በሀያ አምስተኛዉ ሳምንት የሊጉ ሁለተኛ ዕለት ቀዳሚ ጨዋታ ባህርዳር ከተማ ሀምበሪቾ ዱራሜን ማሸነፍ ችሏል።
በጨዋታው መባቻ ሀብታሙ ታደሰ ከያብስራ ተስፋየ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ሳጥን ዉስጥ ከደረሰ በኋላ ቺፕ አድርጎ ወደ ግብ በላካት ኳስ ሙከራ ማድረግ የጀመሩት የጣና ሞገዶቹ ጫና ፈጥረዉ መጫወታቸውን ቀጥለዉ በ15ተኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ፀጋየ አበራ ከሀብታሙ ታደሰ በተቀበለዉ ኳስ ከርቀት ድንቅ ሙከራ አድርገዉ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ ፓሉማ ፓጁ አዉጥቶበታል።
በ23ተኛዉ ደቂቃ ላይ በኃይሉ ተሻገርን በጉዳት ምክንያት አስወጥተዉ በፍቃዱ አስረሳኸኝን ቀይረዉ ያስገቡት ሀምበሪቾዎች በተከታታይ በአጥቂዉ ሀብታሙ ታደሰ ሙከራዎች ከተደረገባቸው በኋላ ፤ በ28ተኛዉ ደቂቃ ላይ በአልዓዛር አድማሱ አማካኝነት የመጀመሪያ ሙከራቸዉን ማድረግ ቢችሉም ግብ ጠባቂዉ ፔፔ ሰይዶ ይዞባቸዋል።
- ማሰታውቂያ -
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ አጋማሹ ሊጠናቀቀት በ45+1 ደቂቃ ላይ የጣና ሞገዶቹ ግብ ማስቆጠር ችለዋል ። በዚህም የመስመር ተጫዋቹ ፍፁም ጥላሁን ከሳጥኑ ዉጭ የመታዉን ኳስ ተከላካዩ ትዕግስቱ አበራ ጨርፎት መረብ ላይ አርፏል።
ሁለተኛዉ አጋማሽ በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ቀጥሎ በ50ኛዉ ደቂቃ ላይ ረጀብ ሚፍታህ ከቀኝ በኩል ያሻገረዉን ኳስ ፍፁም ጥላሁን በግንባሩ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ መልሶበታል። በአጋማሹ በተደጋጋሚ በሀብታሙ ታደሰ እና ፍፁም ጥላሁን ሙከራ ማድረግ የቀጠሉት የጣና ሞገዶቹ በ72ተኛዉ ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዉ ሁለተኛ ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም ከቀኝ በኩል አባይነህ ፌኖ ያሻገረዉን ኳስ ፍፁም ጥላሁን መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል።
በጨዋታዉ ምንም እንኳን በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ተፎካካሪ ይሁኑ እንጅ በሙከራ ረገድ ደካማ የነበሩት ሀምቢቾዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ በአብዱልከሪም ዱግዋ እና አልዓዛር አድማሱ አማካኝነት ሙከራ ማድረግ ቢችሉም በፔፔ ሰይዶ ድንቅ ብቃት ከግብነት ከሽፈዉ ጨዋታዉ በባህርዳር ከተማ 2ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ከጨዋታ ብልጫ ጋር ድሬዳዋ ከተማን 5ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል ።
አመሻሽ 12:00 ሲል በጀመረዉ ጨዋታ በተሻለ የጨዋታ ብልጫ እንቅስቃሴያቸዉን የጀመሩት ኢትዮጵያ መድኖች ከአንድ ሁለት ኢላማቸዉን ያልጠበቁ ሙከራዎች በኋላ በ17ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም ከማዕዘን የተሻማዉን ኳስ የድሬዳዋ ከተማ ተከላካዮች በሚገባ ማፅዳት ባለመቻላቸዉ ምክንያት ኳሱን ያገኘዉ አለን ካይዋ ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
የመክፈቻዋ ጎል ከተቆጠረች በኋላ በ22ተኛዉ ደቂቃ ላይ ሀይደር ሸረፋ ከቆመ ኳስ ወደ ዉስጥ ያሻማዉን ኳስ ብሩክ ሙሉጌታ በግንባሩ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ አብዩ ካሳየ እንደምንም አውጥቶበታል። በ29ነኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ኳስ በዕጅ መነካቱን ተከትሎ የተሰጠዉን ፍፁም ቅጣት ምት አምበሉ ሀይደር ሸረፋ ወደ ግብነት ቀይሮ የክለቡን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።
ሁለት ጎሎች ከተቆጠሩባቸዉ በኋላ ወደ ጨዋታዉ ለመመልስ ጥረት ያደርጉ የነበሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በ37ተኛዉ ደቂቃ ላይ መሐመድ አብዱለጢፍ አሻግሮለት ቻርልስ ሙሰጌ በግባሩ ገጭቶት አቡበከር ባወጣዉ ኳስ ኢላማዉን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በድጋሚ ከሶስት ደቂቃዎች በኋላ አድናን መኪ ከርቀት ድንቅ ሙከራ አድርጎ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ አቡበከር በሚገርም ብቃት ኳሷን አውጥቷት አጋማሹ ተገቧዷል።
ከዕረፍት መልስ ይበልጥኑ የማጥቃት ሀይላቸዉን አጠናክረዉ የቀጠሉት መድኖቸ በ48ተኛዉ ደቂቃ ላይ አለን ካይዋ ከብሩክ ሙሉጌታ በተቀበለዉ ኳስ ድንቅ ግብ አስቆጥሮ መሪነታቸዉን ወደ ሶስት ከፍ ማድረግ ችሏል። አሁንም ጫና ፈጥረዉ መጫወት የቀጠሉት መድኖች በ60ኛዉ ደቂቃ ላይ በጨዋታዉ ላይ ድንቆ ሆኖ ባመሸዉ አለን ካይዋ አማካኝነት አራተኛ ግብ ማስቆጠር ችለዋል ፤ ተጫዋቹም ሀትሪክ መስራት ችሏል።
ድሬዳዋ ከተማዎች አራተኛ ግብ ካስተናገዱ ከአምስት ያክል ደቂቃዎች በኋላ በሱራፌል ጌታቸዉ አማካኝነት ከርቀት ድንቅ ሙከራ ቢያደርጉም የግቡ አግዳሚ መልሶባቸዋል። በቀሪ ደቂቃዎች መድኖች በሙሉ የጨዋታ ብልጫ ተንቀሳቅሰዉ በ90+4 ደቂቃ ላይ በብሩክ ሙሉጌታ አማካኝነት ድንቅ ግብ አክለዉ ጨዋታዉ በኢትዮጵያ መድን 5ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።