መነሻ ገጽ የአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ በ 12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከምድብ ለ ወደ ግማሽ ፍፃሜ አላፊ የሆኑት ቡድኖች ተለይተው ታወቁ።
የአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ

በ 12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከምድብ ለ ወደ ግማሽ ፍፃሜ አላፊ የሆኑት ቡድኖች ተለይተው ታወቁ።

አጋራ
አጋራ

በ 12ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ የስድስተኛ ቀን ውሎ የምድብ ለ የመጨረሻ ጨዋታዎች የተከናወኑ ሲሆን ቅ/ጊዮርጊስ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ግማሽ ፍፃሜውን መቀላቀላቸውን አረጋግጠዋል።
በቅድሚያ 9:00 ላይ የተገናኙት ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና መከላከያ ሲሆኑ ጨዋታቸውን ያለምንም ግብ 0 – 0 ጨርሰዋል። በዝናባማ አየር ታጅቦ በእረጃጅም ኳሶች እና መሀል ሜዳ ላይ ሽኩቻ በተስተዋለበት በዚህ ጨዋታ መከላከያ ጫና በማድረግ ለመጫወት ቢሞክርም ያገኙትን የግብ አጋጣሚ መጠቀም ባለመቻላቸው ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ተስኖታል።
27ኛው ደቂቃ ላይ የመከላከያው በኀይሉ ግርማ የመታውን ቅጣት ምት እንዲሁም 92ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ማራኪ ወርቁ ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ ዮሐንስ በዛብህ በግሩም ሁኔታ አውጥቷቸዋል። 46ኛው ደቂቃ ላይ ቴዎድሮስ ታፈሰ የመታው ቅጣት ምት በግቡ ቋሚ በኩል ሲወጣ 75ኛው ደቂቃ ላይ ምንይሉ ወንድሙ የመታው ቅጣት ምት በግቡ አናት ላይ ወጥቷል።
አንድም ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ የተሳነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሰበሰባቸው ነጥቦች ታግዞ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማለፍ ችሏል።

በጨዋታው ጥሩ ብቃት ያሳየው የመከላከያው አማካይ ስፍራ ተጫዋቾች  ቴዎድሮስ ታፈሰ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ከቀድሞ የአ/አ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ብርሀኑ ከበደ እጅ ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡

11:30 ሲል በደማቅ የደጋፊዎች ዝማሬ የተጀመረው የቅ/ጊዮርጊስ እና የአዳማ ከነማ ጨዋታ በፈረሰኞቹ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። የመጀመሪያውን አጋማሽ ሙሉ ብልጫ ወስዶ የተጫወተው ቅ/ጊዮርጊስ የመጀመሪያውን ግብ ለማስቆጠር የወሰደበት 3ደቂቃዎች ብቻ ነበር። በ3ኛው ደቂቃ ላይ ፎፈና ኢብራሂም ከግራ በኩል ያሻገረውን ኳስ አሜ መሀመድ በግንባር በመግጨት ማስቆጠር ችሏል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ 3ደቂቃዎች ሲቀሩ አዳነ ግርማ ከግራ በኩል ያሻገረውን ኳስ አሜ መሀመድ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል በማስቆጠር ቡድኑን ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማሳለፍ ችሏል። ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ኳስን ተቆጣጥሮ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ያደረገው ተጋባዡ አዳማ ከነማ ከሽንፈት ያልታደገችውን ጎል አልአዛር ፋሲካ የቅ/ጊዮርጊሱ አብዱልከሪም መሀመድን ስህተት ተጠቅሞ በ55ኛው ደቂቃ ላይ ጎል ማስቆጠር ችሏል። ሁለተኛ ግብ ለማግባት ከፍተኛ ጥረት ያደረጉት አዳማ ከነማዎች 65ኛው ደቂቃ ላይ ሱራፌል ዳኛቸው አክርሮ የመታውን ኳስ የቅ/ጊዮርጊሱ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ በግሩም ሁኔታ አድኖበታል።
በጨዋታው ሁለት ግቦችን ማስቆጠር የቻለው የቅ/ጊዮርጊሱ አሜ መሀመድ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡

ሁለቱን የጨዋታ ውጤቶች ተከትሎ ቅ/ጊዮርጊስ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ እኩል 5 ነጥቦችን በመያዝ ግማሽ ፍፃሜውን መቀላቀል ችለዋል።

ክለብ ተጫወተ አገባ ገባበት ጎል ነጥብ

ቅዱስ ጊዮርጊስ 3 3 2 +1 5

ኢትዮ-ኤሌክትሪክ 3 2 1 +1 5

መከላከያ 3 1 1 +0 2

አዳማ ከተማ 3 1 4 -3 1

ቀጣይ መርሃ ግብሮች ሐሙስ ሲቀጥሉ 9:00 ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ እንዲሁም 11:30 ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ተጋባዡ ጅማ አባጅፋር ጋር በግማሽ ፍፃሜ የሚገናኙ ይሆናል።

አጋራ

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ተዛማጅ ጽሑፎች
ኢትዮጵያ ቡናዜናዎችየአዲስአበባ ከተማ ዋንጫ

ኢትዮጵያ ቡና በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እንደማይሳተፍ አስታወቀ

  18ኛው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ከዛሬ ጀምሮ እስከ መስከረም አምስት ድረስ...