በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን በመጨረሻ ደቂቃ በተቆጠረች ግብ ሀድያ ሆሳዕናን 1ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
አስቀድሞ በ14ተኛዉ ሳምንት የሊጉ መርሐግብር ከአዳማ ከተማ ጋር ጨዋታዉን ሁለት አቻ በሆነ ዉጤት ማጠናቀቅ ችሎ የነበረዉ ኢትዮጵያ መድን በሀያ ሰበት ጥቦች ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዉ ጨዋታውን ሲጀምር በተቃራኒው በአስራ አራተኛዉ ሳምንት የሊጉ መርሐግብር በቅዱስ ጊዮርጊስ የ1ለ0 ሽንፈት አስተናግዶ የነበረዉ ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ በሀያ አንድ ነጥቦች 4ተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ የዛሬዉ ጨዋታ ጀምሯል።
የጨዋታው ውጤት በዋንጫው ፉክክር ላይ ለሁለቱም ቡድኖች የሚኖረው ተፅዕኖ ከፍ ባለበት የዕለቱ ጨዋታም በመጀመሪያዎቹ ተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ የተመለከትንበት ነበር ማለት ይቻላል ፤ በጨዋታዉ የመጀመሪያ ደቂቃ ላይ ግን ሀድያዎች ሳይጠበቅ አስደናቂ ሙከራ ማድረግ ችለዉ ነበር በዚህም አማካዩ ፍ/እየሱስ ተ/ብርሐን ከፀጋዩ ብርሐኑ የተቀበለዉን ኳስ ከሳጥን ውጭ ቀጥታ ወደ ግብ ልኮ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ አቡበከር ኑሪ በጥሩ ቅልጥፍና ኳሷን መልሷታል።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው የመጀመሪያ አስራ አምስት ያህል ደቂቃዎች ጥሩ የሚባል የጨዋታ ብልጫ የነበራቸዉ ሀድያዎቹ በዚች አጭር ደቂቃም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረሰ ችለዉ ነበር ፤ በተቃራኒው እምብዛም ወደ ጨዋታዉ ለመግባት ተቸግረዉ የነበሩት መድኖች ደግሞ በ16ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ሙከራቸዉን ማድረግ ችለዋል። በዚህም የፊት መስመር ተጫዋቹ ሀቢብ ከማል በጥሩ ብቃት ከሳጥኑ ጠርዝ አካባቢ አስደናቂ የግብ ሙከራ ማድረግ ችሎ የነበረ ቢሆንም የገብ ዘቡ ፔፔ ሰይዶ አውጥቶበታል።
በተደጋጋሚ የግብ ዕድል መፍጠር ችለዉ የነበሩት ሀድያዎች በ36ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ ጥሩ የግብ ዕድል መፍጠር ችለዉ ነበር ፤ በዚህም ከአማካዩ ፍ/እየሱስ የተሻገረለተን ኳስ እየገፉ ሂዶ ከግብ ጠባቂዉ ጋር መገናኘት የቻለዉ ባየ ገዛኸኝ ኳሷን ሳይጠቀምባት ቀረ እንጅ ምናልባትም ከአጋማሹ በፊት የያሬድ ገመቹ ቡድን መሪ መሆን የሚችልበትን ዕድል መፍጠር ይችል ነበር።
ከዕረፍት መልስ ተመጣጣኝ በሚባል የጨዋታ እንቅስቃሴ ቀጥሎ የነበረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በ56ኛዉ ደቂቃ ላይ ቀይ ካርድ ተመዞበታል። በዚህም የሀድያዉ የመሐል ተከላካይ ፍሬዘር ካሳ ሳይመን ፒተር ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ በሁለተኛ ቢጫ ከጨዋታው ሊወገድ ችሏል። ከዚህ ቅጵበት ከደቂቃዎች በኀላም ነብሮች ጥሩ የግብ ዕድልን መፍጠር ችለዉ ነበር ፤ በዚህም በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረዉ ፍ/እየሱስ ከሳጥን ውጭ በድጋሚ ድንቅ ኳስ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም አቡበከር ኑሪ በድጋሚ አክሽፎበታል።
በንፅፅር ከመጀመሪያው አጋማሽ ይልቅ የተቀዛቀዘ በነበረዉ ሁለተኛዉ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ለመድረስ ሲጥሩ የተስተዋለ ቢሆን በሙከራም ይሁን በእንቅስቃሴ ረገድ ግን ሲቸገሩ ተስተውሏል። በዚህ ሂደት በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ግን በ95ኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ተቆጥሮበታል። በዚህም ተቀይሮ የገባዉ ያሬድ ዳርዛ ከባሲሩ ኡማር በረጀሙ የተላከለትን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር የአሰልጣኝ ገ/መድህን ሀይሌ ቡድን ወሳኝ ሶስት ነጥብ እንዲያሳካ ማድረግ ችሏል።
ዉጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ መድን በ30 ነጥቦች ሊጉን መምራት ሲጀምር የያሬድ ገመቹ ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ በ21 ነጥቦች አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።