የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የ11ኛ ሳምንት የዕለተ ዐርብ የሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታዲየም ጨዋታ ቅድመ ዳሰሳ
የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ አንድ ሁለት እያለ እነሆ 11ኛ ሳምንት ላይ ደርሷል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 11ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ(አርብ) አንስቶ በክልል እና በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚካሄዱ ሲሆን ፕሪምየር ሊጉ ወልድያ ስፖርት ክለብ ከ ቅ/ ጊዮርጊስ በሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታዲየም በሚያደርጉት ጨዋታ ጅማሬውን ያደርጋል።
በሜዳው ሲጫወት ጠንካራ አቋም የሚያሳየው ወልድያ ስፖርት ክለብ በ2009 የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ በሜዳው የተሸነፈው 1ጨዋታ ሲሆን ይህም ጨዋታ ከቅ/ጊዮርጊስ ጋር ባደረገው የ2ኛ ዙር ጨዋታ ነበር። ሚያዚያ 18 2009 በተደረገው በዚህ ጨዋታ ፈረሰኞቹ በአብዱልከሪም ኒኪማ ብቸኛ ግብ አሸንፈው መመለሳቸው የሚታወስ ነው።
በ10ኛው ሳምንት የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ ወልድያ ስፖርት ክለብ ከወልዋሎ አ.ዩ. ጋር ተጫውተው ያለግብ አቻ የተለያዩ ሲሆን ቅ/ጊዮርጊስ በአንፃሩ ጅማ አባጅፋርን አ/አ ስታዲየም ላይ አስተናግዶ በአበባው ቡጣቆ ሁለት ቅጣት ምቶች እና በአዳነ ግርማ የጭንቅላት ኳስ ታግዞ 3-0 ማሸነፍ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
ወልድያ በያዝነው የውድድር ዓመት በበርካታ ጨዋታዎች ላይ የሚጠቀመው 4-2-3-1 የጨዋታ ፎርሜሽንን ነው፡፡ ይህ ክለብ 2 የተከላካይ አማካይን አጣምሮ በመጫወት ላይ ምርጫውን አድርጓል፡፡ በዚህ የጨዋታ ዘይቤ ለቡድኑ ላቅ ያለ ግልጋሎትን እየሰጡ ያሉ 2ተጫዋቾችን ማንሳት ይቻላል። ፍፁም ገ/ማርያም እና ምንያህል ተሾመ። በርከት ባሉ ጨዋታዎች ላይ ፊት መስመር ላይ እየተሰለፉ የሚገኙትን ኤዶም ኮድዞ ወይም አንዷለም ንጉሴ(አቤጋ) በማገዝ ሰፊ ሚና እየተጫወቱ ይገኛል። ሆኖም የቡድኑ ትልቅ ችግር ተብሎ የሚጠቀሰው የሁለቱ የክንፍ ተከላካዮች ነው። ከላይ የጠቀስናቸውን አማካዮች በማገዙ ረገድ እጅግ ደካማ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ተስተውሏል።
ቅ/ጊዮርጊስ በአንፃሩ 4-3-3 የጨዋታ ዘይቤን ይዞ ወደሜዳ እየገባ ይገኛል። አሁንም አጥቂዎቹን ሰልሀዲን ሰዒድ እና አሜ መሀመድን በጉዳት ያጣው የአጥቂ አማካዮቹን ኢብራሂም ፎፋና እና አብዱልከሪም ኒኪማን እንዲሁም አቡበከር ሳኒን በሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ሚና ለማጫወት ተገዷል።
ወልድያ ስፖርት ክለብ በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ በሜዳው ማድረግ ከሚገባው 5ጨዋታዎች መካከል ሶስቱን ብቻ ያደረገ ሲሆን ሁለቱን ማለትም አዳማ ከተማን እና አርባምንጭ ከተማን በተመሳሳይ 2-0 በማሸነፍ በአንዱ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር 0-0 አቻ ወጥቶ ምንም ግብ ሳያስተናግድ 4ግቦችን አስቆጥሮ በሜዳው ያለውን ጥንካሬ አስመስክሯል።
ቅ/ጊዮርጊስ በአንፃሩ ማድረግ ከሚገባው 4 የሜዳው ውጪ ጨዋታዎች 3ቱን አከናውኖ ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡናን በማሸነፍ አ/አ ላይ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር(ባለሜዳው ኢትዮጵያ ቡና ነበር።) እንዲሁም አዲግራት ላይ ከወልዋሎ አ.ዩ. ጋር ያለግብ 0-0 መለያየት ችሏል። ከፋሲል ከተማ ጋር ማድረግ የነበረበት የ2ኛ ሳምንት ጨዋታ ረቡዕ ጥር 09 2010 የሚደረግ መሆኑን ከፌደሬሽኑ የወጣው መረጃ ያመለክታል። ስለዚህ ዛሬ የሚደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመከላከሉ ረገድ ጥሩ ጨዋታ የሚታይበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በአጠቃላይ ወልድያ ማድረግ ከነበረበት 10 ጨዋታዎች 8ቱን አድርጎ ሁለቱን አሸንፎ በአራቱ አቻ ተለያይቶ ሁለቱን ተሸንፎ ማግኘት ከነበረበት 24 ነጥቦች አስሩን ብቻ አሳክቶ 11ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ቅ/ጊዮርጊስም ከ10 ጨዋታዎች 8ቱን አድርጎ አራቱን በማሸነፍ አራቱን አቻ ወጥቶ ያለምንም ሽንፈት ከወልዲያ በ6ነጥቦች ከፍ ብሎ እንዲሁም ከመሪው ደደቢት በ6 ነጥቦች ርቆ በ16 ነጥቦች ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ከቅ/ጊዮርጊስ በኩል ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኙት ሰልሀዲን ሰዒድ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ታደለ መንገሻ አሁንም ለቡድኑ ግልጋሎት አይሰጡም። ከክለቡ እንደተሰማው ሰልሀዲን ሰዒድ እና ታደለ መንገሻ ከቡድኑ ጋር ልምምድ የጀመሩ ሲሆን ይህ ዜና ለቅ/ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እፎይታ የሚሰጥ ነው። በአስረኛው ሳምንት በከባድ የጉንፋን ህምም ምክንያት መጫወት ያልቻለው የአጥቂ አማካዩ አብዱልከሪም ኒኪማ ከህመሙ በማገገሙ በዚህ ጨዋታ የሚሳተፍ ይሆናል፡፡ ከላይ ከጠቀስናቸው የተጎዱ ተጫዋቾች በተጨማሪ አዲሱ ፈራሚ ጋዲሳ መብራቴ እና አሉላ ግርማ ጉዳት ላይ በመሆናቸው በዛሬው ጨዋታ የማይኖሩ ይሆናል። በወልድያ በኩል የቀድሞ የቅ/ጊዮርጊሱ አማካይ ተስፋዬ አለባቸው እና አዳሙ መሀመድ በጉዳት የዛሬው ጨዋታ ላይ መሳተፉቸው አጠራጣሪ ሲሆን በ8ኛው ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሲጫወቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብተው የነበሩት ብሩክ ቃልቦሬ እና አማረ በቀለ የ4 ጨዋታዎች ቅጣታቸውን ባለማጠናቀቃቸው እዚህ ጨዋታ ላይ አይገኙም።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ወልድያ ላይ በሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታዲየም ዛሬ (ዐርብ) 9፡00 ሲል የሚጀምር ይሆናል።