በ2016 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ 30ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ዕለት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ በአሊ ሱለይማን ሁለት ጎሎች ታግዞ ወላይታ ዲቻን ሁለት ለዜሮ በማሸነፍ አመቱን በድል ሲደመድም ፤ በተመሳሳይ ቀን ዘጠኝ ሰዓት ላይ በተደረገዉ ጨዋታም ሀድያ ሆሳዕና በውድድር አመቱ ዘጠነኛ ጨዋታዉን ማሸነፍ የቻለበትን ውጤት አስመዝግቧል።
አስቀድሞ ቀን ሰባት ሰዓት ሲል በሀዋሳ ሰዉ ሰራሽ ሜዳ በተደረገዉ የሀዋሳ ከተማ እና ወላይታ ዲቻ ጨዋታ ገና በጊዜ በሶስተኛዉ ደቂቃ እና በ47ተኛዉ ደቂቃ ላይ ኤርትራዊዉ አጥቂ አሊ ሱለይማን የውድድር አመቱን አስራ ስምንተኛ እና አስራ ዘጠነኛ ጎሎቹን አስቆጥሮ ክለቡ ሀዋሳ ከተማ ጨዋታዉን ሁለት እንዲያሸንፍ ማድረግ ችሏል።
ዉጤቱን ተከትሎ በአሰልጠኝ ዘርዓይ ሙሉ እየተመራ በውድድር አመቱ ከከወናቸዉ ሰላሳ ጨዋታዎች መካከል አስራ አንዱን አሸንፎ በአስራ አንዱ ተሸንፎ ስምንቱን በአቻ ዉጤት ማጠናቀቅ የቻለዉ ሀዋሳ ከተማ 41 ነጥቦችን በመሰብሰብ ውድድር አመቱን ማጠናቀቅ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
በተመሳሳይ በዚያዉ ስታዲየም ቀን አስር ሰዓት ሲል በጀመረዉ ጨዋታ የፊታችን ዕሁድን በመዲናችን አዲስ አበባ የጥሎ ማለፍ የፍፃሜ ጨዋታዉን ከወላይታ ዲቻ ጋር የሚከዉነዉ ኢትዮጵያ ቡና ወሳኝ የሆኑ ተጫዋቾቹን አሳርፎ ጨዋታዉን የጀመረ ሲሆን በተመሳሳይ ሀድያም በርከት ላሉ ወጣት እና የመሰለፍ እድል በአመቱ ላላገኙ ተጫዋች የመሰልፍን ዕድል ሰጥቶ ወደ ሜዳ ገብቷል።
በዚህ ሂደት ጨዋታቸዉን በጀመሩት የሁለቱ ክለቦች መርሐግብር አንተነህ ተፈራ ለቡናማዎቹ የቀዳሚነት ግብ ማስቆጠር ችሎ የነበረ ቢሆንም ለሀድያ የኋላሸት ሰለሞን ሁለት ጎሎችን አስቆጥሮ ሀድያ ከመመራት ተነስቶ በውድድር አመቱ ያሸነፋቸዉን የጨዋታ መጠኖች ዘጠኝ አድርሶ አመቱን ቋጭቷል። ዉጤቱን ተከትሎ የያሬድ ገመቹ ቡድን ሀድያ ሆሳዕና በ41 ነጥብ የሰንዘረዡ ወገብ ላይ ሲቀመጥ ፤ ተሸናፊዉ ኢትዮጵያ ቡናም በ51 ነጥብ አመቱን ደምድሟል።