ የሚካፈሉ አሰልጣኞች
መኖራቸው ሙያው ለመርከሱ እንደምክንያት መውሰድ ይችላል… ?
አቶ አስናቀ፡- …እንግዲህ ምን መሠለህ…!… አሰልጣኞች ላይ አንተ በጥያቄ እንዳነሳኸው የሚወራ በጣም ብዙ ነገር አለ፤ በእርግጥ
በመረጃ እንጂ በማስረጃ ተደግፎ ባለመቅረቡ ነገሩን አስቸጋሪ ቢያደርገውም በጣም በስፋት የሚወራ ነገር አለ፡፡ በሙያው ውስጥ
በዚህ ደረጃ አሳፈሪ ነገር ውስጥ የተዘፈቁ መኖራቸው ሙያው እንዲረክስ እንዲወርድ አድርጎታል ብሎ መናገር ይቻላል…
ሀትሪክ፡- …አንተ የአሰልጣኞች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት እንደ መሆንህ ከወሬ ባለፈ ለማህበሩ የደረሰው ነገር አለ…?
አቶ አስናቀ፡- …ነገርኩህ እኮ… በወሬ ደረጃ ብዙ ነገር ይመጣል… ግን በማስረጃ አስደግፎ ያቀረበው ሰው ግን እስከአሁን አልተገኘም፡፡
የምናወራው እውነት እውነቱን ከሆነ አሁንማ በደፈናው ወይም በጅምላ ከማውራት ይልቅ ስም እስከመጥራትም ተደርሷል፤
ስማቸው ተዘርዝሮ የተጠቀሱ አሰልጣኞች አሉ (ዝርዝራቸውን ከአጀንዳቸው ላይ እያሳየኝ)… ግን እነዚህ ሰዎች ስማቸው ተዘረዘረ
እንጂ ከመረጃ ውጪ በማስረጃ ተደግፎ የቀረበባቸው ነገር የለም፡፡

ሀትሪክ፡- …ማስረጃ አልቀረበም በሚል ይሄን ነገር በዝምታ ማለፉስ አግባብ ነው ትላለህ…?… በጥቂት አሰልጣኞች የሁሉም
የማህበራችሁ አባላቶች ስም መጥፋቱስ አያሳስባችሁም?
አቶ አስናቀ፡- …በጅምላ… ሁሉም አሰልጣኝ የሠራውም ያልሠራውም አንድ ላይ መጨፍለቁን እኛም አንደግፈውም፡፡ ግን ሙያውን
ያረከሰው ራሱ አሰልጣኙ ነው፤ ሙያውን ማስከበር የቆሸሸውን ስሙን ማፅዳትም ያለበት ራሱ አሰልጣኝ ነው። በጥቂቶች ሙያው
ክብሩን እንዲጣ እንዲዋረድ በመደረጉ ይሄን መከላከል ያሰፈልጋል፡፡ ቢያንስ አሁን በሥራ ላይ ያሉ አሰልጣኞች ሙያችን ተዋረደ፣
ያለስማችን ስም ተሰጠን ብለው መጮህ መቃወም አለባቸው፤ አለበለዚያ ዝምታ በራሱ አምኖ የመቀበል ያህል ሊያስቆጥር
ይችላል፡፡ አሰልጣኞች ራሣቸው ካልተከላከሉ ሌላ አካል ሁሉም እየተከላከላቸው ማስቀጠል ከባድ ነው የሚሆነው፤ ስለዚህ
አሰልጣኞች ጥቂቶች በሠሩት ሥራ እኛ መወቀስ ሙያውም መዋረድ የለበትም ብለው ሊጮሁ፣ ንፁህ ስማቸውን ለማስመለስ
ሊታገሉ ይገባል፤ ግን ይሄ እስከአሁን አልተደረገም፡፡ “አህያ በበላ ዳዋ ተመታ…” እንዲሉ አበው በጥቂቶች ስማቸው እየጠፋ
የተከበረው ሙያም እየተዋረደ ነው፡፡ ስለዚህ የቀድሞ መልካሙን ስሙን ለመመለስ በተለይ ሙያ ውስጥ ያሉ የመከላከል ስራ
ሊሠሩ ይገባል፡፡
ሀትሪክ፡-አሰልጣኞችና ሙያው ከመዋረዱ ውጪ እግር ኳሱም ላለማደጉ እንደ አንደኛው ምክንያት አድርጎ መውሰድ ይቻላል….?
አቶ አስናቀ፡- …ለእኔ እንደ አንደኛው ሣይሆን እንደ ዋናው ምክንያት ነው የምወስደው፤ዋናው ወይም ቁልፉ የእግር ኳስ ችግር ነው፡፡
በዚህ አይነቱ አሠራር እግር ኳሱ ከመጠቀም ይልቅ ተጎጂ ነው የሚሆነው፤ ምናልባት በዚህ ተግባር የተሰማሩ ለጊዜው ተጠቃሚ
ይሆኑ ይሆናል እንጂ… ኳሱ በዚህ ከመጠቀም ይልቅ ጉዳቱ ነው የሚያመዝነው፡፡ አሰልጣኝ ቃል ለገባለት ሙያው ኤቲካል (ስነ
ምግባር) ተገዢ የመሆን ግዴታ አለበት፡፡ ምናልባት የአሰልጣኝ ደሞዝ አንሶ ከሆነ ልክ እንደተጨዋቾች እንዲያድግ መታገል እንጂ በሌላ
መንገድ ይሄንን ለማሳካት መሞከርና መዘፈቅ ተገቢ ነው የሚል እምነቱ የለኝም፤ግን በዚህ ዙሪያ ካነሣን ሌላም ችግር… ሌላም
ሀሜት… አለ…
ሀትሪክ፡-… ምን … አይነት… ሀሜት …?… ምን አይነት … ችግር….?
አቶ አስናቀ፡- ….እንደው አሁን ውይይታችንም ትኩረት (ፎከስ) ያደረግነው አሰልጣኞች ላይ ሆነ እንጂ ሁላችሁንም ባይወክልም እናንተ
ጋዜጠኞችም እኮ በዚህ አሣፋሪ ነገር ትታማላችሁ…፤… ጋዜጠኞችም ከሙያቸው ውጪ በዚህ ጎጂ ተግባር ተሰማርተዋል ትባላላችሁ፡፡
አሰልጣኝና ተጨዋች ክለብ በማስገባት በመደለል፣ በማቀባበል ትጠረጠራላችሁ፣ ትታማላችሁ፡፡ ያው ሁላችሁም ናችሁ ባትባሉም
በዚህ ተግባር የተሠማሩ ጋዜጠኞች እንዳሉ ነው የምንሰማው፡፡ ግን እንዳልኩህ እንደ አሰልጣኞች ሁሉ መረጃ እንጂ በማስረጃ የቀረበ
ነገር የለም፡፡ ከጋዜጠኞች ውጪም የክለብ አመራሮችና ደላሎችም እዚህ ውስጥ ገብተው እንደሚዋኙ ነው የሚሰማው፡፡ በዚህ
አይነት በተጨመላለቀ እግር ኳስ ውስጥ እንዴ ነው ጥሩ ነገር፣ ጥሩ ሥራ የሚጠበቀው፡፡ አሁን እኮ ነገሮችን የከበዱ ያደርጋቸው
አሰልጣኝ ብቻ የሚቀበል ቢሆን ሌላው እንዲቆጣጠረው ግፊት ታደርጋለህ፤ሙሉ ስትራክቸሩ እዛ ውስጥ የተዘፈቀበት ሁኔታ መኖሩ
ነገሩን ይበልጥ ውስብስብና ከባድ ያደርገዋል፡፡ 98 በመቶ ክለቦች የመንግሥት በመሆናቸው ገንዘብ የሚወጣው ከመንግሥት ቋት
በመሆኑ መንግሥት ራሱ እጁን ካላስገባበት፣ ትኩረት ካልሰጠው ችግሩ በእኛ ትግል ብቻ የሚፈታ አይደለም፤ ያም ቢሆን ግን
እየታገልን ነው፡፡
ሀትሪክ፡-ቀደም ሲል ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጋር እንደማህበር ተቀራርቦ የመስራት ባህሉ ነበር…አሁንስ…?
አቶ አስናቀ፡-…ከሁለት አመት በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ ከአንተም ጋር አንስተን ተወያይተናል፤ ማህበራችን በተለይ ከስልጠናና
ከአሰልጣኝ ጋር በተያያዘ በግልፅ ልንሳተፍ ይገባል፡፡ ከዚህ መነሻነት እኔና የማህበራችን ዋና ፀሐፊ ከሆነው ከአቶ ሰለሞን አባተ ጋር
በመሆን ከፕሬዚዳንቱ ከአቶ ኢሳያስ ጅራ ጋር በማህበራችን፣ በአሰልጣኞች ዙሪያ ተወያይተናል፡፡ በወቅቱ ከፕሬዚዳንቱ ጋር በነበረን
ቆይታ ጥያቄያችን ሌላ አልነበረም፤ የተሳትፎ እድል ሊሰጠን ይገባል፣ በሚመለከቱን ጉዳዮች ላይ አስተያየት እንድንሰጥ መድረግ
አለበት፡፡ እንደ አሰልጣኝ ተሳትፎአችን ይከበርልን፣ ገለልተኛ አድርጋችሁናል የሚል ጥያቄ ለፕሬዚዳንቱ አቅርበናል፡፡
ሀትሪክ፡-…ከፕሬዚዳንቱ ምን … ምላሽ አገኛችሁ…?

አቶ አስናቀ፡- …በወቅቱ ከፕሬዚዳንቱ ጋር በነበረን ውይይት ጥያቄያችሁ ትክክለኛና የመብት ጥያቄ ነው ብለውናል፤ የሚያሳዝነው
ከቃል ባለፈ ግን የተሰጠን ተግባራዊ ምላሽ የለም፡፡ በጣም የሚገርምህ የአሰልጣኞችን ደረጃ ሁሉ የሚያሳይ ፖሮፖዛል ሁሉ ሠርተን
በማቅረብ ፖሮፖዛሉ የሚታይና የሚፈተሽ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ለመነሻ ይረዳል ብለን አቅርበናል፡፡ መልስ እንኳን ሊሰጠን
የሞከረ የለም፡፡
ሀትሪክ፡- አሁን በቅርቡ ፌዴሬሽኑ ለ60 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢንስትራክተርነት ስልጠና ሰጥቶ አስመርቋል የአሰልጣኞች ማህበር
እዚህ ላይ ሚና ወይም ተሳትፎ ነበረው?
አቶ አስናቀ፡- ከማህበሩ ተሳትፎ በፊት ስለ ኢንስትራክተርነት ስልጠናው ተገቢነት ማንሣትን ላስቀደም፤ በመጀመሪያ ደረጃ ከስሙ
ስንነሣ ኢንስትራክተር ማለት የአሠልጣኞች አሠልጣኝ ማለት ነው፡፡ አንድ ሰው ኢንስትራክተር ለመባል የፊፋንም የካፍንም ሕግ
ማየት ትችላለህ…ወይም እድሜ ለቴክኖሎጂ ኢንተርኔት ውስጥ ገብተህ ማየት ትችላለህ ተጫውቶና አሰልጥኖ ያለፈ ሰው ነው
የኢንስትራክተር ስልጠና የሚወስደው ይላል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ግን ለ60 ሰዎች የኢንስትራክተርነት ኮርስ ተሰጥቶ ተጠናቋል፡፡
አብርሃም መብራቱ እዚህ ውስጥ እንዴት እንደገባ አናውቅም በምናጠራው የምናጠራ ይሆናል፡፡ ከዚህ ውጪ ለዩኒቨርሲቲ ስልጠናው
የተሰጠበትም ሆነ ስልጠናው የሰጡት ሶስቱም አሰልጣኞች ጥያቄ የሚመዘዝባቸው ናቸው…
ሀትሪክ፡- …ማለት ኮርሱን የወሰድትም…ኮርሱን የሰጡትም የህጋዊነት ጥያቄ አለባቸው እያልክ ነው…?
አቶ አስናቀ፡-…እንዴ ምን ማለትህ ነው…ይሄ ዝም ሊባል አይገባውም…፤ የኢትዮጵያ ህዝብም ስልጠናውን ሊያወግዘው፣
ጋዜጠኞችም ልትጮሁበት የሚገባ ጉዳይ ነው፤ ትክክል ያልሆነ ሂደትም ነው፡፡ ኢንስትራክተር ለመባል ተጫውቶ አሰልጣኝ ሆኖ
ማለፉን ይጠይቃል፡፡ ተጫውቶ ያላለፈን አሰልጣኝ ያልሆነን ሰው እንዴት ነው የኢንስትራክርነት ኮርስ ሰጥተህ ኢንስትራክተር ብለህ
የምትጠራው? ይሄ ቀልድ ነው፡፡ ኮርስ ወስደው ኢንስትራክተር የተባሉትን ተዋቸው ይሄን ኮርስ ኢንስትራክተር ተብለው የሰጡት
ሶስቱም ሰዎች እኮ ከዩኒቨርስቲ ተመርቀው እዚሁ ፌዴሬሽን ውስጥ የሠሩ ፊፋ በሚጠይቀው ተጫውተውና አሰልጥነው ማለፉ
ለሚለው መስፈርት ጥያቄ የሚመዘዝባቸው ናቸው፡፡ እንዲህ አይነት አሠራር ምን ማለት ነው? እነዚህ ሰዎች በሙሉ የመጡት
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ አሁንም እየሠሩ ያሉት ይሄንም ነው… የሚሰጡት ላይሰንስ ደግሞ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ብቻ የሚሠራ
አይደለም፡፡ ዩኒቨርስቲ ውጥም ቢሆንም ህፃናት ላይ 15 አመት እድሜ ያላቸው ላይ ነው የሚሠሩት፡፡ የተግባር ሥራ አለው፤ ተጨውቶ
ያላለፈ ሰው እንዴት ነው ኢንስትራክተር ተብሎ ህፃናት ላይ የሚሰራው፡፡ ሕፃናት ተጣመው ማደግ የለባቸውም… ተጣሞ ካደገ በኋላ
የትኛውም አሰልጣኝ ቢያገኘው ሊያቃናው አይችልም…. አሁን የተያያዘው ምን እንደሆነ ታውቃለህ…?
ሀትሪክ፡-…ምንድነው… አላውቅም…?
አቶ አስናቀ፡- …እነዚህ ከዩኒቨርሲቲ ሰለጠኑ የተባሉትን አሰልጣኞች ገበያ ውስጥ በትኖ ከጀርባ ሆነህ እያገዝክ ደግሞ አንድ ሌላ
ትውልድ ለማጥፋት የታቀደ ነው የሚመስለው …..
ሀትሪክ፡-…ማሰልጠንና ትውልድ ማጥፋትን ደግሞ ምን አገናኘው…?…በደንብ ግልፅ ስላልሆነልኝ ነው….?
አቶ አስናቀ፡- …በግልፅ ነው የምነግርህ… አሁን ያለው ሂደት ትክክል ያልሆነ ነው…፤… እንደገና ሌላ ስህተት ለመፈፀም አንድ ቡድን
እየተደራጀ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አንድ ቡድን አንድ ትውልድን ገሎ አሁን ያለው ትውልድ መጥቷል፤ አሁን ያለው ትውልድ ስምንትና
አስር አመት በስልጠና ላይ ስለቆየ የግድ ልንቀበለው ይገባል፤ ልምዶችንም አዳብሯል፡፡ አሁን ደግሞ ይሄንን ቡድን ነቅሎ ሌላ ቡድን
ለመትከል የሚፊልግ ቡደን እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ይሄ የሚሆነው ደግሞ አካባቢው ላይ ባለው ቁጥጥር አልባ የገንዘብ እንቅስቃሴ
ምክንያት ብቻ ነው፡፡ የገንዘብ እንቅስቃሴው ደግሞ በጣም ከፍተኛ ነው፤ ያንን ለመጠቀም ሲባል ብቻ አሁን ሌላ ግሩፕ ተፈጥሮ
ዘመቻ እየተደረገ ነው፤ስለዚህ ይሄንን ህዝቡ አውቆ ሊከላከለው ይገባል፤ ጋዜጠኞችም ብዙ መስራት አለባችሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …እግር ኳሱም ውጤቱም ከማደግ ይልቅ ቁልቁል መሄዱን ተያይዞታል፤ እግር ኳሱ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለ ኢንስትራክተሮች
ግን አንደ አሸን እየፈሩ ነው፡፡ እግር ኳሱ ደክሞ የኢንስትራክተሮች መብዛትን እንዴት ታዘብክ…?

አቶ አስናቀ፡- …እውነት ነው በጣም በዝቷል…፤ የኢንስትራክተር መአት ነው ያለው እግር ኳሱ ግን ታች ነው፤ምክንያቱም በትክክል
አይደለም እየሄደን ያለነው፡፡ ኢንስትራክተር ደረጃ ለመድረስ የምታልፋቸው ሂደቶች አሉ፤ በተለይ ተጫውተህና አሰልጥነህ ማለፍ
አለብህ፡፡ በተለይ ሕፃናት ላይ እንደመስራትህ በዚህ መስመር ማለፍህ ያግዝሃል፡፡ ለምሣሌ የስድስት አመት ልጅን የአካል ብቃት
አታሰራውም፤ ኳሱ ላይ ነው የምታሰራው፤ የፍጥነትና የቴክኒክ ስራዎችን ነው በዋነኛነት የምታሰራው፡፡ ከዚህ አንፃር በኳስ
ለማሠራት ኳስ ተጫውተህ ማለፍ አለብህ፡፡ አንተ ሰርተህ ያላለፍከውን ወይም የማታሰራውን እንዴት ነው ሥራ ብለህ ጫና
የምታደርግበት፡፡ ኮንትሮል፣ ድሪብል አድርገህ ለህፃኑ ካላሳየኸው ያ ህፃን ከየት አምጥቶ ሊሠራ ነው? አንተም በዚህ መስመር
ካላለፍክ ምን እንደምታሰራው ይጨንቅሃል፡፡ አሁን የተያየዘው እዛ ጋር ሌሎች ፍላጎቶችህ ስለተሟሉልህ ብቻ ፍጥጥ ብለህ ትገባለህ፡፡
መስፈርቱ በሚያዘው መሠረት ነው የገቡት የሚለው እራሱ ብዙ የሚያነጋግር ነው፡፡ እንዳልከው ኢንስትራክተርነት እንደ አሸን ፈልቷል
ምን ያህሉ በመስፈርቱ መሰረት ተጫውቶ አሰልጥኖ አልፎ ነው በስያሜው የሚጠራው የሚለውን ሰጪው አካል የሚመልሰው ነው
የሚሆነው፡፡
ሀትሪክ፡-ግን እኮ ቀደም ሲል በሀገር ደረጃ ሁለት የእግር ኳስ ኢንስትራክተሮች ብቻ ናቸው ለረዥም አመታት የነበሩን፤ ኢንስትራክተር
መንግሥቱ ወርቁና ኢንስትራክተር ካሳሁን ተካ… የያኔው ከአሁኑ ጋር ልዩነት አለው ማለት ነው…?
አቶ አስናቀ፡- …በጣም ልዩነት አለው…፤… ኢንስትራክተርነት እንደ አሁኑ ያልረከሰው ኢንስትራክተር የሚባሉት ሰዎች መሰፈርቱን
የሚመጥኑ፣ በስራቸው የተመዘኑ፣ ምሳሌ አርአያ የሚሆኑ በመሆናቸው ነው፡፡ በትልቅ ክለብ፣ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ
ተጫውተዋል፤ አሰልጥነዋል፤ በእግር ኳሱ ዛሬም ድረስ የሚጠቀስ ታሪክ አላቸው፡፡ ለዚህም ነው መንግሥቱ ወርቁ ህይወቱ አልፎ፣
ካሳሁን ተካ ከኢትዮጵያ ውጭ እያለ እግር ኳሱ ዛሬም ድረስ የሚዘከርላቸውና ስማቸውን ከፍ አድርጎ የሚያነሣው፡፡ ኢንስትራክተር
ማለት የአሰልጣኞች አሰልጣኝ መሆኑንብዙ አሰልጣኞች በማሰልጠን በማፍራት ስሙን የሚመጥኑ መሆናቸውን በተግባር ያሳዩ
በመሆናቸው ማንም በእነሱ ኢንስትራክተርነት ላይ ጥያቄ አንስቶ አያውቅም፡፡ በጣም የሚገርምህ ያኔም ከዩኒቨርሲቲ ማስትሬት፣
ዶክትሬት የያዙ ስፔሽላይዝ ያደረጉ መጥተው አብረዋቸው እንዲሠሩ ተደርጓል፡፡ እነዚህ ሰዎች በፉትቦል ውስጥ ታሪክ የላቸውም፤
ታሪክም አንስቷቸውም አያውቅም፡፡ ብ/ቡድንም፣ ክለብም ሁሉ አሰልጥነዋል፤ ግን ታሪክ የላቸውም፤ ጠፍተዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲ
ባገኘኸው ስልጠና ብቻ ሙሉ አሰልጣኝ መሆን አይቻልም፤ ቲዎሪ በባለሙያ ይሞላል፡፡ ሳይኮሎጂ ከሆነ ሳይኮሎሎሲት ፊዚዮሎጂ
ከሆነ ፊዚዮሎጂስት ትቀጥራለህ፡፡ ከዩኒቨርሲቲ የምትማረው ጠቅላላ የስፖርት ሳይንስ ነው፡፡ ይሄ ትልቅ ነገር ቢሆንም ተጫውተህ
አሰልጥነህ ካላለፍክ ትልቅ ነገር ይጎድልሃል፡፡ ሳትጫወት ሳታሰለጥን እንዴት ነው የአሰልጣኞች አሰልጣኝ የምትሆነው? ይሄ ኳስም
ህዝብም ላይ ማፌዝ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …እንደዚህ አይነት ችግሮችን በተመለከተ በሚዲያ ከመቃወምህ በፊት እንደ ማህበር የትድረስ ለመሄድ አስባችኋል በጉዳዩ
ዙሪያስ ስልጠናው ከሰጡት ጋር ለመነጋገር አልሞከራችሁም…. ?
አቶ አስናቀ፡- ይሄ የሀገር ጉዳይ ስለሆነ እንደ ማህበርም በግልፅ በዝምታ የምናልፈው አይደለም…. በዚህ ትልቅና አንገብጋቢ ጉዳይ
ምክንያት አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ እስከመጥራት እንደርሳለን፡፡ ያ ጉባኤ የሚያስቀምጠውን የምናየው ነው የሚሆነው፡፡ እናንተም
ሚዲያዎች ሁላችሁም ይሄንን ልታግዙንና ልትቃወሙ ይገባል፡፡ ዝምታ ሲበዛ እንደ አሰልጣኞቹ ሙያ ውሎ አደር እንደመቀበል
ያስቆጥራል፡፡ እንደ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለውጥ እንጠብቅ ነበር፤ ለውጥ አላየንም፡፡ በስልጠና ያለፈ፣ ስልጠና ህይወቱ የነበረ እንደ
ሰውነት ቢሻው አይነት ሰው የቴክኒክ ዳይሬክተር ሆኖ በሚመራበት ወቅት ነው ይሄ ነገር እየተሰራ ያለው፡፡ ተጫውቶ አሰልጥኖ ያላለፈ
ሰው ፊፋ ካስቀመጠው ደንብ ውጪ የአሰልጣኞች አሰልጣኝ ተብሎ ሲሰለጥን የሰውነት ይሁንታ አለበት ማለት ነው፡፡ ይሄንን ደግሞ
ሰውነት ቢሻው ምረቃቱ ላይ ሣይቀር በመገኘት የምስክር ወረቀት በመስጠት ለጉዳዩ እውቅና ብቻ ሣይሆን ተባባሪነቱን አሣይቷል፡፡
አብርሃም መብራቱ ለኢስትራክተርነት ምን እንደሚያስፈግ ከማንም በላይ እያወቀ ለምን እንደተባበረ አልገባኝም፤እነዚህ ሁሉ ነገሮች
ካልጠሩ ነገ የእግር ኳሱ መከራ እንዲበዛ ነው የምናደርገው፡፡
ሀትሪክ፡-አዲሱን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የእስካአሁንን ሂደት እንዴት አገኘኸው… ?
አቶ አስናቀ፡-አዲስ የሚለውን ቃል ባትጠቀም ነው የምመክርህ፤ ምክንያቱም ፌዴሬሽኑ እኮ አንድ አመት ሞላው፤ አዲስ አይባልም
እናንተም አዲሶች እያላችሁ አታባብሉ። ወደ ስልጣን ሲመጡ አዲስ ነገር ያሳዩን ይሆን? በሚል ጠብቀናቸው ነበር፡፡ አንድ አመት ሙሉ

ፌዴሬሽኑ ግቢ ውስጥ ገብተው ቢያንስ ሮድ ማፕአቸውን ወይንም ስትራቴጂክ እቅዳቸውን እንኳን አላሳዩንም፡፡በስልጣን ዘመናችን
ከዚህ ተነስተን እዚህ እንደርሳለን የሚል ነገር እንኳን አልነገሩንም፤ ሌላው ይቅር ሮድ ማፕአቸውን ስትራቴጂክ እቅድህን ለማሳየት
አንድ አመት ከበቂ በላይ ነው፡፡ ምናልባት የአመት እቅድ ማውጣት ጨዋታ መምራት አንደኛ ዙር መገምገም ካልሆነ በስተቀር
በአምስት አመት የስልጣን ጊዜያቸው ከየት ተነስተው የት እንደሚደርሱ እኔ በግሌ አላውቅም፡፡ ሮድ ማፕ የሌለው የሚጓዘው በጭፍን
ነው፤ እንኳን የሀገሪቱ እግር ኳስ ተወውና ክለቦችም የራሣቸው ሮድ ማፕ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ከዚህ ውጪ ከተጓዙ መነሻና
መድረሻቸው ሳያውቁ ነው የሚጓዙት፡፡ ሮድ ማፕ አስቀምጠው ሣይጓዙ በውድድሮች ተጠምደው አመቱ ይባክንና በቀጣይ ወደ ምርጫ
ትግል ውስጥ ስለሚገቡ ሌላው ስራ ይሸፈንባቸዋል፡፡ ምንም ነገር በእቅድ ሳይሰራ ምርጫው ይመጣና የኢትዮጵያ ህዝብ እስኪሰለች
ድረስ መጮህ ውስጥ ይገባል ልክ ባለፈው እንደተጨቃጨቅነው አሁንም ምርጫው ደረሶ ልንጨቃጨቅ ልንጓተት ነው፤ ወደ ስልጣን
ስትመጣ መነሻና መድረሻ ሊኖርህ ይገባል፡፡ ህዝብ የተቀበለው በደንብ የታወቀ ፕሮግራም ኖሮህ በዚያ ፕሮግራም ውስጥ ያለውን ለውጥ
በተግባር እያሳየህ መሄድ ነወ፡፡ ይሄ ካለሆነ ግን አዲሶች ናቸው እያልን አሮጌ ሆነው ሲወድቁ ልንመለከታቸው ነው፡፡
ሀትሪክ፡- እንደ አሰልጣኝነት ማህበር እንደ አስራት ኃይሌ አይነት የ51 አመት የእግር ኳስ አገልግሎት፣ውጤትና ትልቅ ታሪክ ያለው
አሰልጣኝ በሀገሪቱ እግር ኳስ ውስጥ ቦታ ማጣቱና የረዥም አመቱ ልምዱን አለመጠቀማችንን እንዴት ነው የምታየው…. ?
አቶ አስናቀ፡-ይሄን ጉዳይ በተመለከተ በጣም አዝናለሁ፤ የበርካታ ልምድና የውጤት ባለቤት የሆኑ አሰልጣኞች ይዘን ወደ ፌዴሬሽኑ
ወደ እግር ኳሱ በማስጠጋት ልንጠቀምባቸው ሲገባ እንዳይጠጉ አጥር ማጠርና ማግለልን መምረጣችን ያሳዝነኛል። እነዚህን ሰዎች
እነሱ እንኳን ለምነው እምቢ ቢሉ እንኳን አግባብተን ወደ እግር ኳሱ በማስጠጋት የረዥም አመት ልምድና እውቀታቸውን መዝረፉ
ለትውልድ ማሸጋገር ሲገባ መገፍተራችን እግር ኳሱ በምን አይነት ሰዎችና አስተሳሰብ እየተሰራ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ልብ በል አስራት
ኃይሌ በተጨዋችነትና በአሰልጣኝነት የ51 ዓመት የተካበተ ልምድ አለው፤ ስለውጤታማነት፣ ስለልምዱ ብዙ ጥቅም ልናገኝበት
የሚችል ሰው ነው፡፡ እሺ ማሰልጠኑን እነሱ እንዳሉት ይሁንና ይቅር… ግን አስራትን ወደ እግር ኳሱ ብናስጠጋው አንድ አጥቂ ምን
ዓይነት እንደሆነ… ምን እንደሚጎለው…ምን አይነት ነገር ቢሰራ የበለጠ እንደሚሆን ማማከር… ጥሩ ተጨዋቾችን ለይቶ ማውጣት
ያቅተዋል? እነ ንጉሴ ገብሬ፣ በሀብቱና አካለወልድንም ማንሳት ይቻላል? ማሰልጠኑ ይቅር ከረዥም ዓመት የተጨዋችነትና
የማሰልጠን ልምዳቸው ተነስተው ማማከር ማገዝ ያቅታቸዋል? አያቅታቸውም፡፡ ግን ፌዴሬሽኑ አካባቢ እነሱ እንዲጠጉ አይፈለግም፡፡
መጠጋቱን ተወውና ወደዚያ አካባቢ ድርሻ እንዳይሉ ጭምር ቀይ መስመር ሁሉ ሳይቀር ተሰምሮባቸዋል፡፡ በባትሪ ተፈልገው መምጣት
ሲገባቸው እነሱ ራሳቸው የለፉለትን የደሙለትን እግር ኳስ እናግዝ ብለው ሲጠይቁ “ሲስተም ውስጥ አልገባችሁም” የሚል መልስ
የእነሱን ኢምነት ለእግር ኳሱ ካልሰጡ ሰዎች እንዳሚሰጣቸው ራሱ አስራት ኃይሌ አጫውቶኛል፡፡ በሲስተም ውስጥ ለማለፍ ደግሞ
የእነ አስራት ትውልድ ሞራሉና ህሊናቸው የሚቀበለው አይደለም፡፡ በዚህ ሲስተም ውስጥ የማይገቡ ከሆነ ይገፈተራሉ፡፡ ግን መታወቅ
ያለበት ነገር ዛሬ ሲስተም ሲስተም እያሉ የሚያስተጋቡ ቀይ መስመር አስምረው ድርሽ እንዳይሉ የሚያደርጉ ሰዎች ትናንት የነበሩት
እንደወረዱት እነሱም ይወርዳሉ፤ከቦታውም ዞር ይላሉ፡፡ ይሄንን ስንታገል ነበር ዛሬም መታገላችን የሚቀር አይደደለም፡፡
ሀትሪክ፡- ግን እኮ የአሰልጣኞች ማህበር ታላላቅና ስመ-ጥር አሰልጣኛችን አቅፎ የያዘ ሆኖ እንዳልከውም ጠንካራ ማህበር ቢሆንም
እስከአሁን ድረስ ቢሮ የለውም….?
አቶ አስናቀ፡- በተደጋጋሚ ቢሮ እንዲሰጠን ጥያቄ አቅርበን ከቃል የዘለለ ተግባራዊ ምላሽ አላገኘንም፤በጣም የሚገርምህ በእነ አቶ
ጁነዲን የስልጣን ዘመን የቢሮ ጥያቄ አቅርበን "ጥያቄው ተገቢ ነው ይሰጣቸው” በሚል ተመርቶበት ስንታሽ ሳይሰጠን በወሬ ነው
የቀረው፡፡ ከአሁኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጋር በተገናኘንበት ጊዜም ያነሳነው አንደኛው ጥያቄ የማህበሩን የቢሮ ጉዳይ ነበር፡፡
ከይሰጣችኋል የቃል መልስ ሌላ ያገኘነው ነገር የለም፡፡ አሁን በአዲስ መልክ የተሾሙት የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነርም
እኔና አስራት ኃይሌ ቀጠሮ አስይዘን ሄደን አነጋጋረናቸው እሳቸውም በስነ ስርዓት ተቀብለውን ቃል ቢገቡልንም የተፈፀመልን ነገር
የለም፡፡ አዲስ አበባ ቢሮ ቢሰጠን ጥቅሙ ለእኛ ብቻ አይደለም፤ለእነሱም ነው፡፡ በቅርበት ባለሙያ ስለሚያገኙ ለሚፈልጉት አላማ
ሊጠቀሙብን ይችላሉ፡፡ በነገራችን ላይ የበፊተኞቹ ከማቅረብ ይልቅ ያርቁሃል፤ ማህበሩ ጥንካሬ ኖሮት እንዳይደራጅ አንደኛው ማረቂያ
መንገድ አቅም እንዳትፈጥር መሸርሸር፣ አለማገዝ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የአሰልጣኞች ማህበርን ላለማገዛቸው እንደ አንድ ምክንያት እየቀረበ ያለው እርስ በርሳቸው አይሰስማሙም፣ አንድነት
የላቸውም የሚለው እንደሆነ ነው የሚነሳባችሁ.. ትቀበለዋለህ….?
አቶ አስናቀ፡-እንደ አዲስ አበባ አሰልጣኞች ማህበር በተደጋጋሚ እድል ሰጥተናችሁ አይታችኋል፤ የተደራጀ ማህበር ነው ያለን፡፡ የራሱ ስራ
አስፈፃሚ፣ የራሱ ስብሰባ፣ የራሱን ጠቅላላ ጉባኤ የሚያካሄድበት ቋሚ ፕሮግራም ያለው ማህበር ነው፡፡ አይገባቡም፣ አይስማሙም
የሚለው ተራ ሀሜት ነው፤ መስማማት እኮ ንፅፅር ነው። አንድ ሆነህ በሃሳብ ልትለያይ ትችላለህ፤ ይሄ ግን አለመስማማታችንን
አያሳይም። በጋራ በሚሠሩ ስራዎች አብረህ ትሰራለህ፤ መስማማት ማለት ተለጣጥፈህም መስራት ማለት አይደለም፡፡ ደግሞስ
እንደተባለው መስማማት ባይኖር የፌዴሬሽኑ ሚና ምንድነው መሆን ያለበት? ይሄን አብሮ ማራገብ? ወይስ አጋዥ ኃይል በሚሆኑበት
ዙሪያ መስራት ነው ያለበት፡፡ ለምንድነው አይስማሙም፣ አይግባቡም እየተባለ ሁሌም እንደ ድክመት የሚነሣው፡፡ መቶ ፐርሰንት
አረጋግጬ የምነግርህ በአሰልጣኞች መካከል ከሃሳብ ልዩነት የዘለለ አለመግባባትም ሆነ አለመስማማት የለም፡፡ የፈለከውን
አሰልጣኝ መጠየቅ ትችላለህ ይሄ ችግር የለም፡፡ አሰልጣኞች አይስማሙም፣ ድሮ የተማሩ ናቸው የሚለውን ከማራገብ
አለመስማማት ካለው ተስማምተው እንዲሠሩ፤ ካልተማሩ እንዲማሩ፣ ስልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ያለበት ማነው? ፌዴሬሽኑ ነው።
ምንም ሣታደርግ አይስማሙም፣ አልተማሩም ማለት ለእኔ አይታየኝም፡፡ አሁን የብ/ቡድኑ አሰልጣኝን ፌዴሬሽኑ ውጪ ልኮ
ሊያስተምረው ሊያግዘው እውቀቱን እንዲያሳድግ ሊተባበረው ይገባል፡፡ እንደ ሀገር ኢትዮጵያ እኮ ሀኪሞቿን፣ ዶክተሮቿን፣ ኢንጂነሮቿን
ውጪ ድረስ ልካ አስተምራ ታበቃለች። በእግር ኳስም እድል ባለማግኘታቸው አለመማራቸውን እየመዘዙ ከመኮነን ይሄን መንገድ
በመከተል ማብቃት ነው፡፡ አንድ ጥረት ሣይደረግ ማውገዝ አግባብ ነው አልልም፡፡ ዛሬ ቢፈልጉህ ይከቡሃል፤ ነገ ደግሞ በመጥረቢያ
እግርህን ከትክተው ይጥሉሃል፡ ይሄ ለእግር ኳሱ አይጠቅምም ።
ሀትሪክ፡-በፌዴሬሽኑ ውስጥ በዲሲፒሊን ኮሚቴ ውስጥ ታገለግል ነበር አሁንስ…?
አቶ አሰናቀ፡- አሁን ተገፍቺያለሁ፤ እነሱ ናቸው የገፉኝ፡፡ እንድገፋ ምክንያት የሆነኝ ደግሞ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ላይ ከሕግ ውጭ
የተሰራውን ስራ በመቃወሜ ነው፡፡ ስብሰባ ሲደረግ እንዳይነገረኝ፣ እንዳልመጣ በማድረግ በዘዴ ነው ያገለሉኝ። የኢትዮጵያ
አሰልጣኞች ማህበር የደረሰብኝን መገለል እንዲጠይቅልኝ በደብዳቤ ፌዴሬሽኑ ተጠይቆ መልስ የሰጠኝ አካል የለም፤ምክንያቱም
የተፈለገው በዘዴ ከቦታው ዞር እንድል ስለነበር፤ እዛው ሆኖ የሚታገላቸው ለሕግ የሚወግን ሰው ወደ ቦታው እንዲመጣ በፍፁም
አይፈልጉም። ከእኔ በፊትም አንድ የሕግ ባለሙያ በሕጉ መሠረት ሄዱ ስላለ ዞር አድርገውታል፡፡ አቶ ኃይሉ የሕግ ባለሙያ ነው፤ አዲስ
አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ የሰራ ብዙ ልምድና እውቀት ያለው ነው፤ እሱም እንደ እኔ ነው የተገፋው፡፡
ሀትሪክ፡-የብሔራዊ ቡድን ምርጫ ላይ ቅሬታ አላችሁ፤ በተለይ ብሔራዊ ቡድኑም ኦሎምፒኩም በአንድ አሰልጣኝ መሠልጠኑ ላይ?
አቶ አሰናቀ፡-ይሄ ትክክል አይደለም፤ በአገሪቱም አሰልጣኝ ጠፍቶ ነው፤ አንድ ሰው ከላይ እታች እያለ የሚሰራው? ይሄ ስህተት ነው፤
የምንቃወመው አሰራሩን ነው። ሁሉን ነገር በሞኖፖል ተጠቅልሎ እንዲያዝ ማድረግ የሌላውን አሰልጣኝ በአገሩ በሙያው ተቀጥሮ
የመስራት መብቱን የሚጋፋ ነው፤ በተለይ ብሔራዊ ቡድን ላይ የአሰልጣኝ አቀጣጠር ቋሚ ክራይቴሪያ ሊኖረው ይገበዋል እንጂ ልክ
ለአሰልጣኙ በሚመች መልኩ ተዘጋጅቶ የተስፋ
የቅጥር ማስታወቂያ በማውጣት ግለሰቡን ካልሆነ እግር ኳሱን አይጠቅምም ቀደም ሲል ስንቅወም የነበረው ይሄ አይነቱን አሰራር
ነው፤ አሁን እየተደገመ ያለው ይሄው ነው፤ አብርሃም መብራቱ ባለፈበት ክራይቴሪያ አስራት ኃይሌ ተወዳድሮ የማያልፍበት ምክንያት
ቢቀመጥ አይገባም የአስራትን የስራ ልምድና የውጤት ፋይል ስትመለከት ለቦታው ይመጥናል እድሜ ነው እንዳትል እንኳን እሱ
የዑራጓዩ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ እንኳን በክራንች ተደግፈው ብሔራዊ ቡድናቸውን በታላቁ የአለም ዋንጫ ላይ እንዲመሩ ፌዴሬሽኑ
እምነት ጥሎባቸዋል፤ ምክንያቱም ፌዴሬሽኑ ያየው በዱላ ታግዘው መሄዳቸውን ሳይሆን ጭንቅላታቸውን፣ እውቀታቸው ልምዳቸውን
ነው፡፡ እዚህ ግን እድሜ ማጭበርበሪያ ፍላጎትን ማሳኪያ ነው፤ ወጣት ትውልድ ይባላል ወጣት ትውልድ መምጣቱ ጥሩ ነው ወጣቱ
ልምድ ካለው ጋር አብረው እንዲሰሩ በማድረግ የእውቀት ሽግግር አግኝቶ እንዲመጣ ቢደረግ ጥሩ ነው፤ ብሔራዊ ቡድን ወጣት ነው
ተብሎ በእድሜ ብቻ የሚሰጥ ስጦታ መሆን የለበትም፡፡

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

  • በጣም የሚያሳዝን ነው አንድ የህግ ባለሞያ እንዲህ በድፍረት የግለሰብን ስብእና በሚነካ መልኩ መናገር አግባብ አይደለም። የተገቢነት ጥያቄ እንኳን ቢኖር ግልጽ እና ቀጥተኛ በሆነ መልኩ ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ተገቢ ይመስለኛል። እውነት ለመናገር የዩኒቨርሲቲ መምህር ምን ደረጃ ላይ እንዳለ የሚያውቅ አይመስለኝም፤ ግልጽ ለማድረግ ይህል አንድ በስፖርት ሳይንስ የተመረቀ ያውም የዩኒቨርስቲ መምህር በተግባር እንዲሁም በክፍል (ቲዮሪ) የሚሰጠውን ትምህርት በአግባቡና በብቃት ተወጥቶ ካሉት ምርጥ ከምንላቸው የተመረጡ እና ብቁ ዜጋን እንዲቀርጹ ሃላፊነት የጣለባቸው ናቸው። እንደ ዩኒቨርሲቲ መምህርነቴ በተደጋጋሚ የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ ለምሳሌ እግር ኳስን ተጫውተው አላለፉም። መጫወት እስከየትኛው ደረጃ ነው? በፕሮጀክት፣ በክለብ፣ በብሄራዊ፣ በፕሮፌሽናል••••••• ይህን ካልክ በፕሮፌሽናል ደረጃ ተጫውቶ የዩኒቨርሲቲ መምህር የሆነ ላታገኝ ትችላለህ ነገር ግን ከዚህ በታች ያሉትን ቢያን በክለብ ደረጃ የተጫወቱ እንዲሁም ለሞያው ተገዢ ለመሆን በማሰብ በትምህርት በመደገፍ ለሀገራችን ብቁ እና አምራች ዜጋን ለመፍጠር የሚጥሩና እንቅፋት በሚሆኑ ማንበብ እና መጻፍ በማይችሉ በስመ ተጫውተን አልፈናል ባዮች መንገድ ሲዘጋባቸው ቆይተው አሁን ሲከፈት ይህን አይነት አስተያየት ለእግር ኳሱ እድገት ተቆርቃሪ ነኝ ባይ እንዲሁም ህግን ከሚያውቅ ሰው መስማት ያሳፍራል ሚበጀን ያለብንን የጋራ ክፍተት በመተቻቸት ሳይሆን በመደጋገፍ የሀገራችንን እግር ኳስ አለም ከደረሰችበት ማድረስ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
The BiG Interviewአዲስአበባ ከተማዜናዎች

“ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ አብዛኞቹ አሰልጣኞች ይልቅ 100 ፐርሰንት ጨዋ ነኝ ብዬ አምናለሁ”

"ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ አብዛኞቹ አሰልጣኞች ይልቅ 100 ፐርሰንት ጨዋ ነኝ ብዬ አምናለሁ"...

The BiG Interviewቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግኢትዮጵያ ቡናዜናዎች

“ዲሲፕሊን ሳታከብርና አንደበትህን ሳትቆጣጠር ለሰው ተምሳሌት መሆን አይቻልም” ስዩም ተሰፋዬ /ኢት.ቡና/

በከፍተኛ ሊግ የእግርኳስ ህይወቱን ጀምሯል...በተጨዋችነት ዘመኑ በታችኛው ሊግ የተጫወተው ለሁለት ክለቦች ለደብረብርሃን...