ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 15ኛ ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች አራት ጨዋታዎች በመሸናነፍ ሶስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ 13 ጎሎች ተቆጥረዋል። የጎሎቹ አገባብ ሶስቱ በፍፁም ቅጣት ምት ቀሪዎቹ በጨዋታ የተቆጠሩ ናቸው። በሳምንቱ 23 ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች በቢጫ ካርድ ሲገሰፁ አንድ ተጫዋች ቀይ ካርድ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ አርብ ሐሙስ የካቲት 23 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በተጫዋቾች ፍሬዘር ካሳ(ሀዲያ ሆሳዕና) ቀይ ካርድ አይቶ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ 1 ጨዋታ እንዲታገድ እንዲሁም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የዕለቱን ዳኛ አፀያፊ ስድብ ስለመሳደቡ ሪፖርት የቀረበበት ለፈፀመው ጥፋት ከተቀጣው ቅጣት በተጨማሪ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 3/ሶስት/ ጨዋታ እንዲታገድና ብር 3000/ሶስት ሺ/ እንዲከፍል ሲወሰን ሙና በቀለ(አርባምንጭ ከተማ) እና መናፍ ዐወል(ፋሲል ከነማ) የተለያዩ አምስት ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቅቂያ ካርድ የተመለከቱ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል።
ለገጣፎ ለገዳዲ ክለቡ ከመቻል ጋር ባደረገው የ15ኛ ሳምንት እግር ኳስ ጨዋታ ቡድኑ ባለማቅረቡ ጨዋታው ሳይካሄድ ስለመቅረቱ ሪፖርት ተደርጓል። በመሆኑም ከለቡ በፎርፌ ተሸናፊ ሆኖ 0 ነጥብና 3 የግብ ዕዳ እንዲመዘገብበትና ተጋጣሚው መቻል በፎርፌ አሸናፊ ሆኖ 3 ነጥብና 3 ተደማሪ ግብ እንዲመዘገብለት እንዲሁም ተጨማሪ የዲሲፕሊን እርምጃዎች የለገጣፎ ቡድን ለፌዴሬሽን ያስገባው ኣቤቱታ ውሳኔ እስኪሰጠው ድረስ በይደር እንዲቆይ ተወስኗል፡፡