በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ25ተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ዕለት መርሐግብር የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወላይታ ዲቻን 5ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
ቀን ዘጠኝ ሰዓት ሲል በጀመረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ከጨዋታዉ መባቻ አንስቶ ብልጫ ወስደዉ ሲጫወቱ ገና በጊዜም በአማካዩ ሲሞን ፒተር እና የፊት መስመር ተጫዋቹ ኪቲካ ጀማ አማካኝነት ጥሩ የሚባሉ ሙከራዎችን አድርገዉ በ20ኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር ችለዋል።
በዚህም ሳይመን ፒተር ከግራ ወደ ውስጥ የላካትን ኳስ ተከላካዩ ፍፁም ግርማ በራሱ መረብ ላይ አሳርፎ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ጨዋታዉን እንዲመሩ አስችሏል። ከዚች የመጀመሪያ ግብ መቆጠር በኋላ በተደጋጋሚ ብልጫ በመዉሰድ ሙከራዎችን ማድረግ የቀጠሉት ባንኮች ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላም መሪነታቸዉን ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል። በዚህም ሳይመን ፒተር ከኋላ መስመር የተቀበለዉን ኳስ ለባሲሩ ዑመር አቀብሎት ተጫዋቹም ኳሷን በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሯል።
- ማሰታውቂያ -
በተደጋጋሚ የባንኮችን ሙከራዎች በመከላከል የጨዋታ ጊዜያቸዉን እያሳለፉ የነበሩት ዲቻዎች በ38ተኛዉ ደቂቃ ላይ በብዙዓሁ ሰይፉ አማካኝነት ብቻ ተጠቃሽ ሙከራ አድርገዉ ፤ በ44ተኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ግብ ሶስተኛ ግብ አስተናግደዉ አጋማሹ ተጠናቋል። በዚህም በተጠቀሰዉ ደቂቃ ኪቲካ ጀማ ከሱለይማን ሀሚድ የተሻገረለትን ኳስ ለሳይመን ፒተር አቀብሎት ተጫዋቹም ኳሷን በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሯል።
ከዕረፍት መልስ ይባስኑ ተጠናክረዉ የተመለሱት ተጠናክረዉ የተመለሱት ባንኮች በ55ተኛዉ ደቂቃ ላይ አራተኛ ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም በዕለቱ ድንቅ የነበረዉ ሳይመን ፒተር ከኪቲካ ጀማ የተቀበለዉን ኳስ በቀኝ መስመር በኩል ለኤፍሬም ታምራት አቀብሎት ተጫዋቹም ኳሷን ወደ ግብነት መቀየር ችሏል። በዚህ ሂደት በቀጠለዉ ጨዋታ ባንኮች በ77ተኛዉ ደቂቃ ላይ በኪቲካ ጀማ አማካኝነት አምስተኛ ጎል ማስቆጠር ችለዋል።
ደቂቃዉ የጨመረ በሄደ ቁጥር እንቅስቃሴዉ እየቀነሰ በቀጠለዉ ጨዋታ እጅግ ደካማ የነበሩት ዲቻዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ በአበባየሁ ሀጂሶ እና ብዙዓሁ አማካኝነት ጥሩ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዉ 5ለ0 በሆነ ውጤት ተሸንፈዋል።
በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ፋሲል ከነማ ወልቂጤ ከተማን 1ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል ።
ምሽት 12:00 ሲል በዝናብ ታጅቦ በተከናወነዉ ጨዋታ ሜዳዉ ኳስን በነፃነት ለማንሸራሸር አስቸጋሪ ሆኖ የነበረ ሲሆን ፤ በዚህም በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ደቂቃዎች በሙከራ ረገድም ሁለቱም ክለቦች ይህ ነዉ የሚባል ሙከራ ሳያደርጉ ቆይተዉ 15ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግን ግብ ተቀጥሯል። በዚህም በተጠቀሰዉ ደቂቃ የመስመር ተጫዋቹ ቃልኪዳን ዘላለም ከጋቶች የተቀበለዉን ኳስ ለጌታነህ ከበደ አቀብሎት ተጫዋቹም ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቧ መቆጠር በኋላ በተደጋጋሚ በጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ ቡድን ሶስተኛዉ የሜዳ ክልል ይደርሱ የነበሩት ወልቂጤዎች አደጋዎችን በመፍጠር ረገድ ግን ደካማ ሁነዉ ግማሽ ሰዓት ያክል ተቆጥሯል። በዚህም በአጋማሹ በ30ኛዉ ደቂቃ ላይ ተመስገን በጅሮንድ ከርቀት ድንቅ ሙከራ ቢያደርግም የግብ ዘቡ ሚካኤል ሳማኬ ኳሷን አዉጥቷል። በዚህ ሁኔታ በቀጠለዉ ጨዋታ በአጋማሹ ተጨማሪ ሙከራ ሳይደረግ ክለቦቹ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ሙሉዓለም መስፍን ከርቀት ወደ ግብ ልኳት ግብ ጠባቂዉ ሳማኪ እንደምንም ባወጣት ኳስ በጀመረዉ ሁለተኛዉ አጋማሽ በ60ኛዉ ደቂቃ ላይ ክትፎዎቹ ጌታነህ ከበደ ወደ ግብ የሞከራትን ኳስ የግብ ዘቡ መሳይ ሲመልስ ያገኘዉ ቃልኪዳን በድጋሚ ቢሞክርም ነገር ግን ተከላካዩ ወንድማገኝ አዉጥቶበታል።
በጨዋታዉ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ የአቻነት ግብ ፍለጋ መታተር የቀጠሉት ወልቂጤዎች በአንድ ሁለት አጋጣሚ ዕድሎችን ማግኘት ቢችሉም መጠቀም ሳይችሉ ቀይተዉ በጨዋታዉ 1ለ0 በሆነ ዉጤት ተሸንፈዋል።