ከቀናት በፊት መስከረም 7 አንድ ብሎ መከናወን የጀመረዉ እና ለሚቀጥሉት ሰባት ያህል ቀናት በአበበ ብቂላ ስታዲየም የሚከናወነው 17ተኛዉ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ዛሬም ቀጥሎ ሲከናወን ቀን 8:00 ሰዓት ላይ ሀድያ ሆሳዕና ከሻሸመኔ ከተማ እንዲሁም ቀን 10:00 ሰዓት ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ጨዋታቸዉን አድርገዋል።
በዕለተ ሰኞ የመጀመሪያ ጨዋታቸዉን በተመሳሳይ 2ለ1 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ የቻሉት ሀድያ ሆሳዕና እና ኢትዮጵያ ቡና በዛሬዉ ዕለት ባደረጉት መርሐግብር የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ቡድን ሀድያ ሆሳዕና በያዝነዉ አመት ወደ ሀገሪቱ ከፍተኛዉ የሊግ እርከን ማደግ የቻለዉን ሻሸመኔ ከተማ በፊት መስመር አጥቂዉ ሪችሞንድ አዶንጎ ብቸኛ ግብ አንድ ለዜሮ በሆነ ዉጤት በማሸነፍ ተከታታይ ድል ማስመዝገብ ሲችል በጨዋታውም ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለዉ የፊት መስመር ተጫዋቹ በየነ ባንጃዉ ኮከብ በመባል መመረጥ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
በሌላኛዉ በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በመጀመሪያው ጨዋታ አዲስ አዳጊውን ክለብ ሻሸመኔ ከተማ 2ለ1 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ የቻለዉ የመዲናዉ ክለብ ኢትዮጵያ ቡና ከአሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ቡድን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ሁለተኛ ጨዋታውን ቀን 10:00 ሰዓት ላይ አድርጎ ሁለት አቻ ተለያይቷል።
በዚህም በበርካታ ተመልካቾች ፊት በተከናወነዉ የዕለቱ ተጠባቂ ጨዋታ አዲስ አዳጊዉ ክለብ ኢትዮጵያ ንግድ አጥቂዉ ቢኒያም ጌታቸው ባስቆጠራት የ25ተኛ ደቂቃ ጎል መምራት ቢችልም ቡናማዎቹ በብሩክ በየነ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል አቻ በመሆን የመጀመሪያውን አጋማሽ አጠናቀዋል። ከዕረፍት መልስ ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ባስመለከተዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም አዲሱ የክለቡ ፈራሚ አዲስ ግደይ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም አማኑኤል አድማሱ ለቡና ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዉ ጨዋታዉ ሁለት አቻ በሆነ ዉጤት ፍፃሜዉን አጊኝቷል። በመርሐግብሩም የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አጥቂ በረከት ይግዛዉ የጨዋታዉ ኮከብ በመባል መመረጥ ችሏል።