አሰልጣኝ ውበቱ በጅማው ዝግጅት ያረፈዱትን አምሳሉ ጥላሁንና ታፈሰ ሰለሞንን አሰናብተዋል

ለዋሊያዎቹ አባላት ጅማ ላይ የተደረገው ጥሪ የፊፋን ካላንደር የተከተለ አይደለም መባሉን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ውድቅ አድርጎታል፡፡

አሰልጣኙ እንደተናገሩት “ከፊፋ ካላንደር ውጪ ለተጨዋቾች ጥሪ መደረጉ አግባብ አይደለም መባሉ ተገቢ አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት ለተለያዩ የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት 40 እና 45 ቀናት ሊጉ የተቋረጠው በየትኛው የፊፋ ካላንደር ነው?” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ አሰልጣኙ ከጥቂት አመታት በፊት 49 እና 45 ቀናት ሊጉ መቋረጡ ተገቢ አይደለም ይሄ መስተካከል አለበት ለክለቦቹም ሆነ ለሊጉ ጥሩ ውጤት አያመጣም ያልኩትን መተግበሬ መሞገስ እንጂ መተቸት አልነበረብኝም ሲሉም ተናግረዋል፡፡ “በደብዳቤ ለ30 ቀናት የብሔራዊ ቡድን ዝግጅት እፈልጋለሁ ብል ክለቦቹ አይጎዱም ቅሬታም አይፈጠርም ወይ? ያሉት አሰልጣኙ አሁንም ሊጉ ሳይቋረጥ ክለቦቹ ለጥሪው ተጨማሪ ወጪ ሳያወጡ ዝግጅት ማድረጋችን ተገቢና ምስጋና የሚያስቸረው ተግባር ነው” ሲሉ ለመገናኛ ብዙኃኑ ገልፀዋል፡፡

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጥሪ ከተደረገላቸው 20 ተጨዋቾች ከሶስት ክለቦች ለተመረጡና ከቀሩ 8 ተጨዋቾች ውጪ ከ20ዎቹ ጋር ለ3 ቀናት ጥሩ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ አሰልጣኙ ተጨዋቾቼን አልክም ብሎ ስድስቱን ተጨዋቾች አስቻለሁ ታመነ፣ ጌታነህ ከበደ፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ አቤል ያለው፣ ጋዲሳ መብራቴና አይደር ሸረፋን ካስቀረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ውጪ የቀሩትን ተጨዋቾችንና ክለቦችን ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡
ሀትሪክ ከታማኝ ምንጭ ባገኘችው መረጃ ሁለቱ ተጨዋቾች የፋሲል ከነማው አምሳሉ ጥላሁን /ሳኛ/ እና የኢትዮጵያ ቡናው ታፈሰ ሰለሞን መሆናቸው ታውቋል፡፡

ተጨዋቾቹ ጥር 2/2013 እሁድ ጅማ በመገኘት ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቦላቸው የፋሲል ከነማው አምሳሉ ጥላሁን ሰኞ ሆቴሉ ሲደርስ አሰልጣኙ ጥሪ የተደረገልህ እሁድ ነው ሰኞ ለምን እንደመጣህ አልገባኝም ብለው እንደመለሱት ታውቋል፡፡ ፋሲል ከነማ ከሁሉም ክለቦች ቀድሞ ጅማ የገባ ቢሆንም ተጨዋቹ በተባለው ቀን እሁድ አለመገኘቱና ሪፖርት አለማቅረቡ ግርምትን ፈጥሯል፤ ተጨዋቹ አሰልጣኙን ለማሳመን ቢጥርም በዲሲፕሊን አከባበር የማይታሙት አሰልጣኝ ውበቱ ግን ሳይቀበሉት ቀርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናው ታፈሰ ሰለሞንም ሰኞ ማታ ለመድረስ አሰልጣኙን ለማስፈቀድ ደውሎ ከቤተሰቡ የቅርብ ሰው በመታመሙ በተባለው ቀን መምጣት እንዳልቻለ የነገራቸው ሲሆን ባለበት እንዲቀር ቡድኑን በዚያ ሰዓት መቀላቀል እንደማይችል ነግረውት ሁለቱም ከቡድኑ ውጪ መደረጋቸውን ሀትሪክ ከታማኝ ምንጭ ያገኘችው መረጃ ያስረዳል፡፡

በርካታ አሰልጣኞች በተጨዋቾቻቸው ጥላ ስር በሆኑበት የኢትዮጵያ እግር ኳስ እንደ አሰልጣኝ ውበቱ በዲሲፕሊን መከበር ላይ የማይደራደሩ አሰልጣኞች ጥቂት ናቸው ላለበት ክለብ ለፈረመው አሰልጣኝ እድሜህ እንዲረዝም ቋሚ አድርገህ አሰልፈኝ ከሚለው ተጨዋች አንስቶ ሲቀየሩ የሚሳደቡ ተጨዋቾችን ማየት የተለመደ ነው፡፡ ባደገበት ከተማ በሚገኝ ክለብ ላይ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ አሰልጣኙን በደጋፊዎች ጫና ውስጥ የሚከት ተጨዋችን ማየት የተገደድንበት እግር ኳሳችን ቆራጥና ሁሉን ተጨዋች እኩል የሚያዩ ለዲሲፕሊን መከበር ቁርጠኛ የሆኑ አሰልጣኞች ያስፈልጉናል በማለት የስፖርት ቤተሰቡ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport