“እግር ኳስ በደከምኩት ልክ ከፍሎኛል ብዬ አላምንም”
“በተጨዋቾች ዝውውር የሚገርመኝ የጨዋታ ዘመናቸውን ከአንድ አሰልጣኝ ጋር የሚጨርሱ ተጨዋቾች ብዙ መሆናቸው ነው”
ሚሊዮን ጉግሳ/ሚሊሺያ/ አሰልጣኝና የእግርኳስ ተንታኝ
በስፔን ላሊጋ አትሌቲኮ ማድሪድ ከባርሴሎና ተጠባቂ ጨዋታቸውን እያደረጉ ነው የመጀመሪያ ጨዋታ ሊጠናቀቅ በተቃረበበት ሰአት ላይ የባርሴሎናው ሰርጂዮ ሮቤርቶ በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ይወጣል… ጨዋታው ገና 45 ደቂቃ ይቀረዋል የብስራት ኤፍ ኤም 101.1 ጋዜጠኞች ጨዋታውን በቀጥታ ስርጭት እያስተላለፉ ነበር ከነኚህ መሃል በትንታኔው ጥንካሬ የሚታወቀው የዛሬ እንግዳችን “ሜሲና ሱዋሬዝ አይነኩም ነገር ግን ሊጉን ለመልመድ እየሞከረ ያለው ፊሊፕ ኩቲንሆ ይወጣና ኔልሰን ሴሜዶ ይገባል” ሲሉ ሁሉም ተያዩ ፈጠንክ ባይሆንስ?ያሉትም አልጠፉም። ሁለተኛው 45 ደቂቃ ሊጀመር ተጨዋቾቹ ወደ ሜዳ ሲገቡ ኩቲንሆ አልተመለሰም ኔልሰን ሴሜዶ ሊቀየር ወደ ሜዳው ጠርዝ መጣ…. ጋዜጠኛ ዮናስ አዘዘ ታዲያ ትላንት የታየ ጨዋታ ነው እንዴ የምናስተላልፈው ሲልም መገረሙን ገለጸ…እንግዳችን ተንታኙና አሰልጣኝ ሚሊዮን ጉግሳ /ሚሊሺያ/ እንዲህ ነው… ነገር ግን በኢትዮጲያ ፕሪሚየር ሊግ የዲ ኤስ ቲቪ የቀጥታ ስርጭት ላይ ሲጠበቅ የለም “ማንም ሃላፊነቱን ባልወሰደበት የሚጠየቁ ሰዎች ባልታወቁበት መዘለሌ ቅር አሰኝቶኛል” ሲል ለሃትሪክ ገልጿል። ከዮሴፍ ከፈለኝ ጋር ቆይታ ያደረገው ሚሊሺያ ዘርፈ ብዙ በሆነ ግምገማው እግርኳሱን፣አሰልጣኞችና ተጨዋቾቹን፣ተመልካቹንና አመራሮቹን በአጠቃላይ እግርኳሳዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚሰማውን ተናግሯል።
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስ ተንታኝ፣ጋዜጠኛወይስአሰልጣኝ? የቱይመችኃል?
ሚሊዮን፡- ከሶስቱ ጋዜጠኝነቱ የኔ የስራ ድርሻ አይደለም አሰልጣኝነቱና ተንታኝነቱ ግን በጋራ የተያያዘ ነው የአሠልጣኝ ስራ ነው መተንተን.. ባለፉት 6 አታት በተንታኝነት ሰርቻለው፤የካፍ የቢ ላይሰንስ አለኝ በሬዲዮ የ6 አመት ስራዬ አንድም ቀን ሆስት አድርጌ አላውቅም ኮመንተሪም አልሰራሁም ተሳስቼም አንድም ቀን ዜና ሰርቼ አላውቅም አብረውኝ ከሚሰሩ ጋዜጠኞች አንድ ዜና ቀድሜ ባገኝ ለነርሱ እሰጣለሁ እንጂ ዜና የመስራት ልማድ የለኝም በቀጥታ የሬዲዮ ስርጭት ላይ ግን ትንተና እሰጣለሁ አሰልጣኞች የጨዋታ ማንበብ አቅማቸው እንዲጨምር ትንተና ላይ መስራት ይጠቅማል ብዬ አስባለው ከጋዜጠኝነቱ ውጪ ሁለቱ የኔ ሙያ ናቸው ማለት እችላለሁ፡፡
ሀትሪክ፡-የት የት አሰለጠንክ?
ሚሊዮን፡- በስልጠናው አለም በፍጥነት ከማልጠብቀው ቦታ ነው የጀመርኩት… በጣም ምቹ ባልሆነ አገር እግር ኳስ ውስጥ በኢትዮጵያ ቡና የስልጠና ህይወቴን እጀምራለሁ ብዬ አልሜም አላውቅም ነገር ግን ስልጠናን የጀመርኩት በኢትዮጵያ ቡና የሴቶች ቡድን አሰልጣኝ ሆኜ ነው በርግጥ ከአሰልጣኝ ጳውሎስ ጌታቸው ጋር ከ1999 ጀምሮ አብሬው እያገዝኩ ስሰራ ቆይቻለሁ 2001 ግን ዋናውን ቡድን ሲረከብ የሴቶቹ ኃላፊነቱን ተረክብኩ ኮልፌ ቀራንዮን አሰልጥኛለሁ ከአሰልጣኝ ፈቃደ ትጋ ጋር በመሆን ከ1ኛ ዲቪዚዮን ብሔራዊ ሊግ እንዲገባ አድርገናል በህይወቴ የማልረሳው ምርጥ ስራ የሰራሁበት ቦታ ነው በከፍተኛ ሊግ በአራዳ ክ/ከተማም ሰርቻለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ከኢትዮጵያ ቡና የተሰናበትክበት መንገድም ይገርመኛል ሻምፒዮን ቡድን ሰርተህ ተሰናበትክ?
ሚሊዮን፡- ሳይገባኝ ያገኘሁትን እድል ሲገባኝ አጥቼዋለው ብዬ ነው የማሰበው በ2001 የኢትዮጵያ ቡና ሴቶች ሻምፒዮን ሳደርግ በምን አይነት አቅም ነው ብዬ አስባለሁ አሁን መለስ ብዬ ሳስበው እንኳን ሻምፒዮንስ የሆነ ቡድን ወራጅ ቀጠና ውስጥ ያለ ቡድን የማሰልጠን አቅም እንደሌለኝ ነው የሚገባኝ በዚህ አቅሜም ዋንጫ አንስቻለሁ ይሄ የኳሱን ስታንዳርድ የሚያሳይ ይመስለኛል ሻምፒዮን በመሆኔ ስንብት ነው፡፡ እንዴት ደፍረህ ዋንጫ ታነሳለህ የሚል ነው የሚመስለው ዋንጫ በነሳሁ በነጋታው ከቡድኑ ተሰናብቻለሁ፡፡ በወቅቱ የቀረበው ምክንያት የዋናው ቡድን አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ የራሱን ኮቺንግ ስታፍ ማዋቀር ስለፈለገና በርሱ ስላልተፈለከ ነው የሚል ነበር ከገ/መድህን ጋር ግን ተገናኝቼ አላወራሁም የተባባልነውም ነገር የለም በቢሮ ስራ የተሰራ ይሁን ሌላ ምክንያት ሳይገባኝ ነው የተሰናበትኩት…. ከረጅም ጊዜ በኋላ ግን ከክለቡ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ፈቃደ ማሞ ጋር በእግር ኳስ ጉዳይ ላይ ለማውራት ቢሯቸው ተገኝቼ ስናወራ ቡና ሰርቼ ነበር ስላቸው አላመኑኝም ቡና መስራቴን አያውቁም ብዙ ካወራን በኋላ ግን አስታወሱኝና ለምን ለቀቀ ብዬ ስጠይቅ የወቅቱ ስራ አስኪያጅ የተሻለ ሥራ አግኝቶ መሄዱን እንደነገራቸው ገልፁልኝ እኔ ግን የሄድኩት ወደ እናቴ ቤት ነበር/ሳቅ/
ሀትሪክ፡- ለዋንጫ ሳይሆን ለወረደ ቡድን የሚሆን አቅም አልነበረኝም ካልክ ማሰናበታቸው ተገቢ አይደለም?
ሚሊዮን፡- በዚህ መረዳት ከሆነ የምማርበትን እድል ሰጥተውኛል…. ግንኮ አቅሜን ሊገመግሙ ቀርቶ መስራቴንኮ አያውቁም /ሳቅ/ የሚመዝኑት በውጤት ብቻ ነው የሚሆነው በዚህ ደግሞ የሊጉ ሻምፒዮን ነኝ ዛሬ የደረስብኩበትን አይቼ ትላንቴን ሳስታውስ ነው ያንን ያልኩት እንጂ በወቅቱማ 1ኛ ነኝኮ… ያውም ሻምፒዮን/ሳቅ/
ሀትሪክ፡-ሌላ ገጠመኝ ላስታውስህ የአዲስ አበባ ከተማ ሻምፒዮን ሆነህ ምርጥ አሰልጣኝ ተብለህ ተሸለምክ… ግን ለአዲስ አበባ ምርጥ አሰልጣኝነት 2ኛ የወጣው ተመረጠ?
ሚሊዮን፡- ሌላ ሰው ላይ ተከስቶ አላየሁም የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ባዘጋጀው ውድድር ላይ ከኢትዮጲያ ቡና ጋር ሻምፒዮን በመሆኔ የሴቶች የአመቱ ምርጥ አሰልጣኝ ብለው መረጡኝ በኋላ ግን የአዲስ አበባ ምርጥን የማሰልጠን ዕድል የተሰጠው 2ኛ ለወጣው አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ነበር…ይሄ ደግሞ የአሰልጣኙን ዕድገትን የሚጎትት ይሆናል የሚረባውን የአሰልጣኝነት ዕድል ከልክለውኝ የማይጠቅመውን ወረቀት ሰጡኝ በዚህ መሠል ስራ ወደኋላ የሚቀሩ ባለሙያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ታምኖ መስተካከል አለበት እንደውም በብቃት በምፈልገው ልክ ላለመቀጠሌ ደግሞ ይሄ ምክንያት ትልቁ ድርሻ ይወስዳል። ብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ ካሉ ተጨዋቾች መሃል ከ14 በላይ የአዲስ አበባ ምርጥ ተሰላፊዎች በመሆናቸው ውድድሩ ባላንስ አያደርግም ከአዲስ አበባ ከፍ ብሎ የኢትዮጲያ ሻምፒዮን የመሆን ዕድል ስለነበረው ይህን ከልክለውኛል የኢትዮጲያ ምርጡ አሰልጣኝ ነኝ ብዬ ለብሄራዊ ቡድን ለመወዳደር የነበረኝን ዕድል አጥቻለሁ ከዚህ ዕድል ሁሉ ነው የታገድኩት ይሄን መቼም አልረሳውም
ሀትሪክ፡ ከኛ ሀገር እግር ኳስ ባይኖርብለህየምትመኘው?
ሚሊዮን፡- ስልጠናው ላይ ብዙ የምታዘበው ነገር አለ እግር ኳስ የአሰልጣኞች ነው ብዬ አምናለሁ በዘመናዊ እግር ኳስ መሪዎቹ አሰልጣኞች ናቸው በኛ ሀገር ግን አሰልጣኝ ተደርጎ የሚታሰበው ቴክኒካል ኤሪያ ላይ የሚቆመውን አሰልጣኝ ብቻ ነው ከአሰልጣኝ ጀርባ በርካታ ወሳኝ ባለሙያዎች አሉ በኛ ሀገር ግን ያልተዘጋጁ ሰዎች በቀላሉ የፕሪሚየር ሊጉ አሰልጣኝ ሲሆኑ እመለከታለሁ ይሄ ስጋት ነው፡፡ አሁን ይህ ስሜት ወደ ተጨዋቹ እየመጣ ነው… ብዙ አሰልጣኞች ዝግጅት ሳይኖራቸው አንዳንዶቹ ደግሞ ፍላጎት ባይኖራቸው ገንዘብ ወደ እግር ኳስ መምጣቱ ጋር ተያይዞ የአካባቢ ልጅ ነው በሚል ወደ ስልጠና ሲመጡ ይታያል ብዙ ቦታ አቅም ያለውን አወዳድረው ከመቅጠር ይልቅ በአካባቢ ልጅነት የት ሄዶ ይሰራ በሚል ፕሮፌሽናሊዝምን የሚጣረስ ስራ ሲሰራ ይታያል ያ ደግሞ ወደ ተጨዋቾች ወርዶ ኳስ ተጨዋች መሆኑ እስኪያስደነግጥ ድረስ አቋሙ ወርዶብህ እንዴት ገባ ስትል አገሩ ስለሆነ ነው የሚል የወረደ ምላሽ ይገኛል ይሄ ከባድ ስጋት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቡና እያለሁ ምክትል አሰልጣኝ አልነበረኝም ብቻዬን ነው የሰራሁትና ብቻ መስራት ምን ያህል ከባድ መሆኑን ካዩ ሰዎች መሃል አንዱ ነኝ ለብቻቸው የሚሰሩ በውስን አቅም የሚገኙ በስመ አካባቢ የተቀጠሩ በሙያው ዋናውን አሰልጣኝ የሚረዳ ሳይሆን በስመ የአሰልጣኙ የአባባቢ ልጅነት የሚቀጠሩ በዝተዋል ይሄ ከባድ ነው አሁን የሚታየው እውነት አሰልጣኙን ከመርዳት ይልቅ በአሰልጣኙ በኑሮ የሚረዱ ምክትል አሰልጣኞች አሉ.. እግር ኳስ የሚያድገው በዋናነነት በአሰልጣኙ ነው ይህን ለማሳደግ የሚችል አሰልጣኝ ግን አላገኘሁም ወይም አላየሁም ይሄ ቢጠፋ ደስ ይለኛል፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን እንዴት አገኘኸው?
ሚሊዮን፡-95በመቶ የሚሆኑ ጨዋታዎችን ተመልክቻለሁ አንዳንድ ሚዲያ ሊጉ ተሻሽሏል ይላሉ በኔ እምነት ግን ሊጉ እንዲሻሻል የሚያደርግ መንገድ ተጉዘናል ብዬ አላስብም… ለ10 አመታት የማውቃቸው ተጨዋቾች ሌላ ክለብ ገብተው በሌላ ማሊያ እንዲሁም ከአሠልጣኝአብርሃምና ካሳዬ እንዲሁም የጊዮርጊስ አሰልጣኝ ውጪ በሌላ ክለብ የነበሩ አሁን በሌላ ክለብ ኃላፊነትና በለበሱት ቱታ ካልሆነ በቀር የነበሩ አሰልጣኞችን ነው የማየው…ሊጉ እንዲያድግ የሚያደርግ ነገር ተደርጓል ብዬ አላምንም ከሜዳ ውጪ ደግሞ ከዲ.ኤስ.ቲቪ መምጣት ጋር ተያይዞ የሚታዩ ለውጦች መኖራቸው መረሳት የለበትም በሜዳ እንቅስቃሴ የሚገባውን ነገር ሳይደረግ እግርኳሱ ካደገ አረም ነው ማለት ነው ሳትፈልገው የሚያድገው እረም ነው ለኳሱ እድገት ፍላጎት ቢኖረንም ለእድገቱ የሚረዱ ነገሮችን አድርገናል ብዬ ግን አላምንም ለእድገቱ የሚበጅ ስራዎችን በአግባቡሰርተናልም ብዬ አላምንም… በርግጥ ጎሎች እየተቆጠሩ ነው ይሄስ በተጨዋቾቻችን የማጥቃት እድገት ነው ወይስ በመከላከል ብቃት ማነስ ነው? የሚለውም መመርመር አለበት… አምና ከኢትዮ ፉትቦል ሶሊሽን ጋር በተደረገ ጥናት መሰረት ደካማ የመከላከል አቅም መኖሩን ነው የሚያሳየው…. ዘንድሮም ይሄ መገምገም አለበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንደቀድሞው ከአጥቂ እግር ብቻ ጎል የሚፈልግ ነው… እነኚህ ሁሉ መገምገም አለባቸው፡፡

ሀትሪክ፡- ከሊጋችን በተለይ ከተጨዋቾች ከአሰልጣኞች የታዘብከው ነገር የለም?
ሚሊዮን፡- የታዘብኳቸው ነገሮችማ አሉ፤ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ኦብዘርቭ ማድረግ የአንድ አሰልጣኝ ትልቅ ኳሊቲ ነው ይላሉ… እንደ አሰልጣኝ ብዙ ነገሮችን እገመግማለሁ፡፡ ከተጨዋቾች የታዘብኩት ተቀይረው እንዲገቡ ሲጠየቁ ገብቶ ውጤቱን የመቀየር ወይም የማስጠበቅ ፍላጎታቸው ወርዶ አይቻለሁ ጫማ ለማሰርና መጋጫ ለማድረግ የሚወስድባቸው ጊዜ ሜዳ ላይ የሚታዩበትን ደቂቃዎች የሚያሳጥር ሆኖ አይቻለሁ ጥሩ ነገራቸው እንደ ደጋፊ ጓደኞቻቸውን ሲያበረታቱ ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን ሲጥሩ አይቻለሁ፡፡ ወደ አሰልጣኞች ስዞር ምክትል አሰልጣኝነት ምን ማለት እንደሆነ የመረዳት ችግር አይቻለው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴውን ትተው የሚያማሙቁ ተጨዋች ጋር ሲሄዱ አይቻለሁ ከካሜራ ማን ጋር ስለ ፎቶ ይሁን ሌላ ጉዳይ ወሬ ሲያወሩ አይቻለሁ ይሄ ትልቅ ስህተት ነው… ሌላው የአንዱ ክለብ ፕሬዚዳንት ከትሪቩኑ ቦታቸው ወርደው አሰልጣኙ ጋር በመሄድ አስተያየት ይስጡ ተሳድበው ባላውቅም ሄደው ተናግረው ሲመለሱ ማየቴ ስታዲየም ነበርኩ ወይ ብዬ ራሴን እንድጠይቅ አድርጎኛል ይሄ ደግሞ የራሣቸው የአመራር ድክመትና የአሰልጣኞቹን አቅም ማነስ አሳይቶኛል… በዲ.ኤስ.ቲቪ ዘመን በሀገሬ ኳስ ላይ ይህን ማየቴ አናዶኛል ለ40 ደቂቃ አማሙቆ መኖሩ የተነሳ ጭራሹኑ ያልተቀየረ ተጨዋችም አጋጥሞኛል… እነኚህ ሁሉ መታረም አለባቸው ብዬ አስባለሁ ዋና አሰልጣኞች አሁን የደረሱበት ደረጃ እንደሚደርሱ ያመኑ አይመስለኝም ከዚህ ዘመን በፊት ባለፉት አመታት ያበላሹትና ከሰው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ተከትሏቸው ዛሬ ላይ ለማረም የሚመስሉ ሆነው አግኝቻቸዋለው፡፡
ሀትሪክ፡- በምትታወቅበት ትንተና ዙሪያ ዲ.ኤስ.ቲቪ ላይ የለህም.. ምክንያቱ ምንድነው?
ሚሊዮን፡-በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ በርግጠኝነት እስካሁኑ ሰዓት ድረስ ከሱሪ ይልቅ በቁምጣ ማድጌን በድፍረት መናገር እችላለሁ፤ ተወልጄ ያደኩት አብነት አለሙ ሜዳ አካባቢ እንደመሆኑ ከኳስ ጋር ትልቅ ግንኙነት አለኝ ቤት ቀይረን አየር ጤና ስንሄድም እዚያ በሚገኝ ሜዳ ላይ ስጫወት ኖሬያለሁ ለእግር ኳስ ሲባል የከፈልኩት ዋጋ አለ፡፡ በተጫዋችነት ዘመኔ ከአሰልጣኝ ዘማሪያም ወ/ጊዮርጊስ ጋርበከፍተኝ ዲቪዚዮን በሚሳተፈው ወረዳ 4 ቡድን ውስጥ ተጫውቻለሁ ደቡብ ፖሊስ ተሳክቶ መቀጠል ባልችልም የመጫወት እድሉ ነበረኝ ወንጂ በተካሄደው የሰራተኞች ማህበር ውድድር ላይ ሻምፒዮን በሆነው የኢትዮጲያ መድን ድርጅት ቡድን ውስጥ ተጫውቻለው ያም ቢሆን ግን በመጫወት ውስጥ የምፈልገውን ያህል አልተሳካም ያም ሆኖ የህይወቴን 90 በመቶ ያሳለፍኩት ከእግር ኳስ ጋር ነው ወደ አሰልጣኝነት ህይወት ስገባም ዋንጫ አንስቼ ስንብት ነው የገጠመኝ፡፡ ኮልፌ ቀራንዮን ብሔራዊ ሊግ ስናስገባ ከአቃቄ ጀምሮ በማርሽ ባንድ በሲቲ ባስ ተቀብለውን ከአንድ አመት በኋላ ቡድኑ ፈርሷል አንዳንዴ ለሲቲ ባሱና ለማርሽ ባንድ የተከፈለው ቢቀር ኖሮ ክለቡን አንድ አመት ያስቀጥል ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህ ሙያ ውስጥ አልፋለሁ ብዬ ባላስብም በብስራት ኤፍ ኤም ለ6 አመት በትንታኔ ሰርቻለሁ በርካታ ጨዋታዎችን ተንታኛለሁ ወደ ዲ.ኤስ.ቲቪ ስመጣ እድሉ ሲገኝ ተፈልገው ከሚሰሩ ሰዎች መሀል አንዱ ነኝ ብዬ አምን ነበር መሄድ ይጠብቅብኛል ብዬ አላስብም በታሪኬም ውስጥ ሄጄ ልስራ ያልኩበት ጊዜም የለኝም ተፈልጌ እንጂ ትክክል ባልሆነ መንገድ ሄጄ አላውቅም ነገር ግን እድሉ እስካሁን አልመጣም በእግር ኳስ ውስጥ የኔ ትክክለኛ መንገድ ምን ይሆናል? የትኛውስ ነው? በሚለው እየተፈተንኩ ነው የምገኘው… ጥሩ ስሜት የለኝም፡፡
ሀትሪክ፡- እድሉ የጠፋው በመራጩ አካል አለመፈለግ? ወይስ መሀል ላይ የተሰራ ፋውል አለ?
ሚሊዮን፡- ከመራጩ አካል ነው እንዳይባል መራጩ አካል አይታወቅም መመዘኛውንም አላውቅም የቱ ጋር ነው ችግሩ የሚለው አልገባኝም፡፡ ማህበራት አባላቶቻቸውን መጥቀምአንዱ ጉዳያቸው ነው ነገር ግን ለዚህ ጉዳይ የሚታጩ ባለሙያዎች ብቁነት ግን መመርመር አለበት ባይ ነኝ… ትልቁ ችግር ቡድንተኝነት ይበዛበታል ጋዜጠኛው፣ አሰልጣኞቹ ጋር ይሁን ተጨዋቾቹ ጋር ቡድንተኝነቱ ይበዛል፡፡ ማህበሮቹ መመስረታቸው መልካም ቢሆንም አካሄድ ላይ ግን ችግር አያለሁ እንደሙያ ካየን የኢትዮጲያ አሰልጣኞች ማህበር አባል ነኝ በሁሉም አካባቢ የማያቸው አካሄዶች ግን አይመቹኝም፡፡
ሀትሪክ፡- ብዙም የመናገር መብትን የማስከበር እንቅስቃሴ ላይ አትታይም… ይሄስ ሊጎዳህ አይችልም?
ሚሊዮን፡- እኔ ተደብቄ የምኖር ሰው ነኝ አቅም አጥቼ ግን አይደለም… ማን ምን መስራት እንዳለበት ሁሉም ይተዋወቃል ስለ አቅም ማንሳት ተገቢ አይደለም ስም መጥራትም አልሻም ይሄ የኔ ተፈጥሮም አይደለም ለ6 አመታት በቀጥታ ስርጭት ላይ ሰርቻለሁ ከዚህ በላይ ምን ይጠበቃል? በሚዲያከኔ በላይ የሰሩ አሉ፡፡ በቀጥታ ስርጭት ግን ከመንሱር አብዱልቀኒ ቀጥሎ ረጅም ጨዋታዎችን የሰራሁት እኔ ነኝ ይሄ በውጪ ጨዋታ ላይ የተገደበ አይደለም በሀገር ውስጥም ከነማርቆስ አሊያስ ጋር ሰርቻለሁ ከኢትዮ ፉትቦል ሶሉሽን ጋርም የተመረጡ የሊጉ ጨዋታዎችን በቪዲዮ አናሊሲስ ትንታኔ በኢቲቪ መዝናኛ ላይ ለ2 አመት ሰርቻለሁ ከዚህ በላይ ምን ይጠበቃል? ነገር ግን የምርጫው መስፈርት ስለማይታወቅ መከራከር አልችልም እኔ ግን ትክክለኛው ሰው ነኝ ህዝቡ እድል ቢያገኝ እውነታውን የሚመሰክር ይመስለኛል የኛ ስራ ሰነድ የሚደበቅበት ወይም የሚሰረዝበት አይደለም ፊት ለፊት ነው እናም ሁኔታው ቅር አሰኝቶኛል ተጠያቂም አካል አለመኖሩ ያበሳጫል፡፡
ሀትሪክ፡-አንተ እንድትካተት የሞከሩ ባለሙያዎች የሉም?
ሚሊዮን፡- አሉ.. ትክክል አይደለም አንተ መምጣት አለብህ ያሉኝ በቅንነት የተነሱ ሰዎች አሉ በተለይ ዮናስ አዘዘ በዚህ ውሣኔ ውስጡ ደስተኛ አለመሆኑን አውርተናል ርግጥ ማነው የሚጠየቀው? ባለቤቱ ማነው? የሚለው አይታወቅም ከማን ጋር ማውራት እንዳለብኝ አላውቅም በርካታ ሰዎች መልቲቾይዝ ጋር መሄዳቸውን አውቃለሁ እንደኔ እምነት ግን መልቲቾይዝ ነው ወደኔ መምጣት ያለበት ሰርቼ ያሳየሁ ሰው ነኝ ብዬ አምናለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ዲ.ኤስ.ቲቪ ጥቅሙ እንዳለ ሆኖ የኳሳችንና የዳኞቻችን አቅም ከማጋለጥ አንፃር ስጋት አይሆንም?
ሚሊዮን፡- ብዙ የሚታየኝ ጥቅሙ ነው በኛ ሀገር እግር ኳስ ከሜዳ ላይ ችግር ይልቅ ከሜዳ ውጪ ያሉ ችግሮች ይበዛሉ ብዬ አምናለሁ ሜዳ ላይ ያለው ችግር ስህተት በመቀነስ ሊስተካከል የሚችል ነው ከሜዳ ውጪ ያለው ችግር ስናይ ብዙ ነው ዲ.ኤስ.ቲቪ ሲመጣ ለገበያው አንጂ ለኳሱ ብሎ እንዳልሆነ ይታወቃል ስታዲየሞቻችን ጥቂት ደጋፊዎች ገብተው ትልቅ ስጋት የሚሆኑበት መሆኑ መታረም አለበት ደጋፊዎቹ ጥቂት ሆነው የሚሰሙት ድምጾች ግን ደስ አይሉም እነኚህ መወገድ አለበት አሰልጣኞቻችን ከጨዋታ በኋላ የሚሰጡት አስተያየት ላይ መታረም ያለበት ነገር አለ አንዳንዶቹ ምክትል አሰልጣኞቻቸውን ይልካሉ ከጨዋታ በኋላ ያለውን ሃሣብ ለመግለፅ ምክትል አሰልጣኝ ተገቢ ሰው ነው ብዬ አላምንም ጨዋታውን የሚያቅደው ግጥሚያው ምን አይነት መልክ እንደነበረው መግለጽ የሚችለው ዋና አሰልጣኙ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ ምክትል አሰልጣኞች ዕረፍት ላይ እንኳን ለተጨዋቾች ሃሳብ እንዲሰጡ የማይፈቅድበት አለም ላይ ነው ያለነው… እኛ ሀገር ግን ምክትል አሰልጣኝ አስተያየት ስጥ የሚባለው ልክ አይደለም ከጨዋታ በኋላ ያለውን አስተያየት ምክትላቸው እንዲሰጥ ማድረግ ጤነኛነት አይመስለኝም፡፡ ከጨዋታ በኋላ የሚሰጡ አስተያየቶች ለሳምንት ስራ የሚፈጥሩ ናቸው አሰልጣኙ ምን አለ? ከጨዋታውምን አገኘ? የሚለው ለሚዲያ የሳምንት ስራና መወያያ ነው ይህን አሰልጣኞች ማወቅ አለባቸው፡፡
ሀትሪክ፡- የተጨዋቾች ዝውውር ላይ ያየኸው መታረም ያለበት ጉዳይ አለ?
ሚሊዮን፡- ቡድን በአንድ ቀን አይገነባም ነገር ግን በኛ ሀገር ያለው ይለያል ዛሬ አንድ ክለብ የያዘ አሰልጣኝ ነገ ቡድኑን የት ያደርሳል የሚለው እኛ ሀገር አይታሰብም የአሠልጣኞቹ ኮንትራት አጫጭር በመሆኑ በእቅድ ለውጥ የማምጣት ሃሳብ አይኖራቸውም በዚያ ላይ ከአሰልጣኞቹ ጋር የሚዞሩ በገቡበት የሚገቡ ተጨዋቾች ብዙ ናቸው በየአመቱ 9 ወይም 10 ተጨዋች አስፈርሞ ስለ ቡድን ግንባታ ማውራት ከባድ ነው በየአመቱ በርካታ ተጨዋቾችን ማስፈረም ከእግር ኳሳዊ ምክንያት ይልቅ ከጥቅማጥቅም ጋር የተያያዘ ይመስለኛል በዝውውሩ የሚገርመኝ የጨዋታ ዘመናቸውን ከአንድ አሰልጣኝ ጋር የሚጨርሱ ተጨዋቾች ብዙ መሆናቸው ነው አሰልጣኙ በዋለበት የሚውሉ ባደረበት የሚያደሩ ተጨዋቾች በዝተዋል ይሄ ከታክቲካል ግንዛቤ አንፃር ነው እንዳይባል ብዙ ጊዜ ተጠባባቂ የሚሆኑ ናቸው ይሄ ሁሉ ይገርመኛል በርግጥ አለም ላይም አለ አሰልጣኙ ፖርቱጋላዊ ሲሆን በርከት ያሉ ፖርቱጋላዊያን ቡድኑ ላይ ሊታዩ ይችላሉ በቀላሉ ቡድናቸውን ለመግባባት ለኮሚኒኬሽኑ ስለሚጠቅም ነው በኛ ሀገር ግን አንድ ቡድን ከ10 በላይ ተጨዋቾች በየአመቱ የማዛወር ምክንያት ምንድነው አይታወቅም…ለውጥ ካስፈረሟቸው ተጨዋቾች ጋር በፕሪ ሲዝን አብረው ቆይተው ቡድናቸውን ገንብተው ካዘጋጁ በኋላ በሰሜን የሀገራችን ክፍል በተፈጠረው ሁኔታ የትግራይ ክለቦች ተጨዋቾችን የመቀራመት ነገር ይታያል አብረው የነበሩትን ተጠባባቂ አድርገው ወይም አባረው ከነዚህ ክለቦች ሲወስዱ በፕሪሲዝን ሲሰራ የነበረው ዝግጅት ተገቢ አልነበረም ማለት ነው ያስብላልና የተጨዋቾች ዝውውር ጉዳይ ላይ ቃሉን ባልወደውም የተጨዋቾች ኤጀንቶችን ጨምሮ ብዙ ሊፈተሽ የሚገባው ነገር እንዳለ ይሰማኛል፡፡
ሀትሪክ፡- በሴቶች እግር ኳስ ላይስ ለውጥ ይታይሃል?
ሚሊዮን፡- /ሳቅ/ በምን መነሻ ነው ለውጡ? ተለውጧል የሚሉ ሰዎች አንድ ምሣሌ ቢያሳዩኝ ደስ ይላል፤ ምን አገኘ? ምን ሰጠነውና ነው የሚለወጠው? ምንም አላገኘምኮ… ከኑሮ አንፃር ተቀይሯል በኔ ስር ሲሰሩ የነበሩትን ተጨዋቾች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ስር ይገኛሉ ብዬ አላስብም፡፡ ረውዳ አሊ፣ ሰሚራ ከማል፣ አዲስ ፈለቀ፣ ኢየሩሳሌም ነጋሽ፣ ኦሎምቤና እሙዲን ጨምሮ በርካቶችን ማንሣት ይቻላል ዝም ብለው ይተካሉ ብዬ አላምንም፡፡ በራሣቸው ጊዜ መጥተው ነው የሀገራቸውን ማሊያ ለብሰው ለውጤት የታገሉት በክለብ ደረጃ ትልቁ ደመወዛቸው 800 ብር ነበር ያውም በዛ ተብሎ.. አሁን ገንዘቡ አድጓል ያ ጥሩ ነው ከዚያ የዘለለ ግን ምን ስለሰራን ያድጋል? ያለ ስራ የሚሻሻል እግር ኳስ ካለ አውሮፓውያኑ በታዳጊ ላይ ሰርተው ዋጋ ከፍለው ካፍና ፊፋ ፕሮግራምና በጀት ይዘውለት ለምን ይሰራሉ? ይሄ መታወቅ አለበት የሄድንበት ምንም አይነት የዕድገት ጉዞ የለም የዲ.ኤስ.ቲቪ መመጣት ደስ የሚለኝም ለዚህ ነው ገንዘቡን ምን ያህል ለልማት እናውለዋለን የሚለውም መታየት አለበት ባይ ነኝ፡፡
ሀትሪክ፡- የታዳጊዎች እድገትና ለውጥ አለመኖሩ የአሰልጣኞች ድክመት? ወይስ እንደሚባለው ተተኪ ስለሌለ?
ሚሊዮን፡- በግሌ የወጣት ቡድን አሰልጣኝ ሹመት በደንብ መፈተሽ አለበት ባይ ነኝ.. ተጫውቶ ያሳለፈ በሚል ዝግጅትየሌለው ከጀመረ በኋላ ዝግጅት ይጀምራል ብለን ብናስታምመው እንኳን ፍላጎት የሌለው አሰልጣኝ ይሾማል የክለብ አመራሮችን ተጫውቶ ላለፈ እድል ሰጥተዋል እንዲባሉ እነኚህን ይሾማሉ ይሄ ያስደነግጣል ታዳጊዎች ናቸው ትክክለኛ አስተማሪ የሚያስፈልጋቸው ብሔራዊ ቡድኑ ወይም የክለቦቹ ዋና ቡድን ላይ ብልሽት ቢገጥም ይሻላል የሚል እምነት አለኝ…..ተጫውተው ያሳለፉ ዝግጅትና ፍላጎት ያላቸው ስራ አጥተው የሚያስለጥኑበት ክለብ ተነፍገው ሲንከራተቱ ማየት ያማል ታዳጊ ላይ አሰልጣኝነት ሹመት መሆን የለበትም ለኳሱ ዋጋ የከፈሉ ሰዎችን ማገዝ ጥሩ ነው ነገር ግን በሙያ መርዳት አግባብ ነው ብዬ አላምንም ምክንያቱም ሰው ላይ ነውና የሚሰራው.. ትክክለኛ አሰልጣኝ ታዳጊዎቹ አግኝተዋል ብዬ አላስብም ክለቦችም ታዳጊ ላይ ፍላጎትና እምነቱ የላቸውም ከዋና ቡድን በተረፈ ኳስ የሚጫወት ታዳጊ ቡድን ይዘው ስለልማት ማውራት ጤነኝነት አይደለም ብዙዎቹ ክለቦች ጋር ብትሄድ አምና ዋናው ቡድኑ የሰራበትን ኳስ ነው ለታዳጊ ቡድናቸው የሚሰጡት ታዳጊዎቹ ኳሱን የሚነፉበት አቅም የላቸውም እነኚህን ይዞ አመራሩ ስለልማት ማውራት አለበት ብዬም አላምንም አንድ ታዳጊ ላልተገባ ግንኙነት አይመችም ታዳጊው ሲያድግ ከፍተኛ ክፍያ አይከፈለውምና ጥቅም አይገኝበትም ከሌላ ቦታ አምጥቶ የሚፈልጉትን ጥቅም ማግኘት የሚፈልጉ በመኖራቸውም አንዱ ምክንያት ይመስለኛል ከብዙ በጥቂቱ ታዳጊ ላይ እምነት እንደሌላቸው የሚያሳይ ከላይ ያልኩት ነው ሌላው ከ15 ከ17ና ከ20 አመት በታች አሰልጣኞች ለሰላምታ የማይፈላለጉ መሆናቸውና ከዋናው ቡድን አሰልጣኝ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውም መሆኑ ይጠቀሳል… በተለያየ ስልጠና የሚሰሩ መሆናቸው ስታይ ለምን ክለቦቹ ፈቀዱ ብለህ እንድትጠይቅ ያደርግሃል፡፡ በቅርቡ የሰማሁት ወደ 20 አመት በታች ቡድን አሰልጣኝነት የመጣው ባለሙያ ቀድሞ የነበረው አሰልጣኝ ይዟቸው የነበሩትን አልፈልግም እስከማለት ደርሶ እንደበተናቸውና አቅም ያላቸው ታዳጊዎች ቤታቸው እንደተቀመጡ የሰማሁበት ክለብ አለ እንደዚህ አይነት ሂደት እየታየ ታዳጊዎች እንዴት እንዲፈልቁ ይጠበቃል? መንገዱም ከተበላሸ አሰራር አንፃር የተዘጋ በመሆኑ ታዳጊዎች እንዳይገኙ አድርጓል ባይ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡-ባለፉት 10 አመታት ወደ 4 የፌዴሬሽን አመራሮች አይተሃልና .. ስኬታማ የትኛው ጊዜ ይመስልሃል?
ሚሊዮን፡-የፌዴሬሽን አመራሮች የስራ ዘመን መለካት ካለበት በልማት ስራዎች ነው፡፡ ለኔ ሁሉም አንድ አይነት ናቸው ብዬ ነው የማምነው ምክንያቱም ይህን ያህል ሰርቻለሁ አንተ ደግሞ ከዚህ ቀጥለህ ስራ የሚል ቅብብል ያለ አይመስለኝም ሲቀባበሉ ያየሁት ቁልፉን ነው ሲለቁም ደስተኛ ሳይሆኑ የሚለቁበት መስመር ነው እግር ኳሱ… ስንት ውድድር አወዳደሩ ብለን የነርሱ ባልሆነ ጉዳይ እነ አቶ ሳህሉን፣ አቶ ጁነዲንን አሁን ደግሞ አቶ ኢሳያስን ጊዜ ገምገም አይቻልም ከልማት አንፃር ምንም ያየነው ነገር የለም ማወዳደርም ይከብዳል ከስኬታማነት አንፃር ካየነው በአቶ ሳህሉ ገ/ወልድ ጊዜ ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፋችን ሊጠቀስ ይችል ይሆናል ከዚያ በተረፈ ግን የሚታይ ነገር አለ ብዬ አላምንም፡፡
ሀትሪክ፡- የክለቦቻችን አቅም ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን መገንባት የሚያስችል ነው ማለት ይቻላል?
ሚሊዮን፡- ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን የሚገነባበት መንገዶች ይታወቃል አንዱ ከሀገር ውጪ የሚጫወቱ ተጨዋቾችን ማብዛት ነው በርግጥ ለሀገራት ፈተና እየሆነ መጥቷል ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡና በተለያዩ አሰልጣኝ የሚሰለጥኑ መሆናቸው እነሱን አቀናጅቶ ወደ ራሱ መስመር ለማስገባት ከባድ ሆኗል በተለይ ጊዜው ማጠሩ ለዚህ ምክንያት ሆኗል የአውሮፓና የአለም ዋንጫው በታቸውን እያጡ ነው የሚሉ ወገኖችም ብዙ ናቸው ከድካም አንፃር ማለትም ከሊግ መጠናቀቅ በኋላ የሚካሄድ መሆኑም አንዱ ምክንያት ነው የሌላኛውም ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን የጠንካራ ሊግ መገለጫ እንደመሆኑ የትኛው ጋር ነን የሚለው መታየት ካለበት ግልፅ ነው ከሀገር ውጪ ያለው ል ሽመልስ በቀለ ብቻ ነው በሙሉ በኛ ሊግ ላይ ያሉ ናቸው ለዚህ ነው ሊጋችንን ዞር ብሎ ማየት ያለብን ደግሞ ሊጉ ጠንካራ ሳይሆን ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መጠበቅ ተገቢ አይመስለኝም፡፡
ሀትሪክ፡- የመጨረሻ ቃል?
ሚሊዮን፡- እኔ ባለሁበት ጊዜ ውስጥ በበጎ የሚገፉ ሰዎች ማለት እንዲያደጉ መገገዱን የሚያሳዩትን ማለቴ ነው ማን ማንን ገፍቶ ከፍታ ላይ አደረሰው የሚለውን የብዙዎች ታሪክ አውቃለሁና የሚገፉ ሰዎች መንገድ በማሳየት ብቻ ሣይሆን በሙያም አግዟቸው የሚማሩበትና የሚያሻሽሉበትን ነገር ዕርዷቸው የሚል መልዕክት አለኝ… ተገፍተው ብቻ መጥተው ነገር እያበላሹ ያሉ ሰዎች አሉና ስትደግፏቸው ሁለንተናዊ ድጋፍ አድርጉላቸው ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ይሄ የሙያ ማህበራቱን ይመለከታል ለቦታቸው ትክክለኛ ሰው እንዲሆኑ ማገዝ አለባቸው ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ማህበርም ይህን በትኩረት ማየት አለበት ማነው ጥሩ ዝግጅት ያለው? አቅም የገነባው ማነው? እርሱ ቢሆን ለኳሱ ይመጥናል ወይ ተብሎ ተገምግሞ ቢሆን ደስ ይላል ለእግር ኳሱ የማሰብ ነገር ሊቀድም ይገባል ግለሰቡን ከመጥቀም በዘለለ ለሀገር መታሰቡ መቅደም አለበት ይሄ ሁሉንም የሙያ ማህበራትን ይመለከታልከዚያበተረፈ የክለብ አመራሮች ሚናቸውን ቢረዱ ደስ ይለኛል ትክክለኛ ባለሙያ የማስቀመጥ ግዴታቸውን ቢወጡ ትልቅ ጥቅም አለው ብዬ አስባለው፡፡ ከዚያ በተረፈ እግር ኳሱ በደከምኩት ልክ ከፍሎኛል የሚል እምነት የለኝም የት እንደደረስኩ ባላውቅም አሁን ለደረስኩበት ደረጃ እንድደርስ ያገዙኝን አመሰግናለሁ አሰልጣኝ ሆኜ አሁን ላለሁበት ደረጃ እንድደርስ በተሻለ መንገድ ያገዘኝን የቅ/ጊዮርጊስ ምክትል አሰልጣኝ ደረጄ አንገቴን አመሰግናለሁ ብስራት ሬዲዮ መሰለ መንግስቱን አመሰግናለሁ አቅም ኖሮህ እድል በማታገኝበት ሀገር ላይ ያለምንም መመዘኛ በማይክ ፊት እንድቀመጥ ያደረገው መሰለ ነውና ከልብ ላመሰግን እወዳለሁ ከዚያ ውጪ ጋዜጠኞች ከጎኔ ናቸው በዲ.ኤስ.ቲቪ ፕሮግራም ላይ መገኘት አለብህ አይዞህ ብለው ላበረታቱኝ ላመኑብኝ ከጎኔ ላሉ ጋዜጠኞች ትልቅ ምስጋና አቀርባለው የሀትሪክ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልን ለሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡
አስተያየት ይስጡ