የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ለሴካፋ ሻምፒዮና ዛሬ 10 ሰዓት ሩዋንዳን ይገጥማል

ወደ ኡጋንዳ የተጓዝነው ለተሳትፎ ሳይሆን ዋንጫውን ለማምጣት ነው
እፀገነት ብዙነህ

የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሉሲዎቹ  ለመጀመሪያ ጊዜ በኡጋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ባለው የሴካፋ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ሲሆን የመጀመሪያ ጨዋታቸውንም ከተደለደሉበት ምድብ ሁለት ዛሬ 10 ሰዓት ላይ በኒጂሩ ቴክኒካል ማዕከል ከሩዋንዳ አቻቸው ጋር የሚያደርጉ ይሆናል፡፡  የሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ከታንዛኒያ ጋር አድርጎ 3-2 መሸነፉ ይታወሳል፡፡
የሴካፋው ውድድር በኡጋንዳ እየተደረገ ባለበት በአሁን ሰዓት እስካሁን በተደረጉት የምድብ አንድ ጨዋታዎች ኬንያ አዘጋጇን ኡጋንዳን 4-0 እና ቡሩንዲንም በተመሳሳይ 4-0 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የግማሽ ፍፃሜውን የተቀላቀሉ ሲሆን ሌሎች በተደረጉ ጨዋታዎች ደግሞ ቡሩንዲ  ዛንዚባርን 10-1 እንደዚሁም  በመጀመሪያ ጨዋታዋ በኬንያ ሽንፈት የደረሰባት አዘጋጇ ኡጋንዳ ዛንዚባርን  9-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ሊያሸንፉ ችለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን  በኡጋንዳ ስለሚያደርገው የውድድር ተሳትፎ እና ተያያዥ በሆኑ ጥያቄዎች ዙሪያ ከቡድኑ ተጨዋቾች መካከል በጥሩ ብቃቷ የምትታወቀውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳን እና የሉሲዎቹን የኮሪደር ስፍራ ተጨዋች እፀገነት ብዙነህን የሀትሪክ ስፖርት ድህረ ገፅ አናግሯት ምላሿን ሰጥታለች፡፡

ስለ ሴካፋው  ውድድር ዝግጅታቸው
የተዘጋጀነው ለአጭር ጊዜ ቢሆንም ለውድድሩ
የሚጠቅም እና ጥሩ የሆነ ልምምድን ሰርተናል፡፡
ከእዚህ በኃላም በሚኖረን ቆይታ የተወዳዳሪ ሀገራትን ጨዋታዎች በመመልከት ጭምር  በሚገባ የምንዘጋጅ ይሆናል፡፡

ሩዋንዳን ዛሬ ስለሚፋለሙበት ጨዋታ
የዛሬው  ተጋጣሚያችን ምንም እንኳን በመጀመሪያው ጨዋታቸው የተሸነፉ ቢሆኑም እኛ ወደ ሜዳ የምንገባው ከግጥሚያው የሚያስፈልገንን ሶስት ነጥብ ይዘን ለመውጣት ነው፡፡ ከፈጣሪ እርዳታ ጋርም ሩዋንዳን እናሸንፋለን፡፡

የሴካፋን ዋንጫ ስለማንሳት  እድላቸው
በሴካፋ ተሳትፎአችን ከአንድአንድ ሀገራት ጠንካራ ፉክክር እንደሚገጥመን እናውቃለን ያም ሆኖ ግን እኛ ከያዝነው እና እኔም ከተደሰትኩበት ምርጥ የተጨዋቾች ስብስብ አንፃር  እኛ ወደ ውድድሩ ስፍራ የተጓዝነው ለተሳትፎ ሳይሆን ዋንጫውን ወደ ሀገራችን ይዘን ለመምጣት በመሆኑ ያንን የማናሳካበት አንዳችም ምክንያት የለም፡፡  ብቃቱ ስላለን እመቤቴም ትረዳናለች፡፡

በሴቶች እግር ኳስ እኛ ከሌሎች የአፍሪካ ጠንካራ ሀገራት ጋር ስላለን ልዮነት

በእግር ኳሱ ብቃት እኛ ጥሩ ነገር እንዳለን ብዙዎቹ የሚመሰክሩልን ነው፡፡ እኔም ሆንኩ እኛም እዚህ ላይ በተለይ በቴክኒኩ ረገድ ጥሩ እንደሆንን እናምናለን፡፡ የእኛ ልዮነት በጨዋታ እንቅስቃሴ እንደእነሱ ሙሉ ለሙሉ ቦታችንን ታክቲካል ዲሲፕሊን በሆነ መልኩ ጠብቆ ያለመጫወት እና አንድ ነገርን ማድረግ  እየቻልን ሜዳ ላይ የምንችለውን አለመተግበራችን ነበርና ያንን ችግር ለመቅረፍ እየሰራን ነው፡፡ ሌላው
ልዮነታችን እነሱ ፊዚካሊ ጠንካራ መሆናቸው ነውና
እነዚህ ላይ መስራት ከቻልን ያለን ጥሩ እና
ተፈጥሯዊ ችሎታ ወደፊት የአፍሪካ እግር ኳስን መቆጣጠር እንድንችል ያደርገናል፡፡

ለብሔራዊ ቡድን መመረጥ ስለሚሰጠው ስሜት
ለብሔራዊ ቡድን ከዚህ ቀደም ተመርጬም ተቀንሼም አውቃለሁ፡፡ አሁን ስመረጥ ለሶስተኛ ጊዜ ነው ከአልጄሪያ ጋር በነበረው ጨዋታም ምንሞ እንኳን በአጠቃላይ ውጤቱ ተሸንፈን በመውደቃችን ባዝንም ሀገርን ወክዬ በመጫወቴ
ልዮ ስሜትን ነው የፈጠረብኝ አሁንም ለሴካፋው ተመርጬ ለጨዋታው ስለተዘጋጀው ደስ ብሎኛል፡፡

ሞዴሏ ስለሆኑት ተጨዋቾች
የእግር ኳስ ተጨዋችነቱ ውስጥ ስገባ የእኔ ሞዴል እና ተምሳሌት የሆኑት ተጨዋቾች ብርቱካን ገብረ ክርስቶስ እና ሽታዬ ሲሳይ ናቸው፡፡ ለሁለቱ ከፍተኛ አድናቆት ነው ያለኝ፡፡

በመጨረሻ

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ምኞቴ ነው፡፡  አዲሱ ዓመትም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ብሩዕ ጊዜ እንዲሆንም እመኛለው፡፡ ከዚያ ውጪ በእግር ኳስ ተጨዋችነቱ እዚህ ደረጃ እንድደርስ ከልጅነቴ አንስቶ ለእኔ ተስፋ ሰጥቶ ላሰለጠነኝ እና ላሳደገኝ የትውልድ ክልሌ አዳማ ከተማ አሰልጣኝ አትክልት በቅፅል ስሙ ናአዲግ እና የእኔን ጉድለት በማየት ደግሞ አሁን ላለሁበት የብሔራዊ ቡድን ደረጃ እንድመረጥ ላደረገኝ አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው እንደዚሁም ደግሞ መላው ቤተሰቦቼን አመሰግናለው፡፡

hatricksport team

Hatricksport team

Facebook