“ዳኝነቱ ጥሩ ነበር፤ ፍፁም ቅጣት ምቱም ያሰጣል፤ጊዮርጊስን ማሸነፍ ይገባን ነበር” ሱራፌል ዳኛቸው (ፋሲል ከነማ)

 

በጎንደር ፋሲለደስ ስታድየም የተካሄደው የፋሲል ከነማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጠባቂ ጨዋታ የሁለቱ ቡድን ደጋፊዎች ለየክለቦቻቸው በሰጡት የአማረ እና ምርጥ ድጋፍ ታጅቦ በመካሄድ 2-2 በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል፤ በኢንተርናሽናል አልቢትር ሊዲያ ታፈሰ የተመራው ይኸው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ጠንካራ የመሸናነፍ ፉክክር የተደረገበት ሲሆን በጨዋታው ላይ ከፍተኛ ጫና ከመታየቱ ውጪም ከዳኝነት የውሳኔ አሰጣጥ ጋርም ጭቅጭቅ ተስተውሎበታል፤ በእዚሁ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ግጥሚያው በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅም ለባለሜዳዎቹ የተገኙትን ግቦች ኢዙ አዙካ እና የፕሪምየር ሊጉን የኮከብ ግብ አግቢነት የሚመራው ሙጂብ ቃሲም በፍፁም ቅጣት ምት ሲያስቆጥር ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ አቤል ያለው እና ጋዲሳ መብራቱ ግቦቹን አስቆጥረዋል፡፡
የፋሲል ከነማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስን ጨዋታ በተመለከተ የፋሲል ከነማ ስኬታማው የአማካይ ስፍራ ተጨዋች ሱራፌል ዳኛቸው ከጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ /G.BOYS/ ጋር ቆይታን አድርጎ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሹን ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር የነበራችሁን ጨዋታ በአቻ ውጤት አጠናቃችዋል፤ ግጥሚያው ምን መልክ ነበረው? ውጤቱስ የሚገባችሁ ነው?
ሱራፌል፡- በእኛ እና በቅዱስ ጊዮርጊሶች መካከል የተደረገው የእሁድ ዕለቱ ጨዋታ እንግዳው ቡድን ካሸነፈ መሪነቱን የሚያጠናክርበት እኛ ካሸነፍን ደግሞ መሪነቱን የምንጨብጥበት ሁኔታ ስለነበር በጣም አሪፍ እና ኃይል የተቀላቀለበትም ፍልሚያ ነበር፤ በጨዋታው እነሱ ወደ ጎንደር የመጡት ከቻሉ አሸንፈው ለመውጣት ካልቻሉ ደግሞ ነጥብ ተጋርተው ለመመለስ ነበር፤ ያም ሆኖ ግን እኛ ቀዳሚውን ግብ አስቆጠርንባቸው እና መራናቸው፤ ከዛ በኋላም እነሱ በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ተጠቅመው ሁለት ተከታታይ ግቦችን አስቆጠሩብንና ሊመሩን ቻሉ፤ በ90 ደቂቃ የጨዋታ እንቅስቃሴ ውስጥ እነሱ ለሁለት ጊዜያት ያህል ብቻ ነው ወደ እኛ የግብ ክልል በመምጣት ያገኙትን ግብ የመፍጠር አጋጣሚንና እድልን ተጠቅመው ነጥብ ሊጋሩ የቻሉበትን ውጤት ሊያስመዘግቡ የቻሉት እኛ ደግሞ ወደ እነሱ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ጊዜ የደረሰንበት እና ተሽለንም የተጫወትንበት ሁኔታ ስለነበር ማሸነፍ የሚገባንን ግጥሚያ ነው ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር ባለመቻላችን በኋላ ላይ ባገኘነው የፍፁም ቅጣት ምት ግብ ተጠቅመን ግጥሚያውን በአቻ ውጤት ልናጠናቅቅ የቻልነው፡፡
ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ ያገኘው የፍፁም ቅጣት ምት ያሰጣልም፤ አያሰጥምም በሚል እያከራከረ ይገኛል፤ በእዚህ ዙሪያ ምን የምትለው ነገር አለ?
ሱራፌል፡- እውነት ለማውራት የፍፁም ቅጣት ምትን በተመለከተ ብዙ ጊዜ እኛ ላይም የማያሰጥ ፔናሊቲ ከዚህ ቀደም ተሰጥቶብን ያውቃል፤ መቀለ ላይ በተደረገ ጨዋታም የማያሰጥ ፔናሊቲ ተሰጥቶብን እኛ ስለ እሱ ምንም አላወራንም፤ ዳኛ አንዴ ከፈረደም ፈረደም ብለን ነው የምናስበው፤ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረን ጨዋታ ግን የፍፁም ቅጣት ምቱን ያስገኘሁት እኔ ነበርኩ፤ እኔ ኳሷን ከነካዋት በኋላም ነበር ሄኖክ እግሬን የመታኝና የፍፁም ቅጣት ምቱን ልናገኝ የቻልነው፤ በቫር እንኳን መጠለፌ በድጋሚ ቢታይ ቀጥታ ፔናሊቲ ነው፤ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ግን ይሄን ፔናሊቲ እንደሚያሰጥ እያወቁ ነበር አያሰጥም በሚል ዳኛ በመክበብ እና በማመናጨቅ ጨዋታውን ለመበጥበጥ እና እኛም በጣም ጥሩ በሆንበት ጊዜያትም መሬት ላይ እየወደቁም ሰዓት ሊገድሉም የፈለጉትና አሁንም ደግሜ መናገር እፈልጋለው እኛ ያገኘነው የፍፁም ቅጣት ምት የሚያሰጥ እና ተገቢም የሆነ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የእሁዱን ጨዋታ ከውሳኔ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ዳኝነቱን እንዴት አገኘኸው?
ሱራፌል፡- ዳኝነቱን በተመለከተ ለእኔ አልቢትር ሊዲያ ለእዚህ ቡድን አዳላች፤ ለዛኛው ቡድንም አዳላች የሚያስብላት ምንም ነገርን ስላላየሁባት ከጨዋታው ክብደት እና ሴትነቷ አኳያም የውሳኔ አሰጣቷን በጣም ጥሩ ሆኖ ነው ያገኘሁት፤ በዳኝነቱ ምንም አይነት ቅሬታም የለኝም፡፡
ሀትሪክ፡- ከእናንተ የሽመክት ጉግሳን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ የደስታ ደሙን በቀይ ካርድ ከሜዳ መውጣትን በተመለከተስ የምትለው ነገር አለ?
ሱራፌል፡- አዎን፤ በአጋጣሚ እኔ እንደተመለከትኩት የቀይ ካርዱ ለሁለቱም ተጨዋቾች አያሰጥም ነው የምለው፤ ምክንያቱም ጨዋታው ካለንበት ደረጃ እና ከያዝነው የነጥብ ቅርርብ አኳያም ጫና የነበረበትና ኃይል የተቀላቀለበትና ስሜታዊም የሚያደርግህ ቢሆንም እነሱ እርስ በርስ ከመያያዛቸው ውጪ ያልተመታቱና ምንም ነገርንም ሲያደርጉ አልተመለከትኩምና፤ ስለዚህም ኢንተርናሽናል አልቢትር ሊዲያ ታፈሰ እነሱን አስታርቃና አስማምታ ጨዋታውንም አረጋግታ እንዲቀጥል ማድረግ ትችል ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- ቅ/ጊዮርጊስን ለማሸነፍ አለመ ቻላችሁ አንደኛ እንዳትሆኑ አድርጓችዋል፤ የአቻነት ውጤቱ ለእናንተ መጥፎ ነው ማለት ይቻላል…..? አስቆጭቷችዋልስ?
ሱራፌል፡- አይ አላስቆጨንም፤ የተገኘው ውጤት ግን ለእኛም ሆነ ለተጋጣሚያችን በጣም አስፈላጊ በመሆኑ መጥፎ ነው ማለትም አይቻልም፤ በጨዋታው እንደነበረን የኳስ ብልጫ ግን እኛ ማሸነፍ ነበረብን፤ ብናሸንፍ በጣም ደስ ይለንም ነበር፤ ያም ሆኖ ግን ውድድሩ ገና የአንደኛው ዙር የማጠናቀቂያ ግጥሚያዎች ላይ ያለና ገናም በርካታ ግጥሚያዎች የሚቀሩትም ስለሆነም ወደመሪነት ደረጃው ላይ መምጣታችን አይቀሬ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- በቅዱስ ጊዮርጊስ ብትሸነፉ ኖሮ ወደዋንጫው የመጓዛችሁ እድል ይጠብባችሁ ነበር?
ሱራፌል፡- እንደዛ ብለን እንኳን አናስብም፤ ምክንያቱም ዓምናም በ10 ነጥብ ልዩነት ተበልጠን ለዋንጫው ተፎካክረን ነበርና ያም ሆኖ ግን ነገሮች ግን ሊከብዱብን ይችል ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- መቐለ 70 እንደርታ ሐዋሳ ከተማን አሸንፎ መሪውንም፤ ተከታዮቹን እናንተንም በነጥብ ተጠግቷችዋል፤ አመጣጡ አያስፈራችሁም?
ሱራፌል፡- በፍፁም፤ ምክንያቱም ዓምና እንኳን በእነሱ በ10 ነጥብ ልዩነት በተመራንበት ሰዓትም ራሱ የፈራነው አንዳችም ነገር የለምም ነበርና፤ ባለፈው ዓመት እኛ በእዚያን ያህል የነጥብ ልዩነት ተበልጠን ነበር ከኋላ በመነሳት ነጥባቸው ላይ ልንደርስ የቻልነውና በእነሱ መምጣት ምንም አይነት የስጋት ስሜት የለብንም፡፡
ሀትሪክ፡- ፋሲል ከነማ ዘንድሮ የሊጉን ዋንጫ የሚያነሳበት አቅም አለው?
ሱራፌል፡- በጣም እንጂ ይሄን የምልህ ያለምክንያት አይደለም፤ አሁን እኛ ባለንበት ደረጃም በጣም ደስተኛ ነን፤ ከፊት አለመሆናችን በሜዳችንም ከሜዳችንም ውጪ ለምናደርገው ጨዋታ ጫና ሳይኖርብን እንድንጫወት ስለሚያደርገን እኛ ሻምፒዮና እንሆናለን፡፡

Editor at Hatricksport website

Facebook

መሸሻ ወልዴ

Editor at Hatricksport website