THE BIG INTERVIEW WITH AHEMD RESHID
”ከጋናና ናይጄሪያ የመጡት ተጨዋቾች
ቢችሉ ኖሮ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተውአይጫወቱም…”“የኢትዮጵያ ተጨዋቾች ሁሌ ዝናና
ሙገሳ እንጂ ትችት አይፈልጉም ..”
ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ በተለምዶ አሜሪካ ግቢ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ነው…፤ኳስ
ተጨዋች ባልሆን ኖሮ ነጋዴ እሆን ነበር ሲልም ይናገራል፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ከያዛቸው
ተጨዋቾች ጠንካራ የተከላካይ መስመር ተደርጎ ይጠራል ፤እንደ አጨዋወቱ ድፍረት
የተሰማውና ያመነበትን ሲናገር አይፈራም፡፡ ከ2006 በሚጀምረውና በትልቅ ደረጃ
በሚጠራበት የጨዋታ ዘመኑ የደደቢትና የኢትዮጵያን ቡናን ማሊያ ብቻ አድርጓል….
ባለፈው ሃሙስ ደደቢትን 3ለ1 ሲረቱ አንዷን በተለይ የመጨረሻዋንና የቡና ድሉን
ያረጋገጠችውን ሶስተኛዋን ጎል ከመረብ ያሳረፈው አህመድ ረሺድ/ሽሪላ) ከዮሴፍ ከፈለኝ
ጋር በነበረው ቆይታ ስለ ወቅታዊ አቋማቸው፣ ዳኞችን ለሽንፈት ሰበብ ማድረግ
እንደማይመቸው፣ ስለ ዲዲዬ ጎሜዝና ገዛኸኝ ከተማ ልዩነት፤ ስለደጋፊው ሙገሳና ትችት፣
ከመሪው ጋር ያላቸው የ10 ነጥብ ልዩነት ገና ስለመሆኑ፣ የባዕድ አምልኮ እግር ኳሱ ውስጥ
በስፋት ስለመኖሩ፣ ከደመወዝ ጋር ስላለ ክርክር፣ አፍሪካውያን ቢችሉ እኛ አገር አይመጡም
ማለቱ፣ በቦታው ምርጥ ስለሚለው ተጨዋችና ስላስቸገረው አጥቂ፣ ስለቀጣይ ህልሙና
ለኢትዮጵያ ስለሚመኘው ነገር በድፍረትና በግልፅነት ምላሹን ሰጥቷል፡፡
ሀትሪክ፡-ደደቢትን 3ለ1 ረታችሁ… ድሉ ይገባችኋል?
አህመድ፡- ድሉ ይገባናል ብዬ አምናለው…..ከምንም በላይ ያስፈልገን ነበር
የአሠልጣኞቹ ትዕዛዝ ተከትለንና ጠንክረን ተፋልመን በድል ተወጥተነዋል ብዬ
አስባለው፡፡ በርግጥ ዝናቡ ከአጨዋታችን ውጪ አድርጎናል፡፡ ጨዋታውም መቋረጥ
የነበረበት ጨዋታ ነው፡፡ ኳስ አያስገፋም….አይነጥርም ነበር በቃ ከአጨዋታችን ውጪ
ነበርን፡፡ ከእረፍት በኋላ የተሻለ ሆነን የምንፈልገውን ድል አሳክተናል እንጂ አጨዋወታችን
ግን እንደፈለግነው አልነበረም፡፡
ሀትሪክ፡-ፍፁም ቅጣት ምቷ ልክ ነበረች.. በተለይ አርቢትር ባህሩ ተካ የተሳሳተ
ውሳኔ ሰጥቶ ያገዛችሁ አልመሰለህም?
አህመድ፡- ምንም አይነት እገዛ አልነበረውም፡፡ ፍፁም ቅጣት ምቱ ሲሰጥ አጠገቡ
ነበርኩና 100 በ100 ፍፁም ሊባል የሚችል ንክኪ ነበር፡፡ እንኳን በኛ በቫር ቢታይ
እንኳን ቢጫ ካርድ ጭምር የሚያሰጥ ክስተት ነው በርግጠኝነት ፍፁም ቅጣት ምቱ
ይገባናል ምንም አይነት የዳኛ እገዛ የለውም፡፡
ሀትሪክ፡-የቡና ተከላካይ የመጨረሻ ሰው ሆኖ የደደቢትን ተጨዋች ጎትቶ ያስቆመበት
ክስተትስ ቀይ ካርድ አልነበረውም?
አህመድ፡- ሁሉም ነገር ሲታይ ፍፁምነት ….በ90 ደቂቃ ውስጥ ተሳስቷል
አልተሳሳተም የሚለው ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ይገምግሙት እንደኔ ግን
ዳኛው በራሱ ትክክል ወስኗል ዳኛ እስከሆነ ድረስ ራሱ የመሰለውን የመወሰን መብት
አለው፡፡ ዳኛን እንቃወማለን እንጂ እንኳን እኛ ሀገር ምንም ሳይኖር ቫርና ሌሎች ነገሮች
ባሉበትም ሀገር ዳኞች ይሳሳታሉ… ስህተት ሰርቷል ላልከው ስራዬ አይደለምና ልገመግመው
አልችልም፡፡

ሀትሪክ፡-በሀገ ራችን ከጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች መግለጫ ሲሰጡ ተሸናፊው ዳኛ ላይ
ሲያላክክ አሸናፊው ዳኝነቱ ጥሩ ነው ማለቱ የተለመደ ነው.. አንተስ ስላሸነፋችሁ
ወገንተኛ የሆንክ አልመሰለህም ?
አህመድ፡- (ሳቅ) በኔ እምነት ተሸንፈንም እንኳ ዳኛ ላይ ማሳበብ አይመቸኝም፡፡
ነገር ግን አሰልጣኝም ይሁን ተጨዋች ብትጠይቅ ጠቅላላው ዳኛ በደለን ነው
የምንለው…. ዳኛውኮ ሲሳሳት አንዴ ይሁን ከዚያ ውጪ ያለው የቡድኑ ስህተት ከየት
የመጣ ነው? ፍፁም ከወገንተኝነት በፀዳ መልኩ ነው የማወራው፡፡ መጀመሪያም ዳኛ
ላይ ማሳሰብ አልወድም፡፡ አሰልጣኞቹ መግለጫ ሲሰጡ ሁሉም አሰልጣኝ ማለት
እችላለው ዳኛ በደለን ብለው ያወራሉ ዳኛው ካደረገው ድርጊት በፊት ቡድኔ ምን እየሰራ
ነበር ብለው ራሣቸውን መጠየቅ አለባቸው እኔ ወገንተኛ አይደለሁም… እውነቱ ይሄ ነው፡፡
የዳኛ ውሳኔን ተቃውሞ መክበብ የሚባል ነገር አይመቸኝም ስህተቱን እንዳይደግም
ላወራው እሄዳለው እንጂ አምባጓሮ መፍጠር የማልፈልገው የማይገባም ባህሪ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-ከፋሲል ከነማ ባለው ጨዋታ ምን ይጠበቅ?
አህመድ፡- 3 ነጥብ ብቻ….. ይሄ እንደ ቡና ልናሳካው ያቀድነው ነው ማሸነፍ
ግዴታችን ነው በሜዳችን ማሸነፍ ይገባናል፡፡ ጥሩ የሆነ ሞራል ላይ እንገኛለን የጣልናቸው
ነጥቦች እያስቆጩን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ድሉን ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግ አለብን፡፡
ከፋሲል ሙሉ 3 ነጥብ እናገኛለን፡፡

ሀትሪክ፡- አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜዝ ሄዶ ገዛኸኝ ከተማ መምጣቱ ጉዳቱ ወይስ ጥቅሙ
አመዘነ?
አህመድ፡- በዚህ ላይ ብዙ መናገር አልፈልግም፡፡ አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜዝ የራሱ የሆነ
ብቃት አለው ነገር ግን የቡድኑ ስብስብ ጠባብ መሆኑን ተረድቶ መጠቀም አልቻለም፡፡
የአሁኑ አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ ያለንን አቅምና የቡድኑን ጥበት ተረድቶ በሚገባ እየሠራ
መሆኑ የበለጠ እንድንጠቀም አድርጓል፡፡ ጎሜዝ ይህንን አልተጠቀመም በውሳኔ
ተጨዋቾች ላይ ጥገኛ ነበር፡፡ አቅም ማነስም ይሁን ጉዳት ተጨዋቾቻችንን ሲገጥም
ቡድኑ መሸነፍ ጀመረ፡፡ ያንን መፍትሔ ከመፈለግ የተወሰነ ተጨዋቾቻችን ሲገጥም ቡድኑ
መሸነፍ ጀመረ፡፡ ለሽንፈቱ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ የተወሰነ ተጨዋች ላይ ጥገኛ
መሆንን ሲመርጥ የበለጠ ጎድቶናል አሰልጣኝ ገዛኸኝ ግን የቡድኑን አቅም እያየ
ሁሉንም በሮቴሽን ለመጠቀም እየሞከረ ነው… ያ ደግሞ እኛን ጠቅሞናል ባይ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡-ከ5 ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት በኋላ 2 ተከታታይ ጨዋታ ማሸነፍ ወደ
ጥንካሬ እየተመለሳችሁ መሆኑን ያሳያል?
አህመድ፡- ጠንካራ ነን አይደለንም ብዙ የሚያከራር ነው…. ጠንካራ ነን ብዬም
አላስብም ስኳዱ ውስን በመሆኑ ተጨዋች ቢጎዳብን ድላችንን ማስቀጠል ሊከብደን
ይችላል.. የስኳዱ ውስንነት አስቸግሮናል፡፡
ሀትሪክ፡-አዲግራት ላይ ወልዋሎን አሸነፋችሁ… ብቸኛ ምክንያቱ ምን ይመስልሃል?
አህመድ፡- በጣም በፍላጎት ነው የተጫወትነው… እስከዛሬ የተሸፍነው ሽንፈት ቁጭት
ውስጥ ከቶን ነው ወደ ሜዳ የገባነው.. የለበስነው ማሊያ የትልቅ ክለብ ነው የታሪክ
ተወቃሽ መሆን አልፈልግንም፡፡ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በፍላጎት መብለጣችን እንድናሸንፍ
አድርጎናል፡፡
ሀትሪክ፡-የቡና ደጋፊ ሲያበረታታም ሆነ ሲተች ይታያል የትኛው ይገልጻቸዋል?
አህመድ፡-ሁለቱንም ሲያደርጉ ትክክል ናቸው ብዬ አስባለው ጥሩ ከሆንን መመስገን
አቅም ሲወርድና ሽንፈት ሲመጣ መወቀስ የትም ያለ እውነት ነው…… በርግጥ ወቀሳውን
በተወሰነ መልኩ ቢቀንሱ ደስ ይለናል ግን ወቀሳው አለም ላይ ያለ በመሆኑ ድጋፉንም ሆነ
ተቃውሞውን ባላንስ ልናደርገው ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ ተጨዋቾች ሁሌ ዝናና ሙገሳ እንጂ
ትችት አይፈልጉም የሚሰራ ሰው ይሳሳታል.. ከተሳሳትን መተቸታችን አይቀርም ያን
ባላንስ ማድረግ ይጠበቃል፡፡ በብዙ ሺ የሚገመተው የክለባችን ደጋፊ ስታሸንፍ ላይ
ያወጣህና ስትሸነፍ ደግሞ ይተችሃል…. ከፌዴራል ሆነ ከከተማው ፖሊስ ጋር ተጋጭቶ
ፀሀይ መቶት ዝናብ ደበድቦት እየገባ ስሜታዊ ሆኖ ቢሳደብ መቀበል አለብን ጥላቻኮ
የለውም… ስሜታዊ ሆኖ ሲናገር ከክፋት አለመቁጠር የኛ የተጨዋቾች ፋንታ
ይመስለኛል፡፡
ሀትሪክ፡-የውደድር አመቱ ሲፈፀም ኢትዮጵያ ቡናን የቱ ጋር እናግኘው?
አህመድ፡- አሁንም ቢሆን እንደ ቡድን የዋንጫው አሸናፊ ገና አልታወቀም ብለን
እናምናለን፡፡ አንድ ጨዋታ እስኪቀረው ድረስ እንታገላለን ገና ብዙ እድሎች አሉን
አልቻልንም ከተባለ ሁለተኛ ወይም ሶስተኛ የምንወጣ ይመስለኛል ነገር ግን አሁንም
የዋንጫ ተስፋችን አልሞተም፡፡
ሀትሪክ፡- 11 ጨዋታዎች እየቀሩ ከመሪው መቐለ 70 እንደርታ ጋር ያላችሁ ልዩነት
10 መሆኑ የበዛ አይመስልም?
አህመድ፡- በዛ አልበዛም ማለት አይቻልም በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ማን.ሲቲ
ከሊቨርፑል ጋር የነበረው ልዩነት ሰፊ ነበር፡፡ አሁን ግን ተገልብጦ ፍልሚያው በ2 ነጥብ
ልዩነት ሆኗል፡፡ በዘመናዊው አለምም ልዩነት ይፈጥራል ኳስ ላይ ጠንክሮ የሰራ ጥሩ
ውጤት ያመጣል የማይሆን ነገር የለምና ሰፊ ልዩነት ቢኖረውም ማጥበብ ይቻላል ባይ
ነን፡፡
ሀትሪክ፡- ክልል ላይ ስትጫወቱ ማሸነፍ ይከብዳል…. ምክንያቱ የባለሜዳው ደጋፊ
ጫና ወይስ የዳኛ ስህተት?
አህመድ፡- ጉዳዩ የሚወስደን ወደ ዳኛው ይሆናል ይሳሳታሉ….ለዳኛው ቅሬታ ማሰማት
ግን አልወደም፡፡ ይሳሳታሉ ወይ ላልከው በደንብ ይሳሳታሉ… ክልል ላይ ስትወጣ ብዙ ጊዜ
እንቸገራለን.. በዘረኝነቱ መስፋፋት በክልል ማሸነፍ አስቸግሮናል…..የክልል
የበላይነትን ለማስጠበቅ ሲባል ዘረኝነት ተስፋፍቷል፤ ዳኞቹም ስህተት የሚሰሩት ለዚህ
ይመስለኛል… ሁሉም ክልላችን ዋንጫ ይውሰድ ባይ ሆኗል፡፡ በሳይኮሎጂ ተሸንፈን
መግባታችን ደግሞ ለዚህ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ክልል ያለው የዘረኝነት መንፈስን እያየን
በጨዋታው ግጥሚያውን እንደመርሃ ግብር ማሟያነት እያሰብን መሆኑ ጎድቶናል፡፡
ሀትሪክ፡- የባዕድ አምልኮ በኳሱ አካባቢ ገብቷል የሚሉ ወገኖች አሉ… ገጥሞህ
ያውቃል…?
አህመድ፡- በደንብ አለ እንጂ… የችግሩ ሰለባ ሆኜ ራሴ ላይ የደረሰ በመሆኑ መረጃህ
ትክክል ነው፡፡ ዝርዝሩን እንዳልናገር በሃይማኖትም ስለማይፈቀድ አላደርገውም፡፡
ሀትሪክ፡-ላንተ መፍትሔው ምን ይምስላል?
አህመድ፡- ይህን የሚያደርጉ ሰዎች እምነት አላቸውና ፈጣሪያቸውን ሊፈሩ ይገባል፡፡
እንዲህ አድርግ ማለት መፍትሔ ላይሆን ይችላል… ሁላችንም ህግን ላንፈራ ወይም
ላይገዛን ይችላል ነገር ግን ሁላችንም ክር አስረናል ወይም ፀአዳ ይዘናል እናም
ክርስቲያኑና እስልምናው እንደየዕምነቱ የማይፈቀደውን ባዕድ አምልኮን ባያምን
መልካም ይመስለኛል፤ ባዕድ አምልኮን ለመተው ሁሉም በየዕምነቱ ፈጣሪውን ብቻ
መፍራት ይኖርበታል ለችግሩ ብቸኛው መፍትሔ ይሄ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-ኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾች ከአፍሪካዊያን እኩል አይታዩም ይባላል… እውነት
ነው?
አህመድ፡- ለዚህ ጉዳይ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከፌዴሬሽኑ አመራሮች እስከ ኳስ
አቀባዩ ድረስ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አንድ የአፍሪካ ተጨዋችና የኢትዮጵያ ተጨዋች
የሚሰጣቸው ክብር ይለያያል በአመራር ደረጃ እንኳን ትክክል አይደለም…. ያየሁት ነገር
ስላለ ነው፡፡ በምንም ነገር ላይ ልዩነቱ ይታያል፡፡ ለለውጥ ካልሰራን ካሁን በኋላ እየባሰ
እንዳይመጣ እሰጋለው፡፡ አንድ ኢትዮጵያዊና ሌላ ዜጋ እኩል ችሎታ ኖራቸው ቢታዩ ቅድሚያ
የሚሰጠው ለዜጋው ነው… ይሄ ምንም የማያከራክር እውነታ ነው ያ ተፅዕኖ ዞሮ ዞሮ ሀገር
ላይ ተፅዕኖ እያመጣ ነውና መታረም አለበት፡፡
ሀትሪክ፡- ከአቅም ጋር ተያይዞ ለኢትዮጵያዊያን የሚከፈለው በዛ የሚሉ አሉ…
ትስማማለህ ?
አህመድ፡- ፈፅሞ አልስማማም፡፡ ኳስ ይችላሉ አይችሉም ሌላ ጥያቄ ነው….
ክለቡም ያስፈረመው ይችላሉ ብሎ ነው……. መጠየቅ ያለበት ክለቡ ነው ለምን ካልቻሉ
አስፈረማቸው? እንዲያውም ለኛ ለተጨዋቾች በጣም ያንሰኛል ባይ ነኝ፤ ከልጅነታችን
ጀምሮ ከፕሮጀክት ተነስተን ተሰርቶብን አላደግንም ስንት ችግርና መከራ አልፈን ነው ለዚህ
የደረስነው…… ክለቦች ትችላለህ ብለው አምጥተው ሌላው ቢሳደብ አልገረምም መጠየቅ
ያለባቸውና ስህተቱ ያለው ክለቦቹ ጋር ስለሆነ ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ገንዘቡ ያንሳል እንጂ
አይበዛም ለኛ የሚከፈለው ከጥቅማ ጥቅምና ደመወዝ አንፃር ከዜጋው ጋር
አይገናኝም…. ታኬታኮ ራሳችን ገዝተን ነው የምንጫወተው የክለቡ ታኬታዎች ከሁለት
ልምምድ በላይ አያሰሩም፤…. ለልምምድና ለጨዋታ የሚሆኑ የተለያዩ ትጥቆችን
ራሳችን ገዝተን እንዴት ክፍያው በዛ ይባላል? ተጨዋቹ ተዝናንቶበትም ይጨርስ ለቤተሰቡ
ያውለው ተገቢ ክፍያ ነው ብዬ አላምንም…
ሀትሪክ፡- በፕሪሚየር ሊግም ይሁን በታችኛው ሊጎች የሚጫወቱ አፍሪካዊያን
ተጨዋቾች ይመጥናሉ? ወይስ ደካማዎቹ ናቸው የመጡት?
አህመድ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የሚመጡ ተጨዋቾች የመጡት ስለሚችሉ ነው ከተባለ
አልቀበልም… ከጋናና ናይጄሪያ ሊጎች የመጡት ተጨዋቾች ቢችሉ ኢትዮጵያ ውስጥ
መጥተው አይጫወቱም…የሁለቱ ሀገሮች ሊግኮ ከኛ ይበልጣል.. ቢችሉ እዚያው ይቀሩ
ነበር ነገር ግን ስለማይችሉ ነው እዚህ መጥተው የሚጫወቱት፡፡ በአማካይ ስንቱስ ለሀገሩ
ብሔራዊ ቡድን ይጫወታል..? ዜጋ ስለሆነ ብቻ አምጥተን እንዲጫወቱ ማድረጋችን
ሊያሳፍረን ይገባል፡፡ ተመልከት በየመንደሩ ስንት ከነአቅማቸው የተደበቁ ልጆች አሉ..
መጫወት እየቻሉ እድሉን ያላገኙ… እኛምኮ እድለኛ ሆነን እንጂ ታች ካሉት ልጆች
በልጠንም አይደለም… በጣም ብዙ ታለንት ያላቸው ልጆች አሉ.. የሀገራችንን ኳስ ጥግ
የሚያደርሱ ልጆች በሩ ተዘግቶባቸዋል… እንዴትስ ይደጉ.. ለሌላ ዜጋ እምነት ተሰጥቶ
የሀገር ልጅ እየተረሳ ለውጥ የለም ከወጣት ቡድን አደገ ይባላል… ስንት ክለቦች ናቸው
ይህን እድል የሰጡት..? ስንቱስ አለፈ….? አደጉ ከተባሉትስ ፕሪሚየር ሊግ ገብተው
የሚጫወቱ ስንት ናቸው፣ በቃ እውነቱ ይሄ ነው ከየትኛውም ሊግና ሀገር ይምጡ
ኢትዮጵያ ውስጥ የመጡት ስለማይችሉ ብቻ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-ሸሪላ ቅፅል ስምህ ነው..? ትርጉሙስ ምን ማለት ነው?
አህመድ፡- አዎ የቅፅል ስሜ ነው.. የእናቴ ጓደኛ እትዬ የሺ የሚባሉ አሉና ዱአ ላይ
ተቀምጠው ያወጡልኝ ስም ነው…. ብዙ ትርጉም አለው በዚህ ስም ደስተኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ለመጀመሪያ ጊዜ በክለብ ደረጃ የተጫወትከው መቼና ከማን ጋር ነው?
አህመድ፡- በክለብ ደረጃ የኢትዮጵያ ቡናን ማሊያ አድርጌ ዳሽንን የገጠምኩበት
ጨዋታ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-ባንተ ቦታ ያንተ ምርጡ ተጨዋች ማነው?
አህመድ፡- ያለጥርጥር የፒ ኤስ ጂው ዳንኤል አልቬዝ ምርጡ ተከላካይ እርሱ ነው
እወደዋለው የርሱን አጨዋወት በጣም ነው የምወደውና የማደንቀው.. የርሱን
አጨዋወት መከተል ደስ ይለኛል፡፡ ዳኒ ኤልቬዝ ሙሉ ኮሪደሩ ላይ ሲፈነጭ ሳይ
እደሰታለው፡፡ የርሱን ያህል ግን ወደፊት እንድሄድ አምነው ሂድ አጥቃ ብለው ተጨዋቹን
የሚያበረታቱ አሰልጣኞች ያሉ ግን አይመስለኝም፡፡ በርግጥ ነገሩ ቢከብድም የርሱን
አጨዋወት መከተሌን አልተውም፡፡
ሀትሪክ፡-በተቃራኒ ገጥመኸው ያስቸገረህ አጥቂ ማነው?
አህመድ፡- ብዙ ያስደነገጡኝ አጥቂዎች የሉም ነገር ግን ትንሽ ከበድ ያለኝ ሳላሀዲን
ሰይድ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-የልጅነት ህልምህ ምን ነበር?
አህመድ፡- ኳስ ተጨዋችነት የልጅነት ህልሜ ነበር እነ አብዱረህማን መሀመድ
(አቡሸት) ዳዊት እስጢፋኖስ፣ መስኡድ መሀመድ ይዘውኝ ይሄዱ ስለበር ህልሜ ኳስ
ተጫዋች መሆን ነበር.. አሁንም እድለኛ ሆኜ ህልሜን እየኖርኩ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በቀጣይ አመታት የት የመድረስ ህልም አለህ?
አህመድ፡- ፕሮፌሽናል የመሆን ህልሙ አለኝ…. የተለያየ ሙከራ እያደረኩ ነው
በተለያዩ ሰዎች የማደርገው ሙከራ ይሳካል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-በሀገር ደረጃም ይሁን ከውጪ መጫወት ደስ የሚሉህ ስታዲየሞች የትኞቹ
ናቸው?
አህመድ፡- በሀገር ደረጃ የባህርዳር ስታዲየም ደስ ይለኛል…. ከውጪ በአርሰናሉ
ኤምሬትስ ስታዲየም መጫወት ምርጫዬ ነው በነገራችን ላይ የአርሴ ደጋፊ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ከማን.ሲቲና ሊቨርፑል የዋንጫ ድሉን ለማን ሰጠህ?
አህመድ፡- የጋርዲዮላ አድናቂ ስለሆንኩ ለማን.ሲቲ እጄን አንስቻለው
ሀትሪክ፡- ሶስተኛና አራተኛ ሆኖ ማን ይፈጽም?
አህመድ፡- ሶስተኛ ጭቁኗ አርሴና ቼልሲ ቢያልፉ ደስ ይለኛል ማን ዩናይትድ
አይመቸኝም፡፡
ሀትሪክ፡- አገባህ? ወይስ የፍቅር ጓደኛ አለህ?
አህመድ፡- ጓደኛ አለኝ… በቅርቡ ኒካ ለማሰር አቅጄ ነበር ነገር ግን አባቴ በማረፉ
ቀኑን ወደፊት ገፋ አድርጌዋለው፡፡
ሀትሪክ፡- በነገራችን ላይ ከልምምድ መልስ ነው የአባትህን ሞት የሰማኸው
አሉኝ.. እውነት ነው?
አህመድ፡- አዎ ልምምድ ጨርሰን ከሄድኩ በኋላ መንገድ ላይ ግማሹን መንገድ
ጨርሼ ነው የተደወለው…. ራሴን ስቻለው ያልተጠበቀ ሁኔታ ነበር የገጠመኝ…
ሀትሪክ፡- በተጨዋችነት ያንተ ስኬታማ ጊዜ መቼ ነው?
አህመድ፡- በክለብ ደረጃ ስኬታማ ባልሆንም በግሌ ግን ብዙ ስኬቶችን አይቻለው…
ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ምን ትመኛለህ?
አህመድ፡- በትልቅ ደረጃ አገሬን በአለም ዋንጫ ማየት እመኛለሁ… በዚያ ታሪክ
ውስጥ ለመገኘትና ቀን ከለሊት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል ለሀገሬ ለመስራት ዝግጁ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- እንደ ሀገርስ ምን ትመኛለህ?
አህመድ፡- ኢትዮጵያ በ1440 ነቢያችን የሀበሻን ምድር መርቀዋታልና እስከዛሬም
የኖረችው በምርቃት ነው… በመከባበር በመዋደድ በመተሳሰብ የኖረችውን የበፊቷን
ኢትዮጵያን ማየት እመኛለሁ አሁን… ያላቸውን ሳይሆን ህዝቧ በአንድነት የኖረባትን
ኢትዮጵያ እመኛለሁ፡፡
ሀትሪክ፡ ጨረስኩ .. የመጨረሻ ቃል ካለህ?
አህመድ፡- በኔ ህይወት ላይ አንድ ነገር ጣል ያደረጉ ያገዙኝን ከጎኔ የነበሩት ቤተሰቦቼን
ጓደኞቼ፣ አሰልጣኞቼ በሙሉ ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
አስተያየት ይስጡ