ወለየው፣ አሸብር፣ ተንኮሉ፣ ንጉሱ ሙሉጌታ የእግር ኳሱ ጌታ

(ክፍል አንድ)

ብራዚሊያዊያን ፔሌን፣ አርጀንቲናዊያን ማራዶንና ሜሲን፣ ፖርቹጋላዊያን ክርሲቲያኖ ሮናልዶን የእግር ኳስ ንጉሳቸው አድርገው ይጠራሉ፤ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ አሸብርና ወለዬው በሚል ቅፅል ስሞቹ የሚታወቀውን ሙሉጌታ ከበደን የእግር ኳስ ንጉሳቸው አድርገው እንደሚያስቡ በተለያየ መንገድ ሲገልፁ ይሰማል፤ በእርግጥ ሃሣቡ ብዙዎችን ሊያስማማ የሚችልበት እድል እንዳለ ቢታመንም በርካቶች ግን እስከዛሬ ምትክ ያልተገኘለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ንጉስ እንደሆነ ግን ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከራሉ፡፡

ለ13 አመታት አቋሙ ሳይዋዥቅ በወጥ ብቃቱ፣ በድንቅ ችሎታው እንዲሁም በረቂቅ ጥበቡና በተንኮሉ ጭምር ደጋፊዎቹን ብቻ ሣይሆን የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች እንዲሁም እግር ኳስን የሚወዱትን ሁሉ ሲያስቦርቅ፣ ሲያስጨፍር በደስታ ሲያስለቅስ የነበረው ሙሉጌታ ከበደ (ወለየው) ከ13 አመታት የአሜሪካ ቆይታ በኋላ ወደ አዲስ አበባ መጥቷል፡፡

በኢትዮጵያዊያን ልብ ውስጥ በድንቅ ችሎታው የማይነቃነቅ ሀውልት ለመትከል የበቃውና ሁሉም በአንድ ድምፅ “ተተኪ ያልተገኘት ተጨዋች ነው” በማለት የሚያወድሱት ሙሉጌታ ከበደ ያለ አንዳች መዋዥቅ በወጥ አቋሙ ለ13 አመታት በመጫወት ስሙን በወርቅ ቀለም ያስፃፈ ባለታሪክ ተጨዋችም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

የሙሉጌታን ድንቅ ጥበብና ጨዋታ ቃላቶች የመግለፅ አቅም እንኳን የላቸውም፤ እሱ የእግር ኳስ አምላክ ያለ ስስት ለኢትዮጵያ የሰጣት ምትሀተኛ ተጨዋች ነው በማለት የሚያወድሰው፣ ምስክርነቱን የሚሰጥ የሀትሪክ ጋዜጣ ማኔጂንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ሚዲያዎች የተረባረቡበትን ሙሉጌታ ከበደን ካለበት አፈላልጎ የሀትሪክ እንግዳ በማድረግ ከአንባቢዎቹ ጋር ለማገናኘት ከፊታችን ቀርቧል፡፡

የሙሉጌታ ከበደ የእግር ኳስ ህይወት በሀገሪቱ ሚዲያዎች ሁሉ በስፋት መዳሰሱ ተጨማሪ የቤት ስራ የፈጠረበት ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ በስፋት ርብርቦሽ የተደረገበትን የእግር ኳስ ህይወቱን ላለመደጋገም በማሰብ በሌሎች እያዝናኑ ቁም ነገር በሚያስጨብጡ ጉዳዮች ላይ ያደረገውን ቆይታ ለአንባቢዎች በሚመች መልኩ ከዚህ በታች ባለው መልኩ አጠናክሮ አቅርቦታል፡፡ ሙሉጌታ ከበደ የቁመቱ ማጠር በእግር ኳስ ላይ ስላልፈጠረበት ችግር፣ ስለ ጥላሁን ገሰሰ፣ ከጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር ስለተገናኘበት አጋጣሚ ቤቱ ከአንዴም ሁለቴ በሀራጅ ከመሸጥ ስለመዳኑ፣ ስለ ቤኒኑ ጨዋታ እንዲሁም የስፖርት ቤተሰቡ እያደረገለት ስላለው አቀበባበልና እየሰጠው ስላለው ፍቅር፣ አንዳችም ሳይሰስት አጫውቶታል አብራችሁን ሁሉ፡፡

ሀትሪክ፡- …ሙሌ እንኳን ደህና መጣህ…?…

ሙሉጌታ፡-… እንኳን ደህና ቆየኸኝ….

ሀትሪክ፡- …ሙሉጌታ መጥቷል ነው ወይስ የእግር ኳሱ ንጉሳችን መጥቷል ነው የሚባለው…

ሙሉጌታ፡- …አንተ የተመችህን በለው፤.. እኔ ግን ወለየው መጥቷል ብትለኝ ነው ደስ የሚለኝ…

ሀትሪክ፡- …አንተን አግኝቼ ቃለ-ምልልስ በማድረጌ በጣም ደስተኛ ነኝ… ለቃለ ምልልሱም ስለተባበርከኝ አመሰግናለሁ….

ሙሉጌታ፡-…እኔም አንተን ከረዥም ጊዜ በኋላ በማግኘቴ በሀትሪክ ጋዜጣ ላይ ቃለ ምልልስም በማድረጋችንና ከአንባቢዎች ጋር የምገናኝበትን እድል ስለፈጠርክልኝ በጣም አመሰግናለሁ፤ ከዚህ በፊት አሜሪካ ተገናኝተን ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል፤ በድጋሚ ስላገኘውህም በጣም ደስ ብሎኛል፡፡

ሀትሪክ፡- አሸብር፣ ወለየው፣ አስጨንቅ፣ ተንኩሉ በየትኛው ስም ብጠራህ ይመቸሃል?

ሙሉጌታ፡- …በሁሉም (ሳቅ)…ሁሉም ደስ ይለኛል…ይመቸኛል…በተለይ ግን “ወሎ” ብትለኝ ሁሉም የሰውነት ክፍሌ ይበልጥ ይነቃቃል…ደስ የሚል ስሜትም ይሰማኛል…ስለዚህ ወለየው በለኝ…(በጣም ሳቅ)…

ሀትሪክ፡- …እንደዋዛ ሀገርህን ጥለህ…በስልጣኔና በኢኮኖሚ ጣሪያ ወደነካችው ሀገር አሜሪካ ከሄድክ ስንት አመት አስቆጠርክ…?

ሙሉጌታ፡- …ጊዜው እንዴት ይበራል…?…እውነት ነው የምልህ ጊዜ ክንፍ እንዳለው ያወኩት አሁን ነው…ምከንያቱም ከሀገሬ ከወጣሁ እንደዋዛ 13 አመት ሆኖኛል፤ እኔ በጣም ቅርብ ጊዜ የወጣሁ ነበር የሚመስለኝ…ለካ 13 አመት ሞልቶኛል…ጊዜ ቆሞ አይጠብቅም የሚባለው እንደዚህ ስለሚፈረጥጥ ነው ለካ…(በጣም ሳቅ)…

ሀትሪክ፡- …ብዙዎች ፔሌን የብራ ዚል…ማራዶናንና ሜሲን የአርጀንቲናና የአለም እግር ኳስ ንጉሶች ብለው ይጠራቸዋል…ሙሉጌታስ የኢትዮጵያ አግር ኳስ ንጉስ አድርጎ መጥራት እንደ ስህተት ያስቆጥራል…?

ሙሉጌታ፡- …(በግርምት አይን እያየ)…እኔ ራሴ…ራሴን የእግር ኳስ ንጉስ አድርጌ ልጠራ…?…. (የግርምት ሳቅ እየሳቀ)…ከእኔ በፊት ስንት የእግር ኳስ ንጉሶች እያሉ…?…በፍፁም እንደዚህ አይነት እብደት አልፈፅምም…

ሀትሪክ፡- …ለ13 አመታት በኢት ዮጵያ እግር ኳስ ላሰየኸው የማይዘነጋ ብቃትና ላስመዘገብከው ስኬት ምትክ ያልተገኘልህ የእግር ኳሱ ንጉስ አድርገው የሚጠሩህ ብዙዎች ናቸው…?…ይሄንንስ ትቀበላለህ…?

ሙሉጌታ፡- …እዚህ ላይ እኔ ችግር የለብኝም…ሰዎች በራሣቸው ሚዛን መዝነው ይገባዋል የሚሉትን ፍርድ ሊፈርዱ ወይም ስያሜ ሊሰጡ ይችላሉ…ከዚህ የተነሣ የፈለጉትን ቢሉኝ እኔ ፀብ የለኝም…ራሴን በራሴ ንጉስ አድርጌም አልጠራም…በሀገራችን ከእኔ የበለጠ ብዙ የእግር ኳስ ንጉሶች እያሉ…ራሴን በዛ ደረጃ አልጠራም…እምነቴ ይሄ ቢሆንም ሰዎች በዚህ ደረጀ ስላሰቡኝና ይገባዋል…ብለው ስለጠሩኝ በውስጤ የሆነ ደስ የሚል የሙቀት፣የኩራት ስሜት እንደሚሰማኝ ልደብቅህ ግን አልፈልግም…(በጣም ሳቅ)…

ሀትሪክ፡- …ከረዥም ጊዜ በኋላ ወደ ሀገርህ ስትመለስ ከኤርፖርት ጀምሮ የተደረገልህን አቀበባበልና ህዝቡ ያሳየህን ፍቅር ለሰከንድም ቢሆን አስበኸው ነበር…?

ሙሉጌታ፡- …(በጣም ሳቅ)…በፍፁም አላስብኩትም…ከኤርፖርት ጀምሮ የጠበቀኝ አቀባበል ከምገምተው ከማስበው በላይ በመሆኑ ከደስታ ይልቅ ድንጋጤ ነው በፊቴ ላይ ቀድሞ የመጣው…ከሀገሬ ከወጣሁ ከ13 አመት በላይ ሆኖኛል…እግር ኳስ በ1989 ዓ.ም አካባቢ ነው ያቆመኩት…ወደ 24 አመት አካባቢ ሆኖኛል…ይሄ በጣም ረጅም ጊዜ ነው…ለሀገሬ የሠራሁት ውለታ…በሰው ልብ ውስጥ በዚህ ደረጃ እንደ ሀውልት ቆሟል…ይታወሳል የሚለው ላይ ጥርጣሬው ነበረኝ…ነገር ግን ያየሁት ሁሉ ከግምቴ በላይ የሆነን ነገር ነው፤ከሚገባኝ በላይ ክብርን፣ፍቅርን ሰጥተውኛልና…እግዚአብሔር ያክብርልኝ ለማለት ነው የምፈልገው፡፡

ሀትሪክ፡- …ለ13 አመት ያገለገልከው ክለብህ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች በተለይ በአዲስ አበባ ስታዲየምና በተለያዩ ፕሮግራሞች ላይ ያሳዩህ ፍቅርና አቀባበልስ በውስጥህ ምን አይነት ስሜት ተፈጠረ…?

ሙሉጌታ፡- …ስለ ቅድስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች የምናገርበት ቃላት የለኝም…ድሮም ፍቅር የሆነ እውነተኛ ደጋፊ እንደሆነ አውቃለሁ…አሁን ደግሞ ከረዥም ጊዜ በኋላ ያሳዩኝ ፍቅር እስከ ህይወት ዘመኔ ከውስጤ የማይጠፋና አብሮኝ የሚኖርነው…ደጋፊው በአጭሩ ውለታ የማይረሣ ለሞተለት የሚሞት ደጋፊ እንደሆነ አውቅ ነበር…አሁንም ያረጋገጥኩት ይሄንን ነው፤ “ጀግናችን ነህ፤የክለባችንን ስምና ታሪኩን ከፍ ያደረክ ባለውለተኛችን ነህ ብለው የሰጡኝ ፍቅር በገንዘብ የሚተመን አይደለም…በእርግጥ የጊዮርጊስን ስም ከፍ ለማድረግ አቅሜን፣ጉልበቴን ሁሉንም ነገሬን ለ13 አመታት ያህል ሰጥቻለሁ፤ግን ይሄ ነገር በወቅቱ ሆኖ ያለፈ እንጂ ዛሬም ድረስ በሰዎች ልብና አዕምሮ ውስጥ ተቀምጦ እንደ ትልቅ ውለታም ተቆጥሮ…ጊዜ የማይቀይረው ፍቅር አገኝበታለሁ ብዬ ለሰከንድም አስቤ አላውቅም ነበር… ምንም ጊዜው ረዥም ቢሆን እንኳን የሚያስታውሰኝ እንዳለ ፍቅርም እንደማያረጅ ጊዜ እንደማይለወጠው በአይኔ በብረቱ አይቻለሁ…በዚህ አጋጣሚ በጣም ግርም ያለኝን አንድ ነገር ልንገርህ…

ሀትሪክ፡- …ምን…?

ሙሉጌታ፡- …በጣም የገረመኝ ነገር ፍቅራቸውን ያለስስት የሰጡኝ በጨዋታ ዘመኔ ስጫወት ያዩኝና የሚያውቀኝ ብቻ ሣይሆን የአዲሱ ትውልድ ደጋፊዎች ጭምር መሆናቸው ነው፤ ገና አንድ ፍሬና ለጋ የሆኑ ታዳጊዎች ሳይቀሩ “ሙሌ እንወድሃለን፤ባለውለተኛችን ጀግናችን ነህ” ብለው እግሬ ላይ ጭምር እየወደቁ ያሳዩኝ ፍቅር ግርምት ብቻ ሣይሆን ልብን የሚነካ ሆኖብኛል…አልቅሰው አስለቅሰውኛል… ወጣቶች፣አዛውንቶች፣ጎልማሶች ወንድ ሴት ሳይሉ አቅፈውኝ በደስታ ተላቅሰናል…ግማሾች እግሬ ላይ ወድቀው ለማንሣት ሁሉ ከባድ ነበር…ይሄንን መቼም አልረሳውም በየሄድከበት ሲያዩኝ ስሜ ሲነሣ ሰው ላይ የሚታየው ነገር እንዴ ለሀገሬና ለቅ/ጊዮርጊስ ይሄን ያህል ምን ብሰራ ነው? ደግሞስ ይሄ ሁሉ ነገር ይገባኛል? ብዬ ራሴን እስከመጠየቅ ሁሉ ደርሻለሁ፤ የደጋፊው ሁኔታ በውስጤ ከፈጠረው ከፍተኛ ደስታ የተነሣ አንደገና ሜዳ ውስጥ ገብቼ የማስደሰት እድል አምላክን በድጋሚ ቢሰጠኝ ብዬ እስከመመኘትም ሁሉ ደርሻለሁ፤ሌላው የሚገርምህ ነገር “ጀግናችን ነህ እንወድሃለን” ብለው የተቀበሉኝ የሌላ ክለብ ደጋፊዎች መሆናቸውም ጭምር ነው…የቡና ደጋፊዎች ሳይቀሩ ልክ እንደ ክለባቸው ተጨዋች የተለየ ፍቀርና የጀግና አቀባበል ነው ያደረጉልኝ፤ በዚህ አጋጣሚ እነሱንም የሌላ ክለብ ደጋፊዎችንም አመሰግናለሁ…እናቴ ድሮ “የሰው ፍቅር ይስጥህ” የሚለው ምርቃቷ መሬት ጠብ አለማለቱንም ያየሁበት አጋጣሚ ፤ሌላም አንድ የገረመኝን ነገር ልጨምርልህ…

ሀትሪክ፡- …ምን…?…

ሙሉጌታ፡- …አንድ የ90 አመት አዛውንት በቴሌቪዥን አይተውኝ ሙሉጌታ መምጣቱን አይቻለሁ…ሠምቻለሁ…አምላክ እድሜ ሰጥቶኝ 90 አመት ላይ ደርሻሳለሁ…90ኛ አመት ልደቴን የማከብረው…ኬክ የምቆርሰው…ይሄ ጀግና ሲመጣ ብቻ ነው እሱ ካልመጣ ልደቴንም አላከብርም…ብለው የEBS ልጆች መጥተው ወስደውኝ…የሚገርምና መቼም የማይዘነጋ ጊዜን አሳልፈናል…ልብ በል እኚህ ሰው አዛውንት ናቸው…ግን ዛሬም ድረስ እንዴት ፍቅራቸውን እንደሚገልፁልኝ ተመልከት…ልጆች፣ ወጣቶች፣ ጎል ማሶች፣ አዛውንቶች፣ወንድ ሴት ሣይሉ ሁሉም ፍቅራቸውን ነው ያለስስት የሰጡኝ፡፡

ሀትሪክ፡- …በእርግጥ ካለህ ታሪክና ዝና በመነሳት እንዲሁም የእግር ኳሱ ንጉስ በመሆንህ ከመጣህ ጀምሮ በርካታ ሚዲያዎችና ተረባርበውብሃል፤ከዚህ አንፃር በተቻለኝ መጠን ያልተነሱ ነገሮችን ለማንሣት ጥያቄዎችን ላለመደጋገም ነው የምሞክረው….ሙሌ…ከሁሉም ጥያቄዎችና በፊት…ጎል እምቢ ሲልህ…ሊጠምብህ…ስታደርገው ስለነበረው ነገር እንዳነሳ ትፈቅዳልኛለህ…?

ሙሉጌታ፡- …(በጣም ሣቅ)…ደግሞ ምን ልታመጪብኝ ነው…?…ጎል እምቢ ሲለኝ ደግሞ ምን አደርግ ነበር…?…እናንተ ጋዜጠኞች እኮ የማታመጡት ነገር የለም…(አሁንም ሳቅ)…

ሀትሪክ፡- …ሙሉጌታ ብዙ ጊዜ ጎል እምቢ ሲለው…ሲጠምበት…“ጓደኞቹ ደሴ ደርሶህ ና” ይሉት ነበር…ይባላል…አንተም መጣሁ ብለህ…ወደ ደሴ ሹልክ ብለህ ትሄድ ነበር….ከደሴ ስትመልስ ደግሞ ጎሉን ታዘንበው ነበርና…እስቲ እሷን አጋጣሚ አንሳልኝ…?

ሙሉጌታ፡-…(ያላባራ ረዥም ሳቅ)…ምን ልትለኝ ፈልገህ…እንደሆነ ገብቶኛል…(አሁን ሳቅ)…

ሀትሪክ፡- …እኔ ምንም አላልኩም…ጉዳዩንም ሰዎች ከጥንቆላ የሆነ ነገር አስቀብረህ ከመምጣት ጋር አያይዘው ሲያሙህ እንደነበር አስታውሳለሁ …

ሙሉጌታ፡- ኧረ… በቃ… (አሁንም ሳቅ) …ግን ይሄንን ነገር እንዴት አስታወስከው…እኔ ኮ ረስቼዋለሁ በጣም ይገርማል…እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ በወቅቱ እንደቀልድም እንደተረብም እንደዚህ አይነት ነገር ይባል ነበር፤እኔን እራሱ ጎል እምቢ ሲለኝ ጓደኞቼ “ደሴ ሄደሽ አስመትተሽ ነይ” ይሉኝ ነበር (በጣም ሣቅ) …ደግሞም እውነት ለመናገር ጎል እምቢ ብሎኝ ጠሞብኝ ቆይቼ መጣሁ ብዬ ደሴ ደረስ ብዬ ስመለስ…የክረምት ዝናብ ታውቃለህ ልክ እንደዛ ጎሉን አዘንበዋለሁ…(አሁንም ያላባራ ሳቅ)

ሀትሪክ፡-…ሙሌ ያለፈ ታሪክ ስለሆነ እስቲ በግልፅ እንነጋገር…ጎል እምቢ ሲልህ ወደ ደሴ የምትሄደው ለምንድነው?

ሙሉጌታ፡-…(በጣም እየሳቀ).. ስሟ Sheet ምን ልትለኝ ፈለገህ ነው…?…(አሁንም ሳቅ)…ወደ ደሴ እያንደረደረ የሚወስደኝ የእናቴ የጥሩዬ ፍቅር ነዋ…ሌላ ምንም አይደለም…ብዙዎች ግን ልክ እንደ አንተ ነገሮችን ጥንቆላ ከሆነ ከማስቀበር ነገር ጋር ለማያያዝ ሲሞክሩ እሰማ ነበር…(በጣም ሳቅ)…

ሀትሪክ፡- …አንድ ጊዜ ደግሞ በምስራቅና መከላከለኛው አፍሪካ ዋንጫ ጊዜ የሙዚቃ ንጉሱን ጥላሁን ገሰስን ለመጀመሪያ ጊዜ ስታዲየም ገብቶ ጨዋታ እንዲከታተል ጋብዛኸው የተናገረው ነገር ነበር አሉ እሱንስ ታስታውሰዋለህ?

ሙሉጌታ፡- …(አሁንም ሳቅ) ኧረ አንተ የምትገርም ሰው ነህ… ስትፈለፍል ነው የከረምከው ማለት ነው… (ሣቅ).. እሱ ደግሞ ምን መሠለህ አሁን ላስቬጋስ ያለች ቲጂ የምትባል ፉል ቤት የነበራት ልጅ ነበረች፤ ፉልዋ በጣም ይመቸኛል፤ ባለቤትዋ ደግሞ ከድር አረቦ ይባላል፤ ፉልዋ በጣም ልዩ ስለሆነ እሷ ቤት የማይመጣ ታዋቂና ትልቅ ሰው የለም፡፡ ጋሽ ጥላሁን እዛ ቤት ይመጣል፤ አንድ ቀን ትሬይኒንግ ሰርቼ ፉል ለመብላት ወደ ቲጂ ቤት እሄዳለሁ፤ በወቅቱ ለምስራቅና መካከለኛ አፍሪካ ዋንጫ ለብ/ቡድናችን ተመርጬ ነበር፤ እዛ ስሄድ ጋሽ ጥሌ ተጨዋች መሆኔን አያውቅም…. ማጠሬንና ትንሽነቴን አይቶ “አንቺ አንዴ ነይ እስቲ የሆነ እቃ ገዝተሽ ነይ” ይለኛል፤ እኔም ጥሌ ትልቅ ሰውና ተወዳጅ ስለሆነ እሺ ብዬ በርሬ ያዘዘኝን ላመጣለት እወጣሁ፤ ቲጂ ዞር ብላ ስታየኝ የለሁም፤ የት ሄደ ስትል ጥሌ “እኔ ልኬው ነው” ይላታል… እሷም ውይ ጥሌ እሱን ላከው?” ስትለው “ልጅ አይደለም ምን ችግር አለው? ይላታል” በመሀል የተባልኩትን ይዤ መጣሁ… እሱም አመሰግናለሁ ብሎ ተቀበለኝ… ከሰጠሁት በኋላ አንድ ሃሣብ በስውጤ ተፈጠረ…

ሀትሪክ፡-… ምን አይነት ሃሳብ… ?

ሙሉጌታ፡-.. እንደ ነገ ብ/ቡድናችን ከኡጋንዳ ጋር ጨዋታ አለው… ታዲያ ጥሌ ስጫወት እንዲያየኝ ለምን አልጋብዝውም አልኩና መጣሁ ብዬ መኪናዬን አስነስቼ ወደ ስታዲየም ነዳሁት፣ ያኔ ጋሽ ካሳ ነበሩ ኃላፊው… ቀጥታ እሣቸው ጋ ገባሁና ጋሽ ካሳ ለነገ ጨዋታ አንድ የግብዣ ትኬት ፈልጌ ነበር ስላቸው “እንዴ ሙሌ የተመደበልህን ሁለት ትኬት እኮ ወስደህ ጨርሰሃል” ሲሉኝ ልክ ኖት ይሄ ግን በጣም ትልቅ እንግዳ ንጉስ ነው ስላቸው “ይሄንን ያህል ማንን ልትጋብዝ ፈልገሀ ነው?” ብለው መለሱልኝ… ወዲያው ከአፋቸው ነጥቄ የሙዚቃው ንጉስ ጥላሁን ገሰሰን ልጋብዘው ነው ስላቸው ከአንድ አንድ ትኬቱን ሰጡኝ… ትኬቱን ይዤ እንደገና እየበረርኩ ወደ ቲጂ ፉል ቤት፡፡

ሀትሪክ፡-…ከዚያስ… ?

ሙሉጌታ፡-….እዛ እንደገባሁ ጥላሁን ጋ ሄድኩኝና… ጋሼ እንኳ አልኩት… ኮስተር ብሎ “ምንድነው ይሄ ደግሞ?” ሲለኝ… ነገ ከኡጋንዳ ጋር ጨዋታ አለን… ስታዲየም ገብተህ እየኝ አልኩት… ትኬቱን ተገርሞ ተቀበለኝ… ይገባል ብዬ አላሰብኩም ጥሌ ሊመለከተኝ ስታደየም ገባ፤ ልክ እኛ ከሰርቪስ ወርደን ደጋፊው በጩኸት ሲያቀልጠው ምንድነው ብዬ ዞር ስል ትሪቡን ያለው ደጋፊ ጥሌን በጩኸት ተቀበለው፡፡ ደስ አለኝ የበለጠ ለመጫወትና አንድ ነገር ለመስራትም ተነሳሳሁ፤ በጣም የሚገርምህ በጨዋታውም ጥሩ ነበርኩ ብቻ ሣይሆን ምርጥ ጎልም አገባሁ… ታዲያ በነጋታው ምን ባደርግ ጥሩ ነው…

ሀትሪክ፡-… ምን አደረክ… ?

ሙሉጌታ፡-….በነጋታው በቀጥታ ወደ ቲጂ ቤት ነው የሄድኩት፤ ምክንያቱም ጥሌ ስለማይጠፋ እሱን ማግኘት አለብኝ ብዬ ሄድኩ…ስሄድ እንደ አጋጣሚ የለም… በጣም ተበሳጨሁ፤ ምን እንደተሰማው ሳልጠይቀው ብዬ በጣም ተቆጨሁ… በእንደዚህ አይነት ሃሣብ ውስጥ እያለሁ ጥሌ አይመጣም? ሁላችንም ከመቀመጫችን ስንነሳ ተቀመጡ ማለቱን ትቶ ወደ እኔ እንደ እያመለከተ “አንቺ በጣም ጀግና ተጫዋች ነሽ ለካ፤ በእውነት በጣም ነው ያደነኩህ… በጣም ጎበዝ በርታ” አለኝና “አንተ እኮ ከእኔ ትበልጣለህ” ሲለኝ በጣም ደነገጥኩና… እንዴ ጋሼ እኔ ከአንተ?… ስለው ጥሌም ወዲያው “ስማ እኔ እኮ የማስጨፍረው ከ2 ሺ ሰው አይበልጥም፤ አንተ እኮ 30ሺ ህዝብ ድፍን ስታደየምን ነው የምታስጨፍረው” ያለኝ ዛሬም ድረስ ውስጤ አለ…. ጥሌ በጣም ልዩ ሰው ነው… ከዚያ በኋላ በጣም ወዳጅም ሆንን… አሜሪካ በመጣ ጊዜም እንገናኝ ነበር… ሲጠራኝ እራሱ ሙሊጌታ ሳይሆን “ወሎ” ነበር የሚለኝ፡፡

ሀትሪክ፡-… የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ ጨዋታን ካነሳን አይቀር ከቀደሞው ፕሬዚዳንት ከኮልኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ጋር ስለተገናኛችሁበት አጋጣሚ እናንሳ እስቲ…?

ሙሉጌታ፡- …(በሃሳብ ወደ ኋላ እየሄደ).. ውይ… እሱ አጋጣሚ የማይረሣ ነው… ፕሬዚዳንት መንግ ሥቱ ኃይለማርያምን በቴሌቭዥን ከማየት ውጪ በአካል አይቻቸው ስለማላውቅ ነገሮች ብርቅ ሆኖብኝ ነበር፤ የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ ዋንጫን በማሸነፋችን በቤተ መንግሥት የክብር ግብዣ አድርገውልን ነበር፡፡ ቤተመንግሥት ስንደርስ እሳቸው የሉም፤ ውይ ላናገኛቸው ነው ስንል ስብሰባ ላይ ስለሆኑ ነው ይመጣሉ ተባልን… እስከዛ የፈለጋችሁትን ብሉ ጠጡ ተባልን… ቤተመንግሥት ብርቃችን ነው በተለይ ይሄንን የማናውምቀውን መጠጥ ገለብጥነው፣ እርስ በእርሳችን እየተጫወትን ሳለ ጓድ ብርሃኑ ባየህ አይቶኝ መጣ “ሙሌ” አለኝ አደነቀኝ ከእኔ አልፎ አባቴም በአንተ ፍቅር ልትገድለው ነው አለኝ” እንዲህ እያወራን ሳለ ጓድ ሊቀመንበር መጡ ተባለ… ቤቱ ከጫጫታ በአንዴ እንደ ባግዳድ ፀጥ እረጭ አለ… ፕሬዚዳንት መንግሥቱ እየዞሩ ሁሉንም ተጫዋቾች እያነጋገሩ እኔ ጋር ደረሱ… ትከሻዬን መታ መታ አድርገው “አንተ ሙሉጌታ ወለዬው ነህ?” ብለው ሲጠይቁኝ… በጣም ፈራሁ… በፍርሃት ስሜት ውስጥ ሆኜ አዎን ጓድ ሊቀመንበር አልኳቸው…

ሀትሪክ፡- …ፍርሃትህ ከምን የመነጨ ነው… ?

ሙሉጌታ፡-…ብቻ አላውቅም ፈራሁ…ደግሞም የጓድ መንግሥቱ ወታደራዊ አለባበስ…ግርማ ሞገሳቸው…ኮስታራነታቸው ብቻ ምን ልበልህ ሁለነገራቸው የተለየ ሲሆንብህ ትፈራለህ… “ሙሉጌታ ጎበዝ ተጨዋች ነህ፤ አንተን ኢሠፓ ይፈልግሃል… ምን እናድርግልህ” አሉኝ… ምን እናድርግልህ ሲሉኝ ፍርሃቴ ጠፋ… ወዲያው ጓድ ሊቀመንበር እኔ ከሆቴል ሆቴል የምንከራተት ሰው ነኝ… መኖሪያ ቤት እንኳን የለኝም… ስላቸው በጣም ደነገጡ… “እንዴ ሙሉጌታ ቤት የለህም” አሉኝና ጓድ ብርሃኑ ባየህን ጠርተው በአስቸኳይ መሬት ይሰጠው ብለው በአጭር ጊዜ መሬት ወሰድን፡፡

ሀትሪክ፡- በወቅቱ የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ሻምፒዮን በመሆናችሁ ቴሌቪዥንና የ5 ሺ ብር የገንዘብ ሽልማትም ተሰጥቶአችኋል ቲቪዋ የት ደረሰች?

ሙሉጌታ፡-… ውይ ጊዜው በጣም ረዠም ነው… የት እንዳለች አላስታውስም.. ግን በወቅቱ ከለር ቴሌቪዥን ብርቅ ስለበር ሽልማቱ በጣም አስደስቶን ነበር… የአምስት ሺ ብር ሽልማቱም ቀላል አልነበረም.. ምክንያቱም በዛን ጊዜ አምስት ሺ ብር ማለት የአምስት ሚሊዮን ብር ያህል ብዙ ነበር ማለት እችላለሁ… በብሩ የሆነ ነገር እናደርግበታለን ብለን አንድ ሁለት እያልን ስንመዘው አለቀ… ብሩን እንደተቀበልን ከእነ ሚሊዮን ጋር ድራፍት እየጣጠን ዘና ስንል የተመለከቱን ልንክፍል ስናወጣ “ይሄን ብር መዘዙት” እያሉ ይነጋገሩብን ሁሉ እንደነበር አስታውሳለሁ”

ሀትሪክ፡- … የድሮ ተጨዋቾች ተጠቃሚ አልነበራችሁም እንዴ እንደውም አንተ ከባንክ ገንዘብ ተበድረህ መኖሪያ ቤትህ በሀራጅ ሁሉ ሊሸጥ ነበር… ይሄንንስ ታስታውሳለህ…

ሙሉጌታ፡ ….(በጣም ሳቅ)…ኧረ ምን ጉድ የሆንክ ሰው ነህ… /ሳቅ/ ይሄን ሁሉ እኔ ረስቼዋለሁ ምክንያቱም ረዥም ጊዜ ነዋ… ግን ብሩ ስንት እንደሆነ ታውቃለህ…

ሀትሪክ፡- ብሩን አላስታውስም… ?

ሙሉጌታ፡-(በጣም እየሳቀ)… ብሩ ስንት መሠለህ 13 ሺ ብር ነው፤ አጋጣሚውን ምን መለሰህ… ለሆነ ነገር ብር ይቸግረኝና ከዚያ ለምን ከባንክ አልበደርም እልና ቤቴን ሞርጌጅ አስይዤ እበደራለሁ…ዛሬ ወይም ነገር እከፍላለሁ ስል አልሞላ ይለኝና ጊዜው ያልፋል በዚህን ጊዜ ባንኩ በሀራጅ ሊሸጥብኝ ማስታወቂያ ያወጣል…

ሀትሪክ፡-… ለ13ሺ ብር… ?

ሙሉጌታ፡- …እንዴ ምን ማለትህ ነው 13 ሚሊዮን ብር በለው… ባንኩ አልከፈለኝም ብሎ ማስታወቂያ ሲያወጣ የቀድሞ የምድር ጦር በኋላ የባንክ ተጨዋች የነበረው ተከላካዩ ዘውዱ (ማሙዬ) እዛ ይሠራ ነበርና ነገሩ ያስደነግጠዋል… በኋላ ላይ እኔ ጌታዘሩ ወንድሜ ነው እሱ ጋ ተቀምጬ እያለሁ ይመጣና “ሙሌ ቤትህ በእዳ ምክንያት በሀራጅ ሊሸጥ ነው ከየትም ብለህ ክፈል” ሲለኝ ያልጠበኩት ነገር ስለነበር በጣም ደነገጥኩ… ከዚያ በኋላ በጣም ተረበሽኩ… በዚህ መሀል እያለሁ ጌታዘሩ (ወንድሜ) መጣ ሲያየኝ ፊቴ ተረብሿል… “ሙሌ ምነው ፊትሽ ልክ አይደለም” ሲለኝ ባክህ ጌታ ቤቴ ሊሸጥ ነው ስለው “ለምን?” ሲለኝ በ13 ሺ ብር እዳ ብዬ ስመልስለት እሱም በጣም ደነገጠና “ሙሌ እኔ እያለሁማ የአንተ ቤት አይሸጥም፤ በል ተነሳ አሁኑኑ እንሄድ” ይለኝና ወዲያውኑ 13 ሺ ብር መዥረጥ አድርጎ ከፍሎ ቤቴን አትርፎልኛል፤ ጌታ ባለውለዬ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- …ከዚህ ሌላ እንድ ጊዜ እንዲሁ ቤትህ ላይ የሀራጅ ማስታወቂያ ወጥቶብህ ለጥቂት ተርፈሃል እሱስ…?

ሙሉጌታ፡- …አሁንስ በጣም እየገረምከኝ መጣህ ….ከየት ነው የምትፈለፍለው.. እሱ ደግሞ እኔ ተበድሬ አይደለም ለባለቤቴ ወንድም የተበደርኩት ነው፡፡ እሱ ደግሞ ስንት መሠለህ 100 ሺ ብር ነው… እከፍላለሁ ባልኩ ጊዜ አልከፈልኩም… በኋላ ላይ ባንኩ በሐራጅ ልንሸጠው ነው ብሎ ማስታወቂያ አወጣብን ….ደብዳቤው እቤት ነው የተላከው ባለቤቴና ወንድሟ እንዳልረበሽ ይደነግጣል ብለው ደብቀውኝ ነበር… የባለቤቴ የዘይቱና የወንድም ልጅ ግን ነገሩ ስላልገባው “ጋሼ ከባንክ ደብዳቤ ተሰጥቶናል” ብሎ አሳየኝ… ሳየው በአስቸኳይ 100 ሺ ብሩን ካልከፈላችሁ ቤታችሁ በሀራጅ ይሸጣል ይላል… እውነትም ሳየው ደነገጥኩ፤ በኋላ ምን ላደርግ ብዬ ሳስብ ሸዋረጋ ደስታ ትዝ አለችኝ… ሸዋረጋ የቀድሞ የባንክ ተጨዋች በጣም ጥሩ ቀና ልጅ ነው… እሱ ባንክ ዋናው መ/ቤት ነው የሚሰራው… ለምን እሱ ጋ ሄጄ አድነኝ አልለውም አልኩና እየበረርኩ ሄድኩ..

ሀትሪክ፡- …ከዚያስ…

ሙሉጌታ፡- …ባንክ ስሄድ ሸዋን ቢሮ ቁጭ ብሎ አገኘሁት.. ሸዋዬ ጉድ ሆንኩልህ አልኩት “ምነው?” ሲለኝ ቤቴ ሊሸጥ ነው ብዬ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤውን ሰጠሁት.. እሱም አይቶት ደነገጠ…ወዲያውኑ “ሙሌ የአንተ ቤትማ አይሸጥም ና ተከተለኝ” ብሎ አቶ ሙሉጌታ ገ/መድህን የሚባሉ የባንኩ ከፍተኛ ኃላፊ ቢሮ ወሰደኝ እሳቸውም ገና ሲያዩኝ በጣም ደስ አላቸው “እንዴ ሙሌ ምን እግር ጥሎህ መጣህ” ብለው ከመቀመጫቸው ተነስተው አቀፉኝ.. በኋላ ላይ ሸዋረጋ ደስታ ሙሉጌታ ቤቱ በሀራጅ ተሸጦ ሜዳ ላይ ሊወድቅ ነው” ሲላቸው እሳቸውም “እንዴ ሙሌ ይሄማ አይሆንም ብለው ብሩን ወደተበደርኩበት የአዲስ ከተማ የንግድ ባንክ ቅርንጫፉ ጽ/ቤት ለማናጀሩ ደውሉለት… “እንዴት ሙሉጌታ ላይ የሀራጅ ማስታወቂያ ታወጣለህ? እሱ እኮ የሀገር ጀግና ነው በል አሁኑኑ አስተካክልና ማስታወቂያውን አንሳ… አሉትና ወደ እኔ ዞር ብለው “ሙሌ እስከመቼ ይረዛምልህ” ሲሉኝ ኧረ አንድ አመት በቂዬ ነው… ስላቸው “ለአንድ አመት እፎይታ ሰጠው” ብለው ለማናጀሩ አዘዙልኝ… ወደያውኑ ወደ ተበደርኩበት ባንክ ሥራ አስኪያጅ ስሄድ “ይቅርታ ተጠይቄ ለአንድ አመት ተራዘመልኝ… መጨረሻ ላይ ከፍዬ ነፃ ወጣሁ፣ ይሄንን ነገር እንኳን አነሳህልኝ በዚህ አጋጣሚ የባንኩ ከፍተኛ ኃላፊ የነበሩትን አቶ ሙሉጌታ ገ/መድህንና ሁሌም ለተጨዋቾች ባለውለተኛ የሆነውን ሸዋረጋ ደስታን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ሸዋረጋ ደስታ በጣም ቅን ሰው ነው.. ሰውን በመርዳት የሚደሰት ሰው ነው.. አንዴ እኔና ኃይሌ ካሴም የሆነ ጉዳይ ገጥሞን ሸዋረጋ ደርሶልናል፡፡

ሀትሪክ፡-… ምን ገጥሟችሁ…

ሙሉጌታ፡-… ኃይሌ አሜሪካ ኤምባሲ ለመግባት ይፈልግና የባንክ ቡኩ ላይ በቂ ገንዘብ የለውም… አሁን በክፋት እንዳይተረጎበት እንጂ ጉዳዩን ለሸዋረጋ ስናማክረው “እናንተማ የሀገር ሀብት ናችሁ” ብሎ የባንክ ቡክ አዘጋጅቶ በቂ ገንዘብ ከቶና አመቻችቶ ደብዳቤ አፅፎልን አሜሪካ ኤምባሲ ገብተን ቪዛ እንደናገኝም በጣም ረድቶናል፤ ሸዋ ቅን ልጅ ናት… የተጨዋቾችና የደጋፊዎች ማህበር ፕሬዚዳንትም ሆኖ ብዙ ትልልቅ ስራን የሠራ ሰው ነው… አሜሪካም ተገናኝተን ነበር በዚህ አጋጣሚ በጣም አመሰግነዋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ብቃትህ ሳይወርድ አቋምህ ሳይዋዥቅ 13 አመታት ያለችግር የተጨወትክበትን ምስጢር ለዚህ ዘመን ተጨዋቾች አካፍል ብልህ ምን ትላለህ?

ሙሉጌታ፡- …ትልቁ ነገር ሙያችንን መወደዳችንና ማክበራችን ነው…የጊዮርጊስን ማልያ መልበስ በራሱ ሌላ ኃላፊነት ይጭንብሃል… ትልቅ አደራ የወደቀብህ ያህል ይሰማሀል፤ እኔ ጊዮርጊስ ስጫወት መጠጥ ቤት አልሄድም፤ ራሴን በጣም እጠብቃለሁ፤ ልምምዴን በአግባቡ እሠራለሁ… አሰልጣኞቼ የሚሉኝን በደንብ እሰማለሁ… እተገብራለሁ፤ ከራሳችን በላይ ለክለቡ ነው የምናስበው፤ በቃ አላማ አለን፤ ለክለቡ ለደጋፊው አንድ ታሪክ ለመሥራት ብቻ ነው የምናስበው …እንዳልኩህ ነው ጊዮርጊስ ቤት ስትገባ ኃላፊነቱ አደራው ብዙ ነው… በቃ ይሄው ነው ከዚህ ውጪ የተለየ ነገር የለም፡፡

ሀትሪክ፡- …ባለፈው በቲቪ ቀርበህ 13 አመት ሙሉ ስጫወት ቀይ ካርድ የሚባል አይቼ አላውቅም ማለትህን የተጠራጠሩ አሉ?

ሙሉጌታ፡-…ቀይ ካርድ አይቷል ብሎ ማስረጃ የሚያመጣ ካለ በጣም ደስተኛ ነኝ… ግን አይኖርም… አሁንም እደግመዋለሁ አንድም ቀን በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቼ አላውቅም፡፡

ሀትሪክ፡- … ሙሉጌታ የችሎታውን ያህል ተንኮለኛም ነው በክርኑ ብዙዎችን በመግጨትም የሚታወቅ ነው… እንደዚህ አይነት ስራን እየሠራ እንዴት ቀይ ካርድ አያይም ብለው የሚሞግቱ አሉ?

ሙሉጌታ፡- ጥበብ የሚያስፈልው ሜዳ ላይ ኳስ ስትይዝ ብቻ አይደለም.. ቴክኒካል ፋውል ስትሠራም ጥበብ ያስፈልጋል፤ የዳኛን እይታ አይተህ ነው ፋውል የምትሠራው… ዳኞች አንድም ቀን አግኝተውኝ አያውቁም.. በክርን እንደምማታ የነቃብኝ አለም አስፋ ነው፤ ኪነ ጥበቡም እንዲሁ ነቅቶብኛል፤ ግን ይዘውኝ በቀይ ካርድ አስወጥተውኝ አያውቁም፡፡

ሀትሪክ፡- በአንድ ወቅት አርቢትር በቀለ ኪዳኔ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሊያስወጣህ ሲል ቀይ ካርዱን ከኪሱ ሠርቀሽው ተርፈሃል ብሎ አንዱ አጫውቶኛል… እውነት ነው…?

ሙሉጌታ፡- … መረጃህ እውነትነት ቢኖረውም አዛብተው ነው የነገሩህ … (ሳቅ)… አሁን ገና ተሸወድሽ… (ሳቅ).. ነገሩ ከማን ጋር ስንጫወት እንደነበር ረሳውሁት.. ተከላካያችን ዳኛቸው ደምሴ ፋውል ትሠራለች… ፋውሉ ደግሞ በቀይ የሚያስወጣ ነው.. በቀለ ከኪሱ ቀይ ካርዱን መዞ ሊሰጠው ሲል ሁላችንም ከበን አዋከብነው… ምክንያቱም ቀይ ካርዱን መዞ ለዳኛቸው ቢሰጠው በቃ ጨዋታችን ይበላሻል.. ሁሉም ነገር ያበቃለታል… ከግራ ከቀኝ ስናዋክበው… ስንገፈትረው…ኪሱ መግባቱን ትቶ እኛንም መገፋፋት ውስጥ ገባ… እኔ በዚህን ጊዜ ቀስ ብዬ ቀይ ካርዱን ከኪሱ ሠረኩትና ፓንቴ ውስጥ ከተትኩት… ወደ ኋላ ሄዶ ቀይ ካርዱን ከኪሱ አውጥቶ ለመስጠት ሁሉንም ኪሱን ቢበረብር ቢጫ ካርድ ብቻ ነው ያለው… ቀይ ካርድ አጣው… የመስመር ዳኛውን ቀይ ካርድ ይዛሃል ሲለው እሱም አልያዛኩም አለው… በዚህ ግርግር ዳኛቸው ቀይ ካርድ ሳያይ ተረፈ… እኛም አሸነፍን…. ጨዋታው አልቆ ከሜዳ ስንወጣ ቀይ ካርዱን ከፓንቴ ውስጥ አወጣሁና ለመስመር ዳኛው ስሰጠው ነገሩ እንደ አዲስ አገረሽ… በቀለም በጣም ተበሳጨ… ቆይ በሌላ ጨዋታ እሰራልሀለሁ.. ብሎ ዛተብኝ… ይሄ ዛቻው ረበሸኝ… በነጋታው ጠዋት በቀለ ኪዳኔን ፍለጋ ወደ ካዛንቼስ ሄድኩ…

ሀትሪክ፡- .. ለምን …?

ሙሉጌታ፡- እንዴ ምን ሆነሃል…? ዝቶብኛል እኮ… በዚያ ላይ በሰራሁት ሥራ በጣም ተፀፅቼ ይቅርታ መጠየቅ አለብኝ ብዬ ወስኛለሁ… ያኔ በቀለ ፋርማሲ ነበረው… በቀጥታ ወደ ፋርማሲው ሄድኩ… እዛ ስሄድ እንደ አጋጣሚ በቀለና አንድ እኔን የሚወድ ደጋፊ በእኔ ዙሪያ ይከራከራሉ… “ሙሉጌታንማ አገኘዋለሁ” እያለ በቀለ ይዝታል፣ ይጮሃል… በመሀል ዘው ብዬ ስገባ በቀለ ያየኝና “ደግሞ ምን ፈልገህ መጣህ” ብሎ አፈጠጥብኝ… ጋሼ በቃ አንተን ይቅርታ ለመጠየቅ ነው የመጣሁት… ይቅርታ አድርግልኝ” አልኩት… እሱም እግዚአብሔር ይስጠው ይቅርታዬን ተቀብለ… አሜሪካ ሀገር ከበቄ ጋር ተገናኝተን ይሄንን አጋጣሚ ሁሉ አንስተን ስቀናል፡፡

ሀትሪክ፡- ከዚህ ከዳኝነት ጋር በተያያዘ የቤኒንን ጨዋታ እናንሳ.. ከቤኒን ጋር በነበረው ጨዋታ ያልገባ ጎል አፀድቀህ ኛውን አስቀጥተሃል… ይሄንንስ አጋጣሚ አጫውተኝ እስቲ…?
ሙሉጌታ፡-…ነገሩ ምን መሠለህ… ከቤኔን ጋር ስንጫወት ዲፌንሳቸው የግንብ ያህል ነው… በዚያ ላይ ጎል ጠመመብን… ብንል ብንል ማግባት አልቻልንም… ጠንክር አስናቀ በዚህ በኩል ይቀጠቀጣል… በረኛውም ይመልሳል አንግልም ይገጫል… እኔ በዛ በኩል ስለው ደግሞ እንደዚሁ.. ሚሊዮን በጋሻው ቢለው ቢሠራው ጎል እምቢ ይለናል… ደጋፊው ደግሞ ጎል ጎል እያለ ይጮሃል… ሁኔታው በጣም አስጨነቀን… በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለን ጠንክር አስናቀ ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ አንድ ኳስ ሲመታ ከጎሉ ውጪ ያለውን መረብ ሲነካው ደጋፊው ጎል ገባ ብሎ ይጮሃል… በዚህን ጊዜ እኔም ወዲያውኑ ሮጬ ሄድኩና በጎሉ ውስጥ አድርጌ ኳሱን ከመረቡ ስር ጎትቼ ውስጥ አስገባሁትና ይዤ ወደ መሀል ሜዳ ስሮጥ ዳኛው ጎል ነው ብሎ ወደ መሀል ሜዳ አሳይቶ ፊሽካ ይነፋል..በዚህ ጊዜ ስታዲየሙ ቀውጢ ይሆናል… ይጨፈራል… ቤኒኖች ያብዳሉ… ዳኛው ግን ሊሰማቸው አልቻሉም… በዛች በውሸት ጎል አሸንፈን ወጣው… በኋላ ጎሉ ሲጣራ ጎል አይደለም… ዳኛው በእኔ ተሸውዶ ነው ያፀደቀው… በዚህ የተነሣም ዳኛው ሁለት አመት ቅጣት ተጥሎበታል፡፡ ይሄን ዳኛ አንዴ ኬንያ ላይ ለጨዋታ ሄደን ተገናኝተን ጉድ ሠራሽኝ ግን አንተ የኢትዮጵያ ጀግና ነህ… ኬንያ ላይ በጣም ነው የሚፈሩህ… የአጭሩ አጥቂ መጣላችሁ ነው የምትባለው.. እስከዚህ ድረስ ትፈራለህ ብታጭበረብረኝም ብታስቀጣኝም በጣም ነው የማደንቅህ ብሎኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የአንተ የጨዋታ ዘመንህ ምርጡ አሰልጣኝስ ማነው?

ሙሉጌታ፡-..የጨዋታ ዘመኔ ምርጡ አሰልጣኝ…?… ኡ… ብዙ ናቸው… ከሁሉም ግን….

ሀትሪክ፡- …ከሁሉም ግን ማን… ? ሙሉጌታ ከበደ መልሱን ሳምንት ይነግረናል… ይሄ ብቻ አይደለም ከሙሉጌታ ከበደ ጋር በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ ተጫውተናል… ለዛሬ ግን የቦታ ጥበት ገድቦን ቆይታችንን በዚህ እንቋጫለን… ሳምንት ስንገናኝ ሙሌ ስለ እናቱ… ስለ ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ… ከማን ጋር ተጣምሮ ሲጫወት እንደሚመቸው ከኢት.ቡና ጋር ስለነበራቸው ፍልሚያ… በ2500 ብር ገዝቷት ስለነበረው ቤቢ ፊያት መኪናው… በአንድ ወቅት ከፍቶት ስለነበረው ድራፍት ቤቱ… ስለ አሜሪካ ህይወቱና ስለሚሰራው ሥራ… በቀጣይስ ምን አስቧል? እዚህ ይቆያል ወይስ ወደ አሜሪካ ይመለሳል? ለሚለው አዝናኛና ቁም ነገር ያለው ምላሽ ይሰጠናል… ከወዲሁ ቀጠርዎን ያስተካክሉ፡፡

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.