በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሀያ ዘጠነኛ ሳምንት ሁለተኛ ዕለት ሁለተኛ ጨዋታ የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ቡድን ፋሲል ከነማ አስቀድሞ መዉረዱን ያረጋገጠዉን ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2ለ1 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
በርከት ያሉ የተጫዋቾች ለዉጥ አድርገዉ ወደ ሜዳ በገቡት ፋሲል ከነማዎች የረጃጅም ኳስ እና የቆሙ ኳሶች ማጥቃት እንዲሁም በኢትዮ ኤሌትሪኮች የመሐል ሜዳ የተሻለ እንቅስቃሴ በጀመረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ቀዳሚ ተጠቃሽ ሙከራ በማድረግ ረገድ አፄዎቹ ቀዳሚ ነበሩ ፤ በዚህም በጨዋታው መባቻ 12ተኛ ደቂቃ ላይ አማካዩ ይሁን እንዳሻዉ ከአጥቂዉ ኦሴ ማውሊ የተቀበለዉን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ለጥቂት ወደ ዉጭ ወጥታለች።
ከዚች ሙከራ በኋላ ምንም እንኳን በሜዳዉ የመሐል ክፍል ኤሌትሪኮች የተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም ነገር ግን በመጀመሪያዉ አጋማሽ ተጠቃሽ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረዉ በተቃራኒው የመጀመሪያው አጋማሽ ሊገባደድ አምስት ያህል ደቂቃዎች በቀሩበት ወቅት ግብ አስተናግደዋል። በዚህም በ40ኛዉ ደቂቃ ላይ አጥቂዉ ኦሴ ማዉሊ ከአማካዩ አቤል እያዩ የተቀበለዉን ኳስ ለመስመር ተጫዋቹ አለም ብርሀን ይግዛው አቀብሎት ተጫዋቹ የግል ቅልጥፍናዉን ተጠቅሞ ኳሷን ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
ከዕረፍት መልስ ተሻሽለዉ ወደ ሜዳ የተመለሱ የሚመስሉት አፄዎቹ በ50ኛዉ ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም ከቀኝ የፋሲል ከነማ ማጥቃት በኩል የመስመር ተጫዋቹ ዱላ ሙላቱ በአስገራሚ ብቃት ለአጥቂዉ ለኦሴ ኦሴ ያቀበለዉን ኳስ አጥቂዉ በቶሎ ወደ ግብነት በመቀየር የክለቡን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።
ሁለተኛ ግብ ካስቆጠሩ በኋላ የማጥቃት ሀይላቸዉን አጠንክረዉ የቀጠሉት አፄዎቹ በአማካዩ ይሁን እንዳሻዉ እንዲሁም አጥቂዉ ኦሴ ማውሊ ከርቀት ተደጋጋሚ ሙከራዎችን በማድረግ ለግብ ዘቡ ካክፖሸሪፍ ፈተና ሲሆኑበት ተስተውሏል። በተቃራኒው ሁለት ያህል ግብ ካስተናገዱ በኋላ በመጨረሻዎቹ አስር ያህል ደቂቃዎች ጫና ፈጥረዉ መጫወት የቻሉት ኤሌትሪኮች በ86ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም በተጠቀሰዉ ደቂቃ ከመዓዘን ምት የተሻማዉን ኳስ አብዱራህማን ሙባረክ በግንባሩ በመግጨት ግብ በማስቆጠር ክለቡን ወደ ጨዋታው መመለስ ችሏል።
ኢትዮ ኤሌትሪኮች ወደ ጨዋታዉ የሚመልሳቸዉን ግብ ማስቆጠር ከቻሉ በኋላ አቻ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ማድረግ የቀጠሉት ኤሌክትሪኮች በአብዱራህማን ሙባረክ እና ስንታየሁ ሞለጬ በመሳሰሉ ተጫዋቾች ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ በጨዋታውም በአፄዎቹ 2ለ1 በሆነ ዉጤት ተሸንፈዋል።
ዉጤቱን ተከትሎም በጨዋታው ድል የቀናዉ ፋሲል ከነማ በ42 ነጥብ ወደ አራተኛ ደረጃ ከፍ ሲል በተቃራኒው ሽንፈት ያስተናገደዉ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ በ12 ነጥብ አስራ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።