በዘንድሮው የኢትዮጵያ ኘሪሜየር ሊግ በመጥፎ አጀማመር በመጓዝ ላይ እሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ የአሰልጣኝ ለውጥ ካደረገ ከሳምንታት በኃላ የክለቡን የጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ በማሰናበት በምትካቸው አዲስ ስራ አስኪያጅ መቅጠሩ የክለቡ ይፋዊ ገፅ አስታውቋል፡፡
የክለቡ ይፋዊ የማህበራዊ ገጽ ያሰፈረው እንደሚከተለው ነው፡፡
“የድሬዳዋ ከነማ ስፖርት ክለብ ቦርድ ጥር 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ ክለቡ በአመቱ ካስቀመጣቸው እቅድ አንፃር አፈፃፀሙን መገምገሙንና በዚህም ጠንካራና ደካማ ጎኖቹን መለየቱን ደካማ ጎኖቹን ለማረም ደግሞ የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጡን አስተውቋል፡፡
በስብሰባው ወቅት የክለቡ ጽ/ቤት ስራ አስኪያጅ ሆነው ላለፉት 8 ዓመታት ሲያገለግሉ የነበሩትን አቶ እስከዳር ዳምጠውን በፍቃዳቸው የመልቀቂያ ጥያቄ ማስገባታቸውን ተከትሎ እንዳሰናበታቸውም ቦርዱ ገልፆል፡፡
ቦርዱ አቶ እስከዳር በክለቡ በነበራቸው ቆይታ አቅማቸው በፈቀደ መጠን ክለቡን በተነሳሽነት፣ በቁርጠኝነትና በባለቤትነት ስሜት ላበረከቱት አስተዋፅዖ ያመሰገናቸው ሲሆን በምትካቸው አቶ አንበሳው አውግቸውን መተካቱን አስታውቋል፡፡
አቶ አንበሳው በእግር ኳስ አሰልጣኝነት የሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን ከዚህ ቀደም በድሬዳዋ አጠቀላይ ሁለተኛ ት/ቤት በስፖርት በመምህርነት በስፖርት ኮሚሽን በትምህርትና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ እንዲሁም በልዩልዩ ክፍሎች በባለሙያነት ማገልገላቸው ታወቋል፡፡”
- ማሰታውቂያ -
ድሬዳዋ ከተማ በዘንድሮው የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት 11 ያክል ተጨዋቾችን ማስፈረም ቢችልም በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ በ6ነጥቦች 14ኛ ደረጃ ላይ ሊቀመጥ ችሏል፡፡