

በይስሐቅ በላይ
ሀትሪክ፡- እስቲ እንደማሟቂያ እንዲረዳ
አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ… ከድሮ ጀምሮ ሣውቅህ
አሁንም ሣይህ ሁሌም የምትለብሰው ጨርቅ
ሱሪ.. የምትጫማው ቆዳ ጫማ ነው፤ እንደ
ስፖርተኛ ጅንስና ስኔከር ስታደርግ አይቼህ
አላውቅም…. የተለየ ምክንያት አለህ…?
ሙሉአለም፡- (…. በጣም ሳቅ)…
በጣም ልብ ብለህ አይተኸኛል፤ እኔ ጅንስና
ስኔከር ጫማ ማድረግ አይመቸኝም፤ ሁሌም
የምለብሰው ወይም ምርጫዬ ካኪ ሱሪ በቆዳ
ጫማ ማድረግ ነው፤ በጣም አስገዳጅ ነገር
ካልሆነ በስተቀር ጅንስና ስኔከር በፍፁም
እላደርግም፡፡ ጅንስና ስኔከር ማድረግ ብዙም
ምቾት አይሰጠኝም…
ሀትሪክ፡- ሙሌ ከሌሎች ጥያቄዎች በፊት
ብዙዎችን ወደ አነጋገረው የአንተ ሁለት አመት
ኳስ አቁመህ ዳግም መመለስህን በተመለከተ
በመጠየቅ ነው ቆይታችንን መጀመር
የምፈልገው፤ 21 አመት ሙሉ ተጫውተሃል፤
በዚያ ላይ ደግሞ ሁለት አመት ኳስ አቁመህ
ተመልሰህ በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ መጫወትህ
ብዙዎችን አነጋግሯል…በዚህ ዙሪያ ምን
ትላለህ ?
ሙሉአለም፡- ኳስ አላቆምኩም፤ኳስም
አይቆምም፤ ከአሁን በኋላም
አላቆምም።እንዳልከው ሁለት አመት በክለብ
እግር ኳስ ስላልታየሁ ብዙዎች ኳስ አቁሟል
ወደሚል ድምዳሜ ሄደዋል፡፡ ምናልባት ክለብ
ላትገባ ትችላለህ ክለብ ስላልገባህ ግን ኳስ
አቁሟል ማለት አይቻልም፡፡ እኔም ባለፈው
አመት ሐዋሳ ከመግባቴ በፊት ሁለት አመት
በክለብ ፉትቦል አልታየሁም፤ ክለብ ባልገባም
ግን ከክለብ የማይተናነስ ፉትቦል እየተጫወትኩ
ነው ያሳለፍኩት፡፡ እኔ ሁሌም ግራ የሚገባኝ
የእኔ ረዥም አመት መጫወት ለምን ብዙዎችን
እንዳስገረመ አላውቅም፤ በውጪ እኮ እነ ጊግስ
እስከ 42 አመታቸው በትልቅ ክለብ ደረጃ
ተጫውተዋል፤ ቡፎንን ብትወስድ አሁንም
በዚህ እድሜው የአለማችን ኃያል ክለብ
ወደሆነው የፈረንሣዩ ፒ.ኤስ.ዤ የተዛወረው፤
በውጪ የእድሜ ቁጥር ረዥም አመት
መጫወቱ ሣይሆን ወቅታዊ ብቃቱ ችሎታው
ስለሚታይ በምሣሌነት ይነሣሉ፤ አንድ ትልቅ
ነገርም ይመራላቸዋል። በእኛ ሀገር ግን አቅም
አለው የለውም ከሚለው ይልቅ “ይሄ ልጅ
አይበቃውም እንዴ?” ነው የምትባለው፡፡
ሀትሪክ፡- ሁለት አመት ኳስ አቁመህ
ሐዋሳ መግባትህ ከየአቅጣጫው የተለያዩ
ትችቶች እንዲሰነዘሩ አድርጎ ነበር ይሄንን
እንዴት ነው የምታስታውሰው…?
ሙሉአለም፡- … ሐዋሳ ስገባ ብዙ ቻሌንጆች
(ፈተናዎች) ነበሩ፤ ከሜዳ ላይ ጨዋታው
ይልቅ የከበደኝም የተጨነኩትም በዚህ ነበር፡
፡ ግን ጭንቀቴ ለእኔ ሣይሆን ይሄንን ሁሉ
ጫና ተቋቁሞ፣ የተጫወትኩበትን አመት ቁጥር
ሣይሆን ወቅታዊ አቅሜን አይቶ ኃላፊነቱን ደፍሮ
ላስገባኝ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ነበር፡፡ ውበቱ
ላይ በጣም ጫናዎች ነበሩ፤“እንዴት ሁለት
አመት ኳስ ያቆመን ተጨዋች ታስገባለህ? ሰው
አጥተህ ነው ወይ?” የሚሉና ሌሎች የጠነከሩ
ተቋውሞዎች ቀርበውበት በጣም አዝኜ ነበር፤
ግን ኃላፊነቱን የወሰደው አንድና አንድ እሱ
ብቻ ነው፡፡ እኔም በወቅቱ ማሳየትና ማስተማር
አለብኝ ብዬ የሆቴል፣የምግቤን ወጪ ራሴው
ሸፍኜ ነው የታየሁት፤ይሄን ሁሉ መስዋዕትነት
የምከፍለው በእግር ኳስ ገንዘብ ለመሰብሰብ
ብዬ ሳይሆን በእግር ኳስ ለመርካት ነው፤ ለዚህ
ማሳየው ደግሞ ሐዋሳዎች ሲሰጡኝ የነበረው
ገንዘብ ነው…
ሀትሪክ፡-…ስንት ይከፍሉህ ነበር…?
ሙሉአለም፡-…እንዳልኩህ ነው አሁንም
እይተጫወትኩ ያለሁት ገንዘብን ለማሳደድ
አይደለም ፤ እግር ኳስ መጫወትን ስለምወድ
ነው፡፡ የሆቴል የምግብ ወጪዬን ራሴ ሽፍኜ
ካዩኝ በኋላ አቋማቸውን ቀይረው “በቃ መጫወት
ከፈለገ በዚህ ደሞዝ” ብለው የወሰኑት እውነቱን
ልንገርህ የተጫወትኩት ከግማሽ በታሽ በሆነ
ገንዘብ ነው፡፡ ከፍተኛ ደሞዝ የሚያገኘው
ተጨዋች ቤንችና ኦቨር ቤንች ላይ ተቀምጦ
እኔ መጫወትን ስለምወድ ብቻ ከግማሽ በታች
እየተጫወትኩ ነው አመቱን የጨረስኩት፡፡
ሀትሪክ፡-የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች
የነበረው ኤሪክ ሙራንዳና አንተ ከ10 አመት
በኋላ በትልቅ ክለብ ደረጃና ሊግ መጫወታችሁ
ፕሪሚየር ሊጉ ለመዳከሙና ደረጃውን ማሳያ
ነው በማለት በሊጉ መጫወታችሁን የሚወቅሱ
አሉ… ወቀሳውን ትቀበላለህ… ?
ሙሉአለም፡- የፕሪሚየር ሊጉ መዳከም
ከሆነ እኔ ከዛሬ ሁለትና ሶስት አመት በፊት
እኮ ሊጉ ውስጥ አልነበርኩም፤በ2008
እና 2009 እኮ እኔ በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ
አልተጫወትኩም፤ታዲያ ያኔ ሊጉ እንዴት
ነበር? የሊጉ ደረጃ ጣሪያ የነካ ነበር? የእኔ የአንድ
ተጨዋች ወይም የሁለት ሰው ሊጉ ውስጥ
መግባት ብቻውን እንዴት ነው ለሊጉ መውረድ
እንደ አንድ ማሳያ ተደርጎ የሚወሰደው? እኔስ
ካሉት ተጨዋቾች በጣም የወረደ ብቃት ካለኝ
እንዴት ያንን ሁሉ ደቂቃ እጫወታለሁ?
እንዴትስ ቻሌንጅ አደርጋቸዋለሁ? ይሄን
አይነቱ ሃሳብ አይሰማማኝም፤ ምናልባት
እንደዚህ አይነት አስተያየት የሚሰጠው ለምን
አቅም ኖሮአቸው ተጫወቱ? ካልሆነ በስቀር፡፡
ሀትሪክ፡- የእናንተ ከ10 አመት በኋላ
እንዲሁም ሁለት አመት አቁመህ በፕሪሚየር
ሊግ ደረጃ መጫወትህ የወጣት ተጨዋቾችን
የመታየት እድል እንደመዝጋት አድርገው
የሚያስቡ አሉ… ለአነሱስ ምን መልስ አለህ…
?
ሙሉአለም፡-እንደዚህ ከመሰነጣጠቅ ለምን
ጥረቶችን የማበረታታትና የማድነቅ ባህል
የማይኖረን?፤ ደግሞስ ለምን አሁን በጥያቄህ
ባነሳኸው ደረጃ ብቻ ይታሰባል?ለምን ልምድን
ችሎታን እውቀትን ማካፈል ተደርጎ ማሰብ
አልተፈለገም? ተነሳሽነትን ከመፈጠር ጋርስ
ለምን ተያይዞ አልተነሳም? የሙሉአለም መግባት
ብቻውን የወጣት ተጨዋችትነት እድልን
አይዘጋም፤ሊጉን ከፍም ዝቅም እያደረጋውም፤
ለወጣት ተጨዋቾች የማስተላልፈውን መልካም
ነገርም ማየት ያስፈልጋል፡፡
ሀትሪክ፡-አሁን ከሀዋሳ ከተማ ጋር
ተለያይተተሃል፤ ከዚህ በኋላስ ሙአሉአለምን
በፕሪሚየር ሊጉ ሲጫወት እናየዋለን…?
ሙሉአለም፡- …የሚደፍር አሰልጣኝ
ካለ…? …እኔ የመጫወት ችግሩ የለብኝም፤
አሁንም በፕሪሚየር ሊጉ የሚያጫወት ብቃቱ
አለኝ፤ ነገር ግን ደፋር አሰልጣኝ ካለ ነው
ይሄ የሚሆነው፡፡ አሰልጣኞች የችሎታዬን
ነገር ሳይሆን የወሬውን ነገር ስለሚፈሩ እድሉ
ሊጠብ ይችል ይሆናል እንጂ እኔ ለመጫወት
አቅሙ አለኝ፡፡ የሚገርምህ ነገር በፕሪሚየር
ሊግ ደረጃ ላለ ክለብ ለመጫወት ስለፈለኩ
እንጂ በብሔራዊ ሊግ ደረጃ እንድጫወትላቸው
የጠየቁኝ ክለቦች አሉ፤ ግን እንዳልኩህ ፍላጎቴ
ፕሪሚየር ሊግ ለመጫወት ነው…፡፡

ሀትሪክ፡-…እንዴ…! ሙሉአለም….
ለሌላ… 22ኛ አመት…? ያውም… በፕሪሚየር
ሊግ ደረጃ… ልትጫወት…?
ሙሉአለም፡-… ምን ማለትህ… ነው…?
…አምናም ተጫውቻለሁ… ያውም… ሁለት
አመት… በክለብ ደረጃ መጫወት አቁሜ…፤
አምና ተጫውቼ… ዘንድሮ… መጫወት
አይከብደኝም…፡፡
ሀትሪክ፡-…ታዲያ… በዚህ አይነት…
አንተና… ኳስ የምትለያዩት… መቼ ነው…?
…መቼስ.. ጫማ …ትሰቅላለህ..?
ሙሉአለም፡- …ለምን እሰቅላለሁ?… ሰው
ስላለ ሣይሆን… ውስጤ… ኳስ “በቃህ”…
ብሎ… ሲያግደኝ ነው… ኳስ የማቆመው…
አቅምህ እኮ… ዝም አይልህም ሲበቃህ “በቃህ”
ብሎ ይወስንብሃል፤ ለጊዜው…ግን.. ውስጤ..
ተጫውት ነው የሚለኝ…” እስከአሁንም
እየተጫወትኩ ያለሁት ሰው የሚለውን ሣይሆን
ውስጤ የሚነግረኝን ስላዳመጥኩ ነው፤ …
መቼ… ጫማ… ትሰቅላለህ…? ላልከው…
እስከ አሁን… ውስጤ… አልነገረኝም… መቼ
እንደማቆምም… እስከአሁኗ ደቂቃ ድረስ…
አላውቀውም…፡፡
ሀትሪክ፡- …እሺ… ከዚህ በኋላስ… እስከ
ስንት አመት… የመጫወት…አቅሙ አለህ፤..?
ሙሉአለም፡- …ከዚህ በኋላ…አቋሜ
ሳይወርድ… በጥሩ ብቃት… ሁለት አመት…
እጫወታለሁ… ብዬ አስባለሁ…፤
ሀትሪክ፡-…እስከ… 2013…?
ሙሉአለም፡- …ምነው ተገረምክ…?…
በጣም ረዘመብህ?…አዎን… እስከ 2013…
ያውም… በፕሪሚየር ሊግ…ደረጃ መጫወት
እፈልጋለሁ…፡፡
ሀትሪክ፡- …የሚገርም መልስ ነው…!…
ረጅም አመት በመጫወት ትልቅ ልምድ
አካብተሃል፤ ከዚህ አንፃር… ወደ ስልጠናው
ዓለም… የመግባት ህልምስ የለህም…?
ሙሉአለም፡-…ሁለት ነገር ነው
የማስበው፤ ወደ አሰልጣኝነት ለመምጣት
አንዳንዴ ከተጫወትክበት ካደረከው አንፃር
ኳሱን መረዳት እንደምትችል ሲገመት ወደ
ስልጠናው ብመጣ ምን አይነት ቡድን ልሰራ
እንደምችል የሚገመት ነገር ይኖራል።ሌላው
በእኛ ሀገር በአንዴ ዋና አሰልጣኝ ሆኖ መስራት
ስለማይቻል ምክትል አሰልጣኝ ሆኜ እንዴት
መስራት እንዳለብኝ ሳስብ መልስ አጣለሁ፡
፡ በተጫወትኩባቸው አመታት ለምክትል
አሰልጣኝ የሚሰጠው ቦታ በጣም አናሳ ነው፤
ኮን ከመደርደር ፒልስ (የልምምድ ቲ ሸርት)
ከማደል የዘለለ ሃሳብ እንዲያካፍል እድል
ሲሰጠው አታይም፤ ከዚህ ወጣ ባለ መንገድ
ከማን ጋር ተግባብቼ እሠራለሁ የሚለው
ያሳስበኛል፡፡
ሀትሪክ፡- እስቲ ሙሌ አሁን ደግሞ ወደ
ሌሎች ጥያቄዎች እናምራ?ሙሌ.. አንተም..
ኳስ ሜዳ.. ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ካበረከታቻቸው
ተጫዋቾች አንዱ ነህ.. ልበል…?
ሙሉአለም፡- አልተሳሳትክም…! ተወልጄ
ያደኩት… አዲስ አበባ… አውቶብስ ተራ… ኳስ
ሜዳ… የሚባለው አካባቢ ነው…፡፡
ሀትሪክ፡- ኳስ ሜዳ የሚባለው አካባቢ
ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ ውለታን የዋለ
ሜዳ ነው ብል ተሳሳተሃል የሚለኝ ሰው ይኖርይሆን… ?
ሙሉአለም፡- በፍፁም…! ምክንያቱም
ትክክል ነዋ…! እውነት ለመናገር ኳስ ሜዳ
በክለብም በሀገር ደረጃም ትልቅ አስተዋፅኦ
ያደረጉ ተጨዋቾችን ያፈራ ሜዳ ነው፤ ቀደም
ባለው አመት በክለብም በብሔራዊ ቡድንም
ትልቅ ስምና ታሪክ ያላቸው እና አቦነህ፣
ሠለሞን (ቸርኬ) በኋላም እነ ኃይሌ ኳሴ፣ የላ
ኳሴ፣ ጌቱ ከበደ በኋላ ደግሞ እኔን ጨምሮ
እነ ብርሃኑ (ፋዲጋ) ቢኒያም (ግስላ)ንና
ሌሎች ያልጠቀስኳቸውን በርካታ ተጨዋቾችን
ለክለብም ለብሔራዊ ቡድንም ያፈራ ባለውለተኛ
ሜዳ ነው፡፡ አሁን አሁን ግን በተለይ ከእኛ
በኋላ ተጫዋቾችን በማፍራት የሚታወቀው
የኳስ ሜዳ ማህፀን እየደረቀ የመጣ ይመስላል፤
ብዙ ተጫዋቾችን ማየት አልተቻለም፡፡ !
ሀትሪክ፡- ኳስ ሜዳ ሲነሣ የበርካታ
ባለውለተኞች ስም አብሮ ቢነሣም የኃይሌ
ኳሴና የቤተሰቡ ስም ግን ከፍ ብሎ የሚሰማ
ስም ይመስለኛል፤በርካታ ተጨዋቾች ከኳስ
ሜዳ እንዲወጡ የእነ ኃይሌ ኳሴ ተፅዕኖን
በምክንያትነት ማንሣት ይቻላል… ?
ሙሉአለም፡-ኃይለ ኳሴና ቤተሰቡ ከኳስ
ውጪ ህይወት ያላቸው ናቸው ማለት
ይከብደኛል፤ የቤተሰቡ በተለይ የኃይሌ
ኳሴ ተፅዕኖ የእነሱን ፈለግ ተከትለን ብቅ
ያልነው ተጨዋቾት ላይ ከፍተኛ ነበር ማለት
እችላለሁ። ኃይሌ ኳሴ ኳስ የሚችልን ሰው
በፍቅር የሚወድ ሰው ነው፤ ብዙ ልጆች
ከዛ አካባቢ ተጫዋች ሆነው እንዲወጡ ብዙ
ጥረት የሚያደርግ ሰውም ነው። ብዙውን ጊዜ
በክረምት እረፍት በሚሆኑበት ሰዓት አሸዋ
ሜዳ እየመጡ ይጫወቱ ነበር፤ እነ አሰግድ፣
ሙሉጌታ ከበደን የመሳሰሉ ተጨዋቾች ይመጡ
ስለነበር በዚህ መሀል አንዳንድ ኳስ የሚችሉ
የሠፈር ልጆችን እየቀላቀሉ ያጫውቱ ነበር፡
፡ በዚህም በርካታ ተጨዋቾች እነሱን እያዩ
እንዲያድጉ ድጋፍ በማድረግ ቀላል የማይባል
ተፅዕኖ አሳድረውብናል፡፡
ሀትሪክ፡- በአንተ ችሎታ በጣም ከተገረመና
ትልቅ ደረጃ እንደምትደርስ ከተነበዩ ጊዮርጊስ
እንድትገባም ድጋፍ ካደረጉ ሰዎች አንዱ ኃይሌ
ኳሴ እንደሆነ ሰምቻለሁ እውነት ነው… ?
ሙሉአለም፡- በጣም የሚገርምህ ኃይሌ
ኳሴ ብዙም ደጋግሞ ሣያየኝ ነው ከሀገር
የወጣው፤ አንድ ጊዜ ግን ጫካ ሜዳ ላይ አንድ
ውድድር ተዘጋጅቶ ኃይሌ ኳሴ የክብር እንግዳ
ሆኖ መጥቶ በዛ ውድድር ላይ ስጫወት አይቶኝ
በጣም እንደተገረመ በአንደበቱ ነግሮኛል፡፡
በጣም የሚገርምህ በክብር እንግድነት መጥቶ
በችሎታዬ በጣም ተደስቶ ከሸለመኝ በኋላ ማታ
ላይ አስጠርቶኝ “አንተ በኳስ በጣም ትልቅ ቦታ
መድረስ የሚያስችል አቅም አለህ፤ ገና ትንሽና
ልጅ ብትሆንም ጊዮርጊስ ወይም ሌላ ቡድን
ውስጥ ገብተህ መጫወት የምትችልበት አቅም
አለህ” ብሎ አበረታትቶኝ መክሮኝ ነበር። ኃይሌ
በዚህ ሳያበቃ ለአሰልጣኘ አስራት ኃይሌም” ይሄ
ልጅ ጊዮርጊስን የሚመጥን ለጊዮርጊስ መጫወት
የሚያስችል አቅም አለው” ብሎ ለአስራት ሁሉ
ሣይቀር ነግሮት ነበር፤ ኃይሌ እንደገመተው
ወይም እንደተነበየው የጊዮርጊስን ማልያ ለብሼ
መጫወት ቻልኩ፡፡
ሀትሪክ፡- … ኃይሌ… በልጅነትህ ፤..
እንደገመተው እንደተነበየው የጊዮርጊስን ማልያ
ለብሰህ ሲያይ ምን አለ…?
ሙሉአለም፡- እንደ አጋጣሚ ኃይሌ ይሄን
ሳያይ ነወ ወደ አሜሪካ የሄደው፤ስጫወት
አላየኝም በአካልም አልተገናኘንም፡፡ አኔ ግን
አሜሪካ ስሄድ አትላንታ ሄጄ አግኝቼዋለሁ፤
በጣም ነው የተደሰተው፡፡ ከሀገር ከወጣ
በኋላም ራሱ “አንድ ትንሽ ልጅ አለ፤ ትልቅ
ደረጃ ላይ መድረስ የሚችል” እያለ እዛም ሆኖ
ይናገር ነበር፤ በወቅቱ እንደውም ምን እንዳለኘ
ታውቃለህ…?
ሀትሪክ፡-…ምን… አለህ..?…
ሙሉአለም፡- “አንተ ከመምጣትህ በፊት
ልክ እንደ አንተ ከኳስ ሜዳ ከአውቶብስ ተራ
አካባቢ የሚመጣ አንድ ኳስ በጣም የሚችል
ልጅ ነበር…አሁን የት እንዳለ አላውቅም፤
በጣም ኳስ የሚችል ልጅ ነበር፡፡ ከእሱ በኋላ
ኳስ ሜዳ ውስጥ ኳስ በጣም የሚችል ሁለተኛ
ልጅ ያየሁት አንተን ነው ይለኝ ነበር፡፡” ኃይሌ
በዚህ ደረጃ ያደነቀው ማን ይሆን? ብለን
ስናጣራ ልጁ ማን ሆኖ ቢገኝ ጥሩ ነው…?
ሀትሪክ፡- …ማን ሆኖ ተገኘ…?. አንተው
ንገረኝ እንጂ?
ሙሉአለም፡-ኃይሌ በዚያ ደረጃ ያደነቀውና
ኳስ ሜዳ ውስጥ ኳስ የሚችል ተገኘ ብሎ
ያሞካሸው ልጅ ማንነት ሲጣራ ማን ሆኖ ቢገኝ
ጥሩ ነው ወንድሜ ሆኖ አልተገኘም መሰለህ…!
(ሣቅ)…
ሀትሪክ፡-…እንዴ…! ወንድምህ… በዚህ
ደረጃ… የሚሞካሽ… ኳስ ተጨዋች ነበር…
እንዴ…? …እስቲ …ስለ ቤተሰባችሁም በዚህ
አጋጣሚ ንገረኝ…?
ሙሉዓለም ፡-የቤተሰባችን ብዛት 8 ነው፤
አምስት እህቶችና ሶስት ወንድሞች አሉኝ።
ከቤተሰባችን ከመጨረሻ ሁለተኛው ልጅ
እኔ ነኝ፤ የመጨረሻዋን እህቴን ብቻ ነው
የምበልጠው፡፡ ሁለቱ ወንድሞቼ ታላላቆቼ
ብቻ ሣይሆኑ አልገፉበትም እንጂ ኳስ በጣም
የሚችሉ ናቸው፤ በተለይ ጠለለ በሚለው
የሠፈር ስሙ የሚታወቀው መኮንን ረጋሳ
የሚባለው ወንድሜ በጣም ጎበዝ ተጨዋች ነው፡
፡ እኔ ኳስ ተጫዋች ለመሆን ስሞክር የእነዚህን
የሁለቱን ወንድሞቼን ችሎታ ያዩ ምን
እንደሚሉኝ ታውቃለህ…?
ሀትሪክ፡-… ምን.. ይሉሃል…? ..
ሙሉአለም፡- “አንተ በወንድሞችህ
አይን ስትታይ ኳስ አትችልም፤
እንኳን አንተ እነዛን የመሰሉ ምርጥ
ችሎታ ያላቸው ወንድሞችህም በኳስ
የትም አልደረሱም፤ አንተም የትም
ስለማትደርስ ኳሱን አቁመህ አርፈህ
ብትማር ይሻልሃል ይሉኝ ነበር፡፡”…
ሀትሪክ፡-…በዚህ ደረጃ…
የሚደነቁ… የሚወራላቸው…
ተጨዋቾች ከሆኑ… ከአንተ ከበለጡ…
እንዴት ብዙ ርቀት ሳይጓዙ ቀሩ… ?
ሙሉአለም፡-ኳስ እንደምታውቀው
ችሎታ ብቻ ሣይሆን የእድል ጉዳይም
ነው፤ ብዙዎች በኳስ ትልቅ ደረጃ
ይደርሳሉ ብለው የጠበቁት እኔን ሣይሆን
እነሱን ነው፤ እንዳልኩህ ገበያና ገዢ
ባለመገናኘታቸው እንደተገመቱትና
እንደታሰበው ብዙ ርቀት አልተጓዙም።
አንደኛው እንደ ዕድል ሆኖ በኳሱ
ባይሳካለትም በትምህርቱ ገፍቶ የተሻለ
ቦታ ላይ ሲደርስ እንደኛው ግን
በትምህርቱም በኳሱም የተፈለገው
ደረጃ ላይ ሣይደርስ ቀርቷል፡፡ ከሁሉም
ግን በጣም የሚያሳዝነው ጠለለ ረጋሳ
ወይም በዋናው ስሙ መኮንን ረጋሳ
ብዙዎች የት ይደርሳል ብለውት ብዙ
ርቀት አለመጓዙ ነው፤ እሱን ያዩ
በሙሉ “እሱ በታየበት አንተ ኳስ
አትችልም” ነበር የሚሉኝ፤ ሁለቱም
ብዙ ተጠብቀው ሳይሳካላቸው መንገድ
ላይ ቢቀሩም እኔ የእነሱንም ሰብስቤ
ነው መሠል በኢትዮጵያ እግር ኳስ
ስማቸው ከፍ ብሎ ከሚነሱ ተጨዋቾች
እንዱ ሆኛለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-ቅዱስ ጊዮርጊስ
ከመግባትህ በፊት ቡና ለመግባት
ሞክረህ ተሳክቶልህ እንደነበር
የሰማሁት ወሬ አውነትነት አለው፤.. ?
ሙሉአለም፡-እውነት ነው…!
ግን በወቅቱ ለሙከራ የሄድኩት ቡና
ዋናው ቡድን ሣይሆን ለ”ሲ” ቡድን
ነበር፡፡ ቹቻ የሚባል ግራኝ ልጅ ነበር
አሰልጣኙ ወዲያው ይዞኝ ነበር፤ ነገር
ግን ክለቡ በጀት የለንም በዚህ አመት
ቡድኑን አፍርሰነዋል በማለታቸው ቡና ሲ
ውስጥ የነበረኝ ቆይታ ከሙከራ የዘለለ ሊሆን
አልቻለም፡፡
ሀትሪክ፡- መች ይሄ ብቻ …ሙሉአለም
ከቡና ሌላም ጊዮርጊስም ለሙከራ ሄዶም
ተቀንሶ ነበር በሚል አንዱ ሹክ ብሎኛል
ትክክል.. ነው…?
ሙሉአለም፡-…(ሳቅ)…ይሄም እውነት
ነው… ጊዮርጊስ ሲ ከመሞከሬ በፊት እዛው
ጊዮርጊስ ቢ ነው ለሙከራ የሄድከት፤
በወቅቱ የቢ ቡድን አሰልጣኝና መልማይ
የነበረው አሰልጣኝ ስዩም ከበደ ነበር፤ስዩም
የሙከራ እድል ሰጥቶኝ ካየኝ በኋላ “ለጊዮርጊስ
የሚመጥን ችሎታ የለህም” ብሎ በወቅቱ
ቀንሶኛል…(አሁንም ሳቅ)…
ሀትሪክ፡-ሌላው ደግሞ ጊዮርጊስ ሲ
የተያዝከው በችሎታህ ታምኖብህ ሣይሆን
በሰው እድል ገብተህ ነው ተብሏል ይሄስ
እውነትነት አለው…?
ሙሉአለም፡-… (አሁንም ሳቅ)… ምንድ
ነው መሠለህ… የጊዮርጊስ ሲ ምርጫ ጊዜው
አልፎ ነበር፤ የመብራት ኃይል ተጨዋቾች
የነበሩት ሙሴ ንፍታሌምና አለማየሁ
የተባሉ ልጆች ጊዮርጊስ ሲ ተይዘው ነበር፤
እንደ አጋጣሚ መብራት ኃይል ለቢ ቡድኑ
ሲመለምልም እዛም ተሳክቶላቸው ሁለቱም
ተይዘው ነበር፡፡ በኋላ ላይ ለ ሲ ከመያዝ ቢ
ይሻላል ብለው የጊዮርጊስን ትተው ለመብራት ቢ
ቡድን ለመጫወት ይወስናሉ፤ በዚህን ጊዜ እነሱ
በመሄዳቸው ክፍተት ተፈጠረ፤ በአጋጣሚው
ለመጠቀም ሞከርኩ ተሳካልኝ ወዲያው
ለጊዮርጊስ ሲ ተያዝኩ፡፡ የእነ ሙሴ ንፍታሌም
ወደ መብራት ቢ መሄድ ነው ለእኔ ያልታሰበ
ሲሳይ ወይም እንጀራ ይዞልኝ የመጣው፡፡
እውነቱን ልንገርህ እነዚህ ልጆች በዚህ መልኩ
ባይሄዱና ጊዮርጊስ ለመቀጠል ቢወስኑ ኖሮ
የእግር ኳስ ተጫዋችነቴ ታሪክ ምናልባት ሌላ
ሊሆን ይችል ነበር፤ የእነሱ መውጣት ለእኔ
ጊዮርጊስ ሲ ለመግባቴና ለዛሬው ማንነቴ በሩን
ወለል አድርጎ ከፍቶልኛል፡፡
ሀትሪክ፡- …ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሲ…
ቡድን… በቀጥታ… ወደ ዋናው ቡድን…
አስራት ነው ያሳደገህ… ?
ሙሉአለም፡…በጣም የማገርምህ ጊዮርጊስ
ሲ ቡድን ውስጥ የቆየሁት ለአምስት ወር
ብቻ ነው፤ የሲ ቡድን ተጨዋችም የተባልኩት
ለጠቀስኩልህ ወር ብቻ ነው፤ አሰልጣኝ አስራት
ኃይሌ ከሲ ቡድን በቀጥታ ወደ ዋናው ቡድን
ነው ያሳደገኝ፡፡ በወቅቱ ለጊዮርጊስ ዋናው
ቡድን የሚጫወቱ ወደ 8 የሚሆኑ ልጆች
ጣሊያን ላይ በመጥፋታቸው ዋናው ቡድን
ውስጥ ክፍተት ይፈጠራል፤ በዚህ ምክንያት
አስራት ከ ቢ ቡድን ልጆች ማሳደግ ይፈልጋል፡
፡ ለምርጫ እንዲሆነው የቢ እና የዋናው
ቡድንን በማጫወት የተሻሉት ተጫዋቾችን
ለመመረጥ ያስብና በሁለቱ መካከል መመጣጠን
ስለማይኖር ተጨዋቾች ለመምረጥ አይ
መቸኝም ይልና የመጀመሪያ ሃሳቡን በመቀየርየቢ እና የሲ ቡድኖችን ባጫውት ተመጣጣኝ
ይሆናል ተጫዋች ለመያዝም ይረዳኛል ይልና
የቢ ቡድንና እኔ ያለሁበትን የሲ ቡድንን
ያጫውታል፡፡ በዚህ አጋጣሚ እኔን ያየኛል፤
ከእኔ ጋር አብሮ የሚጫወት ሰለሞን የሚባል
ልጅን ሁለታችንን ከሲ ከቢ ቡድን ደግሞ አንድ
ልጅ በድምሩ ሶስት ልጆችን ለዋናው ቡድን
ያሳድጋል፤ ከአምስት ወር በላይ በሲ ቡድን
ውስጥ ሣልቆይ ወደ ጊዮርጊስ ዋናው ቡድን
የገባሁት በዚህ መንገድ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- አስራት በወቅቱ አንተን ወደ
ዋናው ቡድን በማሳደጉ ከየአቅጣጫው የጠነከረ
ተቋውሞ ቀርቦበት እንደነበር አስታውሳለሁ፤
ይሄን አጋጣሚ መለስ ብለህ አስታውሰኝ
እስቲ…?
ሙሉአለም፡- …እውነት ነው…! በእኔ ወደ
ዋናው ቡድን ማደግ አስራት ከፍተኛ ተቋውሞ
አስተናግዷል፤ብዙዎች እነ ሰለሞን (ቸርኬን)
እነ ሽሪፍን ባየንበት ክለብ እንዴት ይሄን ደቃቃ
ለዋናው ቡድን ያሳድገዋል? በሚል በደጋፊውም
በክለብ አመራሮችም ተብጠልጥሏል፡፡ ብዙዎች
የእኔን መያዝ አላመኑበትም፤ የሰውን ተወውና
እኔም ራሴ ብሆን ለማመን ተቸግሬ ከአዕምርዬ
ጋር ስሟገት ነበር፤ከውጪ ሆኜ ስለ አስራትአስተሳሰብ ወይም የጨዋታ
ፍልስፍናና ስለሚፈልጋቸው
ተጨዋቾች በጣም ብዙ
ነገር እሰማ ነበር፤ አስራት
የሚፈልጋቸው ተጨዋቾች
ፊዚካል የፈረጣጠሙ በጣም
ረዣዥም ተጫዋቾችን
እንደሚያስቀድም ነው ስሰማ
የነበረው፤ እኔ ደግሞ በወቅቱ
ነፍሰ የሌለኝ በጣም ደቃቃ
የምባል አይነት ተጨዋች
ነበርኩ፤ እውነት አስራት
ፈልጎኝ ነው? አስተሳሰቡንስ
ቀይሮ ነው? እያልኩ
ከራሴ ጋር እከራከር ነበር፡
፡ ሰዎችም “አስራት የአንተ
አይነት ተጨዋችን እኮ
አይፈልግም” እያሉ ይሄንኑ
መልሰው ይነግሩኝ ነበር፤ እኔ ግን በወቅቱ
ለእንደዚህ አይነት ነገር ቦታ ሳልሰጥ ኳሱን
ብቻ እጫወት ነበር፤ነገሮች እንደፈለጉትና
እንደገመቱት አልሆነም፡፡ ለካ አስራት
ደቃቃ ሰውነቴን ሳይሆን በደቃቃው ሰውነቴ
ውስጥ ያለውን ችሎታ ተረድቶ ስለነበር
ለተቋውሞው ቦታ ሳይሰጥ “በእኔ ሥራ ጣልቃ
አትግቡ፤ ይሄ ልጅ ትልቅ ቦታ የሚደርስ ልጅ
ነው፤ የጊዮርጊስ መመኪያ ይሆናል፤ እሱን
በተመለከተ ለሚፈጠረው ነገር እኔ ኃላፊነቱን
እወስዳለሁ” በማለት ለተቋውሞው ምላሽ
በመስጠቱ ዋናው ቡድን ውስጥ ተያዝኩ፡
፡ አስራት በዚህ ደረጃ የመጣውን ተቋውሞ
ባይመልስ ኖሮ ጊዮርጊስ ውስጥ የተወለደው
ሙሉዓለም ታሪክ ምናልባትም ሌላ ሊሆን
ይችል ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- ከ “ሲ” ቡድን አድገህ
የጊዮርጊስን ማልያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለብሰህ
የተጫወትከው ድሬዳዋ ላይ ነው…?
ሙሉአለም፡- … አይ… አይደለም…
ከዚያ በፊት የጊዮርጊስ ማልያን ለመጀመሪያ
ጊዜ ለብሼ ለ15 ደቂቃዎች ተቀይሬ ገብቼ
የተጫወትኩት ከመደን ጋር ነው፤ ያኔ
አስራት ቀይሮ ነው ያስገባኝ፡፡ ከዚያ በኋላ
ተስፋ ስላየብኝ ነው መሠል ድሬዳዋ ላይ
ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለመግባት በተደረገው
ጨዋታ ላይ ተሰልፌያለሁኝ፤ ይሄ ጨዋታ
ለጊዮርጊስ ተሰልፌ ከመጫወት በዘለለ ለታዳጊ
ብ/ቡድንም የመመረጥ ሌላ ያልታሰበ እድልን
ይዞልኝ መጥቷል፡፡ ድሬዳዋ ሆኖ ጨዋታቻችንን
ሲከታተል የነበረው አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው
ለታዳጊ ብ/ቡድን ለመጀመሪያ የመረጠኝ በዚህ
ጨዋታ ነው፡፡
ሀትሪክ፡- ከ”ሲ” ቡድን በአምስት ወር
ቆይታ ብቻ ወደ ዋናው ቡድን በማደግ
ለጊዮርጊስና ከታላላቅና ስመ ጥር ተጨዋቾች
ጋር መጫወት አልከበደህም?
ሙሉአለም፡-ከውጪ ሆነህ ስታደንቃቸው
ከነበሩ ተጨዋች ጋር አብረህ የምትጫወትበት፣
የምትሰራበት መንገድ ሲፈጠር ትንሽ
የምትቸገርበት ሁኔታ እንዳለ አድርገህ
ልታስብ ትችላለህ፡፡ እኔ ግን በዚህ በኩል
አልተቸገርኩም፣ አልከበደኝም፤ እነ ስንታየሁ
(ቆጬ)፣ ቦጋለ (ኢንተሎ)፣ ተስፋዬ ኦርጌቾ
እና አሸናፊ ሲሳይ መኖራቸው ነገሮች ከመክበድ
ይልቅ ቀለውልኛል፡፡ እንደውም የእነሱ ድጋፍ
የተሻለ ነገር እንድደርስ ረድቶኛል፡፡ በተለይ
እንደ ተስፋዬ ኦርጌቾ አይነት ተጫዋች
መኖሩ ጊዮርጊስ ቤት ውስጥ ከመክበድ ይልቅ
ይበልጥ ጎልቼ እንድወጣ በሩን ወለል አድርጎ
ከፍቶልኛል…፡፡
ሀትሪክ፡- …እንደ ተስፋዬ ኦርጌቾ አይነት
ተጨዋቾች ስትል….?
ሙሉአለም፡-…ጊዮርጊስ ውስጥ ብዙ ዕድል
እንዳገኝ ለእድገቴ ትልቅ አስተዋፅኦ ካደረጉ
ደግሞም ከማልረሳቸው ተጨዋቾች አንዱ
ተስፋዬ ኦርጌቾ ነው፡፡ “እኔ ከማንም አላንስም
እበልጣለሁ” ሲባል በሚሰማበት ሀገር ተስፋዬ
ኦርጌቾ “በአሁን ሰዓት ከእኔ በተሻለ በጥሩ አቋም
ላይ ያለው ሙሉአለም ስለሆነ እኔ ተቀምጬ
እሱ መሰለፍ አለበት” ብሎ እስከመናገር
የደረሰበት ሁኔታ ነው የነበረው፡፡ እንደ አጋጣሚ
የዕድል ጉዳይ ሆኖ እኔ በምገባበት ሰዓት
ቡድናችን ጎሎችን ያስቆጥር ነበር፤ በወቅቱ
ከሙገር ጋር ስንጫወት ይመስለኛል ወደ 70
ደቂቃ ያህል ጎል ማስቆጠር አልቻልንም፤እኔ
ተቀየሬ ከገባሁ በኋላ ግን በ15 ደቂቃ ውስጥ
ሶሶት ጎል አግብተን ያሸነፍንበት ሁኔታ መኖሩ
የተለየ ነገር ባልሰራም የቋሚ ተሰላፊነት እድል
እንደገኝ ሁኔታዎችን ያፋጠነ ይመስለኛል፡፡
ተስፋዬ ኦርጌቾ በጣም ትልቅ አስተሳሰብ ያለው
ከራሱ ይልቅ ለክለቡ የሚያስብ ትልቅ ተጫዋች
ነው ብቻ ሣይሆን ችሎታዬን አቅሜን አውጥቼ
እንዳሣይ በር የከፈተልኝም ሰው ነው፡፡

ሀትሪክ፡- በጊዮርጊስ የረዥም አመት
ቆይታህ ከውስጥህ የማይጠፋውና ሁሌም
የምታስታውሰው ጨዋታ?
ሙሉአለም፡-ብዙ የማይረሱ ጨዋታዎችን
አድርጌያለሁ፤ አበላልጥ ካልከኝ ከጋናው
ኸርትስ ኦፍ ኦክ ጋር ያደረግነው ጨዋታና
ያገባኃት ጎል መቼም አይረሱኝም፤ ሁሌም
አስታውሳቸዋለሁ፡፡ ከዚህ ውጪ ደግሞ ስሜቱ
ዛሬም ድረስ ውስጤ ያለው በ1995 ከቡና
ጋር ተጫውተን ባለቀ ሰዓት አግብተን ዋንጫ
የወሰድንበት ጊዜ የማልረሣቸውና ልዩ ትዝታን
በውስጤ የፈጠሩ ጨዋታዎች ናቸው፡፡
ሀትሪክ፡- በጨዋታ ዘመንህ በተለይ
ጊዮርጊስ እያለህ ከማን ጋር ስትጫወት
ይመችሃል… ?
ሙሉአለም፡- በተለይ ከቡና ጋር ስንጫወት
የተለየ ስሜት ይሰማኛል፤ የስታዲየሙ ድባብ፣
ከውጪ ጀምሮ ያለው የደጋፊው ሁኔታ ልዩ
ስሜትን የሚፈጥር ነው፡፡በእንደዚህ አይነት
ድባብ ውስጥ መጫወት ያረካል፤ ከቡና ጋር
ስንጫወት ገና ወደ ሜዳ ስገባ ስታደየሙ
በሁለቱ ደጋፊዎች ጢም ብሎ ሞልቶ ሣይ
ሰውነቴን ይነዝረኛል፤ አንደኛ የማላውቀው
ልዩ ስሜትም ይሰማኛል፤ከእነሱ ጋር በየቀኑ
ብትጫወት አይጠገብም፡፡
ሀትሪክ፡-ከማን ጋር ስትጫወትስ
ይከብድሃል ወይም ይቀልሃል…?
ሙሉአለም፡- ሁሉም ጨዋታዎች ለእኔ
ከባድ ናቸው፤ ሁሉም ቡድን ከጊዮርጊስ ጋር
ሲጫወት አሰልጣኞች እኔን የትኩረታቸው
ወይም የሲስተማቸው ማዕከል ያደረጉኛል፡
“ጊዮርጊስን ማሸነፍ ከፈለጋችሁ፤ ጊዮርጊስ
እንዳይንቀሳቀስ ከፈለጋችሁ ሙሉአለምን
ወጥራችሁ ያዙት፤ ሙሉአለምን አጥፉት፤
አሱን ከለቀቃችሁትና ነፃ ካደረጋችሁት በቃ
አለቀላችሁ” በማለት ተጫዋቾች ያዘምቱብኛል፤
በዚህ የተነሣ በየሄድኩበት ቦታ ዱላ ነው
የሚወርድብኝ፡፡ አማካይ ቦታ ላይ ያለ ተጨዋች
ይሄን ቢያደርግ ወይም ጨዋታዬን ሊያበላሽ
ቢሞክር ክፋት የለውም፤ ግን በሄድኩበት ቦታ
ያገኘህ ተጨዋች ገሎ ለማቆም ያህል ነው ዱላ
የሚወርድብኝ፡፡ በጨዋታ ዘመኔ የከበደኝ ቡድን
ሳይሆን ይሄ ነበር፤ አንድ ጊዜ ደብሮም ሐጎስ
ምን እንዳለ ታውቃለህ…?
ሀትሪክ፡-…ምን አለ…?
ሙሉአለም፡-…ደብሮም ሐጎስ ከቡና
ወጥቶ እኛ ጋ ገብቶ ነበር፤ ረዥም የጨዋታ
ዘመን ያሳለፈው በቡና ነበር፡፡ እኛ ጋ መጥቶ
ከቡና ጋር ልንጫወት ስንል ምን አለ መሰለህ…
“አኔ ቡና እያለሁ በየትኛውም አቅጣጫ
ሙሉአለም ከተገኘ ከትክቱና አቆሙት ነበር
የሚባለው፤ ሙሉአለም ሁሌም የትኩረት
ማዕከል ነው ስለዚህ እኛ እሱን ማዳን አለብን፤
እኛ ለመጫወት ከፈለግን እሱን ከእንደዚህ
አይነት ነገር ውስጥ ማውጣት አለብን፤ ሙሌ
ስለማይቆምና ሁሉንም ቦታ ስለሚያካልል
ጊዮርጊስን ለማቆም ምቱት አጥፉት ይባላል፤
ስለዚህ እኛ ልንታደገው ይገባል” እስከማለት
ደርሶ ነበር፡፡ ደብሮም ሐጎስ ከመናገሩ
በፊትም ከየትኛውም ቡደን ጋር ስንጫወት
ማን ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚችል አውቅ
ነበር፤በዚህም ሁሌም ይበልጥ እዘጋጅ ነበር፡
፡ ከጨዋታዎች በላይ ሲከብደኝ የነበረው ይሄ
ነው፡፡
ሀትሪክ፡-የፊርማ ገንዘብ አግኝተህ
ታውቃለህ?
ሙሉአለም፡-በፊርማ ደረጃ ከጊዮርጊስ
ጋር ተደራድሬአላውቅም፤ለክለቡ መጫወት
በራሱ ከምንም ነገር በላይ ነው፤ለ14 ዓመታት
ለጊዮርጊስ ስጫወት ውሌ ሲያልቅ ሄጄ
እፈርማለሁ እንጂ በፊርማ ገንዘብ ዙርያ
ተነጋግሬ አላውቅም።
ሀትሪክ፡- አንተ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከወጣህ
በኋላ በክለቡ እስከአሁን የተዋጣለት የጨረሰ
አማካይ ማግኘት አንተንም መተካት እንዳልቻሉ
የሚናገሩ አሉ፤ እውነት አልተተካሁም ብለህ
ታስባለህ?
ሙሉአለም፡- ይሄ ነገር ሲነገር እሰማለሁ፤
ግን እንደዚህ የሚባለው ተጨዋች ጠፍቶ
አይምስለኝም፡፡ ከእኔ በኋላ እነ ኤልያስ
ማሞ ፣ሽመልስ በቀለ ወጥተዋል በዚህ ቦታ
ስትጫወት ኃላፊነት መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
ምናልባት ኃላፊነት የመወሰድ ችግር ካልተነሣ
በስተቀር ቦታው ላይ ተጨዋች ጠፍቶ ነው
ብዬ አላስብም፡፡ እንደዚህ አይነት አስተያየት
እንዲሰጥ ምክንያት የሆነው በቁርጠኝነት
ኃላፊነትን ደፍሮ የሚወስድ ሰው ካለማየትም
ነው፡፡ እኔ በዚህ ቦታ ስጫወት የተበላሸበትን
ቦታ እዛው ሜዳ ውስጥ እያየሁ መድፈን
እችላለሁ፡፡ የቱ ጋር ነው መገኘት ያለብኝ?
የቱ ጋር ምን ማድረግ አለብኝ? የሚለውን
ስለማደርግ እንጂ ከእኔ በኋላም እንዳልኩህ
የተሻሉ ተጫዋቾች እንደመጡ እርግጠኛ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡-ብዙዎች የስፖርት ቤተሰቦች
ሙሉአለም የአጭር ኳስ አቀንቃኝ እንደሆነ
በማሰብ ሙግት የሚገጥሙ አሉ፤ አጭር
ኳስን ለአንተ ረዥም ኳስን ደግሞ ለአሸናፊ
ግርማ በመስጠት የማነፃፀር ሁኔታ አለ፤ በዚህ
ጉዳይ ላይ አንተ ራስህን የምትገልፀው እንዴት
ነው… ?
ሙሉአለም፡-እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ
ለይቼ የምወስነው ጉዳይ የለም፤ ሁለቱንም
እንደየአመጣጣቸው ነው የምጠቀመው፤
ረዥም ኳስ ላይ አዘንብዬ አልጫወትም አጭር
ኳስንም ቀኑን ሙሉ ስጫወትም አልውልም፤
የጨዋታው እንቅስቃሴ በሚጠይቀው መንገድ
ሁለቱንም እንደየአስፈላጊነታቸው እተገብራለሁ፡
፡ ብዙዎች የአጭር ኳስ ተጨዋች እንደ ሆንኩ
አድርገው የሚያስቀምጡት ብዙውን ጊዜ
ከጭንቀት የምወጣበትን መንገድ፣ በጠበበ
ቦታ ላይ ብዙ ነገር ማድረግ እንደምችል
ሲያዩ ወደዚህ ነገር ይወስዱኛል፡፡ ከዚህ
ውጪ አጭር ኳስ እንጫወት ወይም ረዥም
ኳስ ብቻ እንጫወት ብዬ ወስኜ አላውቅም፤
የጨዋታው እንቅስቃሴ የግዴታ ረዥም ኳስን
እንድጫወት የሚያስገድድ ከሆነ ረዣዥም
ኳሶችን እጠቀማለሁ፤በአጭሩ ሁለቱንምእንደየአስፈላጊነታቸው እጠቀማለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- በኢትዮጵያ እግር ኳስ የአማካይ
ክፍል ሲነሳ ብዙዎች አንተንና አሸናፊ ግርማን
ያነሣሉ ከሁለታችሁ ማን ይበልጣል? ብለህ
መልስህ ምንድነው…?
ሙሉአለም፡- … ሣቅ… አንዱ ከአንዱ
ይበልጣል ሣይሆን ሁለታችንም የየራሳችን
የሆነ ነገር አለን ብል ይሻላል፡፡ ለምሣሌ
አሸናፊ ረዥም ኳስ ላይ በጣም አሪፍ ነው፤
ፕርፌክሽኑም ጥሩ ነው፤ በዚያ ላይ ሹተር ነው፤
ከርቀት በሚመታቸው ኳሶች በጣም ስኬታማ
ነው፡፡ ከዛ እግር የሚወጣ ሹትም አይመስልም፡
፡ ወደ እኔ ስትመጣ ብዙ ጊዜ በጠባብ ቦታ ላየ
የምወጣበት፣ ከችግር የማመልጥበት መንገድ
ለእኔ ቀላል ነው፡፡ ኳስ ከመቀበሌ በፊት ለማን
እንደምሰጥና እንዴት መቀቀል እንዳለብኝ
አስቤ ነው የምቀበለው፡፡ በአጭሩ ሁለታችንም
የየራሳችን ኳሊቲ አለን፤ አሸናፊ ይበልጣል?
ሙሉአለም? የሚለውን ፍርዱን ለተመልካች
ብንተወው ነው የምመርጠው፡፡
ሀትሪክ፡-የቅዱስ ጊዮርጊስ ማልያን ለስንት
አመት ለብሰህ ተጫወትክ…?
ሙሉአለም፡- ድፍን 14 አመታት፤
ሀትሪክ፡-ከ14 አመት በኋላ ከክለቡ ጋር
የተለያየኸው አቋምህ በደከመበት መቀነስ
በሚገባህ ትክክለኛው ሰአት ላይ ነው…?
ሙሉአለም፡- መቼም አንድ ተጨዋች
አቅሙ ቢደክም እንኳን አቋሜ ደክሟል
ብሎ እንደማያምንም አውቃለሁ፤ እኔ ግን
እውነት ለመገር ከክለቡ እንድለይ በተደረገበት
ሰዓት ክለቡን በብቃት ማገልገል የምችልበት
ጥሩ አቋም ላይ እገኝ ነበር፤ አቋሙ ወርዶ
ነው የተቀነሰው የሚለውን እኔ ብቻ ሣልሆን
ሌሎቹም በምክንያትነት አይቀበሉትም፡
፡ የተቀነስኩት በአቋም መውረድ ነው ብዬ
እንዳልደመድም ከጊዮርጊስ ከወጣሁ በኋላ
እኔነቴን፣ አቅሜን የሚመሰክሩና የሚገልፁ
ጨዋታዎችን ተጫውቻለሁ፡፡ ከጊዮርጊስ
ከወጣሁ ከ10 አመት በኋላም እንኳን
ከእነሱ ጋር ያውም በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ
ተጫውቻለሁ፤ ከዚህ አንፃር አቋምህ ወርዶ
ነው የሚለው ከተባለ እንኳን ለመቀበል
እቸገራለሁ፤ ሰው ለራሱ የሚሰጠው ቦታ
ከፍተኛ ነው ቢባልም የተቀነስኩበትን መንገድ
አላውቀውም፤ ቅነሳውም አላሳመነኝም፡፡
ሀትሪክ፡- በወቅቱ የተቀነስክበትን ምክንያት
ለማወቅስ ጥረት አላደረክም… ?
ሙሉአለም፡-ራሴን ለማሻሻል ችግሬን
ለማወቅ ይረዳኛል ብዬ ከጊዮጊርጊስ ጋር
እንድለያይ የተፈለገበት መንገድ ወይም ችግሬ
ምንድነው? የሚለውን በመጠየቅ ለማወቅ
ሞክሬያለሁ፤ በአቋም መውረድ፤ በዲሲፒሊን
ወይም ደግሞ ብዙ አመት በመጫወቴ
ብቻ ይበቃሃልም ከሆነ ከሶስቱ በየትኛው
ነው የተቀነስኩት አላውቀውም፤ ችግሬ
ምንድነው?ብዬ ጠይቄ ነበር መልስ የሚሰጠኝ
ሰው አላገኘሁም፡፡
ሀትሪክ፡- በወቅቱ ከነበረው አሰልጣኝ ሚቾ
ጋር የነበረህ አለመግባባት በጊዮርጊስ የነበረህ
ቆይታ እንዲያጥር አድርጎት ይሆን?
ሙሉአለም፡- ይሄ ግንጥል ነገር ነው፤
ከሜዳ ላይ ብቃቴ ጋር የሚያገናኘው ነገርም
የለም፡፡ ደግሞም እኔና ሚቾን የሚያገናኘን
ወይም የተነጋገርነው ክፉ ደግ ነገር የለም፤
ምናልባት በዚህ ደረጃ የተነጋገርነው ነግር ቢኖር
ይሄ ነገር ስላላስደሰተው ነው ብዬ እንደ አንድ
ምክንያት እወስደው ነበር፡፡ ደግሞም ስንብቴን
ከሜዳ ላይ ብቃት ውጪ ከእሱ ጋር ለማያያዝ
ተሞክሮ ከሆነም ስንብቴን አምኜ እንድቀበል
አያሳምነኝም፡፡ በጣም የሚገርመው አሰልጣኝ
ሚቾ ራሱ ቀንሶኝ የቀነሰበትን ምክንያት ግን
እንደዚህ ነው አላለኝም፤ምክንያቱ ተነግሮህ
ድክመትህን አውቀኸው ብትወጣ ደስ ይልሃል፤
እውነቱን ለመናገር ከጊዮርጊስ መቀነሴን
እንጂ የወጣሁበትን ምክንያት ዛሬም ድረስ
አላውቀውም፡፡
ሀትሪክ፡- መቀነስህ በውስጥህ ቅሬታ
የፈጠረ ይመስለኛል፤ ምናልባት በዚህ ደረጃ ቅር
ያለህ በጊዮርጊስ ቤት ያልጨረስከው የቤት ሥራ
ነበረህ…? ጊዮርጊስ እያለሁ ያላሳካሁት ነገር አለ
ብለህ የምትቆጨው ነገርስ አለ?
ሙሉአለም፡- እንዳልኩህ ጊዮርጊስ የስኬት
ቤት ነው፤ ከክለቡ ጋር ተጨማሪ ስኬቶች
ቢኖሩኝ አልጠላም፤ እንኳን በወቅቱ ዛሬም
ከጊዮርጊስ ከወጣሁ ከ10 አመት በኋላም
አሁንም መጫወት እፈልጋለሁ፡፡ ከክለቡ ጋር
በርካታ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን ከፍ
አድርጌ አንስቼለሁ፤ የሚጎድለኝ ነገር ቢኖር
አንድ አህጉራዊ ታሪክ ቢኖረኝና ያንን አሳክቼ
ብወጣ የክለቡን ቆይታዬ ይበልጥ ደማቅ
ያደርገው ነበር፡፡ በሀገር ውስጥ ውድድር ያለኝን
ደማቅ ታሪክ ያህል በኢንተርናሽናል የውደድር
መድረክ ለክለቡም ለራሴም ስም መጠሪያ
የሚሆን ታሪክ ሳላሳካ መውጣቴ በቁጭት
የማነሳው ነው፤በሴካፋ፣ በአፍሪካ የክለቦች
ሻምፒዮና ላይ አንድ ታሪክ ሳይኖረኝ ከጊዮርጊስ
ጋር መለያየቴ ታሪኬን ጎድሎ ያደረገው ያህል
ይሰማኛል፡፡
ሀትሪክ፡- በዚህ ደረጃ ስለሞትቆጭበትና
ስለተለያየኸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዛሬ ላይ ያለህ
ስሜትስ እንዴት ነው?
ሙሉአለም፡- ከጊዮርጊስ ብለያይም ጊዮርጊስ
ዛሬም የእኔ ነው፤ እውነቱን ልንገርህ ጊዮርጊስ
አሁንም የራሴ ነው ፡፡ ማንም እንደፈለገ
ሊያስብ ይችላል ጊዮርጊስ አሁንም የራሴ ነው፤
ከክለቡ ከተለያየሁ አስር አመት እንደሆነኝ
ባውቅም ውስጤ ግን 10 ደቂቃ እንኳን
እንዳልተለየሁ ነው የሚያስበው፤ በዚህ የተነሣ
የክለቡን የየዕለት እንቅስቃሴ እከታተላለሁ።
ሲያሸንፉ እደሰታለሁ፤ ተጨዋች በነበርኩበት
ሰዓት እንደሚሰማኝ ስሜት ሲሸነፉ ደግሞ
በጣም አዝናለሁ፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም ድሮም
እንደነበረኝ ህልም ጊዮርጊስ አሁን ካለበት የበለጠ
ትልቅ ደረጃ ደርሶ ማየትንም እናፍቃለሁ፤
ለዚህም የራሴን አስተዋፅኦ ከማድረግ ወደ ኋላ
አልልም፡፡
ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ብ/ቡድንም ለቅድስ
ጊዮርጊስ ረዥም አመት እግር ኳሱን እንዳገለገለ
ባለውለተኛ ተጨዋች ተገቢውን ክብር
አግኝቻለሁ ብለህ ታስባለህ… ?
ሙሉአለም፡- ክብር የሚባለው ነገር የቱ
ጋር አንዳለ አይታውቅም፤ ምክንያቱም ከዚህ
በፊት ለክለባቸው፣ ለሀገራቸው የረዥም ጊዜ
ግልጋሎት ሰጥተው የተከበሩ ሰዎችን ስላላየሁ
ክብር የሚባለው ነገር ከቃል ውጪ የቱ
ጋር እንዳለ አላውቅም፡፡ አንድ ለሀገር ትልቅ
ውለታን ውሎ ያለፈ ተጨዋች ብ/ቡድኑ
ሲጫወት ለማየት በክብር ሊጋበዝ ሲገባው
ትኬት ለመቁረጥ በፀሓይ ሲመታና ክብሩን
አጥቶ ሰልፍ ላይ ሲጋፋ ነው የምታየው፤ እንደ
ክለብም ስታይ ብዙ ዓመት ለውጤታማነቱ
የደከመለት ክለብ የአፍሪካ የክለቦች ውደድር
ላይ ሲፋለም፣ የሀገር ውስጥ ጨዋታ ሲኖረው
በክብር መጋበዝ ትኬት መስጠቱን ተወውና
በገዛ ገንዘብህ ቅድሚያ ተሰጥቶህ ከሰልፍና
ግፊያያ ወጥተህ ትኬት ቆርጠህ የደማህለትን
ክለብ እንድታይ ሲደረግ አይታይም፡፡ በአጭሩ
ክብር የሚባለው ነገር ከአንተ በፊት ወይም
በኋላ በመጣ ሰው ላይ ሲደረግ አይተህ
ስለማታውቅ ክብር አገኛለሁ ብለህ አትጠብቅም፡
፡ እኔ በኢትዮጵያ እግር ኳስ እስከ አሁን
የ21 አመት አገልግሎት አለኝ ከዚህ በኋላ 31
አመት ብጫወት እንኳን ክብር የሚባለውን
ነገር አላይም፡፡ ይሄን ያህል አመት ስጫወት
የነበረውም ክብር ፈልጌ አይደለም፤ያላየኸውን
ክብርም አትጠብቅም፡፡ ለእኔ ክብር አልተሰጠኝም
ከሚለው ይልቅ የሚያሳስበኝ ነገ የሚመጣው
ተጨዋች ምን አይቶ? ምን ተስፋ አድርጎ ነው
የሚለው ነው በጣም የሚያሳስበኝ፡፡
ሀትሪክ፡- የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች
ስለሚሰነዝሩብህ ተቋውሞስ አስበህ
ታውቃለህ…?…መለስ ብለህ ስታስበውስ ምንስ
ይሰማሀል…?
ሙሉአለም፡-ስለ ደጋፊዎች ስታነሣ ቀድሞ
የሚመጡት የሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች
ናቸው፤የቅ.ጊዮርጊስና የቡና ደጋፊዎች።
ስለተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች ካነሳህ ደግሞ
የውጤት ተቀናቃኝ ደጋፊ የሆኑት ደግሞ የቡና
ደጋፊዎች ናቸው፡፡ የቡና ደጋፊዎች ከእነሱ
ጋር ስጫወት ብቻ አይደለም ከሌላ ቡድን ጋር
ስንጫወትም እነሱ ሜዳ ከገቡ የመጀመሪያ
ተሰዳቢው ሰው እኔ ነኝ፤ግን ለምንድነው
የሚሰድቡኝ? አውቀዋለህ፤ እኔን በችሎታዬ
ስለሚያደንቁኝና ቡድናቸው ውጤት እንዲያገኝ
ከመመኘት ብቻ ነው፡፡ እንዲያውም አንድ እውነት
ልንገርህ ከጊዮርጊስ ደጋፊ ባልተናነሰ የቡና
ደጋፊዎች እንደሚወዱኝ በደንብ አውቃለሁ፤
በከተማ ውስጥም ስዘዋወር የማገኛቸው የቡና
ደጋፊዎች የሚያረጋግጡልኝም ይሄንኑ ነው፤
“አኔ የቡና ደጋፊ ነኝ፤ ግን አንደኛ የአንተ
አድናቂ ነኝ” በማለት በስሜት የሚያወሩኝ ብዙ
ደጋፊዎች አሉ፡፡ በስድብ ደረጃ ከሄድክ ከእነሱ
ጋር ስንጫወትም ሳንጫወትም ያገር ስድብ ነው
የምሰድበው፤ ግን አንድም ቀን እንኳን ምላሽ
ሰጥቻቸው ቀና ብዬ አይቻቸውም አላውቅም፤
የሚሰድቡኝ ስለሚጠሉኝ ወይም በክፋት
እንዳልሆነ ውስጤ ስለሚያውቅ ቅር ብሎኝ
አያውቅም። ጨዋታዬ እንዲበላሽ፣ ውጤት
እንድናጣ፣ በልጠው ለመገኘት ከመፈለግ የመጣ
እንጂ የችሎታዬ በጣም አድናቂ ናቸው፡፡ ለእኔ
ያላቸው አመለካከት የተለየ ስለሆነ እኔም
ለእነሱ የተለየ አመለካከት ነው ያለኝ፤በወቅቱ
ስድባቸው ጉልበት ስለሚሆነኝ ቅር ተሰኝቼ
አላውቅም፡፡
ሀትሪክ፡- የጊዮርጊስ ደጋፊዎችንስ
ግለፃቸው ብልህ እንዴት ነው የምትገልፃቸው?
ሙሉአለም፡-በሙሉዓለም እድገት ውስጥ
የጊዮርጊስ ደጋፊዎች አሻራ ከፍተኛውን ቦታ
ይይዛል፡፡ ስሳሳት አርመው፣ ስጠነክር ይበልጥ
አበርትተው ለታላቅነት አብቅተውኛል፤ ፍቅራ
ቸውን ድጋፋቸውን ያለስስት ሰጥተውኛል፤
የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ድል የለመዱ
ለድል የተፈጠሩ ልዩዎች ናቸው ማለቱ
ነው የሚቀለኝ፡፡ በጣም የሚገርምህ ከክለቡ
ላለፉት 10 አመታት ተለይቻቸው ዛሬም ልክ
እንደትናንቱ ፍቅራቸውን በተለያየ መንገድ
ይገልጹልኛል፤ አሁንም ጊዮርጊስ ውስጥ ያለው
ያህል ነው የሚሰማቸው፡፡ ከፍቅራቸው የተነሣ
አሁንም ወደ ክለቡ ለምን አትመለስም? የሚለኝ
አሉ፡፡ ሀዋሳ እያለሁ ከእነሱ ጋር ስንጫወት
በርካቶችም ይሄን ያነሱ ነበር፡፡
ሀትሪክ፡- 21 አመታትን በዘለቀው የእግር
ኳስ ህይወትህ በርካታ የሀገር ውስጥና የውጪ
አሰልጣኝ አሰልጥነውህ አልፈዋል፤ ልብህ
ለየትኛው አሰልጣኝ የተለየ ቦታ አለው… ?
ሙሉአለም፡- የተለየ ቦታ ያለኝ ለአንድ
አሰልጣኝ ነው፤ እሱም ለአስራት ኃይሌ፡፡
ብዙ መስዋዕትነትን ከፍሎ አሳድጎ፣ ትልቅ
ደረጃ እንድደርስ፣ እንድቀየር፣ እንድለወጥ፣
ዛሬ ያለው ሙሉዓለም በእግር ኳስ ውስጥ
እንዲፈጠር በማድረጉ ሁሌም በመልካምነቱ
የማያነሳው አሰልጣኝ ስለሆነ ለአስራት የተለየ
ቦታ አለኝ፡፡
አስተያየት ይስጡ