በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ23ኛ ሳምንት የሶስትኛ ቀን ቀዳሚ መርሀግብር ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያ መድኅንን 1 – 0 ረቷል ።
በኢትዮጵያ መድኅን በኩል በ22ኛው ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክን በረቱበት ጨዋታ ላይ በነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ በሲዳማ ቡና በኩልም በሳምንቱ ሀዋሳ ከተማን በረቱበት ጨዋታ ላይ ከነበረው ምርጥ አስራ አንድ ሁለት ለውጦችን በማድረግ በአማኑኤል አንዳለ እና ቡልቻ ሹራ ምትክ ደግፌ አለሙን እና ፊሊፕ አጄህን በቋሚ አሰላለፉ አካተዋል ።
ኢትዮጵያ መድኅን ከመሪዎቸለ ላለመራቅ ሲዳማ ቡና ደግሞ ከወራጅነት ስጋት እፎይታን ለማግኘት ሶስጥ ነጥቡን ፈልገው በገቡበት ጨዋታ በጨዋታው ጅማሬ ገና በአምስተኛው ደቂቃ ላይ ፊሊፕ አጄህ ለሲዳማ ቡና ግብ አስቆጥሯል ።
አጥቂው ከፍሬው ሰለሞን የደረሰውን ኳሶ ተጠቅሞ ኳስ እና መረብነ አገናኝቷል ።
- ማሰታውቂያ -
በቀጣዮቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ደቂቃዎች በሁለቱም በኩል ወደ ፊት ደርሶ የተገጣሚን የኋላ መስመር ለመፈተን ጥረቶች ቢደረጉም ያን ያህል ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ አልቻሉም ።
በ24ኛው ደቂቃ ላይ ይገዙ ቦጋለ ከቅጣቱ ምት በቀጥታ ወደ ግብ የመታው እና በኢትዮጵያ መድኅኑ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑሪ የተመለሰው ኳስ የሲዳማ ቡና ሌላኛው የግብ ሙከራ ነበር ።
በኢትዮጵያ መድኅን በኩል በተለያዩ አማራጮች ወደ ሲዳማ ቡና ሳጥን ለመግባት የተደረጉት ጥረቶች በሲዳማ ቡና ተከላካዮች በተደጋጋሚ ይጨናገፉ ነበር ።
በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ባሲሱ ኡመር ከቅጣት ምት ወደ ግብ ክልል ያሻገረው እና ሀቢብ አግኝቶ ያልተጠቀመበት ኳስ ለአሰልጣኝ ገብረመድኅን ሀይሌው ቡድን አስቆጪ አጋጣሚ ነበር ።
የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በበርካታ ውዝግቦች የታጀበ እና ሶስት የቀይ ካርዶች የታዩበት ነበር ።
የሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ አስር ደቂቃዎች በኋላ የኢትዮጵያ መድኅኑ እና የቀድሞው የሲዳማ ቡና አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ በኢንተርናሽናል አርቢትር ባምላክ ተሰማ ውሳኔ የቀይ ካርድ ተመልክተዋል ።
ከአሰልጣኙ የቀይ ካርድ በኋላ ብዙም ሳይቆይት በመጀመሪያው አጋማሽ ቻላቸውን ተክቶ ወደ ሜዳ የገባው ኪቲካ ጀማ የቀይ ካርድ ተመልክቷል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ በአንፃራዊነት ሲዳማ ቡናዎች ከተጋጣሚያቸው በተሻለ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል ። በተለይም ፊት መስመሩን የሚመሩት ይገዙ ቦጋለ እና ፊሊፕ አጄህ ያመከኗቸው ኳሶች ምናልባትም የሲዳማ ቡናን መሪነት ከፍ ማድረግ የሚችሉ ነበሩ ።
በኢትዮጵያ መድኅን በኩል ግብ ለማስቆጠር የሚደረጉት ጥረቶች በሶስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ሲደርሱ ድክመቶች ነበሩባቸው ። በዚህም መክበብ ደገፉን የፈተኑ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ተቸግረዋል ።
በሲዳማ ቡና በኩል የመሀል ክፍሉን በአስደናቂ መልኩ ሲመራ የነበረው ሙሉቀን አዲሱ በባሲሩ ኡመር እና ቴዎድሮስ ተስፋዬ ላይ በሰራቸው ጥፋቶች በሁለተኛ የቢጫ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ።
በመጨረሻም ሲዳማ ቡና በ1 – 0 ውጤት ከጨዋታው ሙሉ ሶስት ነጥብ ይዞ ወጥቷል ።
ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና ነጥቡን 27 በማድረስ ወደ 12ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ኢትዮጵያ መድኅን በ41 ነጥቦች በነበረበት 3ኛ ደረጃ ላይ ይቆያል ።