“ካሳዬን እንኳን በስልጠናው በስብዕናውም የምትወደው ነው፤ ከእሱ ከተለየሁ በኋላ መጫወት ሁሉ አቅቶኝ ነበር፤ ስልጠናው ለቡናም ለሀገርም ይጠቅማል” ተስፋሁን ጋዲሳ (ኮል)

(የመጨረሻው ክፍል)

“ካሳዬን እንኳን በስልጠናው በስብዕናውም የምትወደው ነው፤ ከእሱ ከተለየሁ በኋላ መጫወት ሁሉ አቅቶኝ ነበር፤ ስልጠናው ለቡናም ለሀገርም ይጠቅማል”
ተስፋሁን ጋዲሳ (ኮል)

በይስሐቅ በላይ

ባለፈው ሳምንት የእጅ ስልኬ ፋታ አልነበረውም…. ከወትሮው በተለየ ደጋግሞ ይጮሀል… ምንድነው ምክንያቱ በሚል ስሜት ከበርካታ ጥሪዎች በኋላ ሳነሳው አብዛኛው አስተያየት ባለፈው ሳምንት እንግዳችን በነበረው ተስፋሁን ጋዲሳ (ኮል) ላይ ያነጣጠረ ነው… በቀድሞው የእግር ኳሱ ባለውለተኛ ተስፋሁን ጋዲሳ (ኮል) በየመን ባጋጠመው ፈተናና የህይወት ውጣ ውረድ የተሰማቸውን የሐዘን እንዲሁም ለሀገሩ መሬት በመብቃቱ የተሰማቸውን የደስታ ስሜት በመግለፅ “አይዞህ ከጎንህ ነን፤ ለተስፋ መቁረጥ በፍፁም እጅ እንዳትሰጥ” የሚል የኢትዮጵያውያንን አጋርነት የሚያንፀባርቅ አስተያየታቸውን እንዳስተላልፍላቸው በተማፅኖ መልክ ጠይቀውኛል፡፡ የተከበሩ አንባቢዎቼ ባዘዙኝ መሠረት መልዕክታቸውን በዚህ መልኩ አስተላልፊያለሁ፡፡ ባለፈው ሳምንት ከተስፋሁን (ኮል) ጋር ፊልም የሚመስል እውነተኛ የየመን አሳዛኝ ታሪኩን አቅርበን ለዛሬ ቀጠሮ መያዛችን ይታወሳል… የሀትሪክ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ ከተስፋሁን ጋዲሳ (ኮል) ጋር ባደረገው የመጨረሻ ክፍል ቃለ ምልልስ በየመንና በተለይ ከ20 አመት በላይ የዘለቀውን የእግር ኳስ ህይወቱን በትዝታ ፈረስ ወደ ኋላ አስጋልቦ ሊያስቃኘን ይሞክራል እንደተለመደው አብራችሁን ሁኑ….፡፡

ሀትሪክ፡- ኮል ባለፈው ሳምንት ከአንተ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ የቋጨነው በየመን አንዲት ነፍሰ ጡር ሀበሻ ላይ የደረሰውን አሳዛኝ ሕልፈት አስመልክቶ ነገረኸን የፅንሱን ወይም የሕፃኑኑ መጨረሻ ሳትነግረን ነው ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥተኸን የተለያየነው… ለመሆኑ ነፍሰ ጡሯ ሀበሻ በሮኬት ፍንጣሪው ሕይወቷ በአሳዛኝ ሁኔታ አለፈ… ፅንሱስ ?… የሕፃኑ መጨ ረሻስ ምን ሆነ? ለሚለው ምላሽ መስ ጠት የሁለተኛ ሳምንት ቆይታችን ብን ጀምስ?…

ተስፋሁን፡- …የእግዚብሔር ተዓምር አያልቅም…ፅንሷ ውስጥ ያለውን ህፃን ሀኪሞች በቀዶ ጥገና አውጥተውት ተረፈ…እሷ ግን እንዳልኩህ አረፈች..ህፃኑ ልጅ አሁን ያለው እህቷ ጋ ነው…እህቷ ግን በመሪር ሀዘን ውስጥ ነች…“…ካልመጣሽ ብዬ ጠርቼ የገደልኳት እኔ ነኝ…”
…በማለት በየቀኑ በፀፀት ታነባለች…ብዙ ሀበሾች ስላሉ ብዙ ነገር ይኖራል…እኔ ግን የማውቀው ይሄንን ነው…ብዙ የመኖች ላይ የደረሰውን ለማውራት ይከብዳል.. ሳስበውም በጣም ይረብሸኛል…

ሀትሪክ፡- የተሻለ ነገር ለማግኘት ሄደህ…በየመን ብዙ ፈተናና መከራ አይተሃል…በዚህ ሁሉ ፈተና ውስጥ ማለፍህን ስታስብ ምሬት ይቀድምብሃል…?…

ተስፋሁን፡- …በህይወቴ እንደዚህ አይነት ከባድ ፈተና ገጥሞኝ አያውቅም…ከዚህ በኋላም ይገጥመኛል ብዬም አላስብም…በጣም ብዙ ተቸግሬያለሁ…በጣም ብዙም ተፈትኜያለሁ…ፈተናዬ በመብዛቱ ግን ብዙም አላማርርም…ምክንያቱም ከእኔ የባሰ ብዙ የከፋ ነገሮችን አይቻለሁ…አካላቸውን፣መተኪያ የሌለውን ህይወታቸውን የገበሩ ብዙ ናቸው…ይሄ እንድማርር ሣይሆን አንድፅናና ያደርገኛል…አምላክ ለተዓምር የፈጠረኝ ሰው የሆንኩ ያህልም ነው የሚሰማኝ…ልጅ ከአባቱ ተነጥሎ…አባት ወይም እናት ከልጃቸው ተነጥለው ሲሞቱ…እግርና እጃቸው ሲቆረጥና…ነፍሰ ጡር ላይ ሚሳኤል ወድቆ ስትሞት አይቻለሁ…ሰምቻለሁ…ብዙ የጭንቅ ቀኖችንምች አሣልፌያለሁ…ግን በሆነው ሁሉ አላማርርም… ከማማረር ይልቅ ፈጣሪ አምላክን ካመንከው፣ከለመንከው ከእሣትና ከፈተና እንደሚያወጣ ተምሬበታለሁ…

ሀትሪክ፡- …ከነፍስ ውጪ…ነፍስ ግቢ ከነበረው የየመን አስፈሪ ህይወት በኋላ…የሀገርህን መሬት ስትረግጥ…ለሀገርህ ስትበቃ መጀመሪያ በአዕምሮህ ብቅ የለው ምንድነው…?…

ተስፋሁን፡- …ከእግሬም ከሁሉም ነገሬ የቀደመው እንባዬ ነው…ሳላሰበው በድንገት አነባሁትም… አን ባዎቼ በሁለቱም ጉንጮቼ እንደ ጎርፍ ነበር የወረዱት…እውነት አምላክ የእ ኔንም የቤተሰቦቼንም ነፍስ ከዛ እሳት አውጥቶ ለሀገራችን አበቃን…?…ብዬ የሁለም ነገር ባለቤት የሆነውን አምላኬን አመሰገንኩት… ከሁሉም በላይ ወላጅ አባቴን ለማየት በጣም ጓጓቼ ነበር፡፡ ምክንያቱም አባቴ በእኔ ላይ የደረሰውን ከሰማ በኋላ በእኔ የተነሳ በጣም በመታመሙ እሱን ለማየት በጣም ጓጉቼ ነበር፡፡ ምክንያቱም የእሱ ጤንነት ከሌሎች ነገሮች ባላነሰ ሲያሳስበኝ ነበርና ከአውሮፕላን ወርጄ እርሱን ለማየት ተጣድፌያለሁ፡፡ ከዘጠኝ አመት በኋላ አባቴንም የናፈቁኝን ቤተሰቦቼን፣ ጓደኞ ቼን ሳገኝ በደስታ አለቀስኩ… ነገሮች ሁሉ እንደተዘበራረቁብኝ አስታውሳለሁ…

ሀትሪክ፡- .. በጦርነት አረር እየተጠበሰች ካላቸው የመን ተዓምር ማለት በሚቻልበት መለኩ ወጥተህ ወደ ሀገርህ ከመጣህ ሳምንታት እያለፉ ነው…ዛሬ ላይ ሆነህ የመን ትዝ ትልሀለች…ያ መጥፎ አጋጣሚስ በአምዕምሮህ ይመላለሳል…?…

ተስፋሁን፡- …የሚገርምህ ነገር… ያ በጣም አስጨናቂና አስፈሪ የሆነ… ጊዜ እንዲህ በቀላሉ የሚረሣ አይደለም፤ በቀንም በማታም በአዕምሮዬ እየተመላለሰ ይረብሸኛል፤ የጥይቶቹ፣ የሮኬቶቹ ድምፅ አሁንም ጆሮዬ ላይ አለ…የሞቱ፣ አካላቸው የጎደሉ ሰዎች በአይነ ህሊናዬ እየመጡ በጣም የምረበሽባቸው ቀኖች አሉ…በተቻለኝ አቅም ከዚህ ስሜት ለመውጣት እየታገልኩ ነው…

ሀትሪክ፡- …ከዚህ በኋላስ የመንን ተመልሰህ የምታያት ይመስልሃል…?

ተስፋሁን፡- …በመከራ፣በፈተና ውስጥ ባልፍባትም ለየመን አሁንም ጥሩ ስሜት አለኝ…ብቻዬን ወደ የመን ሄጄ አራት የሆንኩባት ሀገር ናት…በእግር ኳስም ትልቅ ስም አግኝቼባታለሁ…ብዙ ደጋግ ሰዎችንም ያገኘሁበት ሀገር ናት…በፈተና ውስጥ ሆኜም የአምላክን ተዓምር ያየሁበት ሀገር በመሆንዋ እውነት ነው የምልህ አሁንም ለየመን የተከፈተ ልብ ነው ያለኝ…ሰላምዋ ተመልሶ፣ህዝቧ ከመፈናቀል፣ ከመሞት ድኖ ማየት የሁልጊዜም ምኞቴ ነው…ብዙ ነገሮቿ ተረጋግተው ሰላምዋ ከተመለሰ…አንድ ቀን የመንን በድጋሚ ማየቴ አይቀርም…

ሀትሪክ፡- …እስቲ ስለ ባለቤትህና ልጆችህ አንድ ነገር በለኝ…?…

ተስፋሁን፡- …ባለቤቴን ያገኘኋት በ2012 (እ.ኤ.አ) የመን ውስጥ ነው…ባለቤቴ እየሩስ ትባላለች ሳሌም ተስፋሁን የሚባል የ7 ዓመት ከአራት ወር ወንድ ልጅና አይዳ ተስፋሁን የምትባል የ3 ዓመት ከስድስት ወር ሴት ልጅ አባትም አድርጋኛለች…ባለቤቴ እየሩስ የምር ጀግና ሴት ናት…በዛ ፈተናው በበረታበት…ተስፋ መቁረጥ በከበበኝ ሰዓት ተስፋ ሆና ለዚህ ያበቃችኝ ሰው ናት…ደግሜ ነው የምለው አምላክ የዕውነት ጀግና ሚስት ነው የሰጠኝ…እንደ እሷ አይነት ጠንካራ ሰው ከአጠገቤ ባይኖር ኖሮ ታሪኬ ሌላ ሊሆን የሚችልበት አጋጣሚ ሊፈጠር ይችል ነበር…እኛ ያለንበት አካባቢ ጦርነት ስለሆነ በተለይ እኔ መውጣት አልችልም ነበር…ምክንያቱም ጥቁር ስለሆንኩ ካገኙኝ ሊይዙኝ ይችላሉ…እሷ ግን መስዋዕትነት ከፍላ ወጥታ እኔም ልጆቻችንም እንዳንቸገር ታደርግ ነበር…ብዙ ጊዜ ከአንድ ወንድ ጀርባ ጠንካራ ሴት አለች ሲባል…ዝም ብሎ ለማለትና ለሚዲያ ፍጆታ ብቻ ይመስለኝ…እውነት መሆኑን ግን በእሷ አረጋግጪያለሁ…

ሀትሪክ፡- …ልጆችህ የመን ከመወለዳቸው አንፃር አማርኛ ላይ እንዴት ናቸው…?…የትምህርታቸው ሁኔታስ…?…

ተስፋሁን፡- …በእርግጥ የመን እያለን በጦርነቱ ምክንያት ከቤት ስለማልወጣና አብዛኛውን ጊዜ አብሬያቸው ስለማሳልፍ እቤት ውስጥ አማርኛ እያዋራኋቸው ለማለማመድ ጥረት አደርግ ነበር…ያም ቢሆን ግን ብዙም አይችሉም…አቀላጥፈው የሚናገሩት አረብኛን ነው…እዚህ ከመጣን በኋላ ሁሉም ነገር በአማርኛ ስለሆነ የግድ እየሞከሩ ነው…ትምህርታቸውን በተመለከተ ብዙም እድለኞች አይደሉም… ያለ ኃጢአታቸው፣ያለ ጥረታቸው ብዙ ፈተና አይተዋል…እዛ ጦርነት ስለነበር… አንዴ ይጀምራሉ… ጦርነቱ ሲባባስ ደግሞ ያቆማሉ…እዚህ ከመጣን በኋላም ምንም የታሰበ ነገር የለም ምናልባት… ወደፊት…

ሀትሪክ፡- …ከየመን ስትመጣ ምን ይዘህ መጥተሃል…?…

ተስፋሁን፡- …(እንደመገረም እያለ)…ወይ አንተ ምን ይዤ እመጣለሁ…?… ራሴን፣ባለቤቴንና ልጆቼን ነዋ…?…

ሀትሪክ፡- …በእርግጥ ነገሮች ከባድ እንደነበሩ ባውቅም…ምን አልባት በዘጠኝ አመት የየመን ቆየታህ ንብረት ቢጤ ካፈራህ ብዬ ነው…?…

ተስፋሁን፡- …ኧረ የምን ንብረት አመጣህ…?…በለበስኩት ሸሚዝና ሱሪ ነው የገባሁት…ንብረት ለማለት እንኳን የሚበቁ ባይሆንም…ቤቴ ውስጥ ያሉትን እቃዎች ይዤ አልመጣሁም…ከንብረቱ ይልቅ የእኔንም የቤተሰቤንም ህይወት አትርፎ ከመውጣት በላይ ንብረት አላሳሰበኝም…ምትክ የማይገኝለት ህይወታችን መትረፉ ነው ትልቁ ነገር…በጣም የሚገርምህ የምንኖርበትን ቤት ከእነ እቃው በቅርቡ ወደ የመን ለመጣ አንድ ኢትዮጵያዊ ነው ትተንለት የመጣነው…ልጁ ተሯሩጦ የሚኖር ምስኪን ሰው ነው…በቤት ኪራይም ይሰቃይ የነበረ ሰው ነው…ሹካም ማንኪያም ሳንነካበት ያለችውን ትተንለት ነው የመጣነው…በየመን በአሁን ሰዓት ቤት ማግኘት ከባድ ነው…እኛ ግን ላከራዩን ሰዎች እንደምንመለስና እስከዛ እሱ እንዲጠብቀልን የመጣ መሆኑን ለባለቤቶቹ ገልፀን ነው የወጣነው…እቃችንን ይዘን ስላልወጣን እነሱም አምነውን ተቀብለውታል…እንደዛ ባናደርግ ለልጁ በጣም ከባድ ነበር…ቤቱን ልከራይ ቢል እንኳን እጥፍ ነው የሚጨምሩበት…ምክንያቱም በዚህ ወቅት ቤት አይገኝም…እኛ ግን ልጁ በጣም ምስኪን ስለሆነ…በዚህ መንገድ ዋሽተናቸው አስገብተነው ነው የመጣነው…

ሀትሪክ፡- …ከየመን ልትወጣ ስትል ገንዘብ ካልከፈልክ አትወጣም ተብለህ ብዙ ተጉላልተህ እንደነበር ሰምቻለሁ…ወደ ሀገር ቤት በፍጥነት እንዳትመጣም ምክንያት የሆነው እሱ ነው ልበል…?…

ተስፋሁን፡- …በሁለት ምክንያት ነው…በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው በየመን ለዘጠኝ አመታት የቆየሁበትን ገንዘብ ክፈል አሉኝ…የተጠየኩት ገንዘብ በእነሱ ወደ 3 ሚሊዮን ብር አካባቢ ነው…ለራሴ ሥራ የለኝም…በመከራ ነው የኖርኩት…ከየት አምጥቼ ነው የምከፍለው…?… ስላቸው…“…ለምን በባህር አትሄድም አሉኝ…”…ቢሮአቸው ሳውዲ ስለነበር…ይሄ ጉዳይ ብዙ አመላለሰኝ፣ጊዜም ወሰደብኝ…“…መጨረሻ ላይ የበረራ ትኬትህን ካመጣህ እንለቅሃለን…”…አሉኝ… ትኬቱን ከጅቡቲ አስገዝቼ አመጣሁ…በመከራ ተቀበሉኝ…አንደኛው ያዘገየኝ ይሄ ነው…ከዚህ ከገንዘቡ ሌላ የልጆቼ ጉዳይም አንደኛው ችግር ነበር…ልጆቼ የልደት ሰርተፊኬትም ሆነ ፓስፖርት አልነበራቸውም…ያለ ዶክመንት መውጣት አይቻልም ተባለ…የግድ ፓስፖርት ያስፈልጋቸዋል… የእኔንም የልጆቼንም ፓስፖርት አብሮኝ አየር መንገድ የተጫወተው የኢት.ቡናው አምበል እድሉ ደረጀ ውክልና ሰጥቼው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሯሩጦ አሳክቶልኝ ችግሩ ተፈቶ ወደዚህ ልመጣ ችያለሁ… በዚህ አጋጣሚ እድሉ ጉዳዩን የራሱ ጉዳይ አድርጎ አንዲሳካ በማድረጉ ላመሰግነው እወዳለሁ…

ሀትሪክ፡- …አንተ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣አየር መንገድ፣ መከላከያ፣ ለባንኮችና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጭምር የተጫወትክ…እግር ኳሱ መቼም የማይዘነጋህ ትልቅ ተጨዋች ነህ…ያ ትልቁ ታሪክህ ዛሬ በዚህ መልኩ ተቀይሮ ስታየው በውስጥ ምን ስሜት ተፈጠረ…?…

ተስፋሁን፡- …በቃ ምን ታደርገዋለህ…?…ህይወት እንደዚህ ናት…ሁሉም ነገር በነበረበት እንደማይሄድ ትልቅ ማሳያ ነው…ትናንት ታዋቂ ተጨዋች ነበርኩ…ብዙ ተጨብጭቦልኛል…ብዙ አድናቂ ወዳጆችም ነበሩኝ…ፕሮፌሽናል ተጨዋች እስከመሆንም ደርሼ ነበር…ዛሬ ደግሞ ያ ታሪኬ ተቀይሯል…የሆነውን ሁሉ ለበጎ ነው ብዬ ከመቀበል ውጪ ሌላ አማራጭ የለኝም…አእምሮን ማሳመንና መቀበል ከባድ ቢሆንም…ይሁን ለበጎ ነው ብዬ ከመቀበል ውጪ ሌላ አማራጭ የለኝም…እኔ ወደ የመን የሄድኩት መልካም ነገርን አስቤ ነው…እንደዚህ አይነት የከፋ ነገር ይገጥመኛል ብዬ አስቤ አላውቅም…ህይወታችን መትረፉ በራሱ ትልቅ ነገር ነው…ደግሞም መሽቶ ሲነጋ የሚሆነውን…ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማናችንም አናውቅም…ማን ያውቃል…?…ነገ ደግሞ..ይሄ ታሪክ በእሱ ኃይል ተለውጦ ልናይ አንችላለን…

ሀትሪክ፡- ..አሁን የት ነው የምትኖረው…?..በምንድነው የምትተዳደ ረው…?…

ተስፋሁን፡- …ተከራይቶ ለመኖር አቅሙም ገንዘቡም ስለሌለኝ የምኖረው ቤተሰቦቼ ጋር ነው…ባቤቴንም ልጆቼንም ይዤ ቤተሰቦቼ ላይ ነው የወደኩት…ቤተሰቦቼን መርዳት፣መጦር ሲገባኝ በዚህ እድሜዬ እነሱ ላይ ወድቂያለሁ…ቤተሰቦቼ እነሱ ጋ በመምጣቴ ቢደሰቱም እኔ ግን እጨነቃለሁ…እነሱን እያስቸገርኩ…እነሱ ላይ ወድቄ ነው በቃ የምቀጥለው…?…የሚለው ጥያቄ በአዕምሮዬ እየተመለላሰ እየረበሸኝ ነው…ቤተሰቦቼን የማስተዳድርበት ምንም አይነት መተዳደሪያ የለኝም…እንዳልኩህ ከየመን የመጣሁት ባዶ እጄን በለበስኩት ሸሚዝ ብቻ ነው…እንደመጣሁ አብረውኝ የተጫወቱም ያልተጫወቱም በውጩ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በእነ እድሉ ደረጀ አማካይነት “…አይዞህ አለንልህ ብለው ገንዘብ ልከውልኛል…”…ከዚህ ውጪ ያገኘሁት ምንም ነገር የለም…ከቤተሰቦቼ ትከሻ ወርጄ ራሴንም ቤተሰቤንም የማተዳደር ፍላጎቱ አለኝ…ልጆቼንም እዚህ ለማስተማር አስባለሁ…እንግዲህ እግዚአብሔር የሚያደርገውን ነው በተስፋ እየተጠባበኩ ያለሁት…

ሀትሪክ፡- …በቀጣይስ ምን ለመስራት አስበሃል…?…

ተስፋሁን፡- …የመን ከሰጠችኝ አንደኛው መልካም ነገር ወደ ስልጠናው የሚያስገባኝን ወረቀት ነው…እዛ በግልም፣ምክትል አሰልጣኝ ሆኜም ለመስራት ሞክሬያለሁ…በተጨዋችነት ከ20 አመት የበለጠ በትላልቅ ክለቦች የመጫወት ትልቅ ልምድ አለኝ…በዚህ ሂደት ውስጥ ከኢስትራከተር መንግስቱ ወርቁ እስከ አስራት ኃይሌና ካሳዬ አራጌ ድረስ በብዙ አሰልጣኞችም ሰልጥኜያለሁ..ከእነርሱም ብዙ እውቀትና ልምድን አካብቼያለሁ…የመንም ተምሬያለሁ…እነዚህን የተካበቱ ልምዶችንና ከራሴም ጨምሬ፣ ከስልጠናው ተምሬ…እግር ኳሱን በሙያዬ የማገዝ እድል ባገኝ የሚል ተስፋ በውስጤ አለ…ከመጣሁ በኋላ ስሰማ ስልጠናው አካባቢ መጠጋት ከባድ እንደሆነ ነው…ወደ አልጣኝነት ሙያ ለመግባት መንገዱ እንዴት እንደሆነ አላውቅም…የሚያስጠጋኝ ወይም መንገዱን የሚያሳየኝ ካለ ወደ ስልጠናው የመግባት ሃሣቡ ነው ያለኝ ለጊዘው…

ሀትሪክ፡- …ፈተናዎችህ መከራዎ ችህ ከመብዛታቸው የተነሣ…ለምንስ ተፈጠርኩ…?…ይሄን ያህልስ ምን በደልኩህ…?…እስከ ማለት…እስከ ማማረር የደረስክበት አጋጣሚስ ነበር…?…

ተስፋሁን፡- …በእርግጥ ፈተናዎቼ የበዙ ነበሩ…ግን ለራሴም በሚገርመኝ ሁኔታ ከማማረር ይልቅ ነገሮች ለበጎ ነው የመጡት ብዬ ማመስገንን ነበር ሳስቀድም የነበረው…ብዙውን ጊዜ በፀሎት፣በተስፋና በጥንካሬ ነበር የኖርነው…የባለቤቴ ጥንካሬ አጠንክሮኛል…ነገን በተስፋ አሻግሬ እንዳይም አድርጎኛል… በእርግጥ አንዳንዴ ፈተናው ሲበዛ…ከእኔ አልፎ ባለቤቴንና ምንም የማያውቁት ህፃናት ልጆቼን ሲፈትን ሣይ እንደሰው እንዴ ይሄን ያህል ምን አድርጌ ነው እንደዚህ ፈተናዬ የበዛው…?…ምንስ በድዪ ነው…?…የሚሉ ሃሣቦች በአዕምሮዬ ብቅ የሚልበት አጋጣሚ ቢኖርም…የሞቱትን፣አካላቸው የጎደሉትን፣አይሆኑ የሆኑትን ሣይ እፀናለሁ…ተመስገንም እላለሁ…ከምሬት ይልቅ ማመስገንን ነበር ሳስቀድም የነበረው…የሚገርምህ እምነት እንደሚያድን…ፀሎት እንደ ሚያድን ያወኩት በተግባር ነው… አጋጣሚው ለእኔ መጥፎ ብቻ አልነ በረም… ፈጣሪ አምላክ እንዳለ…ካመ ንከው፣ ከለመንከው… ከእሳትና ከፈተና እንደሚያወጣ ያመንኩበት ነው…

ሀትሪክ፡- …እስቲ አሁን ደግሞ ከየመን ውጣ ውረዶችህ እንውጣና በእግር ኳስ ህይወትህ ዙሪያ እናውራ…የተስፋሁን የመጀመሪያ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው…?…

ተስፋሁን፡- …በ1988 አካባቢ ይመስለኛል…መጀመሪያ ለምርጫ የሄድኩት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው… ለምርጫ ያኔ ብዙ ተጨዋቾች ነበር የሚመጡት…ከ300 እና 400 ተጨዋቾች በላይ ለምርጫ መጥተው በጣም ትንሽ ተጨዋቾች ነበር የሚመረጡት…እንዳልኩህ የሚያውቁኝ ሰዎች…“…ለምን ክለብ አትሞክርም…”…እያሉ ሲጨቀጭኩኝ ጊዮርጊስ ለሙከራ ሄድኩ…በወቅቱ አሰልጣኙ ዳኛቸው ደምሴ ነበር..በጣም ወደደኝ…ለጊዮርጊስ C ተይዤ የእግር ኳስ ህይወቴ አንድ ብሎ ጀመረ…የሚገርምህ ግን ጊዮርጊስ C ብዙም አልቆየሁም…የውድድር አመቱ ሳያልቅ…“…ለዋናው ቡድን ትፈለጋለህ…”…ስባል ጊዮርጊስ የሀገሪቱ ትልቅ ክለብ ስለሆነ በጣም ደነገጥኩ…በአሰልጣኝ አስራት ኃይሌ አማካይነትም ወደ ዋናው ቡድን አደኩ…

ሀትሪክ፡- …ለጊዮርጊስ ዋናው ቡድን የማደግ እድል በፍጥነት ብታገኝም…በዋናው ቡድን ውስጥ ከአንድ አመት በላይ አልቆየህም የዚህ ምክንያቱ ምንድነው…?…

ተስፋሁን፡- …እንዳልኩህ ነው…ጊዮርጊስ በጣም ትልቅ ቡድን ነው…ሀገሪቱ ውስጥ አሉ የተባሉና በጣም ስም ያላቸው ተጨዋቾች ያሉበት ክለብም ነው…እኔ የምጫወተው በአጥቂ ቦታ ነው…በዚህ ቦታ ደግሞ ክለቡ ብቻ ሣይሆን ሀገሪቱ አሉኝ የምትላቸው አጥቂዎችን ይዟል…አሸናፊ ሲሳይ ነበረች…በኋላ ላይ ስንታየሁ ጌታቸው (ቆጬ) መጣ…ፍሰሀ በጋሻውም ነበር…እነዚህ ተጨዋቾች በወቅቱ ከእኔ የበለጠ ስምም ችሎታም ነበራቸውና የመሰለፍ እድሉ በጣም ከባድ ነበር…እኔ ደግሞ መጫወት በጣም እፈልግ ስለነበር…የመጫወት እድል ወደማገኝበት ክለብ መሄድ አለብኝ ብዬ ጊዮርጊስ ቤት አንድ አመት ብቻ ቆይቼ ወደ ኦሜድላ ሄድኩኝ….

ሀትሪክ፡- …የሚገርመው ደግሞ ኦሜድላም ከአንድ አመት በላይ አልቆየህም…?…በሰላም ነው…?…

ተስፋሁን፡- …(እንደ መሳቅ እያለ)…ትክክል ነህ…ኦሜድላ ገብቼ እየተጫወትኩ ሣለ ኢንስትራክተር መንግሥቱ ወርቁ ያየኝና…“…ኮል የሚባለውን ልጅ አምጡልኝ…”…ብሎ አስጠራኝ…መንግሥቱ ያኔ የአየር መንገድ አሰልጣኝ ነበር…መንግሥቱ ወርቁን በሚያክል ትልቅ አሰልጣኝ መጠራት ትልቅ ነገር ነው…እሱ ወዲያው አስፈረመኝና አየር መንገድ ገባሁ…የሚያሳዝንህ ግን መንግሥቱ ለአየር መንገድ አስፈርሞኝ አብሬው የቆየሁት ከአምስት ወር አይበልጥም…እንደ አጋጣሚ መድን ወደ አምስቴ ነው ስድስቴ አይሆኑ አሸናነፍ ስንሸነፍ በጣም ተበሳጨና ጥሎ ሄደ…

ሀትሪክ፡- …በአየር መንገድም በጣም ስኬታማ የሚባል ጊዜ ነበረህ…

ተስፋሁን፡-… አየር መንገድ እያለሁ በጣም ስኬታማ የሚባል ጊዜ ነው የነበረኝ…ሁለት ጊዜ ኮከብ ጎል አግቢ ሆኜ ጨርሻለሁ…አንድ ጊዜ ደግሞ የኮከብ ጎል አግቢ ክብርን በጋራ አሸንፌያለሁ…በአጠቃላይ በአየር መንገድ ሁለት አመት ነው የቆየሁት…ግን በጣም ጥሩ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት…ጎልም በጣም አገባ ነበር…

ሀትሪክ፡- …ብዙ ሰዎች ኮልን ወደ ኢትዮጵያ ቡና ያመጣው…ስዩም ነው…?…ካሳዬ…?…የሚል ክርክር ያነሳሉ…እኔ ግን ስዩም ነው ባይ ነኝ…ትክክል ነኝ…?…

ተስፋሁን፡- …መንግሥቱ ወርቁ አየር መንገድን ከለቀቀ በኋላ ስዩም አባተ ክለቡን ያዘው…የሚገርምህ ስዩም በዚያን ጊዜ ሶስት ቡድን ነበር በአንዴ የሚያስለጥነው…

ሀትሪክ፡- …ሶስት ቡድን…?…ማን ማንን ነው የሚያስለጥነው…?…

ተስፋሁን፡- …አዎን ሶስት ቡድን…አየር መንገድ፣ኢትዮጵያ ቡናንና ብ/ቡድኑን ያሰለጥን ነበር…ጠዋት ላይ አየር መንገድንና ብ/ቡድንን በተለያየ ሰዓት ካሰራ ወይም ሁለቱን የወዳጅነት ጨዋታ ካጫወተ ከሰዓት ቡናን ያሰራ ነበር…ስዩም ሰልጠናው በጣም ደስ ይል ይመች ነበር…አየር መንገድ ሲያስራን በጣም ይወደኝና ወደ ቡና ይወስደኛል…የአየር መንገድ ሕጋዊ ተጨዋች ሆኜ ከቡና ጋር ወደ ሶስት ወር አካባቢ ዝግጅት አብሬ ሠራሁ…ስዩምም በጣም ወደደኝ…በመጨረሻ ለቡና ሊያስፈርመኝ…ሊል ሲል ትልቅ ክርክርና ውዝግብ ተነስቶ ወደ ቡና የማደርገው ዝውውር ከሸፈ እንጂ መጀመሪያ ስዩም ወስዶኝ ከቡና ጋር ሶስት ወር ሙሉ ዝግጅት አብሬ ሠርቻለሁ …

ሀትሪክ፡- …የምን ክርክርና ውዝግብ ተነስቶ ነው ዝውውሩ የከሸፈው…?…

ተስፋሁን፡- …ያኔ ያው ልጅነቱም ጉጉቱም ነበር…በዚያን ሰዓት ስለ ህጉ እውቀቱ ብዙም ስለሌለኝ ሳላገናዝብ…ሁለቱም ሲያጨናንቁኝ ለሁለቱም ፈረምኩ…በዚህ የተነሳ ብዙ ክርክር ተፈጠረ…መጨረሻ ላይ በምንና እንዴት እንደተስማሙ ሳላውቅ…የመጀመሪያ ክለቡ አየር መንገድ ስለነበር ተገቢነቱ ለእነሱ ተብዬ ወደ አየር መንገድ ተመለስኩ…

ሀትሪክ፡- …አንተ በኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ታሪክ የማይዘነጋው የ1995ቱ ቡድን አባል ነበርክ… የቡናን ማልያ የመልበስ እድሉን በካሳዬ የቀጥታ ጥሪ ነው ዳግም ያገኘኸው ልበል…?…

ተስፋሁን፡- …በጣም ትክክል…“ … ኮል ለአጨዋወቴ በጣም ያስፈል ገኛል…”…ብሎ ነው ያስጠራኝ… እዳልኩህ ኢትዮጵያ ቡና የሀገሪቱ ትልቁ ክለብ ነው…ከእነርሱ ጋር ሶስት ወር ያህል ዝግጅት አድርጌ አድርጌ ባለመሳካቱ በጣም ተበሳጭቼ ነበር…በኋላ ላይ በ1995 ካሳዬ አዲስ ፍልስፍና ይዞ ቡድኑን እንዲረከብ ሲደረግ “ኮል ለአጨዋወቴ በጣም ያስፈልገኛል” ብሎ በድጋሚ ከአየር መንገድ አስጠራኝ… እንደ አጋጣሚ ከአየር መንገድ ጋር የነበረኝ ኮንራት ተጠናቆ ስለነበር…አጋጣሚው ጠቀመኝና ለቡና የመጫወት ህልሜን አሳካሁ…

ሀትሪክ፡- …ወደ ኢትዮጵያ ቡና ከመግባትህ በፊት ኢንስትራክተር መንግሥቱ ወርቁን ጨምሮ በተለያዩ አሰልጣኞች ሰልጥነሀል…በካሳዬ አራጌ ስትሰለጥንና ቡና ስትገባ ምን ስሜት በውስጥህ ተፈጠረ…?…

ተስፋሁን፡- …በጣም ነው የተደሰ ትኩት…ምክንያቱም ካሳዬ ካሳዬ ነው…ቡናም ቡና ነው…ካሳዬም ኡትዮጵያ ቡናም በጣም ተወዳጆች ነበሩ…እንደ ዚህ አይነት ቦታ መገኘት የተለየ ደስታ እንዲሰማህም ያደርጋል…ካሳዬ ሲያስጠራኝ እኔ ጋ ያለውን ነገር አይቶ እምነት ጥሎ በመሆኑ በጣም ነው ደስ ያለኝ…ካሳዬ እንኳን ስልጠናው…በስብዕናውም በጣም የምትወደው ሰው ነው…የሚያሰራው ነገር በሙሉ ውስጥህ የሚቀር ነው…በጣም የሚገርምህ በእሱ የአሰልጣኝነት ዘመን በጣም ደስ ብሎኝ ነው አብሬው የሠራሁት፣እጫወትም የነበረው…እንደውም እውነቱን ልንገርህ ከእሱ ከተለየሁ በኋላ ነው መጫወት ሁሉ አቅቶኝ የነበረነው…ምክንያቱም እሱ የሆነ ነገር ውስጤ ከቶ የተለየ ስሜትን ፈጥሮልኝ ነበር…

ሀትሪክ፡- ..ካሳዬ የራሱን ለየት ያለ የጨዋታ ፍልስፍና ይዞ የመጣ አሰልጣኝ ነው…አንተ በካሳዬ ሠልጥነህ ያለፍክ ተጨዋች ነህና የእሱ ፍልስፍና ለኢትዮጵያ ቡናም ለሀገርም ይጠቅማል ትላለህ…?…

ተስፋሁን፡- …እንደ እኔ የግል አስተያየት አዎን ይጠቅማል…የካሳዬ አጨዋወት ፍልስፍና ሣይሆን ባለን ነገር፣በእውቀት፣በምንችለው አቅም እንድንጫወት የሚያደርግ ነው…ብዙውን ጊዜ ኢትዮጵያዊያን ኳስ ይችላሉ የሚል ፍፁም የማይገባኝ ነገር ሲነገር እሰማለሁ…ኳስ መቻል ማለት ዝም ብለህ ኳስ ይዚህ ስትሽካረኮር ስታዲየም ውለህ ማደር ነው እንዴ? በእርጥ ሁሉም ኳስ ይችላል ልዩነት ግን መሠለህ በአዕምሮ ልቀህ መገኘቱ ላይ ነው… ኩስ መቻል ማለት ለእኔ በአዕምሮ ተጫውተህ መውጣት ማለት ነው ለእኔ… ካሳዬ የሚሰራውን ስንለምደውና ስናዳብረው አላማው ይገባሃል… አዕምሮህ እንዲያድግ .. እያሰብክ እንድትጫወት የሚያደርግ ነገር ነው ይዞ የመጣው… እኔ ከካሳዬ ጋር ስሰራ የመቀበል አቅም በጣም ጥሩ ስለነበር… በጣም ቀሎኝ ተመችቶኝ በእውቀት ነበር ስጫወት የነበረው.. ካሳዬ ስልጠናው ብቻ ሣይሆነ ንግግሩም ይናፈቅ ነበር… ሁሉም ፖዘቴቭ ነገር ነው ከአንደበቱ የሚወጣው.. የካሳዬ ፍልስፍና አዕምሮ የሚቀይር ነው…የተጨዋቹ አጨዋወት የቀላል.. አዕምሮ ያሳድጋል ከዚህ አንፃር ለሀገር ይጠቅማል…

ሀትሪክ፡- …በኢት.ቡና ጥሩ ቆይታ ነበርህ…?…

ተስፋሁን፡- …በኢት.ቡና የነበረኝ የሁለት አመት ቆይታ በጣም ጥሩና የማልዘነጋው ነው፤ዋንጫ ባለመብላቴ ብቆጭም በጣም ጥሩ ስብስብ ነው የነበረን…ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሻምፒዮናነት ታሪክ ቢኖረኝ በጣም ደስ ይለኝ ነበር…ያ አለመሆኑ ይቆጨኛል…ቡና የተጫወትኩት ለሁለት አመት ብቻ ነው…ግን…በውስጤ ያለው ስሜት…ሃያ አመት የተጫወትኩ ያህል ነው…

ሀትሪክ፡- …የበርካታ ታላላቅ ክለቦችን ማልያ ለብሰህ የመጫወትህን ያህል የብ/ቡድን ማልያ ለብሰህ ስትጫወት ብዙም አልታየህም…?…

ተስፋሁን፡- …ትክክል ነህ…ይጠሩኛል…እንደገና ይመልሱኛል…

ሀትሪክ፡- …ለምን…?…

ተስፋሁን፡- …አላውቅም…በዛን ጊዜ የነበሩ አሰልጣኞች የካሳዬ ፍልስፍና ተቃራኒ የሆነ አስተሳሰብ ነበራችው…ቆመው ነው የሚጫወቱት…አይሮጡም ብለው ስለሚያስቡ ለመያዝ ይቸገራሉ…አንዴ እንደውም ስዩም ከበደ በእኔ ዙሪያ ተጠይቆ…“…አይነጥቅም…”…ብሎ አስተያየት ሰጥቶ እንደ ነበር አስታውሳለሁ…መንጠቅ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግን እስከዛሬ አልገባኝም…መንጠቅ ማለት በጉልበት መደብደብ ማለት ነው…?…በወቅቱ እኔ ኳስ እነጥቅ ነበር…ግን ሄጄ አልደባደብም…ይሄን መሠል አስተያየት ይሰጡ ስለነበር የመመረጥ እድላችንን አጥብቦት ነበር… ያም ቢሆን ግን በአስራት ኃይሌ ጊዜ ተመርጬ ተጫውቻለሁ…አስራት ስላሳደገኝና በደንብ ስለሚያውቀኝ ጠርቶኝ ለሀገሬ ተጫውቻለሁ…

ሀትሪክ፡-…ካሳዬ ወደ ቡና አሰልጣኝነት ሲመለስ ምን አልክ…?…

ተስፋሁን፡- …የመን ሆኜ ስሰማ በጣም ነው ደስ ያለኝ…ምክንያቱም ያለ ጊዜው የተቋረጠው ሂደት ይቀጥላል የሚል ነገር በውስጤ ስለተፈጠረ ደስ ነው ያለኝ…ለአጨዋወቱ ትክክለኛ ሰው እያገኘ ከሄደ መረዳቱ ካለ አዲስ ነገር እንደሚፈጥርም እምነቱ አለኝ…

ሀትሪክ፡- …ከእናንተ በተቃራኒው የቆሙ አንደንድ ወገኖች የካሳዬን ፍልስፍና የሚከተሉ ወይም የሚያደንቁ ተሯሩጠው የመጫወት ችግር ያለባቸው መንጠቅ የማይችሉ ተጨዋች ናቸው ይላሉ፤ ይሄንን አባባላቸውን በምስሌ ሲያስደግፉ ደግሞ…ነፍሱን ይማረውና አስግድ ተስፋዬን፣ ኩኩሻን፣ አሸናፊንና አንተን የመሮጥ ችግር ያለባችው በማለት ያነሳሳችኋል ሃሣቡ ይስማማሃል…?…

ተስፋሁን፡- …በፍፁም አልስማማም…ከላይም ብዬሃለሁ የማይባል ነገር የለም…አንዴ ባንክ እያለሁ አሰልጣኙ ገና ኳስ ስይዝ…“…ይሄ የካሳዬ ፍልስፍናን እዛ ጥለህ ና…”…ሁሉ ብሎኛል…በአጭሩ እኔ በአባባሉ አልስማማም…አይሮጡም፣ፍጥነት የላቸውም አይነጥቁም ይባላል…ስለ ራሴ ስነግርህ…እኔ በጣም እነጥቃለሁ…በጣም የማልሮጠው ግን በአዕምሮ ስለምጫወት ነው…በአዕምሮ ስትጫወት ጉልበት ትቀንሳለህ…ጉልበት አላባክንም…አንድ ለአንድ ስንገናኝ 10 እና 15 ሜትርም ፈጥነህ መሮጥ እኮ ያስፈልጋል…በካሳዬ ፍልስፍና ስር የተሰበሰበብነው እንደተባለው ሣይሆን በአዕምሮ የምንጫወት ተጨዋቾች ነን…

ሀትሪክ፡- …ከማን ጋር ስትጫወት ጨዋታ ይቀልሀ ነበር…?…

ተስፋሁን፡- …በዚያን ጊዜ የነበረው የጨዋታ ሲስተም ከሁሉም ጋር ተግባብተህ እንድትጫወት የሚያደርግ ነው…አጨዋወቱ አንድን ሰው ብቻ ሣይሆን ብዙ አማራጮችን ነበር የሚፈጥርልህ…አንድ ሰው ኳስ ሲይዝ መቸገር የለበትም…መርጦ እንዲሰጥ ሲስተሙ ብዙ ምርጫዎችን ያቀርብለታል… ስለዚህ ከሁሉም ጋር ተግባብቼ ነበር የምጫወተው…

ሀትሪክ፡- …ሮል ሞዴል አድርገኸው ያደከው ተጨዋችስ አለ…?…

ተስፋሁን፡- …ሞዴል አድርገህ ለማደግ ስታዲየም መግባትና ጨዋታ መከታተል አለብህ…የሚገርምህ ነገር እኔ ጊዮርጊስ C ከመግባቴ በፊት አንድም ቀን ስታዲየም ገብቼ ጨዋታ ተከታትዬ አላውቅም… ስታዲየም ለመጀመሪያ ጊዜ የገባሁት ጊዮርጊስ C ስገባ ነው…የሠፈር ሰዎች ናቸው…“…ለምን ክለብ አትሞክርም…?…”…ብለው ገፋፍተው የላኩኝ እንጂ…ብዙም የመከታተል ዝንባሌው አልነበረኝም… በዚህ የተነሣ እንደ ሞዴል አይቼ የተመኘሁት ተጨዋች እንዳይኖር አድርጓል…በሞዴልነት የምጠራው ተጨዋች የለም…ከጊዮርጊስ C ቡድን ጀምሮ አብሬው በመጫወቴ ለማድነቅ የተገደድኩት ሙሉአለም ረጋሣን ነው…

ሀትሪክ፡- …የጨዋታ ዘመንህ ምርጡ ተጨዋችስ…?…

ተስፋሁን፡- …ሙሉ አለም ረጋሣን ነው የማስቀድመው…እሱ ለእኔ ልዩ ተጨዋች ነው…በጣምም ይለይብኛል…ጊዮርጊስ ባለመቆየቴ ብዙም አብሬው ባልጫወትም…አዕምሮው ፈጣን የሆነ ተጨዋች ነው…

 

ሀትሪክ፡- …ከዚህ በላይ ከአንተ ጋር ብናወራ ደስ ይለኝነር…የአንተን ታሪክ በሁለት እትም ለመቋጨት ማሰብም ግማሽ ይዞ ግማሽ የመጣል ያህል ነው…ግን የቦታ ውስንነት እዚህ ላይ እንድንቆም ያስገድደናልና…አመስግኜህ መልካሙን ሁሉ ተመኝቼ ከመለያየታችን በፊት…ማለት የምትፈልገው ካለ ቦታውን ልልቀቅልህ…?…

ተስፋሁን፡- …በመጀመሪያ ፈጣሪዬን እንዳመሰግን ፍቀድልኝ…ቤተሰቦቼን በተለይ አባቴን በጤና እንዳገኝ ስለረዳኘ…ባለቤቴንና ልጆቼን ከእሳቱ ስላወጣልኝ አመሰግነዋለሁ…ከዚህ ውጪ ሁሉንም መዘርዘር ከባድ ቢሆንም…የፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ማኅበር ኤፍሬም ወንደሰን፣አሜሪካ፣አውሮፓ፣ ደቡብ አፍሪካ ያሉ አብረውኝ የተጫወቱ፣ያልተጫወቱትን ድጋፍ ያደረጉልኝን በሙሉ…ደብዳቤ ከመፃፍ ጀምሮ ከፍተኛ ትብብር ያደረጉልኝን ፌዴሬሽኑን…እድሉ ደረጀንና…ስማቸውን ብዘነጋም በእኔ ጉዳይ የተረባረቡትን በሙሉ አንድ ላይ ማመስገን እወዳለሁ…የሁሉንም ርቦርቦሽ ሣይ ተገርሜያለሁ…ይሄን ያህል ለሀገሬ ምን አድርጌ ነው…?…ብዬ ራሴን እስክጠይቅ ድረስ የተረባረቡትን ከልቤ አመሰግናለሁ… አንተም ክብር ሰጥተህ…ከአንባቢ ጋር እንድገናኝ ምክንያት ስለሆንክ በተመሳሳይ ከልቤ ሳላመሰግንህ አላልፍም…፡፡


ተስፋሁን ጋዲሳ (ኮል) ለመረዳት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 

ቀጥር – 1000378426344


 

የመጀመሪያውን ክፍል ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ 👇

በመከራ ተፈትና የተረፈችው የተስፋሁን ጋዲሳ ህይወት

 

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.