በመከራ ተፈትና የተረፈችው የተስፋሁን ጋዲሳ ህይወት

(የመጀመሪያ ክፍል)
በመከራ ተፈትና የተረፈችው የተስፋሁን ጋዲሳ ህይወት
“ፈጣሪን ከለመንከው፣ ካመንከው ከእሳትና ከመከራ እንደሚያወጣ በችግሬ ተምሬያለሁ”
ተስፋሁን ጋዲሳ (ኮል) የቀድሞው ተጨዋች

የሆነው ሁሉ በጣም ያሳዝናል፤ ለማመንም ይከብዳል፤ የሰሙትን ሁሉ ልብን ይሰብራል፤ የቀድሞው የቅ/ጊዮርጊስ፣ የኦሜድላ፣ የአየር መንገድ፣ የቡና ገበያ፣ የመከላከያና የሐረር ቢራ ተጨዋች የነበረው ሁሉም የስፖርት ቤተሰብ ፍርጥም ባለው ተክለ ሰውነቱና በድንቅ ጥበቡ የሚያስታውሰው ተስፋሁን ጋዲሳ (ኮል) በየመን የገጠመው የብዙዎችን ልብ የሰበረ ነው… ከዛሬ ዘጠኝ አመት በፊት እግሩን ከአዲስ አበባ ነቅሎ በወቅቱ ለእሱ የተስፋይቱ ምድር ወደ ሆነችው የመን ሲያቀና እንደ አሁኑ መከራን፣ ፈተናና ስቃይ የዕለት ተዕለት ህይወቴ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ ለአፍታም ገምቶ አልነበረም፤ ይልቁንም የሞላ፣ የተትረፈረፈ ህይወትን አገኝባታለሁ ብሎ በተስፋ ተሞልቶ ነበር የተጓዘው…. ነገር ግን በየዕለቱ በርካታ ሰዎች የሚረግፉባት፣ አካላቸው የሚጎልባት፣ ጥይት የሚዘንብባት፣ ሮኬት የሚወነጨፍባትና መድፍ የሚያጓራባት የመን እንደ አሰበውና እንደገመተው እጇን ዘርግታ አላስተናገደችውም፡፡

ይልቁንም በየመን በነበረው የዘጠኝ ወር ቆይታ በምድር ላይ አሉ የሚባሉ ፈተናዎችና መከራዎችን አስታቅፋዋለች፤ ታርዟል፣ ተጠምቷል፣ በእጅጉም ተፈትኗል… “ተስፋሁን ጋዲሳ (ኮል) የሚላስ የሚቀመስ አጥቶ ከእነ ልጆቹ በየመን ጎዳና ላይ ወድቋል” የሚለው ዜና በፎቶ ተደግፎ በማኅበራዊ ትስስር ሚዲያ ከተለቀቀ በኋላ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን አይንና ጆሮዎች በፍጥነት ወደ ባህረ ሰላጤዋ ሀገር የመን ተሻግረው በደጋግ ኢትዮጵያውያን ርብርቦሽ የሀገሩን መሬት ለመርገጥ በቅቷል፡፡

ተስፋሁን ጋዴሳ (ኮልን) የጫነችው አውሮፕላን ቦሌ አየር ማረፊያ ደርሳ ተስፋሁን ከባለቤቱና ከሁለት ልጆቹ ጋር ከአውሮፕላን ሲወርዱ ከእግሩና ከአካሉ ይልቅ እንባው ቀድሞ ነው የፈሰሰው… እንደ ዝናብ ሲዘንብ ከነበረው የጥይት አረር፣ ሲተኮስ ከነበረው ሮኬትና ሲያጓራ ከነበረው መድፍ ህይወታቸው ተርፎ በሠላም ወደ ሀገራቸው በመመለሳቸው ደስታና እምባ ፊቱ ላይ እንዲፈራረቁ አድርጓል፤
በጥሩ ባለሙያ የተሰራ ልብ አንጠልጣይና አሳዛኝ ፊልም የሚመስለውን የተስፋሁን ጋዲሳ (ኮልን) የየመን አስጨናቂ እውነተኛ ገጠመኝ ሰምቶ ስሜቱን መቆጣጠር የተሳነውና ክፉኛ የተረበሸው የሀትሪክ ጋዜጣ ኤክስኪዩቲቭ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ይስሀቅ በላይ በሚያስለቅሰው እያለቀሰ በሚያሳዝነው እያዘነ የሰራው በየመን ላይ ብቻ ያተኮረው ቃለ-ምልልስ የመጀመሪያውን ክፍል ከዚህ በታች አቅርቦታል፤ ጋዜጠኛው ከተስፋሁን ጋር በነበረው ቆይታ ያላነሱት፣ ያልዳሰሱት ጉዳይ የለምና አብራችሁን ቆዩ፤ በቀጣይ ሳምንት የተስፋሁን ጋዲሳ የአግር ኳስ ህይወትን ማለትም በቅዱስ ጊዮርጊስ፣ በኢትዮጵያ ቡናና በሌሎች ክለቦች ያሳለፋቸውን ያልተነገሩ የእግር ኳስ ታሪኮቹን አጫውቶናልና የሳምንት ቀጠሮአችሁን ከወዲሁ እንድታስተካክሉ የበአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

ሀትሪክ፡- …ከረጅም አመት በኋላ በአካል ስላገኘሁህና ለቃለ-ምልልሱም ስለተባበርከኝ በቅድሚያ ላመሰግንህ…?…

ተስፋሁን፡- …እኔም በጣም ነው የማመሰግነው…ከስፖርት ቤተሰቡ፣ከህዝቤ ጋር በተለይ በሚዲያ ከተገናኘሁ ረዥም አመታትን አስቆጥሬያለሁ…አንተም በዚህ ፈታኝና አስቸጋሪ ወቅት ከናፈቁኝ የስፖርት ቤተሰቦች ጋር በሀትሪክ ድልድይነት የምገናኝበትን እድል ስለሰጠኸኝ ከልብ አመሰግናለሁ…
ሀትሪክ፡- …ይሄን ያህል ከተመሰጋገንን ይበቃል…ኮል…ከስንት አመት በኋላ ነው የሀገርህን መሬት የረገጥከው…?…

ተስፋሁን፡- …ዘጠኝ…?…አስር አመት አይሆነኝም ብለህ ነው?…ከረዥም ጊዜ በኋላ ነው ወደ ሀገሬ የመጣሁት…

ሀትሪክ፡- …እግር ኳስን እንዴት ጀመርክ….?…ብዬ ጠይቄ…”…ያው እንደማንኛውም ሰው በጨርቅ ኳስ ነው የጀመርኩት…”…የየሚለው አሰልቺ ጥያቄና መልስ በማንሣት ሣይሆን በቀጥታ ወደ ቃለ-ምልልሱ የምገባው “ተስፋሁን ጋዲሳ /ኮል/ ከእነ ልጆቹ በየመን ጎዳና ላይ ወድቆ ምፅዋት እየለመነ ነበር? በሚለው ብዙዎችን ስላስደነገጠው የማህበራዊ ትስስር ዜና ነው? የምጀምረው ትስማማለህ…?…

ተስፋሁን፡- …(እሽታውን አንገቱን በመነቅነቅ እየገለፀ)…ትችላለህ…?….

ሀትሪክ፡- …እውነት ኮል በየመን ልጆችህን ይዘህ ጎዳና ላይ ወድቀህ ነበር….?…ለከፋ ችግርስ ተዳርገህ ነበር…?….

ተስፋሁን፡- …(እንደመተከዝና በሃሳብ እንደመመሰጥ እያለ)…አኔ በተፈጥሮዬ መዋሸት አልወድም… የነበርኩት ከ2014 ጀምሮ በጦርነት እየታመሰች በጥይት አረር…በሮኬት እሳት እየነደደች ባላችው ሀገር የመን ውስጥ ስለነበር…ችግር የሚባል ነገር አልገጠመኝም አልልም…በጣም ተቸግሬ ነበር…በጣም አስከፊና ፊልም የሚመስሉ ዘግናኝ ነገሮችን አስተናግጄያለሁ…ጦርነቱ እኔ ከምኖርበት ቤት በ200 ሜትር ርቀት ውስጥ ስለነበርና አንዳንዴ ደግሞ በ100 ሜትርና በቤቴ ደጃፍ አካባቢ ይካሄድ ስለነበር በጣም ብዙ መከራዎችን አስተናግጄያለሁ…ሥራ የሚባል ነገር ስለማልሰራም የሚላስ የሚቀመስ ነገር ለማግኘት ነገሮች እጅግ በጣም ከባድ ነበሩ…እኔስ ሁሉንም ነገር ልቋቋም እችላለሁ…ሁለቱ ትናንሽ ልጆቼ በማያውቁት ነገር የዚህ ፈተና አካል ነበሩ…በጣም ሲረብሸኝም ሲያስጨንቀኝም የነበረው ይሄ ነው…ከባለቤቴና ከልጆቼ ጋር ቅልጥ ባለ ማባሪያ በሌለው ጦርነት ውስጥ ጥይት እየዘነበ ሮኬት እየተተኮሰ ነው ያሳለፍኩት…አምላክ ያለ ምክንያት አልፈጠረንም…እኔንም ልጆቼንም ከዚህ ከባድ ፈተና አውጥቶናል…እንዳልኩህ ነው መራቡንም መጠማቱንም እንችለዋለን…ግን ህይወትን እስከማጣት የሚያደርስ ነገር ነበር የገጠመን አምላክ ግን አትርፎናል…ከዚህ ውጪ ግን ጎዳና ላይ እስከ መውደቅ እስከመለመን አልደረስንም…

ሀትሪክ፡- …እንዴ ኮል ጎዳና ላይ አልወደኩም እያልክ ነው…?…ልጆችህን አቅፈህ በጣም የቆሸሸ ቦታ ላይ ተቀምጠህ የሚይሳይ ምስል በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ተለቆ ብዙዎች በሀዘኔታ ሲቀባበሉት በስፋት ታይቷል…አብሮም ጎዳና ላይ መውደቅህ ሲዘገብ ነበር…ጎዳና ላይ አልወደኩም…እስከመለመንም አልደረስኩም ካልክ ታዲያ በምስል ተደግፎ በፌስ ቡክ የተናፈሰው ወሬ ውሸት ነው ማለት ነው…?…

ተስፋሁን፡- …አጋጣሚው የሆነው እንዴት መሠለህ…እኔ ባለሁበት አካባቢ ትሬይኒንግ የማሰራቸው ልጆች አሉ…እንዴት አይነት ጥሩ ጥሩ ልጆች አሉ መሠለህ…በዚህ በጦርነት ምክንያት የመጫወቻ እድሜያቸው እየተቃጠለ ያሉ ወጣቶች…በዚህ መልኩ ማሳለፋቸው በጣም ያሳዝንሃል…አንድ ጊዜ ጦርነቱ ትንሽ በረድ ባለ ጊዜ እነዚህን ልጆች እየሠራኋቸው እያለ…እነሱም ቤተሰቦቻቸውም ያለንበትን አስከፊና ፈታኝ ነገር በማየት…“…ኮል ለምን ወደ ሀገራችሁ አትሄዱም…?…እዚህ ያለው ነገር ከባድ ነው…ልጆችህም፣ባለቤትህም አንተም ለከፋ ነገር ልትዳረጉ ትችላላችሁና…መሄድ አይሻላችሁም?…”… ሲሉኝ ኧረ እፈልጋለሁ….ግን ትንሽ ችግር አለ አለኳቸው…“…የምን ችግር…?…”…ሲሉኝ…ፓስፖርቴ ኤክስፓየርድ አድርጓል…በዛ ላይ ስራ ስለሌለኝ ገንዘብ የለኝም…ለአራት ሰው የአውሮፕላን ትኬት መቁረጫ ገንዘብም የለኝም ስላቸው…“…መሄድ የምትፈልግ ከሆነማ ችግር የለም…”…ብለው ለካፒቴን ነቢል ነገሩት…ካፒቴን ነቢል አሰልጣኝ ነው…እኔን መጀመሪያ ወደ የመን ያስመጣኝ እሱ ነው…በጣም አሪፍና ቀና ሰው ነው…እንዳሉት…“…መሄድ ይፈልጋል…”…ብለው ነገሩት…እሱም ሳይውል ሳያድር እቤቴ ድረስ መጥቶ አስጠራኝና…ጠየቀኝ…

ሀትሪክ፡- …ምን ብሎ…?…

ተስፋሁን፡- …“…ኮል ወደ ሀገርህ መሄድ እንደምትፈልግ ሰማሁ…እውነት ነው…?…”…ብሎ ጠየቀኝ…እኔም አዎን እውነት ነው አለኩት…ይሄንን የምናወራው መኖሪያ ቤቴ አካባቢ ባለች አንድ ቦታ ነው…ሀገሩ ጦርነት ስለሆነ የተቀመጥንባት፣የምናወራባት ቦታ…የፈራረሰ ነገርና ቆሻሻ የሚታታይበት አካባቢ ነበር…ከእሱ ጋር በእዚህ ሁኔታ ቁጭ ብለን እያወራን እያለ አንደኛዋ ልጄ መጣች…አቅፌያት…እሱም መሬት ቁጭ ብሎ ማውራታችንን ቀጠልን…“…ኮል አንተ እኮ ትልቅ ታሪክ ያለህ ተጫዋች ነህ…በቃ አታስብ…ሁሉንም ነገር እኔ አመቻቻለሁ…እስክትሄድ ለአንዳንድ ነገር የሚሆን ገንዘብም እልክልሀለሁ…”…አለኝ…ሰውዬውም በጣም መልካም ሰው ስለነበር ምንም የጠረጠርኩት ነገር ስላልነበር እሺ አልኩት…በዚህ መሀል እያለን ለካ አብሮት የመጣው ሰውዬ ፎቶ አንስቶኛል…እውነት ለመናገር ፎቶ እንዴትና በምን ሁኔታ እንዳነሳኝ ዛሬም ድረስ አላውቅም…ለካ እያወራን ልጄን እንዳቀፍኩ ፎቶ አንስቶኛል…ብዙ ካወራን በኃላ…“…አይዞህ…”…ለመሆኑ ቤት ኪራይስ ትከፍላለህ…?…አለኝና ሁሉንም ነገር እንደሚያመቻች ነግሮኝ ሄደ..እንግዲህ ይሄ የሆነው ጠዋት ነው… ወደ አስር…አስራ አንድ ሰዓት አካባቢ…ስልኬ እረፍት አጣ…

ሀትሪክ፡- …ማን ደውሎ…?…

ተስፋሁን፡- …ወንድሜ ደጋግሞ ይደውላል…ሌሎች የማላውቃቸው የሀገር ቤት ስልኮችም ይደወላሉ… ወንድሜ ደጋግሞ ሲደውል…እንዴ ምን ሆኖ ነው…?…ባልተለመደ መልኩ አስሬ የሚደውለው…ይሄኔ አንድ ነገር ሆኗል…ብለው ቤተሰቦቼ ተጨንቀው ይሆናል ብዬ ስልኩን አንስቼ…ሀሎ በሠላም ነው…?… ስለው…

ሀትሪክ፡- …(ድንገት አቋረጥኩትና)…ምን አለህ…?…

ተስፋሁን፡- …“…ምን ሠላም አለ…?…ፌስ ቡክ ላይ የተለጠፈውና ሰው እየተቀባበለው ያለውን ነገር አይተኸዋል…?…”…ሲለኝ ኧረ እኔ ፌስ ቡክ የለኝም…ስልኩም የረባ ስላልሆነ ፌስ ቡክ የሚባል አይቼ አላውቅም…ግን ምን ተፈጥሮ ነው…?…ስለው…“…እንዴ ይሄን ያህል ተቸግረሃል እንዴ…?…ልጅህን ይዘህ ጎዳና ላይ ወድቀህ እስከመለመን ደርሰሃል እንዴ…?…ጎዳና ላይ ልጅህን ይዘህ መውደቅህን የሚያሳይ ፎቶ እኮ ተለቋል…”…ብሎ ድንጋጤና ሀዘን በተቀላቀለበት ስሜት ሲጠይቀኝ…በጣም ደነገጥኩ…የምሰማው ሁሉ እውነት ሣይሆን ቅዥት ሁሉ መሰለኝ…ጩህ ጩህ ሁሉ አለኝ… ትንፋሼን ብስጭቴን ዋጥ አደረኩና…ኧረ ጎዳና ላይ አልወደኩም…ከእነ ልጆቼ እቤቴ ነው ያለሁት.. ብዬ ሳልጨርስለት…ወንድሜ ከአፌ ነጠቀኝና…“…እንዴ ምን ሆነሃል…?…ድረሱለት ጎዳና ላይ ወድቋል” ብሎ ነው አኮ የፃፈው…ፋዘር (አባታችንም) ይሄን ሰምቶ በጣም ደንግጦ እስከመታመም ደርሷል…” ሲለኝ ሰማይና ምድሩ ሁሉ ዞረብኝ…ምክንያቱም ከአባቴ ጋር በጣም እንደዋወል ስለነበር በዚህ ደረጀ አልነበረም የሚያውቀኝ…ከወሬው በላይ የአባቴ በድንጋጤ መታመም ረበሸኝ…ነገሩን ማን እንዳደረገውም ገባኝኝ…በምችለው አቅም ለወንድሜ ለማስረዳት ሞክሬ ስልኩን ዘጋሁ…ግን ከዚያ በኋላ ሠላም ማግኘት አልቻልኩም…በጣም ተበሳጨሁ …እንዴት እንዲህ ያደርገኛል…?…ፌስ ቡክ ላይ ልለቀው ነው እንዴት አይለኝም…?…አልኩ…በጣም ከመበሳጨቴ የተነሣ እንባዬን ሁሉ መቆጣጠር አቅቶኝ አለቀስኩ… ከወንድሜ በኋላ የሀገር ቤት ስልክ ከወትሮው በተለየ አስሬ ይደወላል…ይደወላል ግን አላነሳም…

ሀትሪክ፡- …ማነው የሚደውለው…?…

ተስፋሁን፡- …እኔ ምን አውቃለሁ…?…ለካ ሰውዬው ከፎቶው ጋር ስልክ ቁጥሬን ሳይቀር ለጥፎታል… ስልኬን ከፌስ ቡክ ላይ አግኝተው ብዙዎች ደንግጠው እንደሚደውሉ ገባኝ…እኔ በጣም ስለተረበሽኩና ስለተጨነኩ የሚደውለውን ስልክ አንስቼ ማውራት ሁሉ ስለአቃተኝ…ባለቤቴ ነበረች እያነሳች ስታናግር የነበረው…ድሮ የሚያውቁኝ ወዳጆቼ፣ጓደኞቼ ናቸው ደንግጠው የሚደውሉት…በሁኔታው ባለቤቴም ልጆቼም ተረበሹ…ባለቤቴ ሥራዋን ትታ እኔን ማፅናናት ስራዋ ሆነ…ፌስ ቡክ ላይ የለጠፈው ካፒቴን ነቢል ቃል በገባው መሠረት ገንዘብ ቢልክልኝም ከመበሳጨቴ የተነሣ አልቀበልም አልኩ…ተቀበል ተብዬ ስለመን እምቢ አልኩ…ምክንያቱም ሳያናግረኝ ይሄን በማድረጉ ተበሳጭቼበታለሁ…

ሀትሪክ፡- …ግን እኮ ያልከው ሰውዬ በፌስ ቡክ ከለቀቀው በኋላ ነው ያ ሁሉ ርብርቦሽ የተደረገው… አንተም የሀገርህን መሬት ለመርገጥ የበቃኸው… በዚህ በኩልስ አይተኸዋል…?…

ተስፋሁን፡- …ትክክል ነህ ከተረጋጋሁ በኋላ ሳየው…ነገሩ የሆነው ለበጎ ነው ብዬ እንዳስብ አድርጎኛል… ነቢል በጣም መልካም ሰው ነው…ስላላማከረኝ ነው እንጂ ያንን የደረገው በክፋትት አይደለም…እኔ እንድረዳና ወደ ሀገሬ እንድመለስ ካለው ፍላጎት ነው…በወቅቱ በጣም ተበሳጭቼ ለሣምንታት አላናግረውም ነበር…እንዳልኩህ የላከልኝን ገንዘብ እንኳን አልቀበልም እስከማለት ሁሉ ነበር የደረስኩት…ግን አንዳንዴ ነገሮች ያለ ምክንያት አይሆኑም…ፈጣሪዬ ወደ ሀገሬ እንድመለስ ስለፈለገ ይሄንን ምከንያት አደርጎ ነው…ለበጎ ነው ብዬ ራሴን አፅናንቼያለሁ…በሰዓቱ እሱ ፌስ ቡክ ላይ በመለጠፉ ወደ ሀገር ቤት የመምጣቴን ነገር እንዲፋጠን አድርጎታል…ይሄ ነገር በፌስ ቡክ ከመለቀቁ 15 ቀን በፊት እኔን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ጥረት ሲደረግ ነበር…የፕሮፌሽናል የተጨዋቾች ማኅበር በእነ ኤፍሬም ወንድሰን በኩል ትልቅ ጥረት ሲያደርግ ነበር…ደውለው ሁሉ አነጋግረውኝ ወደ ሀገር ቤት እንድመለስ የሚቻለውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ነግረውኝ ነበር…አየር መንገድ አብረውኝ የተጫወቱት ቢኒያምና አብይ የተባሉ ጓደኞቼ “መምጣት ይፈልጋል” ብለዋቸው እንቅስቃሴ ነበር…በመሃል ይሄ የፌስ ቡክ ነገር መጣና አፋጠነው…ነገሮች ቶሎ እንዲያልቁ ትልቁ ምክንያትም ሆኗል…ለዚህም ነው… ነገሮች ለበጎ ናቸው ብዬ የተቀበልኩት…

 

ሀትሪክ፡- …ወደ ሀገር ቤት ከመምጣትህ በፊት በነበረው ጦርነት ምክንያት እጅግ ፈታኝና ዘግናኝ ጊዜያትን እንዳሳለፍክ ሰምቻለሁ እስቲ እሱን አጫውተኝ…?…

ተስፋሁን፡- …አሁን ነገሮች በአምላክ ኃይል አልፈው ሳወራቸው ፊልም የምትርክልህ ሁሉ ሊመስልህ ይችላል…ግን የሆነው ሁሉ እውነት ነው…እውነት ለመናገር ረሃቡንም መጠማቱንም ትችለዋለህ… ትልቁ ሥጋታችን የነበረው የጦፈ ጦርነት ሲካሄድበት የነበረው ቦታ ከመኖሪያ ቤታችን በ200 ሜትር ርቀት ውስጥ መሆኑ ነው…ቤታችን ውስጥ ነበርን ከማለት ጦርነት ውስጥ ነበርን ማለት ይቀላል… አንዳንዴ እንደውም ጦርነቱ ከመኖሪያ ቤታችን በ100 ሜትር ርቀት አካባቢ ሁሉ ይካሄድ ነበር… በየጊዜው ሮኬቶች ጥይቶች እንደዝናብ ይዘንቡ ስለነበር ነገሮች በጣም አስፈሪ ነበሩ…የሚያጓራው መድፍ…የሚርከፈከፈው ጥይት…የሚወነጨፈው ሮኬት በጣም ሰላምን ይነጥቅ ነበር…በተለይ የተወሰኑ ሌሊቶችን እንዴት እንዳሳለፍን ዳግም ማስታወስ አልፈልግም…በጣም አስፈሪ ሌሊቶች ነበሩ… መንግሠትም አማፂዎችም መኖሪያ ቤታችን በር ላይ ነበር ሲዋጉ ውለው ያደሩት…እነዛን ሌሊቶች መቼም አልረሳቸውም…መሬት ላይ በደረታችን ተኝተን እንቅልፍ ባይናችን ሳይዞር ነበር ሲነጋ የነበረው…

ሀትሪክ፡- …በጣም አስጨናቂነው…ጦርነቱ ከመኖሪያ ቤታችሁ በ100 እና 200 ሜትር ርቀት ውስጥ ከሆነ ለምን ከአካባቢው አልራቃችሁም…?…

ተስፋሁን፡- …ወዴት ነው የምንሄደው…?…በየትኛው ገንዘባችንስ ነው የምንሄደው…?…ሄደንስ የት እናርፋለን…?…ዘመድ፣ማረፊያ፣ገንዘብ ያላቸውማ ሁሉም ጎረቤቶቻችን ሸሽተው ሄደው ብቻችንን ነበር…የቀረነው…በቃ እግዚአብሔር ቀናችሁ ነው ካለን የሚሆነውን ከመቀበል ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም…በማለት ከጥይት እሩምታና ከሮኬት ናዳ ጋር ድብብቆሽ መጫወት በሚመስል መልኩ ነው ያሳለፍነው…

ሀትሪክ፡- …ጦርነቱ በ100 እና 200 ሜትር ርቀት ውስጥ ሆኖ ከአደጋ ማምለጥ የተዓምር ያህል ይመስለኛል…?…

ተስፋሁን፡- ከተዓምርም በላይነው…ከዚህ ሁሉ ፈተናና እሳት የወጣነው በእሱ ነው…በቃ ሌላ ምንም ልልህ አልችልም…የእግዚአብሔር ከለላና ጥበቃ ነው ያተረፈን…እምነታችን፣የልጆቻችን አምላክ ፀሎታችን አትርፎናል…እንጂ…ሮኬት ሳይወድቅብን ጥይት እንደ ዝናብ ሳይዘንብብን ቀርቶ አይደለም… እንዴ በጣም አስደንጋጭ የሆነ ነገር ምን እንደገጠመን ልንገርህ…?…

ሀትሪክ፡- …በእናትህ ንገረኝ…(ለመስማት በጣም በቸኮለ ስሜት)…?…

ተስፋሁን፡- …አንድ ቀን ጦርነቱ በጣም ተፋፍሟል…ጥይቱ፣መድፉ፣ሮኬቱ ይዘንባል…እንደተለመደው ነፍስ ውጪ…ነፍስ ግቢ ውስጥ እያለን…ሳናስበው አንድ ሮኬት ወደ መኖሪያ ቤታችን ይወነጨፍና…በራችን ላይ ይወድቃል…

ሀትሪክ፡- …(ለመስማት በጣም ከመጓጓቴ የተነሳ ከአፉ ነጠኩትና)…ከዚያስ…?…

ተስፋሁን፡- …መቼም ትረፊ ያላት ነፍስ አይደለች…የያዝናት…የተተኮሰው ሮኬት መጥቶ መጥቶ በራችን ላይ ይወድቅና መሬቱን ሰርጉዶ ይገባል…የሚገርምህ ነገር የልጆቻችን አምላክ እንደሚጠብቀን ያወቅነው የኔ ነው…ያ የተተኮሰው ሮኬት በራችን ጋር ወድቆ መሬቱን ሰርጉዶ ቢገባም ባለመፈንዳቱ ሁላችንም ተረፍን…አስበኸዋል…?….ያ ሮኬት ቢፈነዳ ኖሮስ…?…ቤታችን ውስጥ ቢወድቅስ…?…እኔም ቤተሰቦቼም ላይ ምን ሊደርስ እንደሚችል መገመት ይከብዳል…?…በጣም ዘግናኝና ከባድ ነገር ነበር…ነገር ግን የሚወደን አምላክ ቀናችሁ አይደለም ብሎ አድኖን ይሄው እኔም ለመመስከር በቅቻለሁ…የሚገርምህ ከጎረቤታችን ከአካባቢያችን ብዙዎች ሞተዋል…ግማሾች እጃቸው፣እግራቸው ተቆራርጧል…በፍንዳታው ፍንጥርጣሬ ብዙዎች ሠለባ ሆነዋል…ቤታችን በር ላይ ሰርጉዶ የገባውን ሮኬት ወታደሮች መጥተው ሲወስዱት የተመለከቱት ማመን አቅቷቸው…ከዚህ ሁሉ ጉድ የወጡት ምን ያህል በእምነታቸው ጠንካራ ቢሆኑ ነው እስከማለት ሁሉ ደርሰዋል…ይሄን ያነሳሁልህ እንደ ሰበዝ መዝዤ ነው እንጂ…በጣም ብዙ ከባድና ፊልም የሚመስሉ ነገሮች አሳልፈናል…

ሀትሪክ፡- …በየመን ብዙ ኢትዮጵያዊያን አሉ…በዚህ በጦርነቱ በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰ አደጋስ ተመልክተሃል…?…

ተስፋሁን፡- …አሁን በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት ልመጣ ስል ልቤን ያደማ…በጣም ያስለቀሰኝን አንድ መጥፎ አጋጣሚ ላጫውትህ… ልጅቷ አበሻ ናት…ከሰነዓ ከተማ ነው የመጣችው…እኛ ካለንበት 50 ሜትር ርቀት ላይ እህቷ አለች…ከሰነዓ ከተማ ነው የመጣችው ልጅ ነፍሰጡር በመሆንዋ እህቷን ልትንከባከባት፣ልታርሳት ትፈልግና…“…እኔ ጋር ነይ…”…ትላታለች…ነፍሰጡሯም የምትኖርበት ሰንዓ ከተማ ጦርነት የለም…ወደ እኛ ጋ ስትመጣ እንደ አጋጣሚ ጦርነቱ እንደ አዲስ አገረሸ… ሚሳኤሉም፣ሮኬቱም፣ጥይቱም፣የአየር ድብደባውም እንደ ጉድ ይዘንብ ነበር…ጦርነቱ በጣም በመባባሱ ነፍሰ ጡሯም እህቷም በጣም ፈርተው ሸሽተው ወደ ጓዳ ይገባሉ…የሚያሳዝነው ነገር ለነፍሰጡሯ ልጅ ሞት ተደግሶላታል…ቀኗ ተቆርጧል መሰለኝ…የተተኮሰው ሮኬት ተከትሏቸው ጓዳ ውስጥ ወደቀ… ነፍሰጡሯንም ፍንጥርጣሪው መታትና ወደቀች…ደነጋግጠው…አፋፍሰው ሆስፒታል ሲወስዷት እንዳልኩህ ቀንዋ ተቆርጧል…በፍፁም መትረፍ አልቻለችም…አረፈች…

ሀትሪክ፡- …አረፈች…?…በሆድዋ ያለው ፅንስስ…?…

ከዚያስ ምን ተፈጠረ? ሕፃኑ ተረፈ? ወይስ እንደ እናቱ አረፈ….?….ተስፋሁን ይቀጥላል…. ምላሹን ለማወቅ የሳምንት ቀጠርዎ ከእኛ ጋር ይሁን… ለመሆኑ ተስፋሁን ጋዲሳ ከነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ከሆነው የየመን ቆይታው በኋላ የአዲስ አበባን መሬት ሲረግጥ ምን ተሰማው? ለምንስ እንባውን አስቀደመ…? ይሄ ብቻ አይደለም ተስፋሁን በቀጣይ ሣምንት ስለ ልጆቹ፣ ስለ ባለቤቱ፣ ከየመን ንብረቱን ትቶ ባዶ እጁን ስለመምጣቱ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ስለ ኢትዮጵያ ቡናና፣ስለ ካሳዬ አራጌ ስለ ብሔራዊ ቡድን ቆይታው ብዙ የሚያጫውተን ስላለ የሳምንት ሰው ይበለን፡


ተስፋሁን ጋዲሳ (ኮል) ለመረዳት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 

ቀጥር – 1000378426344 


የመጨረሻውን ክፍል ለማንበብ ማስፈንጠሪያውን ይጫኑ 👇

https://www.hatricksport.net/thebiginterviewtesfahun2/

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor.
The First Color Sport Newspaper in the country.

Yishak belay

Hat-trick Weekly Sport Newspaper Founder & Managing Editor. The First Color Sport Newspaper in the country.