“የደጋፊው አቀባበል ከአቅሜ በላይ በመሆኑ ምነው አምላኬ ሜዳ ውስጥ ገብቼ የማስደስትበት ዕድልን እንደገና ቢሰጠኝ ብዬ እስከመመኘት ደርሻለሁ” ሙሉጌታ ከበደ

ሙሉጌታ ከበደ የመጨረሻ ክፍል

ሙሉጌታ የእግር ኳሱ ጌታ

“13 ዓመታት በመጫወቴ ያገኘሁት ነገር የለም፤ ሀብትና ንብረቴ ሕዝቤ ነው፤ በቀን 2 ዶላር አበል እያገኘን ሀብት እንዴት ይጠበቃል”

“የደጋፊው አቀባበል ከአቅሜ በላይ በመሆኑ ምነው አምላኬ ሜዳ ውስጥ ገብቼ የማስደስትበት ዕድልን እንደገና ቢሰጠኝ ብዬ እስከመመኘት ደርሻለሁ”
ሙሉጌታ ከበደ


ስለ እናቱ ጥሩዬ ፈለቀ አውርቶ አይጠግብም፤ ስለ እሳቸው ውለታ ሲያነሳ ከንግግሩ እንባ ይቀድመዋል፤ “እናቴ ለእኔ አይደለም ወሎ ላሉ ስፖርተኞች ሁሉ ባለውለታ ናት፤ ስፖርተኞች ቤታችን መተው በነፃ ይታጠባሉ… ምግብም ይመገቡ ነበር፤ የቤት ሠራተኞች እንኳን አሁንስ ደግነትሽ በዛ ብለው ሰው እንዳይመጣ በር ላይ ውሻ ሲያስሩ እናቴ ግን ለምን ብላ ትቆጣ ነበር፤ በአጭሩ ጥሩዬ ፈለቀ የእኔ ብቻ ሳይሆን የሁሉም እናት ናት” ብሎ ተናግሮ ሳይጨርስ ግድቡን ጥሶ እንደሚፈስ የጎርፍ ውሃ እንባዎቹ በሁለቱም ጉንጮቹ ቁልቁል መፍሰሳቸው የዚህን ዘገባ አቅራቢ ክፉኛ ረብሾታል፡፡ “ብዙ ሰዎች ገንዘብ አባካኝ፣ በታኝም እንደሆንኩ አድርገው ያስባሉ… ግን እኔ ገንዘብ እየበተንኩ እያባከንኩም አይደለም… የተቸገሩ ሰዎችን አይቼ ዝም እንዳልል… ያለኝን አራግፌ እንድሰጥ… ደግነቴን በተግባር አሳይታ ያስተማረችኝ እናቴ ጥሩዬ ናት… ምንላድርግ ደግነትን ከእሷ ነው የወረስኩት… መተው አልችልም” በማለት በእንባና በስሜት በታጀበ መልኩ ምላሽ የሰጠው የእግር ኳሱ ኮከብ (ንጉስ) ሙሉጌታ ከበደ ዛሬ ለሁለተኛ ጊዜ ከእናንተ የተከበራችሁ አንባቢዎቻችን ፊት ቀርቧል፡፡
ሙሉጌታ ከበደ የሚለው ስም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከፍ ብሎ የተሰቀለ፣ በታሪክ መዝገብ በወርቅ ቀለም የተፃፈ የተከበረ ትልቅ ስም ነው… በእርግጥ በዚህ ደረጃ ያለው ስምና በተግባር ያለው የሙሉጌታ ህይወት ተመሳሳይነት ይኖራቸው ይሆን? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ በመሆኑ የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ የገዘፈው ስምህን ያህል የገዘፈ ሀብትና ንብረትስ እግር ኳሱ አትርፎልሃል? የሚል ጥያቄ አቅርቦለት “አንተ ታሾፋለህ እንዴ? የምን ሃብትና ንብረት ነው የምታወራው… በወር 400 ብር ደመወዝ እየተከፈለን… ለጨዋታ ወደ ውጭ ስንሄድ በቀን ሁለት ዶላር እየተሰጠን… እንዴት ሀብትና ንብረት ከእኛ ትጠብቃለህ?… እኔ ሀብቴም ንብረቴም ህዝቡ ነው… በእግር ኳስ ያፈራሁት ሀብቴ የህዝብ ፍቅር ብቻ ነው… ምንም የሌለው ደሀ ታውቃለህ? ያ ማለት እኔ ነኝ… በመደበኛ ህይወቴ የስሜን ያህል ሀብትና ንብረት ባይኖረኝም የህዝብ ፍቅር ስላለኝ በእሱ እየተፅናናሁ እኖራለሁ…”… በማለት አስገራሚ ምላሽ ሰጥቷል፤ ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ በሀትሪክ ጋዜጣ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሁለት ተከታታይ ሳምንት እንግዳ አድርጎ ያቀረበው ሙሉጌታ ከበደ ተዝቆ ከማያልቀው ታሪክ የተወሰነውን ጨልፎ እንዲያጫውተን፣ ትናንትን በዛሬ መነፅር ሊያስቃኘን፣ ዘና እያለ ቁምነገር ሊያስጨብጠን በድጋሚ ይዞት ቀርቧል… የተለመደው አብሮነታችሁ አይለየን፡፡

ሀትሪክ፡- …ሙሌ ባለፈው ሳምንት የነበረውን ቆይታችንን ያቋረጥነው የጨዋታ ዘመንህ ምርጡ አሰልጣኝ ማነው…?…የሚል ጥያቄ አቅርቤ ነበር…ዛሬ ከቆምንበት እንቀጥላለን…ላቅ ያ ቦታ የምትሰጠው የአንተ ምርጡ አሰልጣኝ ማነው…?

ሙሉጌታ፡- …(እንደማሰብም እያለ) …ኧ…የእኔ ምርጡ…

ሀትሪክ፡- …ቆይ…ቆይ…ሙሌ…በጣም ይቅርታ…ለዚህ ጥያቄ መልስ ከመስጠትህ በፊት አንዴ ላቋርጥህ…ያሳለፍነው ሳምንት ለአንተ ጥሩ የሚባል አልነበረም…ወንድምህን በሞት ተነጥቀሃልና በዚህ አጋጣሚ እግዚአብሔር ያበርታህ…ለአንተም ለቤተሰቦችህም መፅናናትን ይስጥህ…ማለትን ማስቀደም እፈልጋለሁ…

ሙሉጌታ፡- …(እንደ መተከዝ ብሎ አንገቱን አቀርቅሮ)…አዎን ትልቅ ሀዘን ላይ የቆየሁት…በአንድ አመት የሚበልጠኝን ታላቅ ወንድሜን መሀመድ ከበደን በድንገኛ አደጋ ተነጥቄያለሁ…በዚህም በጣም ሀዘን ውስጥ ወድቄያለሁ…ወደ አገሬ መጥቼ ከሚወደኝ፣ከሚያደንቀኝ ህዝቤ ጋር ጥሩ የደስታ፣የናፍቆት ጊዜን እያሳለፍኩ ነበር የቆየሁት…በመሀከል ይሄ ያልታሰበ አደጋ ደረሰ…በወንድሜ ሞት ልቤ በሀዘን ተሰብሯል…ያው አምላክ የፈቀደው በመሆኑ የግድ ትቀበለዋለህ…በዚህ አጋጣሚ በገጠመኝ ሀዘን ምክንያት…በርካቶች ከሀገር ውስጥም ከውጭም…ስልክ በመደውል…በአካል በመምጣት አፅናንተውኛልና ሁሉንም ከልቤ ማመስገን እወዳለሁ…፡፡

ሀትሪክ፡- ..ሙሌ በሀዘን ድባብ ውስጥ ሆነህ ለአንባቢዎቼና ለእኔ ክብር ሰጥተህ ለሁለተኛው ቃለ- ምልልስ ስለ ተባበርከኝ በድጋሚ እያመሰገንኩ አሁን በቀጥታ ወደ ጥያቄዬ አመራለሁ…ሙሌ ባለፉት 13 አመታት በርካታ አሰልጣኞች አሰልጥነውሃል…ከአሰልጣኞች ሁሉ ላቅ ያለ…የተለየ ቦታ የምትሰጠው አሰልጣኝ ማነው…?

ሙሉጌታ፡- …እንዳልከው ብዙ ናቸው…መንግሥቱ ወርቁ፣አስራት ኃይሌ፣ካሳሁን ተካ፣ስዩም አባተም በአዲስ አበባ ምርጥ አሰልጥኖኛል…ማበላለጡ ከባድ ቢሆንም ግን…ከሁሉም መንግሥቱ ወርቁን አስበልጣጣለሁ…መንግ የተለየ አሰልጣኝ ነው…ከውሎ ያመጣኝ ለብ/ቡድን የመረጠኝ…በችሎታዬ ትልቅ እምነት የነበረው…በጣም የሚወደኝ የምወደው አሰልጣኝ ነው…መንጌን ማናገር አይደለም አጠገቡ መቆምም እንፈራለን…እንደዛም ሆኖም ግን መንጌ ብዬ የምጠራው እኔ ብቻ ነበርኩ…አንዴ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበረው መንግሥቱን ለምን አትመርጠውም? ብሎ ሲጠይቀው “አርፈህ የቢሮ ስራህን ስራ አይመለከትህም”ብሎታል…ከመንጌ ጋር የቤተሰብም ያህል ነኝ…ከባለቤቱም ጋር ጥሩ መግባባት አለኝ… አሁን ትልቅ ሰው ሆኗል እንጂ ልጁን ኡኒን (ላቃቸውን) በጊዮርጊስ ተስፋ ቡድን አሰልጥኜዋለሁ…መንጌ ኢትዮጵያ በታሪኳያገኘችው ትልቅ ተጨዋችም…ትልቅ አሰልጣኝም ነው…መንጌ አንደተከበረ…እንደተፈራ ያረፈ ሰው ነው…ለአሱ ልዩ ቦታ አለኝ…ከእሱ ሌላ …

 

ሀትሪክ፡- …ከእሱ ሌላ…ምን…?

ሙሉጌታ፡- …ከእሱ ሌላ አስራት ኃይሌም ብዙ አመት አሰልጥኖኛል…አስራት የስራ፣የውጤት ሰው ነው…አስራት ተንኮል የሚባል ነገር የማያውቅ ንፁህ ሰው ነው…አስራት ሁሉንም እኩል የሚያይ ነው…እኔ ሙሉጌታ ልሁን አዲስ የመጣ ተጨዋች እኩል ነው የሚያየን…ለእሱም እንደዚሁ ቦታ አለኝ…ካሳሁን ተካም ትልቅ ጭንቅላት ያለው አሰልጣኝ ነው…ነፍሱን ይማረውና ስዩም አባተም የሀገሪቱ ትልቅ አሰልጣኝ ነው…ብዙውን ጊዜ ከስዩም ጋር የምንገናኘው በአዲስ አበባ ምርጥ ነው፤ እሱ አሰልጣኝ እኔ አምበል ሆኜ…በቃ ከስዩም ጋር መጨቃጨቅ ነው…ስዩም መጨቃጨቅ ይወዳል እንጂ ውስጡ ክፋት የለውም…ስለ ስዩም አባተ ካነሳን አንድ ጊዜ ደሞዙን እንዳስቀጣሁትስ ታውቃለህ…? አስቀጥቶዋለሁ….

ሀትሪክ ፡- …በምን ምክንያት…?

ሙሉጌታ፡…(እየሳቀ)…እሱ ቡናን እያሰለጠነ ነው…ከእኛ ጋር ይጫወታሉ…አንድ ኳስ አገኝቼ ምርጥ ጎል አገባና እናሸንፋቸዋለን…ስዩም በጎልዋ በጣም ተደንቋል መሰለኝ…ጨዋታውን ጨርሰን ስንወጣ ጠብቆ ይጨብጠኛል…ስዩም ይሄን ሲያደርግ…ትሪቡን የነበሩት ኮሚቴዎችና ደጋፊዎች ይከታተሉት ነበር ለካ…“ቡድኑ ተሸንፎ እንዴት ይጨብጠዋል”ብለው አበዱ…በመጨረሻም ደሞዙን እንደቀጡት አስታውሳለሁ…(ሣቅ)…ከእነዚህ ከጠቀሰኩልህ አሰልጣኞች ሌላ ባያለሰጥነኝም በጣም የማደነቀው አንድ ሌላ ትልቅ አሰልጣኝም አለ…

ሀትሪክ፡-…ማን…?

ሙሉጌታ፡- …የመብራት ኃይል አሰልጣኝ የነበሩት ጋሽ ሐጎስ ደስታ…(ነፍሱን ይማረውና)…

ሀትሪክ፡- …ሳያሰለጥኑህ…?

ሙሉጌታ፡- …ባያሰለጥኑኝም ጋሽ ሐጎስን በጣም ነው የማደንቃቸው የማከብራቸውም…ጋሽ ሐጎስ በመብራት የፈጠሩትን አብዮት ልብ ብለህ ስትመለከት ለማድነቅ ትገደዳለህ…ሌላው ሰውነት ቢሻውን ማንሣት ዋእፈልጋለሁ…ሰውነት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ስራ ሠርቷል…ሰውነት ወደ ስልጠናው እንደመጣ ይሄ አሰልጣኝ ትልቅ ስራ ይሠራል ብዬ በጋዜጣ ላይ ሣይቀር የመሰከርኩለት እኔ ነኝ…ያኔ ሰውነት ወደ ስልጠና ሲመጣ ኳስ ተጨውቶ አላለፈም በሚል የሚቃወሙት ነበሩ…ሰውነት ግን በጣም ጎበዝ ተጨዋች እንደነበር እኔ በአይኔ በብረቱ አይቼ ምስክርነቴን ሰጥቼ ነበር…ሰውነት እንደ አስራት፣ ስዩምና ካሳሁን ለብ/ቡድን ሲጫወት ስላልታየ ኳስ እንደማይችል አድርገው የሚያስቡ ነበሩ…እኔ ግን አይችዋለሁ…በጣም ጎበዝ ነው… ኳስም ይችላል…ብ/ቡድኑንም ወደ አፍሪካ ዋንጫ በመመለስም የራሱን ደማቅ ታሪክ በማፃፍ አኩርቶናል፡፡

ሀትሪክ፡- …የጨዋታ ዘመንህ ምርጡ ተጨዋች ብለህ በቅድሚያ የምትጠራው…?

ሙሉጌታ፡- …ብዙ አሉ…ገብረመድህን ኃይሌን /ገብሬን/ አስቀድማለሁ…

ሀትሪክ፡- …በጨዋታ ዘመንህ ከማን ጋር ተጣምረህ ስትጫወት በጣም ይመችሃል…ጨዋታም ይቀልህ ነበር…?

ሙሉጌታ፡- …ከሁሉም ጋር…ምክንያቱም ከበረኛ ደምሮ እስከ አጥቂ ካሉት ጋር በጣም ተግባብቼ ነበር የምጫወተው…ግን አንድ ለይተህ ጥሪ ካልከኝ አሁንም ከገ/መድህን ኃይሌ አልወጣም…ከገ/መድህንጋር ተጣምረን ስንጫወት የአጥቂው ክፍላችን በጣም ያስፈራል…የተቃራኒ ቡድን ተከላካይ ክፍልና ግብ ጠባቂዎች በፍርሃት ይርዳሉ…(ሣቅ)…ከገብሬ ሌላ ማንሣት ካለብኝ ሰለሞን (ቸርኬም)የሚረሣ አይደለም…በጣም የሚግባባኝ…የሚሚመቸኝም ተጫዋችም ነው…ገና ኳስ ስይዝ የት ጋ እንደምገኝም ስለሚያውቅ ኳሱን ይጥልልኛል…ከዚያ በኋላ አለቃ ኳሱን መረብ ውስጥ ነው የምታገኘው…ግን ይሄን ያልኩህ የግድ መጥራት ስላለብኝ እንጂ አብረውኝ የተጫወቱት ሁሉም ይመቹኛል…

ሀትሪክ፡- … የጨዋታ ዘመኔ ምርጡ ግብ የምትለውስ…?
ሙሉጌታ፡- …የቱን ከየቱ ላበላልጥ…?…ምከንያቱም በጣም ብዙ ምርጥ ግቦችን አስቆጥሬያለሁ…ለአንተ መልስ ለመመለስ ያህል ምረጥ ካልከኝ ግን…አንድ ሳይሆን ሁለት ግቦችን በምርጥነትና በልዩ ጎልነት ባነሳ ደስ ይለኛል…

ሀትሪክ፡- …መብትህ ነው ትችላለህ…?
ሙሉጌታ፡- …በተወሰነች ነጥብ የማስበልጣትና የተለየ ስሜት የሰጠችኝ የመጀመሪያዋ ምርጥ ግቤ የምላት…ከሱዳን ጋር በነበረው ጨዋታ ካሳሁን ተካ ለብ/ቡድን ሳይመረጠኝ ቀርቶ በህዝብ ጩኸትና ተቃውሞ ተመርጬ የበረኛውን አቋቋም አይቼ ሱዳን ላይ ከመሀል ሜዳ መትቼ የገባሁት ግብ የእኔ የምንግዜም ምርጧ ግቤ ናት…ያኔ በህዝቡ ጩኸት ነው የተመረጥኩት…ብ/ቡድኑ ራስ ሆቴል ነበር ያረፈው…ህዝብ ራሱ ሆቴል በጩኸት እስኪነቃነቅ ድረስ ተቃውሞውን ካሳሁን ላይ አሰምተው በህዝቡ ጫና ተመርጬ ገባሁ፤የሚገርምህ ከሱዳን ጋር የነበረው ጨዋታ እግር ኳስ ብቻ ርአልነበረም…ፖለቲቲካም ነበረው…ያኔ ሱዳንና ኢትዮጵያ ጥሩ አልነበሩም…በዚህ የተነሣ ትልቅ ውጥረት የነበረው ጨዋታ ነበር…ልክ ጨዋታውው እንደተጀመረ ኳስ ይደርሰናል…ኳሷ ከመምጣት በፊት ቀና ብዬ ሳይ በረኛው ተዘናግቷል…ኳሷ እንደደረሰችኝ ምንም ሳላመነታ ከመሀል ሜዳ አአክርሬ ወደ ግብ ክልል ስልካት ቀጥታ መረብ ውስጥ ገብታ ተሰነቀረች…ስታዲየሙ ቀውጢ ሆነ…ደጋፊው አበደ…ጮኸ …ምክንያቱም ይመለስ ያለው ደጋፊው ስለነበር ዕምነት የጣለብኝን ደጋፊ ባለማሳፈሬና በማስደሰቴ ዛሬም ድረስ ለጎሏም ለጨዋታውም የተለየ ቦታ አለኝ…

ሀትሪክ፡-.. ሁለተኛ ያልከውስ…?

ሙሉጌታ፡-.. በሁለተኛ የማነሣት ጊዮርጊስና አዲስ አበባ ስሚንቶ ከሚባል ክለብ ጋር ስንጫወት ግብ ጠባቂያቸው በጣም ጎበዝና ለአዲስ አበባና ለብ/ቡድን በመጫወት የሚታወቀው ቤተም ከበደ የሚባል ነበር… ብቻ ኳሱን እንዴት ጠብሼ መትቼ እንዴት መረብ ውስጥ እንደተሰነቀረች ዛሬም ድረስ ሳስበው ይገርመኛል… ለዚህች ግብም የተለየ ቦታ አለኝ፡፡ እንደው ማበላለጥ ከባድ ቢሆንም ጅማ ላይ ከኬንያው ብርዌሪ ጋር ስንጫወት ያገበኋቸው ሁለት ግቦችም እንዲሁ በታሪካዊነታቸው ልዩ ቦታ የምሰጣቸው ናቸው፡፡

ሀትሪክ፡- …በጣም የሚያስቸግርህ…አላንቀሳቀስ የሚልህ ተጨዋችስ ማን ነበር…?

ሙሉጌታ፡- …ሁሉም ቡድኖች ለተከላካዮቻቸው…ሙሉጌታን ተጠንቀቁ…ያዙት ብለው መክረዋቸው ስለሚገቡ ሁሉም ለእኔ አስቸጋሪዎች ነበሩ ማለት እችላለሁ…ከሁሉም ሁሉም ግን…በችሎታውም አላፈናፍን ብሎ በጣም የሚያስቸግረኝ የቡናው ተሾመ ተፈራ ነው…ተሼ ብርቱ ወንድ ተከላካይ ነው…፡፡
ሀትሪክ፡- …ከኢት.ቡና ጋር የምታደርጉት ጨዋታንና ፉክክርንስ እንዴት ነው የምታስታውሰው…?

ሙሉጌታ፡- …ኦ…ቡና ገበያ…?…በጣም ምርጥና አስፈሪ ቡድን ነበር…የቡድኑ ስብስብ በጣም ያስፈራል…ምን ማለትህ ነው?እስኪኪተመልከታቸው…ከኋላ ላይ ተሼ ብረቱ፣ጌቱ ተፈራ፣አስራት አዱኛን የመሳሰሉ ግንብ የሆኑ የማይደፈሩ ተከላካዮች አሉት…ከፊት ደግሞ ሙሉጌታ ወልደየስ፣ ሚሊዮን በጋሻው እነ ዮናስ ተፈራ…ኧረ ብዙ አሉ…በጣም ምርጥና የሚገርም ቡድን ነበር…ትልቁ ነገር ግን እኛን አይቻሉንም…(ሳቅ)…ምክንያቱም እኛ ከተጨዋቾች ሌላ በርካታ ደጋፊ አለን…ቡናዎች አሁን እንዳላቸው የደጋፊ ብዛት ቢሆን የበለጠ ያስቸግሩን ነበር…ያም ቢሆን ግን…በወቅቱ እውነቴን ነው የምልህ ስብስቡ በጣም አስፈሪ ነበር…፡፡

ሀትሪክ፡- ሙሌ ብዙዎች ስለ አንተ የሚገርሙበትን አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ…ሙሉጌታ ቁመቱ አጭር ሆኖ ከረዣዥሞቹ በላይ ዘሎ ግብ ያስቆጥራል በዚህም የተለየ ብቃት አለው ብለው በግርምት የሚናገሩ በርካቶች ናቸው…እስቲ ስለዚህ ነገር አጫውተኝ…የቁመትህ ማጠርስ የፈጠረብህ ነገር የለም…?

ሙሉጌታ፡- …ቢፈጥርብኝማ 13 አምት ሙሉ እግር ኳስን ወጥ በሆነ ብቃት አልጫወትም ነበር… ያንን ሁሉ ጎልም አላገባም…ኮከብ ግብ አግቢ…ኮከብ ተጨዋች ተብዬ አልጠራም ነበር…በጭንቅላት ዘልዬ ግብ ማስቆጠሬን በተመለከት ብዙ ሰው ይገርማል…ደግሞም ቢገረሙም እውነት ነው…ግብ የማስቆጥረው ከረዣዥሞች በላይ ዘልዬ ነው….ያኔ የነበሩት ተከለካዮች ርዝመት ብቻ አይደለም ሰውነታቸውም ግንብ ነው….ለምሣሌ መድን እንኳን ውስደው ዘነበ (ቮልቮ)፣አለማየሁ (መለሎ)…ጦሩን ውሰድ እነ አሰፋው ባዩን የመሳሰሉ ረዣዥምና መለሎ የሆኑ ተከላካዮች ናቸው የነበሩት…እኔን ስታይ ጉልበታቸው ጋ ነኝ…ግን ከእነሱ በላይ ዘልዬ ነው ግብ የማስቆጥረው….እዚህ ጋ ያለው ትልቁ ምስጢር መዝለል ብቻ ሳይሆን የምዘል መስዬ ዳኛ ሳያየኝ ቀድሜም ትከሻቸውን በመጫን ወደ ታች እደፍቃቸው ነበር…(ሳቅ)… በዚህ ነገር የተጋጣሚ ቡድን አሰልጣኞችና ደጋፊዎች ሳይቀሩ ይበሳጫሉ… አንዴ የመብራት ኃይል አሰልጣኝ የነበረው ሪኮ ጄላርዲ እንዲሁ ከእነሱ በላይ ዘልዬ ሳገባ “ሞታችኋል ይቺን የምታክል ልጅ እንዴት እናንተ ላይ ዘሎ ያገባባችህኋል” ብሎ ጮሆባቸውእንደነበር አስታውሳለሁ…በዚሁ ዘሎ ግብ ከማስቆጠር ጋር በተያያዘ የመቻሉን አስፋው ባዩን ጦስ ውስጥ እንደከተትኩት ታውቃለህ…?

ሀትሪክ፡- …አረ አላውቅም…?…

ሙሉጌታ፡- …(በጣም ሳቅ)…አስፋው ባዩ በጣም መልካም ሰው ነው… ግን ወደ ጦር ሜዳ እንዲላክ በአንድ ወቅት ምክንያት ሆኜበት ነበር…(አሁንም ሳቅ)…ከመሀል አንድ ኳስ ክሮስ ሲደረግ ሁሉም ሰው አስፋው ረዥም ስለሆነ ጎሉን እንደማላገባው ተስፋ ቆርጠው ነበር፡፡ እኔ ግን ከአስፋው በላይ በልዩ ኳሱን መረብ ውስጥ ከተትኩት… ጉድ ተባለ… የጦሩ ደጋፊዎች አስፋው ላይ ጮሁበት… በተለይ አንድ የጦሩ ከፍተኛ ኃላፊ በቦታው ስለነበር አበደ… ጮኸ… አስፋው በጣም ጨዋ ነበር… ጨዋታው ሲያልቅ መጥቶ ሲጨብጠኝ የባሰ አብዱ… በእለቱ ተናደው ብቻ አላባሩም… አዛዦቹ በነጋታው ወዲያውኑ ወደ ጦር ግንባር የላኩበትን አጋጣሚ አስታውሳለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-… ሙሌ የፊርማ ገንዘብ አግኝተህ ታውቃለህ?

ሙሉጌታ፡-… የምን የፊርማ ገንዘብ? ኧረ በእኛ ጊዜ የፊርማ ገንዘብ የሚባል ነገር የለም፡፡ ያቺው በወር የምናገኛት 400 ብር ደሞዝ ናት… የምትሰጠን እንጂ የፊርማ የሚባል ገንዘብ አግኝቼ አላውቅም፡፡ ሰው ብዙ ገንዘብ የምናገኝ ይመለዋል፤ ያ ሁሉ ተመልካች ስታዲየም ሲገባ ሲመለከቱት ገንዘቡን ሁሉ ለእኛ የሚሰጠን ነው የሚመስላቸው… የሚገርምህ ጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱና ሼህ አሊ አል-አሙዲንም “ደመወዝህ ስንት ነው?” ብለው ጠይቀውኝ 400 ብር ስላቸው ደንግጠው “እንዴ? ያ ሁሉ ጠጠር መጣያ እስኪጠፋ የሚገባው ደጋፊ የሚከፍለው ገንዘብስ?” ብለው ጠይቀውኛል፡፡ እኔ እንደውም በወቅቱ በጣም እድለኛ ነኝ… ከተጨዋቾች ሱፐር ቫይዘር ሆኜ እሠራ ስለነበር ነው ደሞዜ ከፍ ያለው፤ የሚገርምህ እኔ ጌታቸው (ዱላ)፣ እሸቱ ቀጭኑ፣ ጌታቸው አብዶ ደሞዛቸው ሶስት መቶ ምናምን ብር ነው… ልብ በል እነዚህ ሰዎች በጣም ትላልቅና የተከበሩ ሰዎች ናቸው… ደሞዝ ግን እኔ እበልጣቸው ነበር… ከእነሱ ጋር አብሬ በመስራቴ ግን በጣም ደስተኛ ነኝ…. እሁድ ተጨውቼ ሰኞ ከስራ ስቀር ደስ አይላችውም የተለየ ፍቅር ነበር የሚሰጡኝ… አንዴ እንድውም በጣም የሚገርምህ እሸቱ ቀጭኑ ምን አለኝ መሰለህ፣ ሁሉም ተጨዋቾችን እያጋደምኩ በቀኝ አሳይቼ በግራ እያስተኛሁ ሣልፋቸውና ግብ ሳስቆጥር ያይና አንድ ቀን ጠርቶ ምን ይጠይቀኛል መሠለህ?

ሀትሪክ፡-… ምን ጠየቀህ…?

ሙሉጌታ፡-… “አንቺ ሙሉጌታ ለመሆኑ ለእነዚህ ተከለካዮች ገንዘብ ትከፊያቸዋለሽ እንዴ? ሁሉን አንዴ ወደ ቀኝ አንዲ ወደ ግራ እያስተኛሻቸው እኮ ነው ግብ የምታስቆጥሪው… እንዲህ እንዲጋደሙልሽ የምትከፊያቸው ደሞዝ አለ…. (በጣም ሳቅ) ብሎኛል… እኔ ደሞዜ 400 ከዛ ላይ ምን እሰጠቸዋለሁ ብዬ መልሼ አስቄዋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-… ግን ደሞዛችሁ 400 ብር ቢሆንም ደጋፊው ብዙ ነገር ያደርግላችሁ ነበር፤ በተለይ መርካቶ ገብተህ አህያ የማይሸከመው ዕቃ ጭናችሁ ትውጡ እንደነበር ነው የሰማሁት….
ሙሉጌታ፡- … እውነት ነው… (በጣም ሳቅ)… መርካቶ ገብተን አምስት ሣንቲም እንኳን አውጥተን አናውቅም… ደጋፊው ተሻምቶ ነው የምንፈልገውን ዕቃ የሚያሽክመን…በዚህ በኩል ሁሌም መርካቶ እየወሰደ የዕቃ መዓት ተሸክመን እንድንወጣ በማድረጉ በኩል ትልቅ ውለታ ሲውልልን የነበረው ታደሰ ጌታቸው (አፍሮ) የሚባል ደጋፊያችን ነው… ታዴ ለእኔ ብቻ መሠለህ ጊዮርጊስ ፋብሪካ ውስጥ ስንሠራ እነ ገ/መድህን፣ ስዩም፣ ብርሃኑን መርካቶ እየወሰደ ያንበሸብሸን ነበር፤ ታደሰ (አፍሮ) እውነተኛ የቅድስ ጊዮርጊስ ነባር ደጋፊ ነው… አንድ ጊዜ እንድውም ከቤተሰቦቼ ጋር ሆኖ ስለ እኔ በቴሌቪዥን አስተያየት ሲሰጥ አይቼው በጣም ተደስቻለሁ… ብዙ ሰዎች አስተያየቱን አይተው ይሄ ሰውዬ እንዴት ቢወድህና ቢያደንቅህ ነው እንደዚህ የሚናገረው ብለውኛል፡፡

ሀትሪክ፡-በእናንተ የጨዋታ ዘመን ትልቅ ችሎታ ያላቸው ተጨዋቾች የተፈጠሩበት ዘመን ቢሆንም ለአፍሪካ ዋንጫ ሀገራችሁን ማሳለፍና መጫወት አልቻላችሁም…. ?

ሙሉጌታ፡-…የዚህ ጥያቄ መልስ አንተም ይጠፋሃል ብዬ አላስብም ምክንያቱም በዚያን ሰዓት ከችሎታችን ውጪ ያለው ችግር ትረዳለህ ብዬ አስባለሁ… ጥሩ ቡድን ይገነባና ለጨዋታ ወደ ውጭ ስንወጣ አንዴ ዘጠኙ ይጠፋሉ… እንደገና ሌላ ምርጥ ቡድን ሲገነባ ሰባቱ ደግሞ ይጠፋሉ… አሁንም ሌላ ምርጥ ቡድን ሲገነባ ስድስቱ ደግሞ የሆነ አገር ይቀራሉ… ብ/ቡድኑ ያሳለፈለው ሲገነባና ሲፈርስ ነው… ብ/ቡድኑ እንዲህ እየፈረሰ እየተገነባ እንዴት ለአፍሪካ ዋንጫ ሊያልፍ ይችላል? ቢያንስ ከ10 ብ/ቡድን የበለጠ ተጨዋች እኮ ነው የጠፋብን…. በዚህ ሁኔታ ይሄን ማሰብ ከባድ ነው.. በወቅቱ ትልቁ ችግራችን ይሄ ነበር እንጂ ሌላ ነገር አይደለም፡፡

ሀትሪክ፡- ከአንተ ጋር የሚጫወቱ ተጨዋቾች በተለያየ ጊዜ ሲጠፉ አንተ በተደጋጋሚ ሳትጠፋ በመመለስም ትታወቃለህ… ሙሉጌታ ለምን አልጠፋም? ለሚሉ ምን የተለየ መልስ አለህ?

ሙሉጌታ፡-በነገራችን ላይ በወቅቱ ተጨዋቾች የሚጠፉት ሀገራቸውን ጠልተው አይደለም… ፖለቲካዊ ሣይሆን ኢኮኖሚያዊ ስደት ነው… ሁሉም ለሀገራቸው የተለየ ፍቅር አላቸው… ግን የተሻለ ነገር ለማግኘት ህይወታቸውን ለማሻሻል ሲሉ ነው የሚጠፉት እንጂ ሀገራቸውን ይወዳሉ… እኔን በተመለከተ ብዙ ሰዎች “የሀገር ምልክት ዋልያ ነው አይጠፋም ሁሉ ይሉኛል”…. በእርግጥም ብዙ ጊዜ ተጨዋቾች ሲጠፉ እኔ እመለሳለሁ… መጥፋት በሚገባኝ ሰአት ሳልጠፋ ቆይቼ ነው በመጨረሻ አሜሪካ ሄጄ የቀረሁት… ይሄን ውሣኔ እንድወስን ያደገኝ ለልጄ ስል ነው… ልጄ ታማብኝ ስለነበርና የተሻለ ህክምና ማግኘት ስለነበረባት ለእሷ ስል የግድ መወሰን ስለነበረብኝ በመጨረሻ ለመቅረት ወስኛለሁ፤ አለመጥፋቴን በተመለከተ በአንድ ጎኑ ሳየው መልካም ነበር ማለት እችላለሁ… አሁን የሚያየውን ፍቅር ያገኘሁትም በወቅቱ ባለመጥፋቴ በሰው ዘንድ ከተፈጠረ መልካም ስሜት ነው ብዬም አስባለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ከአሜሪካ ወይም ከውጪ የሚመጣን ሰው “እንኳን ደህና መጣህ” እንጂ “ምንድነው ሥራህ? ተብሎ አይጠየቅም” የሚሉ አሉ….ይሄንን አባባል ጥሼ ምንድነው ስራህ ብዬ ብጠይቅህ መልስ ትሰጠኛለህ?
ሙሉጌታ፡- .. ለምን አልሰጥህም… ዙሪያ ጥምጥም መሄድስ ለምን ያስፈልጋል? እኔ አሜሪካን ውስጥ የምሠራው ፓርኪንግ ነው በቃ….

ሀትሪክ፡- ከዚህ ከስራህ ጋር በተያያዘ የታዋቂ የስፖርት ሰዎችን ስም እየጠራህ አሜሪካን ውስጥ ሁላችንም ፓርኪንግ ነው የምንሰራው ብለህ በተለያዩ ሚዲያዎች መናገርህ በተለይ አሜሪካ ያሉትን ሰዎች ቅር አሰኝቷል… ይሄን ልብ ብለሃል….?
ሙሉጌታ፡- … (በጣም እያሳቀ)… ሰው በሚሠራው ሥራ ለምንድነው የሚያፍረው…. አሜሪካን ውስጥ ሥራ አይናቅም… በጣም ጥቂቶችና እድለኞች ከሆኑት ውጪ ሁላችንም በሙያችን ሣይሆን ፓርኪንግ ነው የምንሰራው… በዙ ሰው የሚሠራውን ሥራ አስመልክቶ ለምን እንደሚያፍር ለምን እንደሚዋሽ አይገባኝም… በምንሰራው ሥራ ማፈር የለብንም… ሁሉም የፓርኪንግ ሰራተኛ ነው…. እንደውም እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ የፓርኪንግ ሥራ ጥሩ ሥራ ነው… አንተ እሱን ትላለህ ውሻ ሁሉ የማሸናት ሥራ እንሠራ የለም እንዴ? ለምን እንወሻሻለን መነጋገር ካለብን እውነት እውነቱን ነው….

ሀትሪክ፡- በሜዳ ላይ የእግር ኳስ ህይወትህ ስኬታማ ብቻ ሣይሆን ብልጥ ተጨዋችም ነበርክ… ከሜዳ ውጪ ያለው ህይወትህ ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው የሚሉ አሉ ትክክል ናቸው…?

ሙሉጌታ፡-… በእርግጥ ሁለት አይነት ሰው እንደሆንኩ ይታወቀኛል…. ከሜዳ ውጪ ብልጥ አይደሁም… የእግር ኳሱን ያህል ብልጥ ብሆን ኖሮ የት እደረስ ነበር… እኔ የተቸገረ ሰው አይቶ ዝም ማለት አያስችለኝም… ያለኝን አራግፊ ነው የምሰጠው፤ ብልጠቱን ሜዳ ውስጥ ትቼው የወጣው ያህል ነው የሚሰማኝ፡፡

ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ እግር ኳስ የማይዘነጋ ውለታን ከዋሉ ተጨዋቾች ከፊት የምትገኝ ሰው ነህ፤ እግር ኳሱስ በተራው ውለታዬን ከፍሎኛል ትላለህ?

ሙሉጌታ፡-… ምን አግኝቼ?…. የህዝብ ፍቅር ከሆነ አዎን…ከዚህ ውጪ ከሆነ ግን በእግር ኳሱ አተረፍኩ የምለው ነገር ግን የለም፡፡

ሀትሪክ፡-ወደ ስልጠናው አለም ገብተህ ኒያላን፣ ጊዮርጊስ ተስፋን ኮምበልቻ ጨርቃ ጨርቅንና የዩኒቲ እግር ኳስ ክለብን አሰልጥነሃል ግን አልገፋህበትም… ለምን….?

ሙሉጌታ፡-… እንዴ አላሰራ አሉኛ… እነማን እንደሆኑ ማላውቃቸው ሰዎች እየከታተሉኝ ያባርሩኛል… አንድ ቦታ እንዳልቆይ በሆነ ባልሆነ ነገር ይሸረሽሩኛል… አንዴ ኒያላዎች በጣም ይቸገሩና “ሙሉጌታ ከመውረድ አትርፈን” ብለው ከአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ጋር እኩል ኃላፊነት ሰጥተው ይቀጥሩኛል… ያኔ ኒያላ ውስጥ እነ ጌታቸው ካሳ (ቡቡ) ዘላለም ምስክር (ማንዴላን) የመሳሰሉ ኮከቦች ያሉበት ቡድን ነበር… በቀጣይ ከባንክ ጋር ነበር ጨዋታችን… በዚያ ጨዋታ በባንክ ከተሸነፍን እንወርዳለን… ይሄን ቡድን ማትረፉ አለብን ብዬ ተጨዋቾቹን አነሳሳለሁ… አሰልጣኝ ሆኜ የራሴን ስም አስራ ስድስት ውስጥ ከተትኩ.. ሜዳ ገባን በኋላ አሰፋ የሚባል አንድ ተጨዋች በጣም ደክሞ አየሁት… ከዛ ለአብርሃም ይሄን ልጅ እንቀይረው ስለው እንዴ እሱ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋች ነው እንዴት እንቀይረዋለን? ሲለኝ ብሎ ነገር የለም መቀየር አለበት ስለው አብርሃም ሃሣቤን ሊደግፈው አልቻለም… ከዚያ ወዲያውኑ ትጥቅ አምጡልኝ አልኩና ቀይሬ ወደ ሜዳ ገባሁ… በዚያም በዚያም ብለን ተጨዋቾችን አነሳስቼ ባንክን 2ለ1 አሸንፈን ኒያላን ከመውረድ አተፍኩ… ከጨዋታው በኋላ ወደ ፋብሪካው ስንመለስ ሠራተኛው ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ልክ እንደ መሪ ተቀበለኝ… በዚያው አመት የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ሁሉ አሸነፍን… ግን ብዙም አላቆዩኝም… የጊዮርጊስን ደጋፊ ያሸፍትብናል ብለው ሸረሸሩኝ… አስወጡኝ… ቅ/ጊዮርጊስ ተስፋም የዶ/ር ፍስሀ ዩኒቲም የተሻለ ነገር እየሰራሁ እያለ ተባረርኩ… ማን እንደሚያስባርረኝ እስካአሁን አላውቅም… ግን እየሰራሁ ወዲያው እባረራለሁ… በዚህን ጊዜ በጣም ተበሳጨሁ… እዚህ ሀገር በሙያዬ አሰልጥኜ መኖር አልችልም ብዬ ምርር ብዬ ያለቀስኩበት አጋጣሚ ሁሉ ነበር፡፡

ሀትሪክ፡-. ካለህ ስም፣ ልምድና ችሎታ አንፃር በርካታ ሙሉጌታዎችን መፍጠር ትችላለህ ብለው የሚያስቡ አንተን በቀጣይ ወደ ስልጠናው ተመልሰህ ማየትን ይመኛሉ፣ ከዚያ አንፃር ወደ ስልጠናው የመመለስ ሃሣቡ የለህም… ?

ሙሉጌታ፡-ምነው… ምን አደረኩህ ቢሆንና ብሠራ በጣም ደስ ይለኛል… ግን አያሠሩኝም እየተከታተሉኝ በጣም አማረሩኝ እኮ… አሁን ያለው የእግር ኳስ ፖለቲካ ደግሞ እንደከበደ ነው የሚነግሩኝ፡፡ ከዚህ አንፃር ወደ ስልጠናው ስለመመለስ እንዳለስብ ነው የሚያደርገኝ፡፡

ሀትሪክ፡-ከዚህ ከስልጠና ጋር በተያያዘ በአንድ ወቅት ስልጠና አቁመህ ጉዳይ አስፈፃሚ ሁሉ ሆነህ የሠራህበት አጋጣሚም ነበር ብለውኛል እውነት ነው?

ሙሉጌታ፡-.. ስልጠና ካቆምኩ በኋላ አቶ አብነት ገ/መስቀል ምስጋና ይድረሰውና “በቃ አርፈህ ቁጭ በል፣ በየወሩ ደሞዝህን እኔ እስጠሃለው..” ብሎ ወደ 3ሺ ብር አካባቢ ይከፈለኝ ነበር… ስራ አልሠራም አቶ አብነት ግን በየወሩ ይከፍለኝ ነበር… ስራ ሣልሠራ እቤቴ ተቀምጬ ነበር የምውለው… ይሄ ነገር ባለበቴን አላስደሰታትም…. አንድ ቀን ወንድሟ ሲመጣ ስትነግረው በጣም አዘነ “ሙሉጌታ አንተን የመሰለ ሰው እንዴት ተቀምጦ ይውላልህ?” በል ተነስ ብሎኝ ጉዳይ ማስፈፀም ጉዳይ ገዳይ ሆንኩኝ …(በጣም ሳቅ)… በተለይ ቦሌ ክፍለ ከተማ የኔ ነበር አሪፍ ጥቅምም አገኝ ነበር፡፡

ሀትሪክ፡-…አንተ በእግር ኳስ የነገስክ፣ ስምህ በጣም የሚታወቅ ሰው ነህ…ታዋቂ ሆነህ ጉዳይ ገዳይ መሆን አላስቸገረህም?

ሙሉጌታ፡- … ምንም አላስቸገረኝም… ታዋቂነቴ እንደውም በጣም የጠቀመኝ ይመስለኛል፤ ደግሞም እኮ ጥሩ ነገር አገኝበትም ነበር…. ሰዎች ስለሚያውቁኝ ነገሮች ከሌላው በተለየ ቶሎ ያልቁልኝ ነበር…. በተለይ አንድ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊ ነበሩ የእሣቸውን የቤት የመኪናና የተለያዩ ጉዳዮች እገል ነበር፡፡

ሀትሪክ፡-.. .በአንድ ወቅት የምታሽከረክራት ፊያት መኪና ነበረችህ… ግን በግፊ ሰውን ሁሉ አማራ “ከእሷ መኪና በእግር መሄድ ይሻላል” ሁሉ እስከመባል ደርሰህ ነበር… አሉ እሱንስ ታስታውሳለህ?

ሙሉጌታ፡-… (እየሳቀ) … ይሄን የሚያስወራው ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ነው፤ መኪናዋ ቤቢ ፊያት ናት…. የገዛኋት ወደ 2500 ሺህ ብር አካባቢ ነው፤ የመኪና ባለቤት መሆኔን የሚያሳይ ሊብሬ አላት እንጂ ስቃዬን ነው ያሳየችኝ… ያኔ ገነት ሆቴል ነበር የምናርፈው… ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ሜታ ይጫወት ነበርና እነሱም እዛ ያርፋሉ… ሁሌም ገነነንና ኃይሌ ኳሴን ስጭን መኪናዋ ታስቸግረኛለች… አንዴ ላስቸግራችሁ ግፉልኝ እያልኩ ሁሌም ሳስገፋቸው በጣም ተማረሩ… አንድ ጊዜ ኑ ላድርሳችሁ እንሂድ ስላቸው “ላድርሳችሁ ከምትል ኑ ላስገፋችሁ አትልም” ብሎ ገነነ የተናገረኝ ነገር ትዝ ይለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- … በአሜሪካን በርካታ የቀድሞ ተጨዋቹች አሉ የምትገናኙበትና በእግር ኳሱ ዙሪያ የምትወያይበት አጋጣሚ አለ…?
ሙሉጌታ፡- .. በተለየ በኢትዮጵያዊያን ውድድር ላይ ስንገናኝ በጣም እናወራለን.. ከዚያ ውጪ ግን ከእነ ኃይልዬ ጎላዬ ጋር ብዙ ጊዜ እንገናኛለን.. እንደዋወላለን… አትላንታ እነ ኃይልዬ ጋር ስሄድ እንደ እንቁላል ነው የሚንከባከቡኝ… አንዴ ጎላ ቤት የተለየ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ስፖርተኛ በሙሉ እዛ ተገናኝተናል..ከዚያ ውጭ ግን እንደዋወላለን… እንጫዋወታለን…

ሀትሪክ፡- በአንድ ወቅት ሀትሪክ ለቢሮነት የተከራየችው ቤት ውስጥ ድራፍት ቤት ከፍተህ ስትሠራበት እንደነበር ባቤቶቹ አጫውተውኝ ነበር… እውነት ትነግድ ነበር …?

ሙሉጌታ፡- … በጣም ሰነፍ ነጋዴ ነበርኩ እንጂ አዎን ፍልውሃ ወይም አሮጌ ቄራ የሚባለው አካባቢ ድራፍት ቤት ከፍቼ ነበር…ገበያው ተወው ሌላ ነበር… ችግሩ ምንድነው እኔ ለንግድ የምሆን ሰው አለመሆኔን ነው… ትንሽ እንደሰራሁ ምን ተፈጠረ መሠለህ? አንድ ጊዜ ድራፍቱ አልሸጥ ይልና ይተርፋል… ያኔ ድራፍት እንደ አሁኑ ፓስቸራይዝድ ስላልነበር ማደር የለበትም ብለን እኔና ሠራተኞቼ የተረፈውን በርሜል ሲጥ እናደርጋዋለን… ድራፍቱን ገልብጬ ወደ ቤቴ ስሄድ ወንድሜ ከሳውዲ መጥቶ እቤት ተኝቷል… እኔ ሞቅ ብሎኛል ሲያየኝ በጣም አዘነ… ይሄ ስራ ከሙሌ ጋር አብሮ አይሄድም ይልና ከሃይማኖት አንፃርም ይሁን እኔ እንዳልጎዳ ፈልጎ አላውቅም ብቻ ሥራውን መተው አለበት ብሎ ያከራዩኝ ሰዎች ጋር ሄዶ ገንዘባቸውን ከፍሎ ሥራው አስቆሞኛል፤ ወንድሜ በዚህ በኩል ባያስቆመኝም እኔ ለንግድ አልተፈጠርኩም… በዚህ መንገድ ከንግድ ጋር ተለያየን፡፡

ሀትሪክ፡- ሙሌ የአንተ ታሪክ በሁለት እትም የሚጠናቀቅ አይደለም.. ለሌላ ጊዜ በተለየ መልኩ እንመለስበታለን… የዛሬውን ቆይታችንን ከማጠናቀቃችን በፊት የመጨረሻ ጥያቄ ልጠይቅህ ወደ ኢትዮጵያ የመጣህበት የተለየ ምክንያት አለህ? ወደ አሜሪካስ ትመለሳለህ? ወይስ ጠቅልለህ ነው የመጣኸው?

ሙሉጌታ፡- ከሀገሬ ከወጣሁ 13 አመቴ ነው… በህዝቡ በተለይ በቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊ፣ በቤተሰቦቼ ፍቅር ስቃጠል ነው የኖርኩት… የምሠራበት ፓርኪንግ ኮምፒውተር ላይ የፀሐዬ ዮሐንስን “ማን እንደ ሀገር” እየሠማሁ… እያለቀስኩ… ነው ጊዜዬን ያሳለፍኩት… ስለ ሀገሬ… ስለህዝቤ ሳስብ በጣም ነው የማለቅሰው… እንባዬን የጨረሰው “ማን እንደ ሀገር” የሚለው የፀሐዬ ዮሐንስ ዘፈን ነው… አንዴ በዚህ ዘፈን ሳለቅስ ዋናው አለቃችን ፈረንጁ አይቶ ከላይ መጥቶ ደንግጦ ሁሉ ጠይቆኛል… ሲያደንቁኝ ሲያበረታቱኝ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼን፣ ደጋፊዎቼን፣ ወንድሞቼን አግኝቼ የሰው ረሃቡ አሁን ታግሶልኛል… የደጋፊው አቀባበል ከአቅሜ በላይ በመሆኑ ምነው አምላኬ ሜዳ ውስጥ ገብቼ የማስደስትበትን እድል እንደገና ቢሰጠኝ ብዬ እስከመመኘት ሁሉ የደረስኩበት አጋጣሚ ነበር… የቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊ ፍቅር መናገር ከምችለው በላይ ነው፡፡

ሀትሪክ፡-ሙሌ ከአንተ ጋር የነበረኝ ረዥምና ሰፋ ያለ ቆይታ በዚህ ብናጠናቅቀው መልካም ነው በመጨረሻ የማመሰገን እድሉ ልስጥህና እኔም አመስግኜህ እንለያይ?

ሙሉጌታ፡- ..ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብን በተለይ የቅ/ጊዮርጊስን ደጋፊዎች ማመስገን እፈልጋለሁ… ወደ ሀገሬ ላከኝ ብዬ በጠየኩት ጊዜ ለሰከንድም ሳይያስብ ትኬት አስቆርጦ ወደ ሀገሬ የላከኝና ከሚወደኝ ህዝብ ጋር ወዶኘ ህዝብ ጋር እንድገናኝ እድሉን የሰጠኝን አቶ ከተማ ከበደን (kk) በጣም ነው የማመሰግነው… ሁሌም ለሀገር ባለውለተኞች ለስፖርተኞች ሟችና ከጎናቸው በመሆን የሚታወቀው ታዬ ወግደረስና ወንድሙ ግርማ ወግደረስን የማመስግንበት ቃላት የለኝም … በሰው ሀገር እንዳይከፋን ለሚያደርጉልኝ ነገር በሁሉም ተጨዋቾች ስም ላመሰግናቸው እወዳለሁ… ሌላው ትግራዮ የሚባል ወንድም አለኝ… ትግራዮንም እንዲሁ አመሰግንልኝ… ብዙ ጊዜ ትልቅ ስራ እየሠራ ለኢትዮጵያዊያኖች ውለታ እየዋለ ብዙም የማይታይና ድምፁ የማይሰማ አንድ መልካም ሰው አለ… እሱን ማመስገን እፈልጋለሁ.. የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ ወንድም ኤልያስን…. ኢልያስ የተማሩ ነጮች ማናጀር ሆኖ የሚሠራው ሁሌም ከባለውለተኞች ጎን የሚቆም ለእኔም ለብዙ ሰዎችም ትልቅ ውለታ የዋለ ስራ ያስቀጠረ ሰው ነውና ኤልያስን ከልብ አመሰግነዋለሁ፤ ከእሱ ሌላ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ሀበሾች የስራ እድል የፈጠሩ የU Street ባለቤቶች ሄኖክና ያሬድ ተስፋዬ ምርጥ ኢትዮጵያዊያን ናቸው… ለእነሱም እንደዚሁ የከበረ ምስጋና አቀርባለሁ… ሀበሻ ወደ አሜሪካ ሲመጣ የሥራ እድል ብቻ ሣይሆን እንግሊዘኛም የሚማረው እነሱ ጋር ሲቀጠር ነው ማለት ትችላለህ… ከሁለቱም ሌላ አክስታቸው አዩም መልካመ ሰው ናት… ሌላው ማመስገን የምፈልገው የአሜሪካው ወንድሜ አይናለምን ነው….

ሀትሪክ፡- .. እንደ ሙሌ ምስጋናው አላለቀም..?

ሙሉጌታ፡- ….በጣም ይቅርታ ዘመደ ብዙ ስለሆንኩኝ ነው… እዚህ ሀገር ቤት አቶ አብነት ገ/መስቀልና ጀማል አህመድ እነሱ ቤተሰቦቼ ናቸው… ህወቴን ሙሉ አግዘውኛል …እነሱን ማመስገን እፈልጋሁ…. በእርግጥ ከመጣሁ አብነትንም ጀማልንም አላገኘኋቸውም.. ግን እነሱም ማመስገን እፈልጋለሁ፤ ተቀብለው እያስተናገዱኝ ያሉት ጌታዘሩ እሱ ወንድሜ ነው… አሰፋ ክፍሌን የመኪና ቁልፍ ከነ ሹፌሩ የሰጠኝን ሲሳይን አሜሪካም አዲስ አበባም የሚንከባከበኝን አቶ አይናለም እሸቴን የቅ/ጊዮርጉስ ደጋፊ ብርሃኑ ኃይለ ስላሴ (ፈየራ)ን ከሁሉም በላይ አብሮ አደጌ የልጅነት ጓደኛዬ የሆነው ወልደልዑል ሽፈራውና ባለቤቱ መስታወት ዘለቀን የማመሰግንበት ቃላት የለኝም… የልጅነት ጓደኛዬን ወልደ ልዑልን ከልብ አመሰግነዋለሁ…. ከእነሱ ሌላ ኤፍሬም በክረፅዮን፣ ፋሲል ጎንደሬውን፣ ካቻን በጣም በጣም ከልብ ነው የማመሰግናቸው…. ከዚህ በተረፈ ከጎኔ የሆኑትን ሁሉ ብዘረዝር ቦታ አይበቃህም.. ስለዚህ ስማችሁን ያልጠራኋችሁና ፍቅራችሁን ያለ ስስት የሰጣችሁኝን ሁሉ እግዚአብሔር ይስጥልኝ ውለታችሁን አምላክ ይክፈልልኝ ማለት እፈልጋለሁ፡፡


የመጀመሪያውን ክፍል ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ👇

ወለየው፣ አሸብር፣ ተንኮሉ፣ ንጉሱ ሙሉጌታ የእግር ኳሱ ጌታ

 

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.