በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ29ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን መርሐግብሮች በዛሬው ዕለትም ቀጥለው ሲደረጉ በቀዳሚው ጨዋታ አዳማ ከተማ ኢትዮጵያ መድኅንን 3 – 0 አሸንፏል ።
በጨዋታው በአዳማ ከተማ በኩል በ28ኛው ሳምንት ከሀድያ ሆሳዕና አቻ በተለያዩበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ አድናን ረሻድን በአሜ መሐመድ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል ። በኢትዮጵያ መድኅን በኩል በሳምንቱ ኢትዮጵያ ቡና በረቱበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ሶስት ለውጦች በማድረግ ሀቢብ መሐመድ ፣ ያሬድ ካሳዬ እና እዮብ ገብረማርያምን በተካልኝ ደጀኔ ፣ ፀጋሰው ድማሙ እና ሀቢብ ከማል ምትክ አሰልፈዋል ።
በጥሩ የሜዳ ላይ ፉክክር የተጀመረው ጨዋታ በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን በማድረግ የጀመሩት ነበር ። በአንፃራዊነት በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ የነበሩት ኢትዮጵያ መድኅኖች የአዳማ ከተማን የኋላ መስመር አልፈው የግብ ዕድል ለመፍጠር ደቂቃዎች ወስደውባቸው ነበር ።
- ማሰታውቂያ -
በአዳማ ከተማም ሆነ በኢትዮጵያ መድኅን በኩል የነበረው የጨዋታ እንቅስቃሴም በግብ ሙከራዎች ሳይታጀብ እስከ 17ኛው ደቂቃ ተጉዞ ነበር ።
በ17ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ የግብ ሙከራ የተደረገ ሲሆን ሳይመን ፒተር የአዳማ ከተማው ግብ ጠባቂ ሰይድ ሀብታሙ ከግብ ክልሉ መውጣቱን ተመልክቶ ወደ ግብ የመታውን ግብ ጠባቂው ለጥቂት ግብ ከመሆን አድኖታል ።
በአዳማ ከተማ በኩል ቀዳሚው ጠንካራ የግብ ሙከራ ከተጋጣሚያቸው የግብ ሙከራ አራት ደቂቃዎች በኋላ የተደረገ ነበር ። አጥቂው ዳዋ ሆጤሳ በኢትዮጵያ መድኅን ሳጥን ውስጥ ወደ ቀኝ ባደላ ቦታ የደረሰውን ኳስ አክርሮ ወደ ግብ ቢመታም በግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ተመልሶ ወጥቷል ።
በ28ኛው ደቂቃ ላይ በኢትዮጵያ መድኅን በኩል ከግራ መስመር አቅጣጫ የተሻገረውን ኳስ ቴዎድሮስ በቀለ በግንባር በመግጨት ለባሲሩ ኡመር ቢያቀበልም ከባሲሩ ቀድሞ ሰይድ ሀብታሙ ኳሱን ተቆጣጥሮታል ።
በፈጣን እንቅስቃሴዎች የኢትዮጵያ መድኅንን የተከላካይ መስመር ለመፈተን የቻሉት አዳማ ከተማዎች በ32ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አስቆጥረዋል ።
መስዑድ መሐመድ ከማዕዘን ከሳጥኑ ውጪ ለነበረው ደስታ ዮሐንስ ያቀበለውን ኳስ የግራ መስመር ተከላካዩ ደስታ ከርቀት አክርሮ በመምታት አስደናቂ ግብ ከመረብ አሳርፏል ።
የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜም በአዳማ ከተማ የ1 – 0 መሪነት ተጠናቀቀ ።
በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ መድኅኖች ወደ አቻነት ለመመለስ ጥረቶችን በማድረግ የጀመሩት ቢሆንም ወደ ግብ ክልል ደርሶ ጠንካራ የግብ ዕድሎች ከመፍጠሩ አንፃር አዳማ ከተማዎች የተሻሉ ነበሩ ።
በአጋማሹ ቀዳሚ የግብ ሙከራም በ57ኛው ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ታረቀኝ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባር ገጭቶ ለማስቆጠር ያደረገው ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።
ከስድስት ደቂቃዎች በኋላም ቢንያም አይተን ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ በአቡበከር ኑራ ተይዟል ። አዳማ ከተማዎች በፈጣን እንቅስቃሴዎች የተሻለ የግብ ዕድል መፍጠር ችለው በቀጠለቡት የሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ መድኅኖች ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ ተቸግረው ቆይተዋል ።
ጨዋታው 78ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስም የቢንያም አይተን ድንቅ ግብ የአዳማ ከተማን መሪነት ወደ 2 – 0 ከፍ አድርጓል ። ቢንያም አይተን ከሀብታሙ ሸዋለም ስህተት ያገኘውን ኳስ አንድ ለአንድ ከተገናኘው አብዱልከሪም መሐመድ ጋር ተፋልሞ ለአቡበከር ኑራ ምንም ዕድል ሳይሰጥ ግሩም ግብ አስቆጥሯል ።
ከስምንት ደቂቃዎች በኋላም አዳማ ከተማዎች መሪነታቸውን ወደ 3 – 0 ያደረሱበትን ግብ በዳዋ ሆጤሳ አማካኝነት አስቆጥረዋል ። ኤልያስ ለገሰ ከቀኝ አቅጣጫ ይዞ ገብቶ ለዳዋ ሆጤሳ የቀነሰለትን ኳስ አጥቂው ከመረብ አሳርፎታል ።
በመጨረሻም በአዳማ ከተማ የ3 – 0 አሸናፊነት ጨዋታው ፍፃሜውን አግኝቷል ።