በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ23ተኛ ሳምንት መርሐግብር ሶስተኛ ዕለት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና ጨዋታቸዉን ያለ ግብ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።
በእኩል ሰላሳ አንድ ነጥብ በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ ተቀምጠዉ የዕለቱ ጨዋታቸውን ለማከናወን ወደ ሜዳ በገቡት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ቀዳሚ የሚያደርጋቸዉን ግብ ለማስቆጠር እና የጨዋታዉ የበላይ ለመሆን ሲጥሩ በጨዋታዉ መባቻ ላይም ሀድያዎች ጥሩ የግብ ዕድል መፍጠር ችለዉ ነበር ፤ በዚህም ተመስገን ብርሀኑ ከብርሀኑ በቀለ የተቀበለዉን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂዉ መሐመድ ሙንታሪ ኳሷን ወደ ዉጭ አውጥቶታል።
የመጨረሻ ተከላካዮቹን የሜዳዉ መሐል ድረስ አስጠግቶ ይጫወት የነበረዉን ሀድያ ሆሳዕና ለማጥቃት ለፈጣን የመስመር አጥቂዎቻቸዉ በሚልኳቸዉ ረጃጅም ኳሶች በጨዋታዉ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የነበሩት ሀይቆቹ በኤርትራዊው አጥቂ አሊ ሱለይማን እና ሙጅብ አማካኝነት በአጋማሽ ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ ተስተውሏል።
- ማሰታውቂያ -
በተለይ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች በቀሩበት ወቅትም ሀይቆቹ በአብዱልባሲጥ አማካኝነት ድንቅ ሙከራን ማድረግ ቢችሉም በግብ ጠባቂዉ ፔፔ ሰይዶ አማካኝነት ኳሷ ግብ ከመሆን ከሽፋለች።
ከዕረፍት መልስ የተወሰደባቸውን ብልጫ ለመመለስ በሚል በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ቀይረዉ ወደ ሜዳ ያስገቡት ሀይቆቹ ነገር ግን ባሰቡት ልክ ያን ያህል ጥሩ ሲንቀሳቀሱ አልተስተዋለም። በተቃራኒው በመጠኑም ቢሆን ጥሩ የሚባል የመሐል ሜዳ ብልጫ የነበራቸዉ ነብሮቹ በሁለተኛዉ አጋማሽም ኳስ እና መረብን ለማገናኘት እንዲሁም ተጠቃሽ ሙከራም ለማድረግ ሲቸገሩ ተስተውሏል።
በዚህ ሂድት የቀጠለዉ እና ያን ያህል እምብዛም በሙከራ ያልታጀበዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም በመደበኛዉ ዘጠና ደቂቃ እንዲሁም በጭማሪዉ አምስት ደቂቃም ግብ ስይቆጠርበት ጨዋታዉ 0ለ0 በሆነ አቻ ዉጤት ተገባዷል። ዉጤቱን ተከትሎም ሀዋሳ ከተማ በ32 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ፤ በተመሳሳይ በዕለቱ ጨዋታ አንድ ነጥብ ያሳካዉ ሀድያ ሆሳዕናም በ32 ነጥብ በግብ ክፍያ ተሽሎ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።