THE BIG INTERVIEW WITH FETUDIN JEMAL

በይስሀቅ በላይ
የኢትዮጵያ ቡናን ማልያ መልበስ ከጀመረ ወራቶችን ብቻ ነው ያስቆጠረው፤ለክለቡ እየሰጠ ያለው ጠቀሜታና እያገኘው ያለው ስኬት
ግን ከቆይታው በጣም የገዘፈ ነው፤ የዛሬው እንግዳዬ የኢትዮጵያ ቡናው ፈቱዲን ጀማል።ኢትዮጵያ ቡና አሉኝ ከምትላቸውና ቡድኑ
ለሚከተለው አጨዋወት በብቃት እየተጠቀመ ያለው ፈቱዲን ጀማል የክለቡ ቁልፍ ተጨዋች ከመሆን በዘለለ ከእሱ
በእድሜም፣በታሪክም፣በስኬቱም ከሚበልጡት ታላላቅ ተጨዋቾች ልቆ የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ኮከብ ተጨዋችነት ክብርን ለመጎናፀፍ
በቅቷል፡፡ ጥቁር ከለር ያለውUnder Armour ቲ-ሸርት በቱታና ቀለል ባለ ጫማ አድርጎ ሰባ ደረጃ በሚገኘው ኢንሀስ ህንፃ አራተኛ
ፎቅ ወደ ሚገኘው የሀትሪክ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ቢሮ በእንግድነት የተገኘው ፈቱዲን ጀማል የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር
ከሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ጋር ስለ ኢትዮጵያ ቡና፣ስለ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ፣ክለቡ ስለሚከተለው የጨዋታ ፍልስፍና እና በአንድ
ወቅት ለፈተና ዳርጎት ስለበረው ተክለ ሰውነቱ ዙሪያ ጥያቄ ቀርቦለት ከዚህ በታች ምላሹን ሰጥቷል፡፡
ፈጣን ጥያቄዎች ለፈቱዲን ጀማል
የክለባችሁ DJ የሙዚቃ አጫዋች ማነው?
ከታዳጊ ቡድን ያደገው አልዓዛር እኔ እንደውም አልአዛርን የጥምር ሙያ ባለቤት አድርጌ ነው የምወስደው ከሚያደርገው ነገር ሳየው ነፍሲ
ወደ ሙዚቃ ትስበዋለች ለጨዋታ ስንሄድ በድሮም ጀምሮ ስታዲየሞች እስከምንደርስ የክለባች መዝሙር እየዘመረን ነው የምንሄደውና
አልዓዛርን የምመርጠው፡፡
የመልበሻ ቤት (Dressing Room) አዝናኝ (ኮሜዲስ)?
በዚህ ነገር ዙሪያም ከአልዓዛር ውጪ ሌላ ሰው አልጠራም፤ አልዓዛር ተርበና አዝና ሰውም ነው
የክለቡ ሸቅርቅርና ዘናጭ ተጨዋች?
ሁሌም የክለቡ ተጨዋች አለባበስ ላይ ቀልድ አያውቅም እንደውም በአለባሳቸው አንፃር ሊታያቸው ሁም የደረሱ ፕሮቶኮል ያለው ይመስል
ዝንጥ ያሉ ናቸው፡፡ የግድ አንድ ሰው ምርጥ ካልከኝ ኮክሻ በጣም ይለያል ለጨዋታ ስንሄድ ዝንጥ ብሎ መነፅር ሁሉ አድርጎ ነው
የሚሄደው፡፡

ደግነት የሚያበዛውና ሩህሩህ የሚባለው የክለቡ ተጨዋች?
በዚህ በኩል ራሴን ከምጠራ እነሱ ታምሩን ብል ነው የምመርጠው፤ እነሱ ሲበዛ ደግናት፣ ችግር ካወራህበት የሚጨክን አንጀት የላትም፡፡
በጣም አዛኝ ሩህሩህ ብቻ ሳትሆን ስብዕና ያላት ተጨዋች ናት፡፡
ብርድ ካልሆነ ኪሱ የማይገባ ቆንቋና ተጫዋችስ?
ቡና ውስጥ? ኦ…(በጣም ሳቅ)…ይሄ በጣም ከባድ ጥያቄ ነው ይለፈኝ…
ከሀገር ውጭ ቀልብህን የሳበው ክለብ?
ባርሴሎና ሁሌም ከፊት ነው፤ ከእንግሊዝ ደገሞ ማንቸስተር ሲቲ
ከባህር ማዶ አሰልጣኞችስ?
ፍልስፍናው ከኳስ ጋር የተከለኝ ደጋፊን ብቻ ሣይሆን ለእግር ኳስ ደንታ የሌለው ሁሉ የሚያስደስት አጨዋወት ነው የሚከተለው፡፡
ከውጪ ብ/ቡድንስ?
የስፔን ብሔራዊ ቡድን
አጠገብህ ማን አብሮህ ሲጫወት ጨዋታይቀልሃል?
ወንድሜነህ፣ ከወንድሜነህ ጋር ተጣምሬ ስጫወ ጨዋታ ይበልጥ ይቀለኛል በሃሣብም ቶሎ እንግባባለን ይሄን ያልኩት ዝም ብዬ
አይደለም ባለፈው እሱ ተጎድቶ ባልተሰለፈ ጊዜ የተቸገርኩትን እኔ አውቃለዋለሁ፡፡
ከተቃራኒ ቡድን ተጨዋች የሚያስቸግርህ?
ስህተትህን ተጠቅሞ ጉድ የሚሰራህ እንደ ሳላሀዲን ሰይድ አይነት ተጨዋች በጣም ያስቸግረኛል፤እንደ ሳላሀዲን ሰይድ አይነት ተጨዋች
የምትሳሳታቸውን ስህተቶች ግብ አግብተው ነው የሚያርሙህ ከዚህ አንፃር ለ እኔ አስቸጋሪው ሰው ሳላሀዲን ሰይድ ነው፡፡
በቦታህ ወይም ከተከላካይ ተጨዋቾች አድናቆትህን ያለስስት የምትሰጠው?
አስቻለው ታመነ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውንም ሰው ሴንትራል ዴፌንስ ላይ ማንን ታደንቃላችሁ?ብለህ ብትጠይቅ ከአ ስቻለው ታመነ ስም ሌላ አይጠሩልህም፡፡
ሀትሪክ፡- ቢሮአችን ድረስ መጥተህ ስለጎበኘኸን ለቃለ-ምልልስም ስለተባበርከን ከልብ አመሰግናለሁ…. ?
ፊቱዲን፡-…እኔም አክብራችሁ ስለጋበዛችሁኝ፤ቢሮአችሁንም በማየቴ በጣም ደስ ብሎኛል፤እድሉንም ስለሰጣችሁኝ ከልብ
አመሰግናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-…ፊቱዲን…ሁለት አይነት ሰው ነህ እንዴ?
ፊቱዲን፡-… (እንደመገረም እያለ)…ሁለት አይነት ሰው ስትል?…አልገባኝም…?
ሀትሪክ፡- …ሜዳ ውስጥ ስትታይ ትንሽ ገዘፍ ትላለህ…ከሜዳ ውጪ ደግሞ በጣም ትንሽና ቀጭን ሆነህብኛል…?
ፊቱዲን፡- …(ሳቅ)…እንግዲህ ሜዳ ውስጥ የገዘፍኩብህ የለበስኩት የቡናን ማልያ ስለሆነ ይመስለኛል…እንጂ…ሜዳ ውስጥም…ከሜዳ
ውጪም…የምታየው ይሄንኑ ሰውነት… ይሄንኑ ፊቱዲንን ነው…(በጣም ሳቅ)….
ሀትሪክ፡- …ደፈርከኝ አትበለኝና ስንት ኪሎ ትመዝናለህ…?
ፊቱዲን፡- …ሆ…(ሳቅ)…ደሞ እንደዚህ አይነት ጥያቄ ገና ከመጀመሪያው ምን የሚሉት ነው?…ግን ኪሎዬን ማወቅ ለምን
ፈለክ…?

ሀትሪክ፡- ጥያቄዬን በጥያቄ የመመለስ መብት ለጊዜው የለህም…አንተ ብቻ ኪሎህን ንገረኝ…?
ፊቱዲን፡- …(ሳቅ)…ይሄን ያህል ኪሎዬን ለማወቅ በጣም ከጓጓህ መቼስ ምን አደርጋለሁ 68 አካባቢ ነኝ…፤ቀጥሎ ደግሞ ቁመቴን
መጠየቅህ ስለማይቀር 1ሜትርከ 72 ነኝ ብዬ ቀድሜ ነግሬህ ብገላግልህ ይሻላል…(በጣም ሳቅ)…
ሀትሪክ፡- …ኪሎህን አስረግጬ የጠየኩህ ያለምክንያት አይደለም…ብዙ አሰልጣኞች እንደ አንተ ቀጠን ካሉ ተጨዋቾች ይልቅ ገዘፍ፣በአካል
ብቃታቸው ፈርጠም ያሉ ተጨዋቾችን መምረጥ ላይ በማተኮራቸው ብዙ ቀጭን ተጨዋቾች ሰለባ ሆነው መንገድ ላይ ቀርተዋል…ፊቱዲንስ በዚህ
መልኩ አልተፈተነም…?…የሚለውን ለማወቅ ፈልጌ ነው…
ፊቱዲን፡-…መች ይቀራል…!…ኧረ እኔም በአንድ ወቅት ተፈትኜ የዚህ አይነት አስተሳሰብ ሰለባ ከመሆን ለትንሽ ተርፌ ነው ለዚህ
የበቃሁት እንጂ…በጣም ምርር ብዬ እግር ኳስ ያስጠላኝ ጊዜ ሁሉ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡-…ይሄን ያህል የሚያማርር ነገር ውስጥ የገባኸው ምን ቢገጥምህ ነው….?
ፊቱዲን፡- …ኳስ ጨዋች ስትሆን ኢትዮ ጵያ ውስጥ ብዙ ፈተናዎች ያጋጥ ሙሃል፤ በቃ አሁን ባለኝ በምታየው ተክለ ሰውነቴ የተነሣ
ብዙ ፈተናዎችን ተፈትኛለሁ፤አንዳንዴ መስፈርቱ ችሎታ አይሆንም፤አንዳንድ አሰልጣኞች ለክብደት ማንሣት ይሁን ለሌላ ከባድ ስራ
የሚፈልጉህ ይመስል ጠብደል ካልሆንክ አይፈልጉህም፡፡ “ችሎታ አለህ ግን አካል ብቃት የለህም” የሚለው አመለካከት እኔንም ተጭኖኝ
ነበር፤በዚህ የተነሣ በጣም ምርር ብሎኝ ኳስን ገና ጠግቤ ሳልጫወተው ተስፋ እንድቆርጥ አመለካከቱ ተጭኖኝ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- “ኳስ ትችላለህ ሰውነት (አካል ብቃት) ግን የለህም” ስትባል…ምን አልክ…? ለመወፈር…ምግብ በደንብ ልብላ አልክ…ወይስ
በምሬት “ለምን አልተወውም ከዚህ ሁሉ” የሚል ሃሣብ በአዕምሮህ መጣ…?
ፊቱዲን፡-… በእርግጥ “ኳስ ትችላለህ አንደኛ ነህ…ግን ሰውነት የለህም..” የሚለው የአሰልጣኞች አስተያየት በጣም ያበሳጨኝ
ስለነበር እውነቴን ነው የምልህ በጣም ምርር ነበር የምለው፤በጣም እረበሽ እንደነበርም አስታውሳለሁ…ይሄንን አላህ የሰጠኝን ሰውነቴን
ምን ላድርገው?ብዬ በእሱ ስራ ሁሉ እስከመማረር ሁሉ እደርስ ነበር… አንዳንዱ ምግብ በደንብ ብላ ይልሃል…ሌላው ደግሞ ለምን ሰውነትህ
እንዲፈረጥም ብረት አታነሣም ይለኛል?ብቻ ምን ልበልህ የተለያዩ ሰዎች የተለያየ ነገር ይሉሃል፤ በምክር ሰከርኩ…በጣምም ተረበሽኩ፡፡
አኔን አሰልጣኞች የሚፈልጉኝ ለክብደት ማንሣት ውድድር ነው እንዴ? መታየት ያለበት በዋናነት ችሎታዬ መሆን ነበረበት ግን እንዳልኩህ
በዚህ አይነት አመለካከት ወደ አንድ አመት ከግማሽ አካባቢ በጣም ብዙ ተፈትኜ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ገጥመውኝ ነበር፡፡ በኋላ ላይ
ግን አንድ የጨዋታ አጋጣሚ ናት የእግር ኳስ ህይወቴን የቀየረችው፡፡

ሀትሪክ፡- …ምን አይነት አጋጣሚ…?
ፊቱዲን፡- ..እውነቴን ነው የምልህ ያ አጋጣሚ የእግር ኳስ ህይወቴ ትልቁ የመነሻ ነጥብ ነው፤ ክብረ መንግስት ሜዳ ላይ አላባን
2ለ1 ስናሸንፍ የተመለከተኝ ሚሊዮን አካሉ የሚባለው አሰልጣኝ “አንተ ኳስ ትችላለህ…በጣም ነው የምፈልግህ…ዛሬውኑ ማታ
(ከጨዋታ በኋላ)ይዤህ ካልሄድኩ” አለኝ፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ያ ጨዋታ የአንደኛው ሲዝን የመጨረሻ ጨዋታ ስለነበር ቀሪ ግማሽ አመት
ስለበረኝ አልችልም አልኩት…እንጂ እሱ የፌዴሬሽኑን ፕሮሰስ እኔ እጨርስልሃለሁ ግማሹን አመት እኔ ጋ ተጫወት አለኝ፤ክለቤ ግን በዚህ
ሊስማማ አልቻለም፡፡ በኋላ ላይ ግን አመቱን ስጨርስ ገባሁኝ፤ይሄ አጋጣሚ ቀላል ይመስልሃል…ግን በህይወቴ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣ
ከምሬትና በቃ አይሣካልኝም ብዬ ለተስፋ መቁረጥ እጅ እንዳልሰጥ ያደረገ አጋጣሚ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …አሰልጣኞች ከችሎታ ይልቅ ተክለ ሰውነት ላይ ትኩረት በማድረጋቸው ብቻ “ሰውነት የላችሁም” በሚል ሠለባ ሆነው ከመንገድ
የቀሩ ተጨዋቾች በየቤቱ አሉና ይሄንን አጋጣሚ ተጠቅመህ ምን ትላለህ…?
ፊቱዲን፡- …በጣም ትልቅ ነገር ነው ያነሳኸው…ከእኔ በፊትም በእኔ ጊዜም ትልቅ አቅም ይዘው ግን ሰውነት የላችሁም ተብለው
ከህልማቸው የተጨናገፉ ሀገር የሚጠቅሙ ብዙ ተጨዋቾች አሉ፤አሁን አሁን በተወሰነ መልኩ እየተቀረፈ የመጣ ይመስላል እንጂ
አሰልጣኞች ከችሎታ ይልቅ ፊዚካል ላይ ማተኮራቸው ብዙዎችን ሰለባ አድርጓል፡፡ ኳስ ለመጫወት እኮ የግድ የፈረጠመ፣የብረት አንሺ
ሰውነት እንዲኖረው መገደድ የለበትም፤ ከገዘፈው ሰውነቱ ይልቅ ችሎታው ላይ ትኩረት ቢደረግ ነው የምለው፡፡ በዓለም ላይ የነገሱትን እነ
ሊዮኔል ሜሲን ብንመለከት ቁመትም የተጋነነ ሰውነትም የላቸውም፤ግን ሰውነታቸው ከገዘፉ ተጨዋቾች በላይ የሚሠሩትን ተዓምር
እያየን ነው፡፡ በሀገራችንም እነ ሽመልስ በቀለ ጥሩ ማሳያ ናቸው፤ሽመልስ በቀለን ስታየው ግዙፍ ሣይሆን ደቃቃ የሚባል ተጫዋች
ነው፤ችሎትው ግን የገዘፈ ነው፤ ለዚህም ነው ከሀገር አልፎ ግብፅ ሊግ ድረስ በፕሮፌሽናልነት መጫወት የቻለው፤ግብጾች ሰውነቱን ሣይሆን
ችሎታውን በማየታቸው ነው ይሄንን ሁሉ አመት መጫወት የቻለው፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ግዙፉ የሚባሉትን የኮትዲቫሮችን
ተጫዋቾችን አልፎ ግብ እንዲያስቆጥር የሰውነቱ ማነስ እንቅፋት አልፈጠረበትም፤ከዚህ አንፃር በተክለ ሰውነት ብቻ ሣይሆን በችሎታም
ቢታመን ነው የምለው፡፡

ሀትሪክ፡- …ብዙዎች የሀዋሳ ልጅ ነው የምትመስላቸው ትክክል ናቸው…?
ፊቱዲን፡- …አይደለም…ሀዋሳ ብዙ ጊዜዬን ያሳለፍኩባት ከተማ ናት እንጂ…ትውልዴ ከሀዋሳ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው
ክብረ መንግሥት ናት፡፡
ሀትሪክ፡- …ክብረ መንግሥት ውስጥ ከአንተ በፊት የወጣ ትልቅ ተጨዋች አለ…?
ፊቱዲን፡- …እርግጠኛ አይደለሁም…፤ ከክብረ መንግሥት ተገኝቼ በትልቅ ክለብ ደረጃ የተጫወትኩት እኔ እንደሆንኩ ነው እስከአሁን
የማውቀው፡፡ ግን አንድ ትልቅ እውነት ምንድነው መሠለህ እንደ እኔ እድሉን አግኝተው አይወጡ እንጂ የክብረ መንግሥት መሬት ያፈራቻቸው
ብዙ ጎበዝ ተጨዋቾች አሉ እንደ እድል ሆኖ በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ ባይጫወቱም በብሔራዊ ሊግ ውስጥ የሚጫወቱ ብዙ ጥሩ ልጆች አሉ፡፡
ሀትሪክ፡- …ተሳሳትክ ካልከልኝ በስተቀር የቀደሞ የቅ/ጊዮርጊስና የበርካታ ክለቦችን እንዲሁም የብ/ቡድን ማልያን በመልበስ ትልቅ ታሪክ
የሰራው ይልማ ተስፋዬ (ካቻ) የክብረ መንግሥት ልጅ እንደሆነ ሰምቻለሁ… ስለ እሱ የምታውቀው ነገር አለ…?
ፊቱዲን፡- …እኔ በወሬ ደረጃ ከመስማት በዘለለ ስለ እሱ ብዙም አላውቅም፤ሲጫወትም አላየሁትም፤እኔ በዛን ሰዓት በጣም ልጅ
ልሆን እችላለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …በ2003 ኢት.ቡና የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያነሳ አንተ የት ነበርክ…?
ፊቱዲን፡- …ትዝ ይለኛል…ቡና ዋንጫ ሲወስድ እኔ ገና ከተስፋ ቡድን ወደ ክብረ መንግሥት ከነማ ከተስፋ ቡድን ያደኩበት ጊዜ ነበር፤
ቡና ዋንጫ ሲወስድ ጨዋታው በቴሌቪዠን ሲተላለፍ ሰለነበር ትዝ ይለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- … በወቅቱ ኢት.ቡና የሊጉ ሻምፒዮን የሆነበት ጨዋታ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ነበረውና በዛን ወቅት የዚህን ክለብ ማልያ
ስለመልበስና ስለመጫወት ልብህ ጠርጥሮ ነበር…?
ፊቱዲን፡- …(ሣቅ) በእርግጥ የነበረው ድባብና የደጋፊው ስሜት አንዳች ነገርን በውስጥህ የሚያጭር ነበር፤በተለይ የደጋፊው ሁኔታ
እንድትጓጓ ክለቡን እንድትመኝ የሚያደርግ ነበር፤ተጨዋቾቹ በዚያ ሁሉ ደጋፊ ፊት ሲጫወቱ ስታይ እኔም እግዚአብሔር ረድቶኝ እዚህ
ውስጥ ብገኝ ብለህ እንድትመኝ የሚያደርግህ በመሆኑ በለጋ አዕምሮዬ በዚህ ደረጃ ተመኝቻለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ከፍ ካልክ በኋላስ ቡና ስለመጫወት የተመኘህበት አጋጣሚ ታስታውሳለህ…?
ፊቱዲን፡- ..እስታውሳለሁ ሀዲያና ድሬዳዋ ከነማ ፕሪሚየር ሊጉን የተቀላቀሉ ጊዜ ፕሪሚየር ሊግ ለመግባት ከተፋለሙት 10 ክለቦች
አንዱ እኔ የምጫወበት አላባ ከነማ ነበር፤በውድድሩ እንደውም 3ተኛ ወጥተን ነው የቀረነው እንጂ ፕሪሚየር ሊግ ለመግባት ተቃርበን
ነበር፡፡እዚያ ስጫወት የተመለከቱ የቡናን ማልያን ለብሼ እንድጫወት በጣም ጥረት ያደረጉ ነበር፤እኔም ለቡና መጫወት ትልቅ ክብር
መሆኑን በማወቅ ፍላጎቱ ቢኖረኝም ለአላባ ቀድሜ በመፈረሜ በወቅቱ ሳይሳካ ቀረ እንጂ እድሉ ቀድሞ መጥቶ ነበር፡፡ የሚገርምህ ለቡና
የመጫወት ጉጉቴ ከፍተኛ ቢሆንም በወቅቱ ባለመሳካቱ ብዙም አልተከፋሁም፤ ምክንያቱም እድሉ ተመልሶ እንደሚመጣ ሙሉ እምነቱ
ነበረኝ፤እንደገመትኩት ወይም ተስፋ እንዳደረኩት ያ እድል ተመልሶ መጥቷል፤ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡- …ሁሉም ነገር ጊዜውን ጠብቆ ራስህን በዚህ ክለብ ውስጥ ስታገኘው ምን አልክ…?
ፊቱዲን፡- …ይሄ መታደል ነው…በእንደዚህ አይነት አስደማሚ ደጋፊ ታጅ በህ መጫወት ትልቅ ስሜት በውስጥህ እንዲፈጠር
ያደርጋል፤በጣም የሚገርምህ የቡና ደጋፊ በብዛት የሚታወቀው አዲስ አበባ ውስጥ ነው፤ግን በየክልሉ እግር ኳስ ብዙም
በማይዘወትርባቸው ቦታዎች ሳይቀር የቡናን ማልያ ለብሰው የሚደግፉ ብዙ ናቸው፡፡ እኔ የተወለድኩበት ክብረ መንግሥትን ብትወስድ
እንኳን እኔ ለቡና ከመፈረሜ በፊት ብዙ ደጋፊዎች ነበሩ፤ከፈረምኩ በኋላ ደግሞ እንደዛው፤እና በዚህ ሁሉ ደጋፊ ውስጥ ሆነህ መጫወህ
ለእኔ መታደል ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ለኢት.ቡና እንድትጫወት ያስገደደህ ወይም ምክንያት የሆነህ ምንድነው ብልህ ምን ትመልስልኛለህ?
ፊቱዲን፡- …ሁለት ነገሮች ናቸው፤ አንደኛው የክለቡ አጨዋወት ነው…አጨዋወታቸው ለተጨዋች ብቻ ሣይሆን ለተመልካችም
የሚያረካ መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያቴ ደግሞ የክለቡ ደጋፊ አደጋገፉ ነው ለክለቡ ብጫወት ብዬ እንድመኝ ያደረገኝ፤ ደጋፊው በደጋፍ
አሰጣጡ ይማርክሃል፤ ልብህ እንዲሸፍት የሚደረግ አንዳች አቅምም አለው፤በእነዚህ ምክንያት ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ለክለቡ እንድትፈርም ያስገደ ደህን የኢት.ቡናን ደጋፊ ግልፅልኝ ብልህ እንዴት ትገልፃቸዋለህ?
ፊቱዲን፡- እነሱን የምገልፅበት ቃላት የለኝም፤ ልዩና ፍቅር የሆነ ደጋፊ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለእነሱ ያለኝን ክብርና ፍቅር ግለፅልኝ!
ሀትሪክ፡- …ለመጀመሪያ ጊዜ የኢት.ቡና ተጨዋች መሆንህን አረጋግጠህ ማልያውን ለብሰህ የተጫወክ እለት ስሜትህ እንዴት
ነበር…?…ሌሊቱንስ እንዴት አሣለፍክ…?
ፊቱዲን፡- …በእርግጥ የቡናን ማልያ ለብሶ በዚህ ደጋፊ መሀል መጫወት የተለየ የደስታ ስሜትን ነው የሚፈጥረው፤በእለቱ ልዩ የደስታ
ስሜት ተሰምቶኛል።እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ ግን ከዚህ ይልቅ ለእኔ ቃላት ያጣሁለት፣የተለየ የደስታ ባህር ውስጥ የሰጠምኩት ለቡና
የፈረምኩ እለት በትውልድ ሀገሬ ክብረ መንግሥት ህዝቡ የቡናን ባንዲራ ይዞ ማልያውን ለብሶ ባጃጆች ላይ የእኔ ፎቶ ተለጥፎ በክለቡ
ባንዲራ አሸብርቆ ያየሁበት ቀን ነው፡፡ በወቅቱ የተሰማኝን የደስታ ስሜት አሁን ግለፅልኝ ብትለኝ እውነተኛውን ስሜቴን መግለፅ
ይከብደኛል፡፡ ግን በቃ ምን ልበልህ የሆነ በቃላት የማይገለፅ ትልቅ የደስታ ስሜት ነው የተሰማኝ፤የጠበከኝ ያልተጠበቀ ድጋፍ ከደስታ በላይ
ለክለቡ ትልቅ ነገር ማድረግ እንደሚጠበቅብኝም ያረጋገጠ ስለነበር የተሰማኝ የደስታ ስሜት ፍፀም ልዩ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡-…የአዲስ ፍልስፍና ባለቤት የሆነው ካሳዬ አራጌ ሲጫወት አይተኸዋል…?
ፊቱዲን፡- …ኧረ በፍፁም…እላየሁትም…
ሀትሪክ፡- …ወደ ቡና መጥተህ ከመቀላቀልህ በፊት ስለ እሱስ ምን ያህል ታውቅ ነበር….?

ፊቱዲን፡- …ስለ ካሳዬ በተለይ ኢት.ቡና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ስለሰራችው ነገሮች በጣም ብዙ ነገር እሰማ ነበር፤በጣም የተረጋጋ
ቁጥብ አንደበት ያለው፣ኳስ በጣም የሚችል ምርጥ አማካይ እንደነበር ሰዎች ነግረውኛል፤ደግሞም እውነት ነው የቡና ደጋፊ ብቻ ሣይሆን
ሁሉም የሚወዱት በኢትዮጵያ እግር ኳስ በጣም ከሚወደዱና ከሚደነቁ ተጨዋቾች አንዱ እንደሆነ ተረድቻለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …በዚህ ደረጃ የገዘፈ ስም ያለው ሰው ዛሬ አሰልጣኝ ሆኖ የጨዋታ ፍልስፍናው ከአንተ ጋር ይሄዳል ተብሎ ወደ ቡድኑ ሲያመጣህ
ምን አይነት ስሜት በውስጥህ ተፈጠረ…?
ፊቱዲን፡- …አሁንም ሁለት አይነት ስሜት ነው በውስጤ የተፈጠረው፤በዚህ ደረጃ ሲከበርና ሲደነቅ የነበረ…በክለቡ ትልቅ ታሪክ ባለው
አሰልጣኝ የምሰለጥንበት እድል በማግኘቴ በጣም ነው የተደሰትኩት።ሌላው ደግሞ በዚህ ደረጃ በምገልፀው አሰልጣኝ ለሚከተለው የተለየ
የጨዋታ ፍልስፍና ትመጥናለህ ተብዬ ስታጭ በእውነት ነው የምልህ በጣም ነው የተደሰትኩት፤ለቡና ብቻ ሣይሆን ለሀገር እግር ኳስ
መፍትሔ ይሆናል ተብሎ ለሚታሰበው የጨዋታ ፍልስፍና ለዚያ ትመጥናለህ ተብዬ ነገሩ ወደ እኔ ሲመጣ በእውነት ነው የምልህ በጣም ልዩ
ስሜት ነው የተሰማኝ፡፡ እንደዚህ አይነት የተለየ አመለካከት ባለው አሰልጣኝ መወጫት ብቻ ሣይሆን መታጨት በራሱ ትልቅ ነገር ነው…?
ሀትሪክ፡- …ቀደም ሲል በወላይታ ድቻ፣በሲዳማ ቡናና ከዚያ በፊት በተለያዩ አሰልጣኞች የመሰልጠን እድል አግኝተሃል በካሳዬ መሰልጠን
የተለየ ነገር አለው፤…
ፊቱዲን፡- …አዎ…በጣም የተለየ ነገር አለው…
ሀትሪክ፡- እስቲ አባባልህን በምሳሌ አስደግፈህ አስረዳኝ…?
ፊቱዲን፡- …ከዚህ በፊትም በብዙ ሚዲያዎች ላይም ተጠይቄ ተናግሬያለሁ፤ ሌሎች ቡድኖችም ኳስ ይዘው መጫወትን ይጫወታሉ…ግን
ከበረኛ ጋር አስገድደው ወይም ዋነኛው የጨዋታ አካል አድርገው ሲጫወት አይታይም፡፡ ኳስ ሲጠለዝ አሊያም ከስንት አንዴ መስርተው
ሲጫወቱ ወይም ብልጭ ብሎ ድርግም የሚል ነገር ልታይ ትችላለህ፡፡ እኛ ጋ ስትመጣ ግን ከበረኛ ጋር ተጀምሮ እስከ አጥቂ…አንዳንዴ
አስቸጋሪ በሚሆንበት ሰዓት ከአጥቂ ሁሉ ተመልሶ ወደ በረኛ ጋር መጥቶ የሚደራጅበት ሁኔታ አለ፤እነዚህ ነገሮች የእኛን አሰልጣኝ ከሌሎች
የተለየ ያደርገዋል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ከዚህ ሌላ በሌሎች አሰልጣኞች ላይ ባላየሁት ሁኔታ ካሳዬ ተጨዋቾችን አሳልፎ የማይሰጥ
ለማንኛውም ነገር ኃላፊነቱን ደፍሮ የሚወስድ አሰልጣኝ መሆኑ በዚህም የተለየ ያደርገዋል፤በትሬይኒንግም በጨዋታም፣በውጤትም
ኃላፊነቱን ደፍሮ የሚወስድ… ተጨዋቾችን አሣልፎ የማይሰጥ አሰልጣኝ ያየሁት እሱን ነው፡፡
ሀትሪክ፡- …ከካሳዬ ጋር ከአራት ወራት በላይ አብረህ ሠርተሀል…እንደ ሰውስ ምን አይነት ስብዕና ያለው ሰው ሆኖ አገኘኸው?

ፊቱዲን፡- …እኔ እንጃ…ምን አልባትም እንደ አሰልጣኝ ብቻ ሳይሆን የአባት፣የታላቅ ወንድም የቤተሰብ ያህል የምታየው አይነት ሰው ሆኖ
ነው ያገኘሁት፤ካሳዬ ለእድገትህ የሚያስብ፣በጣም የታረመ አንደበት ያለው፣በጣም ሰው የሚያከብር፣ለስራው ታታሪ የሆነ አይነት ሰው
ነው፤ለክለቡ ብቻ ሣይሆን ለሀገርም ትልቅ ራዕይ ያለው ሰው እንደሆነ ነው በቅርበት መታዘብ የቻልኩት፡፡ ካሳዬ በውስጡ “ይሄ ደጋፊ
የሚገባውን አላገኘም”የሚል ቁጭት ያለውና ለመካስ እንቅልፍ የሚያጣ አይነት ሰው ነው፡፡ ለካሳዬ ትልቅ ቦታ ነው ያለኝ በጣምም ነው
የማከብረው፡፡
ሀትሪክ፡- ካሳዬ ይዞት የተነሣውን ፍልስፍና በተመለከተ በተለይ በሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታዎች ላይ መንገጫገጭ ነበር፤ በስታዲየም ውስጥ
ሣይቀር የተቋውሞ ድምጾች የተደመጡበት አጋጣሚም ነበር፤ይሄ ነገር በውስጥህ ስጋት የፈጠረበት ሁኔታ ነበር?
ፊቱዲን፡- …በእርግጥ መጀመሪያ ላይ እንደዚህ አይነት ስሜቶች ነበሩ…ያም ቢሆን ግን በእኔ ላይ ምንም አይነት ስጋት
አልፈጠረም፤ከካሳዬ ብዙ ነገር ከመጠበቅ የሚፈጠሩ ነገሮች ደግሞም እንደ እኔ ካሳዬን በጥልቀት የማያውቁ ይኖራሉ፤በጊዜ ሂደት
የሚመጣውን ካለመገንዘብ ከስሜታዊነት አንፃር ተዓምር የመጠበቅ ነገርም ይመስለኛል፡፡ ግን እንደ አዲስ እንደተገነባ ቡድን፤ እንደ አዲስ
ፍልስፍና ነገሮች ወደ ውጤት እስኪቀየሩ ጊዜ ሊጠይቁ ይችላሉ፤በአጠቃላይ መጀመሪያ ላይ የነበረው ስሜት አሁን ብዙም አይደመጡም፡፡
ቡድኑን ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ ስለመጣ…ነገሮች እየቀነሱ ይሄዳሉ፤ከዚህ አንፃር እንደ ተጨዋች ብዙም አልሰጋንም…ምክንያቱም እኛ
ውስጡ ስላለን በሂደት ውስጥ እንደለን ነገሮች ሊለወጡ እንደሚችሉ ስለምንረዳ አልሰጋንም፡፡ የያዝነውን እያሳደግን ከመጣን ስጋት
ያጫረባችው ቢኖሩ እንኳን ወደ እኛ መምጣታቸው አይቀሬ እንደሆነ ነው የምረዳው፤ዋናውና ትልቁ ነገር ትዕግስት ነው… ደጋፊው በትዕግስት
ከጠበቀን ክፍተቶቻችንን ደፍነን ከአላህ ጋር ጥሩ ነገር እንሰራለን ብዬ ነው የማስበው፡፡
ሀትሪክ፡- …ደጋፊው ለሁለት የተከፈለበት ስሜት እንዳለ ይሠማል…የካሳዬን ፍልስፍና የሚደግፉና…የትም አይደርሰም ወይም ፍልስፍናው
አያዋጣም በሚል የሚቃወሙ፤ በዚህ ዙሪያ ፈቱዲን ምን ይላል?
ፊቱዲን፡- …እንደዚህ ሲባል እሰማለሁ…ደጋፊው ለሁለት ተከፍሏል ሲባል…ግን ወደ ሌላ ነገር የሄደ ነገር የለም…፤…ክለቡን እንደ
ራሣቸው…
የቤተሰብ ያህል ስለሚወዱት ፍራቻ ያላቸው ሰዎት መፈጠራቸው ብዙም የሚገርም ነገር አይደለም፤ከፍቅራቸው አንፃር የሚጠበቅ
ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ማለት የምፈልገው…የሚደግፉን በዚሁ ድጋፋቸው ጠንክረው እንዲቀጥሉ ነው፤የሰጉትም ትዕግስትን ጨምረው ወደ
እኛ እንዲመጡ ነው የምጠይቀው፡፡ ምክንያቱም የደገፉትም፣ስጋት ያደረባቸውም፣ እኛም፣ አሰልጣኛችንም እየለፋን ያለነው ለክለባችን
ነው፤በዚህ በኩል ልዩነት የለም፡፡ ካሳዬም ክለቡን ስለሚወድና ደጋፊውን በውጤትም በጨዋታም ለመካስ እየጣረ እንደሆነ ልንረዳ
ይገባል፡፡

ሀትሪክ፡- …ይሄ የካሳዬ ፍልስፍና በስተመጨረሻ ኢትዮጵያ ቡናን ከህልሙ ጋር ያገናኘዋል ብለህ ታምናለህ…?
ፊቱዲን፡- …ደጋግሜ እየነገርኩህ ነው…አሁን የተያዘው ነገር እያደገ ከመጣ ለኢት.ቡና ብቻ ሣይሆን ለሀገር ሁሉ ሊጠቅም የሚችል
ነገር እንደሆነ ነው የማምነው፤ከጨዋታ ጨዋታ በሄድን ቁጥር ትልቁ ችግራችን የነበረው የማገባት ችግራተን እየተቀረፈ ስለመምታጣቸው
በሀዋሳም ከሐዲያ ጋር በነበሩት ጨዋታዎች ፍንጮችን እያየን ነው፡፡ ስለዚህ ከክለብ አልፎ ለሀገርም ጠቃሚ ነው፡፡ የእኛን ተወው
ብ/ቡድናችን ላይም ተመሳሳይ ነገር ይስተዋላል…አሰልጣኙ ይሄንን አጨዋወት የሚከተል ነው የሚመስለው፤
በአፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ ስም ያላትን በአካል ብቃት ከእኛ ልጆች የላቁትን ኮትዲቫሮችን ኳስ ይዘው ነው ጉድ የሠራቸው፤ስለዚህ
አጨዋወቱ ካደገ ከክለብ አልፎ ለሀገር ይጥቅማል ባይ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- …ኢት.ቡና የሊጉን ዋንጫ ካነሣ ድፍን 12 አመት ሞልቶታል…ይሄ ነገር በእናንተ የጨዋታ ዘመን የሚያከትም ይመስልሃል…?
ፊቱዲን፡- …የሁላችንም ምኞትና ህልም ይሄንን ነገር ማስቆም ነው…ከዚህ በላይ ተጨማሪ አመታትን መፍቀድ የለብንም፤አሁን
የያዝነውን ነገር እያሳደግን ከሄድን የ2003ቱን የደስታ ታሪክ በእኛ የጨዋታ ዘመን እንደግመዋለን ደጋፊዎቻችንም ጮቤ እናስረግጣለን ብዬ
አስባለሁ፤በእኛ የጨዋታ ዘመን ቡና በአሸናፊነት ስሙ ተደጋግሞ እንደሚነሳ ነው የማረጋግጥልህ፡፡
ሀትሪክ፡- …ኢትዮጵያ ቡና ከመምጣትህ በፊት የምታደንቀው እንደሱ ብሆን ብለህ የምትመኘው ተጨዋች ነበር…?
ፊቱዲን፡- …አዎን ነበር፤ ለመሰዑድ መሀመድና ለዳዊት እስጢፋኖስ የተለየ አድናቆት ነበረኝ…ተቃራኒ ሆኜ
ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ ቡና ሕልምህ ምንድ ነው?
ፊቱዲን፡- የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊ የፕሪማየር ሊጉን ዋንጫ ካነሣ 12 አመታትን አስቆጥሯል፤ ይሄ ቁጥር ከዚያ በላይ እንዳያልፍ
የማቆም አላማ ነው ያለኝ፤ በአጭር አገላለፅ የሀገሪቱ ክለቦች የበላይ ሆኖ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ እንዲያነሳ ነው የምመኘው፡፡
ምክንያቱም ይሄን ማሳካት ከቻልን ሀገር ወክለን በአህጉሪቱ የውድድር መድረክ የመቅረብ እድል እናገኛለን፤ ከቡና ጋር ህልሜ ይሄ ነው፡፡
ሀትሪክ፡-.. ራስህን በፕሮፌሽናል ተጨዋ ችነት የማየት ህልምስ?
ፊቱዲን፡- …እሱማ ግድ ነው…ቡና ውስጥ የማገኘው ስኬት ነው ወደዚህ መንገድ የሚያንደረድረኝ፤ፕሮፌሽናል ተጨዋች ሆኜ ክለቤንም
ሀገሬንም የማስጠራት ትልቅ ህልም አለኝ፡፡ ለዚህ ደግሞ በአቅምም በአካልም፣ በቴክኒክም የተሻልኩ ለመሆን ጠንክሮ መስራት
ይጠበቅብኛል፤ያንንም እያደረኩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡አፈጠንከው ካልከኝ በስተቀር ከአላህ ጋር በጣም በቅርቡ…በቀጣይ አመትም ሊሆን
ይችላል እድሉ ይመጣል የሚል የጠነከረ እምነት አለኝ፡፡
ሀትሪክ፡- …ብዙዎች የአንተን ተክለ ሰውነትና አጨዋዋት በማየት ከቀድሞ የክለቡ ተጨዋች ሣሙኤል ደምሴ (ኩኩሻ) ጋር
ያመሳስሉሃል…ይሄን ነገር ልብ ብለሃል…?
ፊቱዲን፡- …የሚገርምህ ነገር…አህን አሁን እንደዚህ አይነት አስተያየቶችን በብዛት መስማት ጀምሬያለሁ፤ በእርግጥ ኩኩሻን
አላውቀውም…ሲጫወትም አላየሁትም፤ በቦታው ግን በጣም ምርጥ የክለቡ ተጨዋች እንደነበር በወሬ ደረጃ እየሰማሁ ነው፡፡ ብዙዎች
“የኩኩሻ ምትክ” ነህ ሲሉኝና ነገሮች ሲደጋገሙብኝ አንድ የሚያመሳሰለን ነገር ቢኖር ነው ብዬ ማሰብ ጀምሬያለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- አብረህ ተጣምረህ የምትጫ ወተው ከወንድሜነህ ጋር ነው ሁለታችሁም የገዘፈ ተክለ ሰውነት የላችሁም ይሄን ጥምረት እንዴት
አየኸው…?
ፊቱዲን፡- …እውነት ነው…ወንድሜነህ ከእኔ ብዙም የሚገዝፍ ተጨዋች አይደለም…ነገር ግን ባለው ነገር ሁላችንም ተግባብተን ጥሩ
ነገር እያደረግን ነው… ተመቻችተናልም…ብዙ ተግባብተናልም…ከዚህ በላይም ብዙ እንሰራለን፡፡
ሀትሪክ፡- …ወደ እግር ኳስ እንድትሳብ ምክንያት የሆነህ…?
ፊቱዲን፡- …ምናልባት ብዙ ሰው ካስታወሰው አላውቅም ደደቢት ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ሲገባ ትልቅ ሚና የነበረውና በኮከብ ግብ
አግቢነት የጨረሰው ይገረም ተሾመ ሲጨወት በጣም ያስደስተኝ ነበር፤በጣም ጎበዝ አጥቂም ነበር፡፡ በኋላ ላይ የጉልበት ጉዳት አጋጥሞት
አቆመ እንጂ እሱ የተለየ ተፅዕኖ አሳድሮብኛል፤በኃይሉ ደመቀም እንዲሁ፤ እነዚህ ተጫዋቾች እንደ እነሱ ብንሆን ብለን እንድናስብ
በችሎታቸው ተፅዕኖ አድርገውብኛል፡፡
ሀትሪክ፡- ቡናን ከተቀላቀልክ በኋላ በጣም አጭር በሚባል ጊዜ በጣም የምታደንቀውን ሣላህዲን ሰይድን ሳይቀር በልጠህ የሲቲ ካፑ ኮከብ
ተጨዋች ተብለህ ተመርጠሃል… በዚህ ደረጃ መመረጥህ ምን ስሜት ፈጠረብህ…?
ፊቱዲን፡- …በጣም ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ…ሽልማቱም የሚያኩራራ ሣይሆን በቀጣይ ለምሰራቸው ሥራዎች ትልቅ ጉልበትም
የሚሰጥ ነው፤ሣላሀዲን ሰይድን የመሰሉ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ችሎታና ታሪክ ያላቸውን በልጬ መሸለሜ ድንጋጤም የማያባራ
የደስታ ስሜት ነው በውስጤ የፈጠረው፤ ታችኛው ሊግ ላይ ስጫወት ለሣላህዲን የተለየ ክብርና አድናቆት ይዤ ነው ያደኩት፤ሣላህዲን
የሚሰራቸውን ስራዎች አውቃለሁ፤እሱን በልጦ መሸለም አይደለም በዚያ ደረጃ ከማደንቀው ተጨዋቾች ጎን መቆም በራሱ ለእኔ ትልቅ
ክብር ነው፤ከእሱ ጋር ተፎካክሬ መሸለም ልክ እንደ እሱ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የማይረሣ ታሪክ መስራት እንዳለብኝም ትልቅ ቁም ነገር
ያለው መልዕክት ነው ያስተላለፈልኝ፡፡
ሀትሪክ፡- የኮኮብነት ሽልማቱ የፕሪሚየር ሊጉን ሽልማትም አሻግረህ እንድታስብስ አላደረገህም…?
ፊቱዲን፡- …አልዋሽህምአድርጓል፤ ኮከብ መባሌ ትልቅ ኃላፊነት በራሴ ላይ እንዲወድቅ አድርጓል፤ክለቤም ሀገሬም ከእኔ የበለጠ ነገር
ስለሚጠብቁ በረትተህ ጠንክረህ መስራት አለብህ የሚል አደራ ነው የጣለብኝ፤ሽልማቱ ከመኩራራት ይልቅ ጠንክሬ እንድሰራ
የሚያስጠነቅቅ ነው፡፡ ሌላው ለካ ከጠነከርኩ የተሻለ ነገር ከሰራሁ የሚሾመኝ የሚሽልመኝ እውቅና የሚሰጠኝ አካል አለ፤ስለዚህ
ጠንክሬ በመስራት የሊጉን የኮከብነት ክብር ማምጣት አለብኝ ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል፤ግን አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ከግል ክብሬ
ይልቅ የክለቤን ድል አስቀድማለሁ፤በመቀጠል የሊጉን የኮከብነት ክብር ለማሳካት ነው የማስበው፤ ከአላህ ጋርም አሳካዋለሁ ብዬ
አስባለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ለዛሬው ማንነትህ ድጋፍ ያደረጉልህን ሰዎች ምን ትላቸዋለህ?
ፊቱዲን፡- …ያለ እናንተ ድጋፍ ለዚህ ክብር አልበቃም ነበር ነው የምላቸው፤በዚህም በጣም ነው የማመሰግናቸው።ከሁሉም በላይ ግን
ይሄ እንዲሆን የፈቀደው አላህ ነውና በጥረቴ በድካሜ ውስጥ እየተገኘ፣እያበረታ፣እያገዘ ለዚህ ክብር ስላበቃኝ በመጀመሪያ ምስጋና ለእሱ
ነው ማቅረብ የምፈልገው፤በመቀጠል ቤተሰቦቼ…የእነሱ ደጋፊ የማይዘነጋ ነው…በእርግጥ እናቴ በትምህርት እንድገፋ ነበር
የምትፈልገው…ከእኔ በታች ያሉት እህቶቼ ራሣቸውን በትምህር ያበቁ ስለነበር…አባቴም ትምህርት ቢሮ ይሠራ ስለነበር የእናቴ ፍላጎት
በእነሱ መንገድ እንድትጓዝ ነበር፡፡ አባቴ ግን በምርጫው ይጓዝ የሚል አቋም ስለነበረው…የእናቴን ፍላጎት ጥሼ ገፋሁበት፤እናቴ ዛሬ
የደረሰኩበትን ስታይ በጣም ነው የተደሰችው…ከደስታዋ ብዛት በየስከንዱ እየደወለች…በላህ ወይ…?…ጠጣህ ወይ…?እያለች
የምትከታተለኝ የምትጠይቀኝ ሰው ናት፡፡ ከእነሱ ሌላ የሁሉንም ስም ባልጠራም በእኔ እድገት ላይ ግልፅ አሻራቸውን ያስቀመጡ…ያገዙኝን
ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- …ፈቱዱን ለቃለ-ምልልሱ ፈቃደኛ ሆነህ ቢሮአችን ድረስ መጥተህ ስለተባበርከን በጣም አመሰግናለሁ…ከመለያታችን በፊት ግን
ቀሪ የምትለው ካለ…ግን …ቆይ ከዚያ በፊት…በግል ህይወት ዙራያ ምንም ሳትተነፍስ ልንለያይ…?…ለፍቅር ደርሰሃል…?
ፊቱዲን፡- …(በጣም ሳቅ)…አረ አልፌያለሁ…(አሁንም ሳቅ)…ባለ ትዳር ነኝ…
ሀትሪክ፡-…እንደ አግበተህ አብረህ መኖር ጀምረሃል…?
ፊቱዲን፡- …አብረን እንኖርም…ምክንያቱም በአሁን ሰዓት እሷ አሜሪካን ነው የምትኖረው፤አሜሪካን መኖር ከጀመረች ከአንድ አመት
ከስድስት ወር በላይ ሆኗታል፤ወደ አሜሪካ ከመሄዷ በፊት እዚህ ኒካ (ቀለበት) አስረን ነው የሄደችው፡፡
ሀትሪክ፡- …የወደፊቷ የትዳር አጋርህ ባለቤትህን አስተዋውቀኝ…እስቲ እንዴት ተጠባበሳችሁ… ?
ፊቱዲን፡-…(ሳቅ)…ባለቤቴ የሀዋሳ ልጅ ናት ፈቲያ ትባላለች፤የተገናኘው የሆነ ቦታ ነው እሷ ከጓደኞቿ ጋር ነበረች፤ሠላም አሉን
ሲጠቋቆሙብን ነበር…በአጋጣሚ እሷም አናገረችኝ…የሆነ የሚያውቃት ሰው ነበር…በእሱ አማካኝነት ከዚያች ቀን በኋላ በተደጋጋሚ
መገናኘት ጀመረን…ሳያት በጣም የምታስፈልገኝ ሰው ናት ይሂችማ ልታመልጠኝ አይገባም አልኩ እሷጋም ተመሳሳይ ጥሩ ነገር ነበር ብዙም
ሳንቆይ አንድ ላይ መኖርን አስበን ወደ ኒካ (ቀለበት) ማሰር ነው ያመራነው፤አስፈላጊዬ እንደሆነች አፈላጊዋ እንደሆንኩ ተማመነን ኒካ
(ቀለበት) በጋብቻ ተሳሰረናል፡፡
ሀትሪክ፡- .ፍቅር ተራርቆ ማዶ ለማዶ ሆኖ ትችዋለህ ?
ፊቱዲን፡- …(ሳቅ)…በጣም ከባድ ነው…ይፈትንሃል…ናፍቆት ያሰቃይሃል…ዋትስ አፕና ቫይበር መኖሩ ትንሽ ቀለል ያደርግልሃል እንጂ
ከባድ ነው…ግን አላማ ስለሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም…ቢከብድህም የግድ ትቋቋ መዋለህ፡፡
አስተያየት ይስጡ