ምርጫ ያልሸፈነው ተጠባቂው የበርሊን ማራቶን
ቀነኒሳ ለሌላ አዲስ ታሪክ የሚጠበቅበት የበርሊን ማራቶን የብዙዎቹን ትኩረት ስቧል
በእርግጥ በጀርመን ምርጫ እየተካሄደ ነው፤ ጀርመን አዲሱን ቻንስለር ወይም መሪዋን ለመምረጥ ደፋ ቀና ስትል ከርማለች፤ ግን ይሄ የሀገሪቱ ትልቁ አጀንዳ የአለማችንን ትልቁን ማራቶን አልሸፈነውም፡፡ ከሀገሪቱ ምርጫ ባልተናነሰ የብዙዎች አጀንዳ፣ የጋዜጦች የፊት ገፅ ማድመቂያ አብይ ጉዳይ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደው 47ኛው የበርሊን ማራቶን የብዙዎች አይን ማረፊያ ሆኗል፡፡ የፕላቲኒየም ደረጃ ያለው የበርሊን ማራቶን የብዙዎችን ትኩረት እንዲያገኝ ምክንያት ከሆኑት አንኳር ነጥቦች አንዱ የዓለማችን ሁለተኛው የማራቶን ሰአት ባለቤት የሆነው ኢትዮጵያዊው አትሌት ቀነኒሣ በቀለ በውድድሩ ላይ እንደሚሳተፍ ቀደም ብሎ ማረጋገጫ በመስጠቱ ነው፤ በ2019 በኤሉድ ኪፕቾጌ ተይዞ የነበረውን የአለም የማራቶን ሪከርድን ለመስበር ተቃርቦ በ2 ሰከንድ ምክንያት ሳይሳካለት የቀረው አትሌት ቀነኒሣ በቀለ የፊታችን እሁድ በሚካሄደው የበርሊን ማራቶን ለአለም ህዝብ አዲስ ነገር ሊያሳይ ይችላል ተብሎ ከወዲሁ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶታል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ለመሮጥና ሪከርድ ለመስበር ምቹ ቦታ ነው፤ በሚባለው የበርሊን ማራቶን ከዚህ በፊት ሁለቴ የሮጠው አትሌት ቀነኒሣ በቀለ በ2016 2፡03፡03 በ2019 ደግሞ 2፡01፡41 በሆነ ምርጥ ሰዓት በመግባት በግሉም ሆነ በውድድሩ ታሪክ የምርጥ ሰዓት ባለቤት የሆነበት ታሪካዊ ቦታው ነው፡፡
የዓለምና የኦሎምፒክ የሁለት ጊዜ አሸናፊ የሆነው አትሌት ቀነኒሣ በቀለ ከውድድሩ በፊት ለዜና ሰዎች እንደተናገረው ከሁለት አመት በፊት የዓለም ሁለተኛውን ምርጥ የማራቶን ሰዓት ሲያስመዘግብ ከነበረው ዝግጅት የተሻለ ተዘጋጅቶ ለውድድሩ እንደቀረበ ተናግሯል፡፡
የቀነኒሳ አሰልጣኝ የሆነው ሀጂ አዴሎ ከOlympic.com ጋር ባደረገው ቆይታ “ቀነኒሣ በዚህ አመት ለተሻለ ውጤት ይሮጣል፤ ባለፈው በርሊን ላይ ሲሮጥ ከነበረው በተሻለ ተዘጋጅቶ ነው” የቀረበው በማለት የቀነኒሳን ሃሣብ የሚያጠናክር አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
“አሁን በተሟላና በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛል” በማለት አስተያየታቸውን ለድረ-ገፁ የሰጡት አሰልጣኝ ሀጂ አዴሎ “በውድድሩ ለማሸነፍ የሚረዳው ከፍተኛ የራስ መተማመን አለው፤ በጥሩ ብቃትም ላይ ይገኛል” ብለዋል፡፡
የአለም ሁለተኛው የማራቶን ምርጥ ሰዓት ባለቤት እንዲሁም የአለም የ5 ሺ እና የ10 ሺ ሜትር የሪከርድ ባለቤት የሆነው አትሌት ቀነኒሣ በቀለ በአፕሪል 2020 ለኦሎምፒክ ድረ-ገፅ በሰጠው አስተያየት “ሁለት ሰከንድ ምን እንደሆነ ታውቃለህ? የአለም ሪከርድን ለመጨበጥ ሁለት ሰከንድ ብቻ ነበር የቀረኝ፤ ይሄ በጣም ያስቆጫል በጣምም ያማል” በማለት መናገሩ የሚታወስ ሲሆን የፊታችን እሁድ በሚደረገው ውድድር ይሄንን ቁጭቱን የሚያስረሣ አዲስ ታሪክ ለመስራት ወደ በርሌን እንደመጣ የሚገልፅ አስተያየት ሰጥቷል፡፡
የ39 አመቱ ቀነኒሣ ብቀለ የፊታችን እሁድ በበርሊን ማራቶን የሚሮጠው ከ18 ወራት ቆይታ በኋላ ሲሆን በ42 ቀናት ጊዜ ውስጥ የበርሊን ማራቶንን ጨምሮ ሁለት ማራቶኖችን የመሮጥ እቅድ መያዙም ነው የተሰማው፡፡
እየወጡ እንዳሉ መረጃዎች ከሆነ ቀነኒሣ በ42 ቀናት ውስጥ የበርሊን ማራቶንን ኖቪምበር 7 የሚደረገውን የኒውዮርክ ማራቶንን የመሮጥ እቅድ እንዳለው ታውቋል፡፡ ለ18 ወራት ከውድድር ውጪ ሆኖ መቆየቱን አስመልክቶ ለስፖርት ኢሉስትሬትድ አስተያየቱን የሰጠው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ “ሙሉ አመቱን ያለ ውድድር ነው ያሳለፍኩት፤ ይሄ ደግሞ ለአትሌቶች በጣም ከባድ ነው፤ በዚህ ውድድር ላይ በመካፈል ምን ሊፈጠር እንደሚችል አይበታለሁ” ብሏል፡፡
በ42 ቀናት ውስጥ በሁለት የአለማችን ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች ላይ መካፈሉን አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡት አሠልጣኝ ሀጂ አዴሎ “በተጠቀሱት ቀናት ውስጥ ሁለት ማራቶኖች መሮጥ በሳይንሱም የማይመከር ነው፤ ነገር ግን ቀነኒሳ በቀለ በተፈጥሮው የተለየ ስጦታ ያለው ነው፤ እሱ ጉልበትን ከጠንካራ ስራ ጋር አጣምሮ የያዘ በጥሩ ጤንነትና በጥሩ ብቃት ላይ የሚገኝ በመሆኑ የበርሊኑንም የኒውዮርኩንም ማራቶን በተጠቀሱት ቀናት ውስጥ ይሮጣል፤ በችሎታው የሚተማመን ሰው ነው” ብለዋል፡፡
ከሰዓታት በኋላ በሚካሄው የበርሊን ማራቶን ከቀነኒሳ በቀለ ሌላ በውድድሩ ለአሸናፊነትና ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ በ2017 ኤሊዩድ ኪፕቾጌን ተከትሎ ሁለተኛ የወጣው ጉዬ አዶላ እንዲሁም በ2020 በዱባይ ማራቶን ውጤታማ የነበረው የ22 አመቱ ወጣት አሊካ አዱኛ የተሻለ ግምት የተሰጣቸው አትሌቶች ናቸው፡፡ በሴቶች የበርሊን ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ ህይወት ገ/ኪዳን እንዲሁም በ2015 የኮፕንሃገንና የሊዝበን ማራቶን አሸናፊ የሆነችው ኬንያዊቷ ፕሩቲ ሪዮኖሪታ የሚያደርጉት ፉክክር ከወዲሁ የሚጠበቅ ነው፡፡
በርሊን የማራቶን ሪከርዶች ሂደት
ሴፕቴምበር 2019 ቀነኒሣ በቀለ (ኢትዮጵያ) 2፡01፡41
ሴፕቴምበር 2018 ኤሊዮድ ኪፕቾጌ (ኬንያ) 2፡01፡39
ሴፕቴምበር 2014 ዴኒስ ኪሜቶ (ኬንያ) 2፡02፡57
ሴፕምበር 2013 ዌልሰን ኪፕሳንግ (ኬንያ) 2፡03፡23
ሴፕቴምበር 2011 ፓትሪክ ማካኢ (ኬንያ) 2፡03፡38
ሴፕቴምበር 2008 ኃይሌ ገ/ስላሴ (ኢትዮጵያ) 2፡03፡59
ሴፕቴምበር 2007 ኃይሌ ገ/ስላሴ (ኢትዮጵያ) 2፡04፡26
ሴፕቴምበር 2003 ፓልቴርጋርት (ኬንያ) 2፡04፡55