አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጥሪ ካደረጉላቸው 25ቱ ተጨዋቾች 17ቱ በተባሉት ቀን ሪፖርት ሲያደርጉ የቀሩት 8ቱ ከቀናት በኋላ ትላንት ተቀላቅለዋል።
ዕረፍት የተሰጣቸው የፋሲል ከነማዎቹ አስቻለሁ ታመነና ያሬድ ባዬ እንዲሁም አልገደድም በማለት በአሰልጣኛቸው ያልተለቀቁት 6ቱ የፈረሰኞቹ ተጨዋቾች አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ አቤል ያለው፣ ጋቶች ፓኖም፣ ምኞት ደበበ፣ ደስታ ዮሀንስና ቸርነት ጉግሳ ቡድኑን ተቀላቅለዋል።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የጊዮርጊስ ተጨዋቾች እስከ አርብ ካልተቀላቀሉ ተተኪ ተጨዋች እጠራለሁ የሚል ጠንካራ አቋም በመያዛቸው ፌዴሬሽኑ ከጊዮርጊስ አመራሮች ጋር ተደራድሮ የትላንት ጠዋት ልምምድ ከሰሩ በኋላ ባህርዳር አቅንተው ብሉናይል አቫንቲ ሆቴል ከቡድኑ ጋር እንዲቀላቀሉ ተደርጓል።
ከዚህ ውጪ የኢትዮጵያ ቡናው ታፈሰ ሰለሞንም በፋሲል ከነማው በዛብህ መለዮ ተተክቶ ቡድኑ ጠንካራ ዝግጅት ማድረጉን ቀጥሏል። ቡድኑ ዛሬ ባረፈበት ሆቴል የመስቀል በዓልን ያከበሩ ሲሆን ለአዲሱ ሙሽራ አስቻለሁ ታመነ ደስታቸውን ገልጸውለታል ተብሏል።
ከቀናት በኋላ ለሚካሄደው የዋሊያዎቹና የባፋና ባፋና ጨዋታ ሊቢያዊው አርቢትር ኢብራሂም ሙታዝ መመደባቸው ይታወቃል።
አስተያየት ይስጡ