በቤትንኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአራተኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ ሀይቆቹ ክትፎዎቹን 4ለ3 በሆነ ዉጤት አሸንፈዋል።
በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ ጥሩ እንቅስቃሴ ይስተዋልበት በነበረዉ የጨዋታው መጀመሪያ አካባቢ ገና በ8ኛዉ ደቂቃ ላይ ሀይቆቹ መሪ መሆን ችለዋል። በዚህም የመስመር ተጫዋቹ አሊ ሱለይማን ያቀበለዉን ኳስ አጥቂዉ ሙጅብ ቃሲም ሲሞክር ግብ ጠባቂዉ ሲመልሰዉ በአቅራቢያው የነበረዉ ኤፍሬም አሻሞ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
ገና በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ ላይ ግብ ካስተናገዱ በኋላ በቶሎ የአቻነቷን ግብ ለማግኘት ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ክትፎዎቹ በ12ኛዉ ደቂቃ ላይ በአጥቂው ጌታነህ ከበደ አማኬኝነት ጥሩ ለግብ የቀረበ ሙከራን ማድረግ ችለዉ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካላቸዉ ቀርቶ በተቃራኒው ግብ አስተናግደዋል። በዚህም በ16ኛዉ ደቂቃ ላይ አሊ ሱለይማን ከርቀት የሞከረዉ ኳስ የግቡ ቋሚ ሲመልሰዉ በቅርበት የነበረዉ ሙጅብ ቃሲም አስቆጥሮ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ለዜሮ ከፍ አድርገዋል።
- ማሰታውቂያ -
ወደ ጨዋታዉ ለመመለስ በቻሉት መንገድ ጥረት ማድረጋቸውን የቀጠሉት ወልቂጤዎች በ31ኛዉ ደቂቃ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም ሳምሶን ጥላሁን ከርቀት አክርሮ ማስቆጠር ችሏል። ወደ ጨዋታዉ የሚመልሳቸውን ግብ ማስቆጠር ከቻሉ በኋላ ተጭነዉ መጫወት የቀጠሉት ወልቂጤዎች አጋማሹ ሊጠናቀቅ ባለበት ሰዓት ተጨማሪ የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም የኋላሸት ሳሙኤል ያቀበለውን ኳስ አጥቂዉ ጌታነህ በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮ ክለቡን አቻ አድርጓል።
ከዕረፍት መልስ ሁለቱም ቡድኖች በጥሩ የጨዋታ እንቅስቃሴ ጥሩ ጥሩ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን ተሳክቶላቸው ሶስተኛ ግብ በማስቆጠሩ ግን ሀይቆቹ ቀዳሚ ነበሩ በዚህም ተከላካዩ ሰለሞን ወደሳ በረጅሙ ያሻገረለትን ኳስ አጥቂው ሙጅብ ቃሲም ወደ ግብነት ቀይሮ ለራሱ ሁለተኛውን እንዲሁም ለክለቡ ሶስተኛዉን ግብ ማስቆጠር ችሏል።
ከደቂቃዎች በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን ነገር ግን የተሻሉ የነበሩት ሀይቆቸለ መሪነታቸውን ወደ አራት ከፍ ያደረጉበትን ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም በ75ኛዉ ደቂቃ ላይ የመስር ተጫዋቹ አሊ ሱለይማን በመልሶ ማጥቃት ያገኘዉን ኳስ ለሙጅብ አሻግሮለት አጥቂዉ በግንባሩ በመግጨት ግብ አስቆጥሮ በግሉ ሀትሪክ መስራትም ችሏል።
በጨዋታው መገባደጃ ወቅትም የሀዋሳዉ ተከላካይ ኳስ በእጁ መንካቱን ተከትሎ የተገኘዉን ፍፁም ቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ አስቆጥሮ ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 4ለ3 አሸናፊነት ተጠናቋል።