ኢትዮጵያ ውሃ ስራ የአማራ ውሃ ስራውን አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛውን በኃላፊነት ሾሟል

 

ኢትዮጵያ ውሃ ስራ የአማራ ውሃ ስራውን አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛውን በኃላፊነት ሾሟል::
-አቶ አበባው ከልካይ ስራ አስኪያጅ ሆነው ተቀጥረዋል
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ተወዳዳሪ የነበረውን የአማራ ክልል ተወካይ አማራ ውሃ ስራን ላለፉት ጥቂት ዓመታት ያሰለጠነው አሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛው በዛሬው ዕለት የኢትዮጵያ ውሃ ስራን ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ለማሰልጠን በኃላፊነት ተሾሟል፤ የአሰልጣኝነትU ሕይወት ውስጥ ከአማራ ውሃ ስራ ባሻገር በሌሎች ክለቦችም በመስራት የሚታወቀው አሰልጣኝ ደግአረግ የአማራ ስራ ጋር ውሉን በማራዘም ይቀጥላል ተብሎ ቢጠበቅም አዲሱን ክለብ በይፋ ተቀላቅሏል፡፡
የኢትዮጵያ ውሃ ስራን ኃላፊነት በመረከብ ፊርማውን ማኖር የቻለው ደግአረግ ከአሰልጣኝነቱ በተጨማሪ  በተጨዋችነት ዘመኑ በአሁን ሰዓት በሕይወት በሌሉት በአሰልጣኝ እና ኢንስትራክተር በነበሩት ታዋቂው የሀገራችን እግር ኳስ ተጨዋች መንግስቱ ወርቁ በመመልመል ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በ1981 መጨረሻ ላይ የክለቡን የዝግጅት ጊዜ እና የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ላይ በመቀላቀል ቆይታ አድርጎ የነበረ ሲሆን ከእዚያ ባሻገር በኢንስትራክተር ካሳሁን ተካ በሚመራው የባህር ኃይል እና በአሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በሚመራው የጉምሩክ ቡድን ውስጥም ተጫውቶ ማሳለፉ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ላይ በዘንድሮ የውድድር ዘመን በምድብ አንድ የተደለደለውን የአማራ ውሃ ስራን በአሰልጣኝነት በመምራት ያሳለፈው ደግአረግ ከምድቡ ባደረጋቸው 30 ጨዋታዎች ምድቡን በ4ኛነት በማጠናቀቅ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማለፍ ለጥቂት እድሉ ያመለጠው ሲሆን የመጪው ዓመት ላይ አዲሱን ክለቡ በማሰልጠን ወደፕሪምየር ሊጉ ለማለፍ ሌላኛውን ዕድሉን የሚሞክርም ይሆናል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ውሃ ስራ የቀድሞ ስራ አስኪያጁን አሸናፊ እጅጉን ከኃላፊነት ካነሳ በኋላ አዲስ ስራ አስኪያጅ ቀጥሯል፤ ወደ ውሃ ስራ የገቡት አዲሱ ስራ አስኪያጅም ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ እና በሚንስትር መስሪያ ቤት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ላይ ሲሰሩ የነበሩት አቶ አበባው ከልካይ ናቸው፡፡ ከእነሱ ባሻገር ክለቡ ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የመጣውን ዳንኤል የተባለ ቴክኒካል ዳይሪክተር መቅጠሩም ተሰምቷል፡፡

hatricksport team

Hatricksport team

Facebook