የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር ጨዋታዎች በዛሬው በመቻል እና ሀድያ ሆሳዕና ጨዋታ በይፋ ተጀምረዋል ።
በ15ኛው ሳምንት በኢትዮጵያ መድኅን የተረቱት ሀድያ ሆሳዕናዎች በጨዋታው ከተጠቀሙት የመጀመሪያ ምርጥ 11 ሶስት ለውጦችን በማድረግ በፍሬዘር ካሳ ፣ ሳምሶን ጥላሁን እና ተመስገን ብርሀኑ ምትክ ቃልአብ ውብሸት ፣ ግርማ በቀለ እና ሰመረ ሀፍተይ ተሰልፈዋል ።
በመቻል በኩል ደግሞ በ14ኛው ሳምንት
ከኢትዮጵያ ቡና አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ላይ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ግሩም ሀጎስ ፣ ኢብራሂም ሁሴን ፣ ግርማ ዲሳሳ እና በረከት ደስታን በዳዊት ማሞ ፣ አህመድ ረሺድ ፣ አሚን ነስሩ እና ሳሙኤል ሳሊሶ ምትክ አሰልፈዋል ።
ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ በዛሬው ዕለት በመከበር ላይ ያለውን 127ኛውን የአድዋ ድል አስመልክቶ ደማቅ ስነ ስርዓት ተካሂዷል ።
- ማሰታውቂያ -
በተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በጀመረው ጨዋታ መቻሎች በሁለቱም በኩል ጭቃማ ከሆነው ሜዳ ጋር እየታገሉ ወደ ፊት ለመድረስ ጥረቶችን አድርገዋል ።
የተሻለ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል የደረሱት መቻሎች በ11ኛው ደቂቃ መሪ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል ።
ግሩም ሀጎስ ከግራ መስመር አቅጣጫ ያሻገረውን ኳስ እስራኤላውያን እሸቱ አግኝቶ ለማስቆጠር ያደረገውን ጥረት ግብ ጠባቂው ለጥቂት ማዳን ቢችልም አምበሉ ሄኖክ አርፊቹ ኳስ ከግብ ለማራቅ በሚጥርበት ወቅት ከነአን ማርክነህ ተደርቦ ኳስ እና መረብ ተገናኝቷል ።
ግቡ ከተቆጠረ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ መቻሎች ሁለተኛ ግብ አግኝተዋል ። በአጋጣሚው ፍፁም አለሙ ከመሀል የሜዳው ክፍል ከሄኖክ አርፊቹ ጀርባ የተጣለውን ኳስ በረከት ደስታ አግኝቶ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይም መቻሎች በማጥቃቱ ረገድ የተሻሉ ሆነው መቀጠል ችለዋል ። በዚህም በ31 እና 33ኛው ደቂቃ ላይ በሀይሉ ግርማ እና በረከት ደስታ ከሳጥን ውጪ የሞከሯቸው ኳሶች የሚጠቀሱ ነበሩ ።
ሀድያ ሆሳዕናዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥሩ መንቀሳቀስ በጀመሩባቸው ደቂቃዎች ላይ የመጀመሪያ ግባቸውን አስቆጥረዋል ። ባዬ ገዛኸኝ ከሳጥኑ የቀኝ መስመር አቅጣጫ ወደ መሀል የቀነሰውን ኳስ ነፃ የነበረው ፀጋዬ ብርሀኑ በ37ኛው ደቂቃ ላይ ከመረብ አሳርፎታል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች በግቡ በመነቃቃት የአቻነቱን ግብ ፍለጋ ጥረቶችን ማድረግ ቢችሉም ወደ መቻል የግብ ክልል ከመድረስ አንፃር ግን ደከም ብለው ነበር ።
የመጀመሪያው አጋማሽም በመቻል የ2 ለ 1 መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ ሀድያ ሆሳዕናዎች ወደ ፊት በመድረስ የተሻሉ ሆነው የታዩበት ቢሆንም የጠራ የግብ ዕድል ከመፍጠር አንፃር ግን ክፍተቶች ነበሩባቸው ።
በአጋማሹ በተለይም በረጃጅም ኳሶች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሲጥሩ የነበሩት መቻሎች በ57ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን ከፍ የሚያደርጉበትን ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ።
ከሀድያ ሆሳዕናዎች ያልተሳካ የማዕዘን ምት የተገኘውን ኳስ ከነአን ማርክነህ በረጅም የላከለትን ኳስ በረከት ደስታ ኳሱን እየገፋ ሄዶ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም ኳሱን ከግቡ አናት በላይ ልኮታል ።
ሀድያ ሆሳዕናዎች ምንም እነኳን ሜዳው ኳስ ለመያዝ አስቸጋሪ ቢሆንም በአንድ ሁለት ቅበብሎች በተደጋጋሚ የተጋጣሚያቸውን የኋላ ክፍል አልፈው ለመግባት ያደረጓቸው ጥረቶች እስከፍፃሜው ሳይሳካ ቀርቷል ።
በአጋማሹ በሀድያ ሆሳዕና በኩል ብቸኛ የነበረው ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ በ80ኛው ደቂቃ ላይ ብርሀኑ በቀለ ከሳጥን ውጪ ቢመታውም ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ ተቆጣጥሮታል ።
በመጨረሻም ጨዋታው በመቻል የ2 ለ 1 አሸናፊነት ፍፃሜውን አግኝቷል ።
በ17ኛው ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው መጋቢት 3 (እሁድ) 10:00 ላይ መቻል አዳማ ከተማን ሲገጥም መጋቢት 2(ቅዳሜ) ምሸት 1:00 ጀምሮ ሀድያ ሆሳዕና ከሲዳማ ቡና ይጫወታል ።