“ኢኳቶሪያል ጊኒ ለሙከራ ሄጄ ብ/ቡድኑኑ ባለመቀላቀሌ ጥፋት ሰርቻለሁ፤ ለዚህም ይቅርታ እጠይቃለሁ”መስፍን ታፈሰ /ሐዋሳ ከተማ/

 

በመሸሻ ወልዴ


ሐዋሳ ከተማን ከታዳጊው ቡድን አንስቶ እስከ ዋናው ቡድን ደረጃ በአጭር ጊዜ የተጨዋችነት ዘመን ቆይታው በማገልገል በጥሩ ብቃቱ እየተጫወተ ይገኛል፤ ከክለቡ ባሻገር ለብሔራዊ ቡድንም በተመረጠበት የአጭር ጊዜ የቡድኑ ቆይታው ሀገሩን መጥቀም ጀምሯል፤ በሐዋሳ ከተማ ቄራ ሰፈር የተወለደው ይሄ ተጨዋች መስፍን ታፈሰ ሲባል ወደፊት በእግር ኳሱ ትልቅ ደረጃ ላይ ይደርሳል ተብሎም በብዙዎች ዘንድ ግምት ተሰጥቶታል፡፡
በቅርቡ የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ሙከራን ለማድረግ ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ አምርቶ የነበረው እና ከተመረጠበትም የብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውጪ ለመሆን የቻለውን መስፍን ታፈሰን የሀትሪክ ስፖርቱ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ አናግሮታል፤ ተጨዋቹም ለቀረበለት ጥያቄ ምላሹን ሰጥቷል፤ ተከታተሉት፡፡


ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ አምርቶ ስላደረገው የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ሙከራው


“በፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ደረጃ ውጪ ሀገር ወጥቶ ለመጫወት ባለኝ ፍላጎት ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ ሄጄ ያደረግኩት የመጀመሪያው የክለብ ሙከራ በጣም የተሳካ እና የአማረ ነበር፤ እዛ ስጓዝ በቅድሚያ ከክለቡ ጋር ልምምድን ነበር የሰራሁት ቀጥዬ ደግሞ በአንድ ከካሜሮን ክለብ ጋር በተደረገ የአቋም መለኪያ እና እዛው ከሄድኩበት ሀገር ከሚገኙ ቡድኖች ጋርም ነበር ሶስት ያህል ግጥሚያዎች በማደረግ የሙከራው እድል የተሰጠኝ እና ሁሉንም የሙከራ ጊዜያቶቼን ነው በብቃት ልወጣ የቻልኩት፤ ያም ሆኖ ግን ሙከራውን በእዚህ መልኩ ላደርግ እና ወደ ሀገሬ ልመለስ ብችልም እዛ ከሚሰጠው አነስተኛ ክፍያ አንፃር ተመልሼ ወደዛ ለመሄድ አልቻልኩም”፡፡


የኢኳቶሪያሉ ክለብ ለእኔ ሊሰጠኝ የፈለገው ክፍያ አነስተኛ ነው ስትል


“ለሙከራ የሄድኩበት ቡድን እኛ ሀገር ላይ ከሚከፈለው ክፍያ አንፃር ያነሰ ነው ሊሰጡኝ የፈለጉት፤ ከዛ በተጨማሪ በጥቅማ ጥቅም ደረጃም ቢሆን በብዙ ነገር ሊጠቅሙ የሚችሉበት ሁኔታ ስለሌለ እና እግር ኳሳቸውም ቢሆን ከእኛ ይበልጣል ብዬም ስላላሰብኩ ተመልሼ ለመምጣት ችያለሁ”፡፡


የኢኳቶሪያሉ ክለብ የተሻለ ክፍያን ቢሰጠው ኖሮ ለቡድኑ ይጫወት እንደነበር


“አዎን፤ ቡድኑ ጥሩ ክፍያን ቢፈፅምልኝ ኖሮማ እዛ ሄጄ እጫወት ነበር፤ ምክንያቱም የእኔ ዋንኛ ዓለማዬ ራሴን ወደ ውጪ ሀገር በማውጣት ከሌሎች ተጨዋቾች ጋር ማፎካከርና በተለይ ደግሞ የእኔንም ሆነ የቤተሰቦቼን ህይወት እና ኑሮን መለወጥም በጣም እፈልግም ስለነበር ወደዛ ማምራቴ የማይቀር ነበር”፡፡


ወደ ውጪ ወጥተህ የፕሮፌሽናል ተጨዋችነት ሙከራን ማድረግ መቻልህ ያስገኘልህ ጥቅም አለ…?

“አዎን፤ ወደዛ መሄዴ መጀመሪያ የራሴን አቋም በሚገባ ፈትሼበታለው፤ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተጨዋቾች ጋርም በአቋምና በብቃት ደረጃ ምን አይነት ልዩነት እንዳለኝም የተረዳሁበት ነገሮች ስላሉ ነገም ወደሌሎች በእግር ኳሱ ሻል ወዳሉት ሀገራት በመሄድም ሙከራን እንዳደርግ ከፍተኛ ድፍረትን እንዳገኝም ያስቻለኝ ሁኔታ እና ራሴንም አንድ ደረጃ ከፍ ያደረግኩበት ሁኔታ አለና ይሄን በዋናነት እጠቅሰዋለሁ፤ ሌላው ሳላነሳው የማላልፈው ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ አምርቼ በሄድኩበት ያለፉት አንድ ወራት የሙከራ ጊዜ ቆይታዬ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት የአገራችን እግር ኳስ በተቋረጠበት ሰዓት ምንም አይነት የዝግጅት እንቅስቃሴን በጋራ የመስራት ሁኔታ አልነበረምና ለእኔ ግን እዛ መሄዴና የክለብ ሙከራዬን ማድረግ መቻሌ ለአዲሱ የውድድር ዘመንም በብቁ ሁኔታ እንድቀርብ አዘጋጅቶኛልና ይሄን በመልካምነቱ ነው የምጠቅሰው”፡፡


ወደ ኢኳቶሪያል ጊኒ በተጓዝክበት ወቅት የእነሱን እና የእኛን የእግር ኳስ እንቅስቃሴ ስታነፃፅረው


“ከእኛ አንፃር እነሱን እንደጠበቅኳቸው አላገኘዋቸውም፤ ኢትዮጵያኖች ምርጥ ችሎታም እንዳላቸው ነው በንፅፅር ደረጃ የተረዳሁት፤ በሙከራው ወቅትም እኔ የተሳካ ጊዜን ስላሳለፍኩና በራሴ እንዳላፍርም ስላደረገኝ ያ ሊያስደስተኝም ችሏል፤ በኢኳቶሪያል ጊኒ ቆይታዬ ሌላ ያስተዋልኩት እና ላነፃፅርም የፈለግኩት ጉዳይ የእነሱ ቡድኖች በባለ ሀብቶችም የተያዙ መሆናቸው ነው፤ ከዛ ውጪም የመጫወቻ ሜዳዎቻቸውና ስታድየሞቻቸውም ምርጥ ናቸውና በዛ እነሱ ተሽለው ይታያሉ፤ ሌላው ለኳስ ያላቸው ፍቅርም በጣም ደስ ይላል”፡፡


ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመመረጥ እና የመጠራት እድሉ ገጥሞት ቡድኑን ስላልተቀላቀልክበት ሁኔታ


“በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ በሚመራው የብሔራዊ ቡድን ውስጥ የመጠራት እድሉ ሲገጥመኝ እኔ በኢኳቶሪያል ጊኒ የሙከራ እድል ላይ ነበርኩ፤ ከዛም ይሄ ሙከራ አልቆ ወደዚህ ልመጣ ስል የመመለሺያዬን ትኬት ዛሬ፣ ረቡዕ፣ ዐርብ እያሉ አዘገዩብኝና በዛ ምክንያት ነው ወደዚህ ሀገር በመምጣት ቡድኑን ቶሎ ልቀላቀል ያልቻልኩት፤ እዚህ ከመጣሁ በኋላም ወደ ቡድኑ ካምፕ ለመግባት ዘግይቼ ነበርና ለአሰልጣኙ ምንም ነገርን ሳልል ወደ ቤቴ ነበር የተጓዝኩት፤ ከዛም አሰልጣኙ ውበቱ አባተ ሲደውልልኝ ያለውንና ብሔራዊ ቡድኑን ለመቀላቀልም ስለዘገየሁበት ምክንያትም ይቅርታ በመጠየቅ ጭምር አስረዳሁትና ከእሱ ጋር በእዚህ መልኩ ተነጋግረን ለሌላ የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ራሴን እንዳዘጋጅ ነግሮኝ ልንለያይ ቻልን”፡፡


በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ባለመኖሩ የቁጭት ስሜት ተፈጥሮበት እንደሆነና በእዛ ዙሪያ ሊያስተላልፍ ስለሚፈልገው መልዕክት


“የእዚህ ቡድን አባል ሆኜ ሀገሬን ባገለግላት ኖሮ በጣም ነበር ደስ የሚለኝ፤ ያም ሆኖ ግን በራሴ ጥፋት ምክንያት ጥሪው ደርሶኝ የቡድኑን ስብስብ ቶሎ ለመቀላቀል ስላልቻልኩና በቡድኑ ውስጥም ስለሌለሁበት አሁን ላይ የምቆጭበት ነገር የለም፤ ምክንያቱም በቀጣይነት ይሄን የመመረጥ እና የመጫወት እድልን ማግኘቴ አይቀርምና፤ ከቡድኑ ውጪ የሆንኩበትን ሁኔታ በተመለከተ ለማስተላለፍ የምፈልገው የአሰልጣኙን ውሳኔን ተቀብዬዋለሁ፤ አሁንም በድጋሚ እሱንም እንደዚሁም ደግሞ የስፖርት ቤተሰቡን ቡድኑን ቶሎ ባለመቀላቀሌ ይቅርታን እጠይቃለሁ”፡፡


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የመመረጥ አጋጣሚን በድጋሚ ያገኝ እንደሆነ


“በዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ ከዚህ ቀደም የመጠራት እድሉ አጋጥሞኝ ጎሎችን እስከማስቆጠር ደረጃም ላይ ደርሼ ነበር፤ ለኢትዮጵያ ተተኪ ቡድንም ተመርጬ የተጫወትኩበት አጋጣሚም አለ፤ አሁንም በእዚሁ ለምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫ እና ለአፍሪካ ዋንጫም ለሚካፈለው የወጣት ቡድን ውስጥም ተመርጬ ከቡድኑ ጋር ልምምዴን በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና በሚመራው ቡድን ውስጥ ልምምዴን ጠንክሬ እየሰራው ስለሆነም የብሔራዊ ቡድናችንን በድጋሚ አሁን ላይ ካለኝ ገና የወጣትነት እድሜዬ በመነሳት ተመርጬ የማገልግልበት ጊዜ ሩቅ አይደለም”፡፡


በኢትዮጵያ ወጣት ብሔራዊ ቡድን ውስጥ እያደረጉት ስላለው ዝግጅት እና ሊያመጡት ስላሰቡት ውጤት


“የእስካሁን ዝግጅታችን በጣም ጥሩ ነው፤ ውድድሩ በሚፈቅደው መጠንና መልኩም በወጣቶች የተገነባ ምርጥ ስብስብን ይዘንም ለጨዋታው በሚገባም እየተዘጋጀንም ነው የሚገኘው፤ ስለምናመጣው ውጤት በተመለከተ ካለፈው ቡድናችን እና ስህተታችን ብዙ ነገርን እንማራለን፤ እስከ ዋንጫው በሚያስጉዘን ደረጃም ውጤትን ለማምጣትም እየተዘጋጀን ነው የምንገኘው”፡፡


ከሐዋሳ ከተማ ክለብ ጋር ዘንድሮ ስለሚያሳልፈው የፕሪምየር ሊጉ የተጨዋችነት ቆይታው


“ለሐዋሳ ከተማ ስጫወት እስካሁን የነበረኝ ቆይታ በጣም ጥሩ እና የተሳካም ነበር፤ በአንድ ዓመት ከግማሽ ወር በቆየሁባቸው ጊዜያቶችም 12 የሚደርሱ ጎሎችንም ላስቆጥር ችያለሁ፤ ከዛ ውጪም እንደ ቡድን በመጫወትም ክለቤን ጠቅሜያለሁ፤ ዘንድሮ በሚኖረን የውድድር ቆይታም እነዚህን ስኬቶቼን መድገምና በሊጉ የውድድር ዘመን ቆይታዬም ራሴን ለኮከብ ግብ አግቢነት ማፎካከርንም ከእቅዶቼ ውስጥ አስገብቻለውና እነዛን ነው በመጠባበቅ ላይ የምገኘው”፡፡


በፕሪምየር ሊግ ተሳትፎአቸው ሐዋሳ ከተማን የት ደረጃ ላይ ሊያስቀምጡት እንደተዘጋጁ እና ስለ አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት


“ሐዋሳ ከተማ አሁን የገነባው ቡድን በጣም ጠንካራ እና በወጣት ተጨዋቾችም የተዋቀረ ነው፤ ከዛ ውጪም ቡድኑን ሊያጠናክሩ የመጡ ልምድ ያላቸው ተጨዋቾችንም በቡድኑ ውስጥ አካቷል፤ ከእዚህ በመነሳት እኛ ወደ ውድድሩ የምንገባው የሊጉን ዋንጫ ለማግኘት ነውና በዛ ደረጃ ነው የምንፎካከረው፤ አሰልጣኛችንን ሙሉጌታን በተመለከተ እሱ ጥሩ አሰልጣኝ ነው፤ ኳስን መሰረት አድርጎ የሚጫወት ቡድንን ለመገንባትም ተዘጋጅቷልና በክለባችን ቆይታው ጥሩ ነገርን ይሰራል ብዬም ነው የማስበው”፡፡


በእግር ኳስ ተጨዋችነቱ ባለው ችሎታ አሁን ላይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደሆነ


“ገና ምኑን ተጫውቼ ነው እንደዛ የምለው፤ አሁን ላይ ገና ጀማሪ ተጨዋች ነኝ፤ ለትልቅ ደረጃም ለመድረስ ነው ጥረትን እያደርግኩ የምገኘውና ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ደግሞ ያን ምኞቴን ማሳካቴ የማይቀር ነው”፡፡


በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኑ ስለሚያደንቃቸው ታዋቂ ተጨዋቾች እና በልጅነቱ እድሜ ተምሳሌቱ ስለነበረው ተጨዋች


“የእግር ኳስን በደንብ ሳውቅ አድንቄ ያደግኩት ተጨዋች ጌታነህ ከበደን ነው፤ ከእሱ ጋርም ከአጠገቡ አብሬው ብጫወት በጣም ደስ ይለኛል፤ ሌላው የማደንቀው ተጨዋች አዲስ ግደይን ነው እሱም ጥሩ ችሎታ አለው፤ ልጅ በነበርኩበት ሰዓት ላይ ደግሞ የእኔ ሞዴሌ የነበረው ተጨዋች አሁንም ጌታነህ ከበደ እና አዳነ ግርማ ናቸው”፡፡


ቹንኬ ተብሎ ስለሚጠራበት ቅፅል ስሙ


“ስሙን ወላጅ እናቴ ነበር ያወጣችልኝ፤ ልጅ ሳለሁ በጣም ወፍራም ነበርኩ፤ ከዛም ተነስታ ነው ልጠራኝ የቻለችሁ”፡፡


ስለ ባህሪው


“ከምንም ነገር ነፃ ሰው ነኝ፤ ተጨዋችም ነኝ፤ ቶሎም አኮርፋለው፤ ሽንፈትንም አጥብቄ እጠላለሁ”፡፡


በመጨረሻ


“በእግር ኳስ ተጨዋችነት ዘመኔ ዛሬ ላይ ለደረሱኩበት ደረጃ በቅድሚያ የፈጠረኝን አምላክ ማመስገን እፈልጋለሁ፤ ከዛ ቀጥዬም ቤተሰቦቼን በተለይ ደግሞ አባቴ ታፈሰ ሌመኔን ብዙ ነገሮችን ስላደረገልኝ ከምስጋና ውጪ በጣሙን ላከብረውና ለእናቴም ታደለች አቲቶም እና አባቴም ፈጣሪ እድሜና ጤና እንዲሰጣቸውም እመኛለሁ፤ ሌላ ላመሰግናቸው የምፈልገው ለእኔ ጥሩ የሚያስቡልኝን የሰፈር ጓደኞቼን፣ በተለይ የቅርብ ጓደኛዬን ተመስገን ዓለሙንና አሰልጥነውኝ ያለፉትን በሙሉ ልጠቅስም እፈልጋለሁ”፡፡

Hatricksport website editor

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Hatricksport website editor