ቅዱስ ጊዮርጊስና ማታሲ ሊለያዩ ይሆን?

 

” እኔ ትልቅ ተጫዋች ነኝ የትም ሄጄ መጫወት እችላለው ” ፓትሪክ ማታሲ

” በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ታሪክ ውስጥ የውጭ ሀገር ተጫዋች እንደ ማታሲ የታገስነው የለም ” አቶ ዳዊት ውብሸት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ስራ አመራር ቦርድ አባል

 

በፈረሰኞቹ ቤት ያለፉትን አመታት ቁጥር አንድ ግብ ጠባቂ በመሆን ያሳለፈው ፓትሪክ ማታሲ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ከ ሸገር ደርቢው የቀይ ካርድ በኋላ የውሀ ሽታ ሆኖ ከዋናው የቡድን ስብስብ እርቆ ይገኛል ።

ከአመታት በፊት ፈረሰኞቹን መቀላቀል የቻለው የኬንያ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ በክለቡ መጉላላት እየደረሰበት እንዳለ ከ ሀትሪክ ስፖርት ጋር በነበረው ቆይታም ገልጿል በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በኩል ተጫዋቾች ላነሳው ቅሬታ የክለቡ የቦርድ አባል አቶ ዳዊት ውብሸትንም ምላሽ አካተናል።

ከ ሀትሪክ ስፖርት ፀሀፊ ቅዱስ ዮፍታሔ ጋር ቆይታን ያደረገው ፓትሪክ ማታሲ ከ ክለቡ ጋር ስላለው ወቅታዊ ጉዳዮች ሀሳቡን አጋርቶናል ።

” ሶሰት እና አራት ጉዳዮችን ማንሳትን እወዳለው ፣ በመጀመሪያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ጋር ያለኝ ግንኙነት በአሁን ሰዓት ጥሩ አይደለም ። ምክንያቱ እንደሚመስለኝ ከሸገር ደርቢው የቀይ ካርድ በኋላ ብዙ ነገሮች በ ቡድኑ ውስጥ እኔን በተመለከተ እንደ ከዚህ ቀደሙ አይደሉም ።

ቡድኑ ከጅማ የሊጉ ጨዋታዎች ቆይታ ሲመለስ ደብረዘይት ወደ ሚገኘው ካምፕ ካቀና በኋላ ወደ ባህር ዳር ከመጓዛችን አስቀድሞ ለክለቡ ይፋዊ አመራሮች ደብዳቤ አስገብቼ ነበር ፣ ባስገባሁት ደብዳቤም ኮንትራቴን በማቋረጥ ከ ክለቡ ጋር መለያየትን እንደምፈልግ አሳውቄያቸዋለሁ ። ምክንያቱም ከ ክለቡ ጋር ያለኝ ግንኙነት ጥሩ ካለመሆኑም ባሸገር እንደ ክለቡ አንድ የቡድን አባል እየታየሁም አልገኝም ነበር ።አሰልጣኙም ቢሆን እኔን ለማሰለፍ ፍላጎት አልነበረውም ፣ ለዚህም ኮንትራቴን ለማቋረጥ መገደዴን አሳውቄያቸዋለሁ ።

ለክለቡ የመልቀቂያ ደብዳቤ ካስገባሁ በኋላ ክለቡ ሊለቀኝ ፈቃደኛ አመሆናቸውን እና ኮንትራቴን መሰረዝ እንደማይፈልጉ ገልፀውልኛል ። ከዚህ በተቃራኒው ደብዳቤ ሲፅፉልኝ ለሁለት ሳምንታት ወደ ሀገሬ እንድመለስ እና አጋጥሞኝ የነበረውን የቤተሰብ ችግር እንድፈታ ፈቃድ ሰጥተውኝ ነበር ። ይህም ሊሆን የቻለው የእኔን ስልክ ሊያነሱም ሆነ ሊያናግሩኝ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ ጠበቃዬ የላከላቸውን መልዕክት ተከትሎ ነበር ። ሆኖም ግን ለአንድ ሳምንታት ብቻ ( ሰኞ እለት ወደ ኬንያ ሄጄ በሳምንቱ ማክሰኞ ) ብቻ ቆይቼ ተመልሰሻለው ።

ከ ኬንያ እንደተመለስኩኝ ለ ክለቡ ከፍተኛ አመራር በተደጋጋሚ ስደውል መልእክቶችን ብልክም እነርሱም ሆኑ የቡድን መሪዎቹ በተመሳሳይ መልእክቶቼን እና የስልክ ጥሪዎቼን አይመልሱም ነበር ።

በመጨረሻም ከዚህ ሁሉ ጊዜያት በኋላ ማግኘት የቻልኩት አቶ ሰለሞንን ሲሆን ከቀናት በፊት ቡድኑ አርብ ከመጫወት በፊት ዕሮብ ጠዋት ላይ ነበር እናም አዲስ አበባ ሆኜ ቡድኑን እንድጠባበቅ ተገልፆልኛል ።

በቤተሰብ ምክንያት ወደ ኬንያ ባቀናሁበት ሰዓት ቡድኑ ሌላ ግብ ጠባቂ ለሙከራ ለማምጣት ወሰነ ፣ ግብ ጠባቂው ለሙከራ እንደመጣ ነግረውኛል ። የእኔ ጥያቄ ግን የነበረው ከ ዩጋንዳ ሌላ ግብ ጠባቂ ከመጣ የእኔ ሚና በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ምንድነው የሚል ነበር ። ይሄም የሚያሳየው እነርሱ የእኔን ግልጋሎት እንደማይፈልጉ እና መጠናቀቁን ነው ። ለክለቡ ከፍተኛ ሀላፊዎችም የነገርኳቸው ነገር መልቀቂያን ሰጥተው እኔ ሄጄ አዲሱን ለሙከራ የመጣውን ግብ ጠባቂ ማስፈርም እንደሚችሉ ነው ። ነገሮችን ወደ ህግ ቦታ ወደ ጠበቃዬ ፣ ካፍ እና ፊፋ መውሰድን አልፈልግም ፣ የእኔን አገልግሎት ስላልፈለጉ ሌላ ግብ ጠባቂ አምጠተዋል ፣ የምፈልገው እና የነገርኳቸውም እንዲለቁኝ ብቻ ነው ።

አሁንም የምገኘው በአዲስ አበባ በሚገኘው የክለቡ መኖሪያ ቤት ነው ፣ አሁን እየጠበኩኝ ያለው የኬንያ ብሔራዊ ቡድን ነው ፣ የብሔራዊ ቡድን ጥሪ ቀርቦልኛል ከፊታችን ትልቅ ጨዋታ ይጠብቀናል ። ከግብፅ ብሔራዊ ቡድን ጋር በ ኬንያ ከባድ ጨዋታ አለብን ፣ ከዚህ ጨዋታ በመቀጠል ደግሞ ከ ቶጎ ብሄራዊ ቡድን ጋር እንጫወታለን ። ለእኔ ይሄ ትልቅ አጋጣሚ ነው ፣ በብሔራዊ ቡድን ተሰልፌ በመጫወት ራሴን የማሳይበት ትልቅ የውድድር መድረክ ነው ።

አዲስ አበባ የምጠበቀው የክለቡን ምላሽ ብቻ ነው ያናገረኝም አካል የለም ። ከ አቶ ዳዊት ውብሸት ከቀናት በፊት መልዕክት የተላከለኝ ሲሆን ኮንትራቴ ያላለቀ መሆኑን የሚገለፅ ፅሁፍ ልከውልኛል ። የእኔ ትልቁ ጥያቄ ግን ለምን የፅሁፍ መልዕክት ብቻ እንደሚልኩልኝ ነው ፣ ከዚህም ባለፈ ደውለው በአካል ሊያናግሩኝም አይፈልጉም ። ሁሌም የሚያደርጉት የፁሁፍ መልዕክት ብቻ መላክ ነው ፣ ይህ ደግሞ ጥሩ አይደለም ። እኔ የምፈልገው እነሱ ግልፅ እንዲሆኑ ነው ፣ እንለቅሀለንም አንለቅህም በግልፅ እያሉኝ አይገኙም ፣ እኔ ትልቅ ተጫዋች ነኝ የትም ሄጄ መጫወት እችላለው ።

ለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች መናገር የምፈልገው ነገር ክለቡ ምንም ያለኝ ነገር የለም ፣ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ በመመለስ ቡድኑን እንዳገለግል ይፈልጋሉ ። ሆኖም ግን አንድም የክለቡ ይፋዊ አመራር ደውሎ ቁጭ ብለን እናውራ ብሎ ወደ ቢሮ የጠራኝ አካል የለም ።

እኔ አሁንም ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ልዩ ፍቅር አለኝ ደጋፊውም ከ እኔ ጎን ነበር ፣ እነዚህ ችግሮች ቡድኑ ወደ ድሬደዋ ከማቅናቱ በፊት መፈታት አለባቸው ። በ ቡድኑ ውስጥ አሁንም የምካተት ከሆነ ቡድኑ መድረስ ያለበት ደረጃ ለማድረስ ዝግጁ ነኝ ካልሆነ ግን ሊለቁኝ የሚያስቡ ከሆነ አሁኑኑ ሊለቁኝ ይገባል ሲል ፓትሪክ ማታሲ ስላለበት ወቅታዊ ሁኔታ ሀሳቡን አካፍሎናል ።

” በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ታሪክ ውስጥ የውጭ ሀገር ተጫዋች እንደ ማታሲ የታገስነው የለም ”

አቶ ዳዊት ውብሸት የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ስራ አመራር ቦርድ አባል

ተጫዋቹ የአቋም መውረድ ችግር አለበት ይህም በግልፅ በቴሌቪዥን የሚታይ ነው ፣ መልቀቂያ አንድ ተጫዋች ስላስገባ ብቻ ዝም ብለን አንለቅም ። ቅዱስ ጊዮርጊስ የክለቡን መመሪያ ተከትሎ በ ቦርድ ስብስባ ላይ የተለያዩ ውሳኔዎችን የሚያስተላልፍ ይሆናል ።

ከሳምንታት በፊት የወላጅ እናቱን ህልፈተ ህይወት ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰብአዊነት ይቀድማል በሚል ክለቡ ሙሉ የአየር ቲኬት ወጪውን ሸፍኖ ወደ ሀገሩ እንዲሄድ አድርጓል ። በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ታሪክ ውስጥ እንደ ማታሲ የታግሰነው የውጭ ሀገር ተጫዋች የለም ፣ ከዚህ ቀደመም በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሀገሩ ለመሄድ ቤተሰባዊ ምክንያቶችን ሲያስቀምጥ ቆይቷል ። ማታሲ ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ ቡድኑም ሆነ የክለቡ አመራሮች ባህር ዳር ላይ ስለነበሩ ተቀምጠን ለመነጋገር አልተቻለም ። ማታሲን በምንችለው መንገድ ደግፈናል ማንም ሰው እኔንም ጨምሮ ግን ከጊዮርጊስ በታች ነው ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ አሁን ላይ ያሉበትን ክፍተቶች ለመሙላት እና በቀጣይ ራሱን አጠናክሮ ለመቅረብ ክፍተት የሚታይባቸውን ቦታዎች ለመሙላት እየሰራ ይገኛል ። በግብ ጠባቂ ቦታ ላይ ብቻ ሳይሆን በተለያየቱ ቦታዎች ያለቡንን ክፍተቶች ለመሙላት እየሰራን እንገኛለን ። ለምሳሌ በግራ ተመላላሽ ቦታ ላይ ዩጋንዳዊ ተጫዋች አምጥተን ሙከራ ላይ ነበር ፣ የሙከራ ጊዜውን ማለፈ ስላልቻለ ወደ ሀገሩ ሸንተነዋል ።

በአካል አናናግረም ያለው አካል የለም እኔ እና አቶ አብነት ገብረ መስቀል አብረን ሆነን ማስተካከል ስለሚገቡት ነገሮች ተመካክረናል ከዚህ በተጨማሪም ከ አንዴም ሶስቴ ከሌሎች የክለቡ አካላት ጋር ተቀምጠን ለመነጋገር ችለናል ።

የክለቡ ቦርድ በመጪው ቀናት አጠቃላይ የቦርድ ስብሰባ እና ግምገማ ስለሚያካሂድ የማታሲ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የፀባይ ግድፈት ያሳዩ ተጫዋቾችን የምንመረምርበት እና ውሳኔዎችን የምናስተላልፍበት ጊዜያት ይሆናል ።

ከባህር ዳር ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ከ ቡድን ተጫዋቾቹ ጋር ምሽቱን ተገናኝተን ስላሉት ነገሮች ተነጋግረን አበረታተን ሸኝተናል ። ከፊታችን ሶስት ሳምንት የእረፍት ጊዜ መኖሩ የተለያዩ ችግሮቻችንን እንድንፈትሽ ይረዳናል ።

Hatricksport website Editor

Twitter

kidus Yoftahe

Hatricksport website Editor