የባህርዳር ከተማ የመጀመሪያው ዙር ጉዞ ሲዳሰስ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዙር የመዝጊያ ጨዋታዎች ፍፃሚያቸውን ሲያገኙ በዛሬው ጉዳያችን የባህርዳር ከተማ የመጀመሪያው ዙር ጉዞ ምን ይመስል ነበር የሚለውን ነገር እንደሚከተለው በቁጥራዊ መረጃ አስደግፈን አቅርበንላችኋል።

በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመሩት የጣናው ሞገዶች 23 ነጥቦችን በመሰብሰብ 5ኛ ደረጃን ይዘው የመጀመሪያውን ዙር አጠናቀዋል። ተደጋጋሚ የወሳኝ ተጫዋቾቻቸው ጉዳት በጉዟቸው ተፅእኖ ፈጥሮባቸው በወጣ ገባ አቋም የመጀመሪያውን ዙር ያጠናቀቁት ባህርዳሮች አሁን የሚገኙበት ደረጃ ከነበሯቸው ችግሮች አንፃር ጥሩ ቢሆንም ቡድኑ በወጥነት እንዳይጓዝ ጫና ባይፈጥርበት ኖሮ በሊጉ አሁን እየተስተዋለ ያለው የክለቦች ነጥብ መቀራረብ በትንሹም ቢሆን ሊፈታ ይችል ነበር። በተለይም የአሰልጣኙ የአጨዋወት ዘዴ ጥሩ ኳስ መቆጣጠር የሚችል ሲሆን በተለይ አፍሳሹ ተከላካይ መስመራቸው ግብ እንዲቆጠርባቸው ከማድረጉ ባሻገር ከሜዳ ውጭ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ነጥብ እንዳይዝ ሆኗል። ባህርዳሮች በአብዛኛዎቹ ጊዜ የሚጠቀሟቸው የጨዋታ ስልት ከሳምሶም ጥላሁን እና ፍፁም አለሙ ከመሀል ሜዳ መሰረት አድርገው የሚነሱ ኳሶች በተለይም በግራ እና ቀኝ መስመር ላይ ኳሶችን በመጣል ወደ ተጋጣሚ ግብ ለመድረስ ይጥሩ ነበር።

ባህርዳር ከተማዎች ካደረጓቸው 15 ጨዋታዎች በ7 አሸንፈው በ6 ተሸንፈው በቀሪው 2 ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል። በሜዳቸው ካደረጉት 7 ጨዋታ ሁሉንም በድል ሲወጣ። ይህም ባህርዳር ከተማ በሜዳው ምን ያክል ጠንካራ እና ለመሸነፍ ለተጋጣሚ ትልቅ ፈተና መሆኑን ያሳያል። በሜዳቸው ባደረጓቸው ጨዋታዎች በተጋጣሚው ላይ 18 ግቦችን ቢያስቆጥርም 10 ግቦች ለማስተናገድ ተገዷል። በሜዳው በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች በየጨዋታው 1.2 ሲያገባ 0.6 የሚያስተናግድ ቡድን ነው። ቁጥራዊ መረጃው እንደሚያሳየው ከሆነ ግብ የሚያስቆጥርበት ሚዛኑ ቢደፋም ግብ ደግሞ ላለማስተናገድ ምንም ዋስትና የለውም።

የጣናው ሞገዶች ከሜዳቸው ውጭ ካደረጓቸው 8 ጨዋታዎች በስድስቱ ሽንፈት አስተናግዶ በ2 ነጥብ ሲጋራ ምንም ማሸነፍ አልቻለም። ባህርዳሮች ከሜዳቸው ውጭ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ተራራ የመግፋት ያክል ይከብዳቸዋል። ከሜዳቸው ውጭ ካደረጓቸው ጨዋታዎች በተጋጣሚያቸው ላይ 3 ግብ ብቻ ከመረብ ያሳረፉ ሲሆን በአንፃሩ 13 ግቦችን አስተናግደዋል። በሜዳቸው ሲጫወቱ የሚያስቆጥሯቸው ግቦች ከሜዳቸው ውጭ ሲጫወቱ የሚያስቆጥሯቸው ግቦች ጋር ሲነፃፀር የሰማይ እና የምድር ልዩነት የሚታይባቸው የጣናው ሞገዶች የመከላከል አቅማቸው በሜዳቸውም ከሜዳቸው ውጭም ደካማ መሆኑ ያመላክታል። በሜዳው ግብ በማስቆጠር ጥንካሬ ያለው የፊት መስመራቸው ከሜዳ ውጭ ግን ግቦች ለማስቆጠር እንደሚቸገርም ያስረዳል። ይህም ከሜዳቸው ውጭ በሚያደርጉት ጨዋታ በአማካይ 0.2 ግብ ሲያስቆጥሩ 0.8 ይቆጠርባቸዋል። በአጠቃላይ የጣናው ሞገዶች በመጀመሪያው ዙር 22 ግብ አስቆጥረው 23 ተቆጥሮባቸዋል። ይህም ማለት በየጨዋታው 1.4 ሲያስቆጥር 1.6 በአማካይ ይቆጠርበታል። በዚህኛው ዙር ከፍተኛ ግብ ያስቆጠሩበት ድሬዳዋ ላይ ሲሆን 4-1 ባሸነፉበት ጨዋታ ነበር። በአንፃሩ ከፍተኛ ግብ የተቆጠረባቸው በሲዳማ ቡና 3-1 ሲሸነፉ ነው። በአንድ ጨዋታ ብቻ ግብ ሳይቆጠርባቸው ሲወጡ በ 6 ጨዋታ ደግሞ ግብ ሳያስቆጥሩ ወጥተዋል። በተከታታይ አምስት ከሜዳቸው ውጪ ያደረጓቸው ጨዋታዎች ላይ ሽንፈት ማስተናገዳቸው በመጀመሪያው ዙር በርካታ ነጥብ እንዲጥሉ አድርጓቸዋል። ፍፁም አለሙ 7 ግቦችን በማስቆጠር ከፍተኛ የቡድኑ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ የመጀመሪያውን ዙር አጠናቋል። ባለፈው አመት የጣናው ሞገዶች 22 ነጥቦችን ሰብስበው 7ኛ ደረጃ ላይ ነበር ማጠናቀቅ የቻሉት።

የባህርዳር ከተማ ጠንካራ እና ደካማ ጎን

ምንም እንኳን የሶስት ለሁት ውጤት ቢደጋገምበትም በሜዳው አይደፈሬ መሆኑን በዚህኛው ዙር አሳይቶ ሲያልፍ ከሜዳ ወጥቶ ነጥብ ይዞ ለመመለስ ግን እጅጉኑ የሚያዳግተው እንደሆነ አስመልክቶን አልፏል። የፊት መስመራቸው ግብ ማምረት ቢችልም የኋላ መስመራቸው በእጁጉኑ ተጋላጭ ነበር።

በሁለተኛው ዙር የሚጠበቅባቸው

የኋላ መስመራቸውን በሚገባ በመጠገን ግብ አምራቹነቱን በሁለተኛው ዙር የሚያንፀባርቁ ከሆነ፣ እንደመጀመሪያው ዙር በወሳኝ ተጫዋቾች ጉዳት የማይታመሱ ከሆነ ከዚህ በተሻለ መልኩ ተፎካካሪ ሆነው መቅረብ የሚችሉበት ሰፊ እድል አላቸው።

Hatricksport website Editor

Facebook

ሚሊዮን ኃይሌ

Hatricksport website Editor