በአራተኛ ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ቀን ጨዋታ የተገናኙት አርባምንጭ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና ጨዋታቸዉን በአቻ ዉጤት አጠናቀዋል።
ያን ያህል ለዕይታ ማራኪ ባልነበረዉ የመጀመሪያዉ አጋማሽ አርባምንጭ ከተማዎች ረጃጅም ኳሶችን ለፊት መስመር ተጫዋቾቻቸዉ በመጣል አንዳች ነገርን ለመፍጠር ሲጥሩ በተቃራኒው ሀድያ ሆሳዕናዎች በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ለመድረስ ሲጥሩ ተስተውሏል።
- ማሰታውቂያ -
በዚህ ሂደት የቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም አንድም ተጠቃሽ ለግብ የቀረበ አደገኛ ሙከራ ሳይስተዋልበት አጋማሹ ይጠናቀቅ እንጅ ሀድያዎች በጥቂቱም ቢሆን ብልጫ ለመዉሰድ ሲችሉ በተለይ በአማካዮቹ ፍቅረየሱስ እና ብሩክ ማርቆስ ተደጋጋሚ ኳሶች ለአጥቂዎቹ ቢደርሱም የሀድያ የፊት መስመር ተጫዋቾች ጥሰዉ ለመግባት ሲቸገሩ ተስተዉሏል። በዚሁ የጨዋታ መንገድም ሁለቱም ክለቦች ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ምንም እንኳን ጥቂት የተሻሉ ነገሮች የነበሩ ቢሆንም እንደ መጀመሪያዉ አጋማሽ ሁሉ ያን ያህል በሙከራ የታጀበ ነበር ለማለት አያስደፍርም። በጨዋታው 55ኛ ደቂቃ ላይ ግን ቡጣቃ ሻመና ከግራ መስመር በኩል ያሻገራትን ኳስ ወርቅይታደስ አበበ ሲሞክር የግራ መስመር ተከላካዩ ሔኖክ አርፌጮ እንደምንም ያወጣት ኳስ በጨዋታው ተጠቃሽ የመጀመሪያ ሙከራ ነበረች ማለት ይቻላል።
ከዚህ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ተቀይረው ወደ ሜዳ በማስገባት ከጨዋታዉ አንዳች ነገርን ለማግኘት ሲሞክሩም ተስተዉሏል። በዘዚህም በጨዋታው ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለዉ የመስመር ተጫዋቹ ቡጠቃ ሻመና ያቀበለዉን ኳስ አጥቂዉ አህመድ ሁሴን ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም በግብ ጠባቂዉ ጥረት ኳሷ ወጥታለች። በሙከራም ሆነ በጨዋታ ረገድ ደካማ የነበረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም 0ለ0 በሆነ አቻ ዉጤት ተጠናቋል።