የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በፓሪስ 2024 ኦሎምፒክ የማራቶን ወድድር ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ዝርዝር ይፋ አድርጓል።
ባለፉት ሁለት ኦሎምፒኮች ሳይሳተፍ የቀረው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ዳግም ኢትዮጵያን በመድረኩ የሚወክልበትን እድል አግኝቷል።
በወቅታዊ ብቃት ጥሩ አቋም በማሳየት ላይ ከሚገኙት የማራቶን አትሌቶች አንዱ የሆነው የ41 ዓመቱ ቀነኒሳ በቀለ በቡድኑ መካተቱ አይቀርም ተብሎ ይጠበቅ ነበር።
አትሌት ቀነኒሳ ከሳምንታት በፊት በለንደን ማራቶን የ2ኛ ደረጃን ይዞ ካጠናቀቀ በኋላ በኦሎምፒኩ ውጤታማ ለመሆን ዝግጁ መሆኑን ተናግሮም ነበር።
- ማሰታውቂያ -
ቀነኒሳ ከ21 ዓመታት በፊት የመጀመሪያ የዓለም ሻምፒዮና ሜዳልያውን ፓሪስ ላይ ማስመዝገቡ የሚታወስ ሲሆን ከ10 ዓመታት በፊት ደግሞ የመጀመሪያ ማራቶኑን ፓሪስ ላይ መሮጡ አይዘነጋም።
በውድድሩ በተለይም ከኬንያዊው አትሌት ኤሉድ ኪፕቾጌ ጋር የሚያደረገው ትንቅንቅ ከአሁኑ የዓለምን ትኩረት የሳበ ሆኗል።
ከአትሌት ቀነኒሳ በቀለ በተጨማሪም አትሌት ሲሳይ ለማ እና አትሌት ደሬሳ ገለታ ፓሪስ ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ናቸው።
በተጨማሪም አትሌት ታምራት ቶላ እና ኡሰዲን መሐመድ በተጠባባቂነት ተመርጠዋል።
በሴቶች ዘርፍም የአትሌቶች ዝርዝር ይፋ ሲደረግ የማራቶን ባለክብረወሰኗ አትሌት ትዕግስት አሰፋ ፤ የዓለም ሻምፒዮኗ አትሌት አማኔ በሪሶን ጨምሮ አትሌት መገርቱ አለሙ ተካተዋል።
አትሌት ጎይተቶም ገብረስላሴ እና አትሌት ቡዜ ድሪባ በተጠባባቂነት የተያዙ አትሌቶች ናቸው።