መነሻ ገጽ The BiG Interview “ዘንድሮ ምንም የሰራሁት ነገር የለም የኔ ምርጥ አቋም ገና ወደፊት የሚመጣው ነው” ቸርነት ጉግሳ (ወላይታ ድቻ)
The BiG Interviewቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግወላይታ ድቻ

“ዘንድሮ ምንም የሰራሁት ነገር የለም የኔ ምርጥ አቋም ገና ወደፊት የሚመጣው ነው” ቸርነት ጉግሳ (ወላይታ ድቻ)

አጋራ
አጋራ

በእርግጠኝነት ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ምን አበረከታችሁ ቢባሉ ኮራ ብለው ምላሽ ከሚሰጡ ጥቂት ክለቦች መሀል አንዱ ወላይታ ድቻ ነው፤ የዛሬ 5 አመት ለቡድኑ ከ17 አመት በታች ቡድን ሲጫወት በአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ አይን ውስጥ በመግባቱ ከ1 አመት ቆይታ በኋላ ወደ ዋናው ቡድን አደገ፡፡

እድለኛ ሆነና በኮንፌዴሬሽን ካፕ ወላይታ ድቻዎች የግብፅን ከፍ ሲል ከአፍሪካ ልዕለ ኃያል ክለቦች መሀል አንዱ የሆነው ዛማሌክን የረታው የአሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሃ ስብስብ ውስጥ የመካተትና ታሪክ የመስራት እድል ተቀይሮ በመግባት አግኝቷል፡፡ ያኔ የተጀመረው የፕሪሚየር ሊጉ ተሳትፎው በየአመቱ እያበበና እያደገ መጥቶ ባለፉት 4 አመታት ወላይታ ድቻን ሲጠቅም ቆይቶ ሰኔ 3ዐ/2ዐ13 ውሉ ይጠናቀቃል፡፡

ይህን ተከትሎ በርካታ መላምቶች ተሰጥተዋል ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጣይ ማረፊያው ሆኗል አይ ፋሲል ከነማ ጣልቃ ገብቶበታል ውሸት ነው ለአሳዳጊ ክለቡ ውሉን ለማደስ ተሰማምቷል የሚሉ መረጃዎች ሲወጡ ሰንብተዋል፡፡

የሀትሪክ እንግዳ የሆነው ቸርነት ጉግሳ ወንድሙ ሽመክት ጉግሳን እያየ ማደጉን ተምሣሌቱ እርሱ መሆኑን ይናገራል፡፡ የሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ከቸርነት ጉግሳ ጋር በነበረው ቆይታ ቀጣይ ማረፊያ ክለቡንና ሌሎች ወሳኝ የተባሉ ጥያቄዎች አቅርቦለት ተጨዋቹ የሰጠው ምላሹ ከታች ያለውን ይመስላል፡፡

ሀትሪክ፡- ቸርነት ጉግሳ … የሻምፒዮናው ሽመክት ጉግሳ ወንድም መሆን ምን ስሜት አለው…?

ቸርነት፡- /ሳቅ/ ከቤተሰብ አንዱ ትልቅ ደረጃ ቢደርስ በጣም ነው የምትደሰተው.. ወንድም ሲሆን ደግሞ የባሰ ደስ ይላል በርሱ ደስታ በጣም ተደስቻለሁ በግሌ ለኔ ትልቅ ነገር አድርጎልኛልና አመሰግነዋለው ደስ ስላለው ተደስቻለሁ… እስካሁን በአካል አልተገናኘንም በቴክስት እንኳን ደስ ብለህ ብዬዋለው…

ሀትሪክ፡- ከሽመክት ጋር ሳወራ ቤት ደርቢ ነው አለ ቤተሰቦቻችሁ የእውነት ድጋፋቸው ምን ይመስላል አቻ ስትወጡ ነው የሚደሰቱት አሉኝ… እውነት ነው?

ቸርነት፡- /ሳቅ/ ማዘር ናት በይበልጥ የምታስበው…ለኛ ብትሆንም አቻ ስንወጣ ትደስታለች /ሳቅ/ወደ ሽመክት ነው የምታደላው…. መከበር አለበት ነው የምትለው /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- በወላይታ ሶዶ… ተተኪ የሚሆኑ ተጨዋቾች አሉ ማለት ይቻላል…?

ቸርነት፡- በደንብ አሉ እድሉን ያላገኙ ብቃት ያላቸው ነገ ሀገር መጥቀም የሚችሉ ታዳጊዎችና ወጣቶች አሉ… ወላይታ ድቻንንም እንዴት እንዲጠቀሙት አይተናል… አሰልጣኞችም ሄው ቢያዩ የቡድናቸው ማገር የሚሆኑ ተጨዋቾችአሉ ብዬ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የአካባቢህ… ሰው ላንተ ያለው ስሜት ምን ይመስላል…?

ቸርነት፡- ጥሩ ስሜት አላቸው… ከብዙ ጊዜ ቆይታ በኋላ ስለሆነ ወደ ሶዶ የምንሄደው ጓደኞቼና አብሮ አደጎቼ የሰፈር ሰዎች እንኳን ደስ አላችሁ ብለው ይቀበሉናል ጥሩ ስሜት እንዳላቸው አውቄለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ቸርነትን ድሪብል ያስተማረው ሰው አለ… በዚህ ደረጃ ለሀገገርና ከሀገር ውጪ የምታደንቀው ሰው አለ…?

ቸርነት፡- ከሀገር ውስጥ አለ ማለት ይከብዳል ከውጪ ግን የተለያዩ ቪዲዮችን አውርጄ ስለምመለከት ምርጥ ምርጥ ድሪብል ስራዎች አሉ… በዚያም ላይ ለልጅነቴ ሰርቼ የመጣሁት አለ የብራዚሉ ኔይማር የአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ የመሰሉ ድሪብል ስራዎችአሉ የነርሱን ቪዲዮ እያለሁ… ትልቅ ትምህርት ሰጥተውኛል፡፡

ሀትሪክ፡- የቸሬ ምርጥ ብቃትን አሁን እያየነው ያለ ነው ወይስ… ገና ምርጡን አቋምህን አላየነውም…?

ቸርነት፡- አሁንኮ ምን ሰራሁ…? ዘንድሮ ምንም የሰራሁት ነገር የለም የኔ ምርጥ አቋም ገና ወደፊት የሚመጣው ነው አቋሜን ገና መች አወጣሁት… ገና ነኝ የመጨረሻ እድገቴ አልቆመም ገና ወደፊት እየጨመርኩ እሄዳለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ለ24ቱ የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታ 21ዱ ላይ ቋሚ 3ቱ ላይ ተጠባባቂ ነበርክ ተቀይረህ ገብተህ 24ቱን ተጫውተሃል… ታዲያ ይሄን እንዴት ገመገምከ…?

ቸርነት፡- ከ2ዐ11-2ዐ12 ይሻላል ከ2ዐ12-2ዐ13የተሻ ጥሩ ነበርኩ ተስፋ የማደርገውም ከ2ዐ13-2ዐ14 የተሻለ እንደሚሆን ነው በየአመቱ አቅሜን እያሳደኩ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- 24ቱ የወላይታ ድቻ ጨዋታዎችን እንዴት አየሃቸው?

ቸርነት፡- መጀመሪያ አካባቢ የውጤት ማጣት ተከስቶብን አሰልጣኝ እስከመቀየር አድርሶናል የአሰልጣኙ ለውጥና በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ሌሎች ተጨዋቾች ተክተው የተሻለ ውጤት አምጥተናል፡፡ በርግጥ ከዚህ ደረጃ የተሻለ ማግኘት እንችል ነበር፡፡ በራሣችን ጥቃቅን ስህተት አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ የተሸነፍንባቸው 5 ጨዋታዎች 8ኛ ሆነን እንድናጠናቅቅ አድርገውናል የተሻለ ደረጃ ላይ የመገኘት እድላችንንም አበላሽቶብናል፡፡

ሀትሪክ፡- በሀዋሳ 3ለ2 የተረታችሁበት አይረሳም… በረኞችን አጠቂ ያደረጋችሁበት የኮቪድ 19 ችግርም አስተዋፅኦ ነበረው… እስቲ ጨዋታውን አስታወሰኝ…?

ቸርነት፡- ግብ ጠባቂዎቹን አጥቂ አድርገን ተጫውተንምኮ ምንም የተለየ ነገር አልገጠመንም እንደውም ሲጫወቱ አሪፍ ስለነበሩ የተለየ ከባድ ፈተና አልገጠመንም ብዙም አልከበደንም ሰፊ ልዩነትም አልነበረም 2ለ2 አለቀ ሲባል ነው ያገቡብን… ያኔ በጣም ተበሳጭቻለሁ ደረጃችንን ዝቅ ያደረገብን ይሄ ጨዋታ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ቅዱስ ጊዮርጊስን የረታችሁበት ጨዋታስ…?

ቸርነት፡- ጥሩ ጨዋታና ጣፋጭ ድል ካገኘንባቸው ጨዋታዎች አንዱ ጊዮርጊስን የረታንበት ነው… ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ ብዙ ውዝግብም ነበር ተደጋጋሚ ነጥቦችንም ጣልን በዚያ ወቅት ይህን ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብተን ያሸነፍነው ጨዋታ ነው በማሸነፋችን ተደስቻለሁ…. አሰልጣኙ በመቀየሩና መነሣሣት በመፈጠሩ ድሉ ቀንቶናል፡፡

ሀትሪክ፡- ኮቪድ 19 ከ12ቱ ክለቦች በላይ ተጋጣሚ አልሆነባችሁም…?

ቸርነት፡- ከባድ ጊዜ ነበር በርግጥ አዲስ አበባ፣ ጅማና ባህርዳር ላይ ምንም ተፅዕኖ አልፈጠረብንም ችግርም አልነበረውም… ድሬደዋ ስንሄድ ግን ብዙ ሰው ተያዘብን ይሄ ትልቅ ችግር ፈጥሮብናል በድሬደዋ ከባድ ጊዜ አሳልፈናል ያለ ተቀያሪ የገባንበት በረኞችን አጥቂ አድርገን ለመግባት የተገደድንበት ጊዜ ነበር ይሄ ትልቅ ፈተና ሆኖብናል…ከፈጣሪ ጋር ግን አልፈነዋል፡፡

ሀትሪክ፡- ድሬደዋ ኮቪድ አለባችሁ ሐረር የለባችሁም የሚለው ውጤት አላዘናጋም…?

ቸርነት፡- በጣም ከባድ ጊዜ ነበር እንደቀልድ አለብህ እንደ ቀልድም የለብህም ስንባል ነበር ይሄ ለቀጣዩ አመት መስተካከል አለበት… የተጣራ መረጃ ሊቀርብ ይገባል አሊያም ችግሩ የከፋ ይሆናል፡፡

ሀትሪክ፡- በሊጉ የፋሲል አሸናፊነት የአቡበከር ናስር ኮከብነት አሳምኖሃል…?

ቸርነት፡- ምን ጥያቄ አለው… ፋሲል ድሉ ይገባዋል ልዩ ቡድን ነው ማለትም ይቻላል ኮከብነቱ ደግሞ ለአቡበከር ይገባል የሁለቱም ስኬት አሳማኝና የሚገባቸው ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የዲ.ኤስ.ቲቪ መኖር.. ገቢ መገኘቱ የፈጠረው በጎ ተፅዕኖ አለ… አንተስ ምን ትላለህ…?

ቸርነት፡- በጎ ተፅዕኖው የጎላ ነው ዛሬ ያደረግነውን ጨዋታ አይተንና ገምግመን ነገ ተሻሻለን ለመምጣት እንድንችልኮ እድል ፈጥሮልናል ይሄም ትልቅ ጥቅም አለው… ክለቦቹ ገቢ ማግኘታቸው ለመጠናከራቸው ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ብዬ ነው የማምነው፡፡

ሀትሪክ፡- በወላይታ ድቻ የ5 አመት የተጫዋችነት ቆይታህ…. እነማን አሰለጠኑህ…?

ቸርነት፡- ከ17 አመት በታች ቡድን አንድ አመት ከተጫወትኩ በኋላ የዋናው ቡድን አሰልጣኝ የነበረው አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ አሳደገኝ ከዚያ በዋናው ቡድን ውስጥ አሰልጣኝ ዘነበ ፍሰሃ፣ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ፣ አሰልጣኝ ገ/ክርስቶስ ቢራራ፣ አሰልጣኝ ደለለኝ ደቻሳና አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው /ሞውሪንሆ/ አሰልጥነውኛል እነኚህን ሁሉ አመሰግናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- በህይወቴ ላይ ልዩ አቅም ጨመረ የምትለው አሰልጣኝ ማነው…?

ቸርነት፡- ያሰለጠኑኝ በሙሉ ድርሻ አላቸው ባላቸው አቅም ልክ ሁሉም ለአሁኑ ቸርነት የሚችሉትን አድርገዋል ባይ ነኝ በዚህ አጋጣሚ አመሰግናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ሁሉም እኩል ድርሻ አላቸው ማለት ይቻላል…?

ቸርነት፡- የጎደለኝ ነገር ላይ ሞልተዋልኮ… ድሪብል ሳደርግ ከዘገየሁ ያንን ክፍተት የሞላልኝ አሰልጣኝ አለ… ፍጥነቴና ጥንካሬዬ ላይ የነበረውን ጉድለት የሞሉ ናቸውና ለይቼ ሳይሆን ሁሉንም አሰልጣኞች ማመስገን ነው የምፈልገው፡፡

ሀትሪክ፡- አሪፍ ዲፕሎማት ነህ…?

ቸርነት፡- /ሳቅ በሳቅ/

ሀትሪክ፡- ከ5ቱ ከተሞች ደካማ የነበራችሁት የት ነው ጠንካራ ውጤት የተመዘገበውስ…?

ቸርነት፡- ባህር ዳር ላይ ምርጥ ውጤት አስመዝግበናል ካደረግናቸው 5 ጨዋታዎች ሁለት አቻ 3 ድል አስመዝግበናል ደካማው አዲስ አበባ ላይ ተመዝግቧል ከ6 ጨዋታዎች መሃል 1 አቻ ወጥተን 5ቱን ተሸንፈናል… በደረጃችን ላይ ትልቅ ችግር የፈጠረብን የአዲስ አበባው ይመስለኛል፡፡

ሀትሪክ፡- በኛ ሀገር ደረጃ ሊጉ አድርጓል ማለት ይቻላል…?

ቸርነት፡- አዎ ለውጥማ አለው…. ከአንዱ አንዱ አመት ለውጥ አለው በተለይ ዘንድሮ ዲ.ኤስ.ቲቪ መኖሩ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል እንደ ቡድንም ሆነ እንደ ተጨዋች ለውጥማ ታይቷል፡፡ ከዚህ የተሻለ ግን መቀጠል አለበት ባይ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ማሳካት ፈልገህ ያልቻልከው ምንድነው… ?

ቸርነት፡- ጥሩ ጊዜ አሳልፊያለው ብዬ አምናለው እንደ ቡድን ግን 8ኛ ደረጃ ላይ ማጠናቀቃችን ቅር ያሰኛል ሌላው ደግሞ በርካታ ግብ አስቆጥራለሁ ብዬ የተሳካልኝ 5 ግብ ብቻ መሆኑ ቅር አሰኝቶኛል፡፡ በ2013 ጥሩ ጊዜ ባሳልፍም ያስቆጠርኩት ግብ 5 ብቻ መሆኑ ቅር አሰኝቶኛል፡፡ በቀጣይ አመት ግን እንደማሳካው ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሀትሪክ:- ውልህን ጨርሰሃል.. እቅድህን የምታሳካው ቅዱስ ጊዮርጊስ ፋሲል ከነማ ወይስ እዚያው ወላይታ ድቻ… ?

ቸርነት:- አይታወቅም ከሰኔ 3ዐ በኋላ የማውቀው ነው…ያኔ እነግርሃለሁ /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- 2.7 ሚሊዮን ብር አካውንትህ ገብቷል ከፋሲልም ጥሩ ገንዘብ ቀርቦልሃል እየተባለኮ ነው

ቸርነት፡- /ሳቅ/ ምንም ነገር የለም ወሬው ፈጠራ ነው… ሰኔ 3ዐ/2ዐ13 ድረስ ውል አለኝ የማውቀው ይህን ነው ለመረጃው ሀምሌ 3/2ዐ13 ደውልልኝ ያኔ ልንገርህ /ሳቅ በሳቅ/

ሀትሪክ፡- ለወላይታ ድቻ ደጋፊዎች የምትለው አለ?

ቸርነት፡- በዝግ ጨዋታዎች ከመካሄዳቸው በፊት ልዩ ደጋፊ መሆናቸውን አሳይተውናል ከጎናችን ሆነው አግዘውናል አበረታተውናል ከኮቪድ በኋላ በዝግ ሲሆን ሆቴል ድረስ መጥተው አበረታተውናል ትልቅ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል፡፡

ሀትሪክ፡- ፍቅረኛ አለህ? ወይስ አገባህ… ?

ቸርነት፡- /ሳቅ በሳቅ/ ኧረ ምንም ነገር የለም ገና ነኝ ብዙ የማስቀድመው ጉዳይ አለኝ፤ ሁሉ ነገር ይደረስበታል /ሳቅ/

ሀትሪክ፡- ለዋሊያዎቹ የመሰለፍ ፍላጎትህ ምን ይመስላል…?

ቸርነት፡- ፍላጎትማ አለኝ፡፡ ሀገሬን ለማገልገልም ዝግጁ ነኝ ጥሩ አቋም ላይ መገኘቴን አውቃለው ነገር ግን ምርጫና ፍላጎቱ የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ነው፡፡ አሁን ለ23 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተመርጫለሁ ጥሩ ብቃቴን አሳይቼ ለዋሊያዎቹ ልጠራ እንደምችል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- በምን ዘና ትላለህ….?

ቸርነት፡- ፊልምና ሙዚቃ ማየትና ማድመጥ እወዳለሁ በተለይ የሀገር ውስጥ ፊልም ላይ ትልቅ ፍላጎት አለኝ፡፡ ካየኋቸው ፊልሞች ደግሞ “ረቡኒ” ተመችቶኛል፡፡

ሀትሪክ፡- ጨረስኩ..የምታመሰግነው አለ…?

ቸርነት፡- አዎ በደንብ መመስገን ያለባቸውማ አሉ ቅድሚያውን እግዚአብሔር ይወስዳል ጤናዬን ጠብቆ እድሜ ሰጥቶ ለዚህ ያበቃኝ እርሱ ነው ቤተሰቦቼ፣ ጓደኞቼ ፣ አሰልጣኞቼ፣ የወላይታ ድቻ ደጋፊዎችና ትልቅም ይሁን ትንሽ ነገር በኔ ላይ አስተዋፅኦ ያደረጉትን በሙሉ አመሰግናለሁ፡፡

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ወላይታ ድቻዜናዎችየኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግየዝውውር ዜናዎች

ወላይታ ድቻ ሁለት ወጣት አሰናብቶ ሁለት ዜጋ ተጫዋች አስፈረመ

ከቀናት በፊት እንደጠቆምናችሁ ወላይታ ድቻ ሁለት የውጪ ተጫዋቾችን የግሉ አደረገ። ከቀናት በፊት...