” አወዳዳሪው አካል የሀገሪቱን እግርኳስ ህግ በሚጻረር መልኩ ያዘዋወርናቸውን ተጨዋቾች እንዳንጠቀም በማድረግ 6 ነጥብ አሳጥቶናል”
ለገጣፎ ለገዳዲ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተሳታፊ የሆነው ለገጣፎ ለገዳዲ ህገወጥ ድርጊት ፈጽሞብኛል በማለት በሊግ ኩባንያው ላይ የሚያሰማውን ተቃውሞ አጠናክሮ ቀጥሏል።
ክለቡ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዛሬ በላከው ደብዳቤ ከሲዳማ ቡናና መቻል ጋር የነበረው ጨዋታ ውጤት ተሽሮ እንዲደገም ጠይቋል። “ከሲዳማ ቡና ጋር ከነበረው ጨዋታ በማስገደድ መብታችንን ጥሰው እንድንጫወት ተደርገናል ከመቻል ጋር በነበረውም ጨዋታ ቡድን መሪው የተጨዋቾችን ስም ዝርዝር ልኮ እያለ አይቻልም በማለት አምስት ህጋዊ ተጨዋቾች ብቻ ናቸው ያሉት በሚል ሌሎቹ ከመልበሻ ቤት እንዳይወጡ በማድረግ ፎርፌ እንዲሰጥ አድርገውብናል በአጠቃላይ
አወዳዳሪው አካል የሀገሪቱን እግርኳስ ህግ በሚጻረር መልኩ ያዘዋወርናቸውን ተጨዋቾች እንዳንጠቀም በማድረግ 6 ነጥብ አሳጥቶናል” ሲሉ ከሰዋል።
ክለቡ በአራት ዓበይት ጉዳዮች ላይ ባነጣጠረው ደብዳቤው ” አወዳዳሪ አካሉ ህግ በመጣስ ያጣነው የሁለቱ ጨዋታ ነጥብ እንዲታይልን ፤በተጨዋቾቻችን ላይ የደረሰው እንግልትና ሞራላዊ ጥሰት ታይቶ ካሳ እንዲደረግልን፤ አሰልጣኙና ቡድን መሪውን ለምን መብታችሁን ጠየቃችሁ ብለው ያስፈራሩትን እንዲያቆሙ፤ የክለቡ አመራሮች ደውለው ሲያናግሩ ቀና ምላሽ አለማግኘታቸው ታይቶ ህጋዊ ምላሽ እንዲሰጠን እንጠይቃለን” ሲል ፌዴሬሽነን ጠይቋል።
- ማሰታውቂያ -
የክለቡ የደብዳቤ ማሳረጊያ በጠንካራ ቃላት የታጀበ ሲሆን “ከላይ የጠየቅነው ጥያቄ ምላሽ ካላገኘን በቀጣዩ ጨዋታ ላይ ለመገኘት እንቸገራለን” ሲል ላቀረበው የፍትህ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጠው አሳስቧል። ፌዴሬሽኑም እስካሁን የተጣሰውን መብታችንን እንዲያስከብርልን አወዳዳሪ አካሉም ከተመሳሳይ ድርጊቱ እንዲቆጠብ እንዲደረግልን አበክረን እንጠይቃለን” ሲል አሳስቧል።
በሊግ ኩባንያው የውድድር መርሃግብር መሠረት በ16ኛው ሳምንት መርሃግብር ለገጣፎ ለገዳዲ ከሀዋሳ ጋር የዛሬ ሳምንት ሰኞ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ እንደሚጫወቱ ታውቋል።