“እንኳን ተጨዋቹ ወጌሻው በዲ.ኤስ.ቲቪ ለመታየት ብሎ ቦርጩን አጥፍቶ አሯሯጡን ለማስተላከል እየሰራ ነው” ዳንኤል ደምሴ /ድሬዳዋ ከተማ/

 

“እንኳን ተጨዋቹ ወጌሻው በዲ.ኤስ.ቲቪ ለመታየት ብሎ ቦርጩን አጥፍቶ አሯሯጡን ለማስተላከል እየሰራ ነው”
ዳንኤል ደምሴ /ድሬዳዋ ከተማ/


አሁን ድረስ ህልም ይመስለዋል… ከከባድ የአደጋ ገጠመኞች ተርፎ ለዚህ መብቃቱን እንደገና መወለድ ነው ይለዋል፤ ከመቐለ አፋር ከአፋር አዲስ አበባ የነበረውን የጭንቅ ጉዞ የጭንቅ አማላጂቷ ጋርዳን ከጓደኞቼ ጋር መጥተናል እግዚአብሔር ይመስገን ሲልም ያመሰግናል፤ ለኢትዮጵያ ቡና፣ ለመቐለ 70 እንደርታ፣ ለወልዋሎ አዲግራት /አንድም ቀን ልምምድም ጨዋታም ባያደርግም/ አሁን ለ2013 ውድድር ለድሬደዋ ከተማ ፈርሟል፤ በመቐለ የአንድ አመት ቆይታዬ ከ16 ጨዋታ በ15ቱ ቋሚ ሆኜ ኮንትራቴ አይታደስም መባሉ እግር ኳሱ ወዴት እየሄደ ነው ብዬ እንድጠይቅ አድርጎኛል ይላል በታዳጊነቱ የፀጉር አቆራረጡን በመቃወም በመቀስ ፀጉሩን ለቆረጠው አሰልጣኝ አስራት ኃይሌ ትልቅ ክብር አለው… የዛሬው እንግዳችን ዳንኤል ደምሴ ከሀትሪኩ ዮሴፍ ከፈለኝ ጋር በነበረው ቆይታ ስለ አስፈረው የአፋርና የመቐለ ቆይታው፣ መቐለን ስለተሰናበተበት ሂደት፣ ስለ ወልዋሎ አዲግራት ውሉና፣ አሁን ስላለበት የእግር ኳስ ሂደት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል፡፡

ሀትሪክ፡- ለወልዋሎ አዲግራት ፈርመህ የቆየኸው መቐለ ከተማ ነው…ለምን?

ዳንኤል፡- እዚህ ላይ መናገር የምፈልገው እግዚአብሔር እኔን ከጉድ እንዳወጣኝ ጓደኞቼንም በሠላም እንዲያወጣቸው ነው እየፀለይኩ ያለሁት…መቐለ ስንገባ 14 ሆነን ነበር እኔ ደግሞ የኮቪድ ምርመራ ሳደርግ ማሽኑ የለብህም ወይም አለብህ አይልም “ሪፒት” ነው የሚለው…በነጋታው የተጨዋቾቹ ውጤት መጥቶ ኔጌቲቭ በመሆናቸው ወደ አዲግራት ሄዱ እኔ መቐለ ቀረሁ…በአጋጣሚው ጦርነት ተነሳ…መቐለ ሆቴል ተቀምጬ እያለሁ አንድ ሰው ዞር ብሎ አላየኝም…የወልዋሎ አዲግራት አንድም ሰው አጠገቤ አልነበረም…አምኞቸው ሄጄ የሚንከባከበኝ አንድም ሰው አጣሁ…የስፖርተኛ ህይወት ያሳዝናል…መቐለ ከተማ እያለሁ ከቡድኑ ጋር ግንኙነት በመፍጠር ከተወሰኑ ተጨዋች ጋር በአፋር አድርገን አዲስ አበባ ገባን…እግዚአብሔር ይመስገን ማለት እፈልጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ጉዞው እንዴት ነበር?

ዳንኤል፡- ጉዞው ከባድ ነበር……እግዚአብሔርም አላሳፈረንም ለቤታችን አብቅቶናል፡፡

ሀትሪክ፡- ቤተሰቦችህስ አይንህን እስኪያዩ የነበሩበት ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

ዳንኤል፡- ቤተሰቦቼ ከምልህ በላይ ተጎድተዋል ለቅሶ መቀመጥ ነው የቀራቸው…ቤት ስትሄድ ያለው ሁኔታ ለቅሶ ነው የሚመስለው…የሚመጣው ሰው ቁጥር ያስደነግጣል…በጣም ጎድቻቸዋለው እግዚአብሔር ይመስገን ተርፌ ለቤቴ በቅቼ ቤተሰቦቼን ለማሳረፍ ችያለው፡፡

 

 

ሀትሪክ፡- የ4 ክለቦችን ማሊያ ለብሰሃል…የተለያዩ ከተሞች እንደመጓዝህ ቱሪስት የሆንክ አልመሰለህም?

ዳንኤል፡-/ሳቅ በሳቅ/ በለው…ልክ ነህ ማለት ይቻላል…ላንድክሮዘሩ ቀረ እንጂ ቱሪስት ነኝ /ሳቅ/ ሀገሬን አውቃለሁ ብዬ መናገርም እችላለሁ…ቢያንስ ማምለጫ ቋንቋ ለምጃለሁ…ረብሻ ቢነሳ ማምለጫ ቋንቋ አለኝ፡፡

ሀትሪክ፡- ለመቐለ 70 እንደርታ 1 አመት ፈርመህ ነበር ቆይታህን እንዴት ትገልፀዋለህ?

ዳንኤል፡- በአንድ አመት የነበረኝ ቆይታ ጥሩ ነበር፤ ነገር ግን የሀገራችን ኳስ አካሄድ ያማል…አንድ ተጨዋች 3 እና 4 አመት መፈረም አለበት…ምክንያቱም የቡድኑ አድቫንቴጅ መጠበቅ ስላለበት ይባላል አንዳንዴም የተጨዋቾች አድቫንቴጅ መታየት አለበት…እዚህ ግን የለም፡፡ በጥሎ ማለፍ 90 ደቂቃ ጀምሮ ከ17 ጨዋታ 16 የሊጉ ግጥሚያ ላይ ቋሚ ነበርኩ…አሰልጣኙ ባይፈልገኝና ባይረካብኝ አያቆየኝም…ይሄ እውነት ነው…የተሻለው ነገ ኳሱ እንዲያድግ የተጨዋቾች መብት መከበር አለበት ከመቐለ የወጣሁበት ምክንያት ያስቃል…ያለህን ቀሪ ብር ትተህ ፈርም ተብዬ እምቢ ስላልኩ ከመቐለ 70 እንደርታ ተሰናበትኩ…ስፖርተኛን ተጠቃሚ ያደረገ መስመር መሰመር አለበት…የኢትዮጵያ እግር ኳስ አድጎ ኳስ አቁም ብባል ደስ ይለኛል…መቐለዎች ያደረጉት ለኔ አይገባኝም ነበር…በጣም ቅር ብሎኛል፡፡

ሀትሪክ፡-ውልህ እንደማይታደስ ስትሰማ ምን አይነት ስሜት ፈጠረብህ?

ዳንኤል፡- ቅርማ ያሰኛል…ከ17 ጨዋታ 16ቱን ተጫውቼ ከኔ ይልቅ 2 ጨዋታ ብቻ ተጫውቶ ውል የተራዘመለት ተጨዋች አለ…ይሄ ያስደስነግጣል…በጣምም አሞኛል…ቶሎ ወጥቼ ለሌላ ቡድን መጫወት ወይም ሌላ ስራ ልሰራ ብዬ ነው የተመኘሁት…የልፋቴ ውጤት ማየትን መከልከል ያበሳጫል…ከ15 በላይ ጨዋታ ጥሩ ሆነው ተጫውተው…ለብሔራዊ ቡድን ሳይመረጡ በ3 እና 4 ጨዋታ የተመረጡም አሉ…ይሄ ሚዛናዊነት የጎደለው ስራ መቆም አለበት…ውጪ ስታይ የማን.ዩናይትዱ ግሪንውድ የማን ሲቲው ፎደን ሲመረጡና ሀገራቸውን ሲያገለግሉ እነ ግሪሊሽም ሲመረጡ ምክንያቱ ወቅታዊ አቋማቸው ታይቶ ነው በሀገራችን ግን ለምን ይሄ እንደማይሰራ አይገባኝም ትልቅ ቡድን ተጫወተ ተብሎ ሳይሆን ብቃታችን ብቻ ሊያስመርጠን ይገባል፡፡

ሀትሪክ፡- ከመቐለ 70 እንደርታ ቆይታ በኋላ ለወልዋሎ አዲግራት ፈርመህ ሳትጫወት ነው ወደ ድሬዳዋ የገባኸው… እስቲ ሂደቱን አውራኝ?

ዳንኤል፡- ከክለቡ ጋር ተስማምቼና ፈርሜ ገባሁ፤ ጥቅማጥቅሜን አስከብሬ ነው ወደ መቐለ ያመራሁት ከዚያ ውስጥ የሚለቀቅ ተብሎ ቼክ ተሰጥቶኝ ነበር፡፡ መቐለ ባንክ ቤት ገብቼ ላወጣ ስሄድ ምንም ብር የለም…ወቅቱ ደግሞ ደመወዝ ምናምን አልነበረምና ተናደድኩ…በቀጥታ ወደ ፌዴሬሽኑ ስሄድ ቆይ ጠብቅ አሉኝ…ያለውን ነገር አስረድቼ ተቀባይነት አገኘሁ…ችግሩን ተረድተው ውሳኔ ላስተላለፉት የፌዴሬሽኑ አመራሮች አመሰግናለሁ…ያለው ሁኔታ አይተው ፈቀዱልኝና ወደ ድሬዳዋ ገባሁ የፌዴሬሽኑ ውሣኔ መነሻ እኔ ሆኜ ነው ደንብ ሆኖ የፀደቀው፤

ሀትሪክ፡-ለአንድ አመት ከድሬዳዋ ፈርመሃል.. ያለህበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

ዳንኤል፡-ድሬደዋ ዝግጅት ላይ ነው ያለው በዚህ መሀል ክፍተት አለበት ባሉበት ቦታ የኔ በመሆኑ ደውሉልኝ አብሬያቸው የተጫወትኳቸው ጓደኞቼ ነበሩና እነርሱ ጥቆማ አቀረቡ… እነ ኤሊያስ ማሞ… እነ ሄኖክና እነ ያሬድ የሚባሉ ጥሩ መሆኔን ነግረው እንድፈርም ተደረገ ከመከለካያ ጋር በተደረገ የወዳጅነት ጨዋታ ላይም ተሳትፌያለው ደስተኛ በመሆናቸው ከወኪሌ ጋር ተገናኝተው እንድፈርም ተደርጓል ውሉ በፌዴሬሽን በይፋ ፀድቋል፡፡

ሀትሪክ፡- ቅዳሜ ፕሪሚየር ሊጉ ሲጀመር የመጀመሪያው ጨዋታ ከሰበታ ጋር ነውና ምን ውጤት ይጠበቅ?(ቃለ ምልልሱ የተሰራው ሐሙስ ምሽት ነው)

ዳንኤል፡- ቡድኑ ጥሩ እየተዘጋጀ ነው…እንዳየሁት የፊትነስ ችግር ግን አለ…ሌላ የወዳጅነት ጨዋታ ማድረግም ነበርብን…ከብዙ ጊዜ ቆይታ በኋላ ስለመጣን ወደ ሪትሙ ለመመለስ ጊዜ ይወስዳል…የተሻለ ነገር ለመስራት ዝግጁ ነን…ነገር ግን የጌም ፊትነስ ለማምጣት ድግግሞሽ ጨዋታ የግድ ነው…እርሱን ነው ትንሽ ክፍተቱ…ጌም ላይ ምርጥ የሚያደርገን ድግግሞሽ ግጥሚያ በመሆኑ ይሄ መስተካከል ነበረበት…አሁንም ከእግዚአብሄር ጋር ጥሩ ነገር ለማሳየት እንጥራለን…በወጣቶች የተገነባ ቡድን ነው… የቡድን መንፈሱ አሪፍ ነው…በባህሪ ተግባብተናል ጥሩ ውጤት ይመጣል ብዬ አስባለው፡፡ መጫወት የሚችሉ ልምድ ያላቸውን ለማምጣት በመታሰቡ ጥሩ ቡድን ይኖረናል ብዬ አምናለው በነገራችን ላይ አሁን እንደ ድሮ አይደለም…ዘሎ በቴሌቪዥን የመታየት ህልም ያለው ተጨዋች የለም…ሁሉም ፕሮፌሽናል የመሆን ህልም ያለው በመሆኑ አቅማቸውን አውጥተው የተሻለ ነገር እንሰራለን ብዬ አምናለሁ፡፡

 

ሀትሪክ፡- የአመቱ የፕሪሚየር ሊግ ውድድር በዝግ የሚካሄድ መሆኑ ጉዳት አለው ወይስ ጥቅም አለው?

ዳንኤል፡- ለኛ ለተጨዋቾቹ በደጋፊ ታጅበን ብንጫወት ደስ ይለኛል ይሄ ባለመሆኑ ያለውን ነገር መቀበል ግድ ይላል እዚህ ላይ መናገር የምፈልገው እንደተጨዋች ብዙም አልተሰራብንም.. በደጋፊ ማሊያ ተጫውተናል፡፡ አምና በመጨረሻ ጨዋታ መቐለ ከሀዲያ ሲጫወት ሜዳው ተቀጥቶ ስለነበር በዝግ ነበር የተጫወትነው… 2ለ1 በረታንበት በዚህ ጨዋታ የነበረን እንቅስቃሴ የሚገርም ነበር አሁንም በዝግ ጥሩ ጨዋታ ልናሳይ እንችላለን ብዬ አስባለው፡፡

ሀትሪክ፡-ጥሩ ቡድን ይሰራል ብለህ ማንን ገመትክ?

ዳንኤል፡- ያለጥርጥር ኢትዮጵያ ቡናንን ነው…ልጆቹ ወጣተች እንዲመሆናቸው የደጋፊ ጫና ባይችሉትም አሰልጣኙ በሚሰጣቸው የስልጠና ሂትና ጫና የመቋቋም አቅም የተሻለ ስራ ይሰራሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለው፡፡

ሀትሪክ፡- ጥሩ ቡድን ይሰራል ብለህ የምትገምተው የትኛውን ቡድን ነው?

ዳንኤል፡-ያለ ጥርጥር ኢትዮጵያ ቡናን ነው ልጆቹ ወጣቶች አንደመሆናቸው የደጋፊውን ጫና ባይችሉትም አሰልጣኙ ካሳዬ አራጌ በሚሰጣቸው የስልጠና ሂደትና ጫና የመቋቋም አቅም የተሻለ ስራ ይሰራሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡-ከስብስብ አንፃርስ ቅዱስ ጊዮርጊስ አያስፈራም?

ዳንኤል፡- አንዳንዴ ስብስብ ብቻ ዋጋ የለውም ጅማ አባጅፋርም 2 ተጨዋች ይዞኮ ዋንጫ በልቷል የቡደን መንፈስ ይወስነዋል፡፡ ስብስቡ ይጠቅማል አይካድም ዋናው የቡድን ስልጠናና መንፈሱ ወሳኝ ናቸው በስብስብ ብቻ ቢሆን እንግሊዝ ሁሌ የአለም ዋንጫን ታሸንፍ ነበር ልዩ ስብስብ የያዘው ወልዲያም ወርዷል እነ ምንያህል፣ተስፋዬ አለባቸውን፣እነ ፍፁምን ይዘን ወረድን…ዋናው ስብስብ ብቻ ሣይሆን አጨዋወትና የቡድን መንፈስ ያስፈልጋል ባይ ነኝ፡፡

ሀትሪክ፡-በዲ.ኤስ.ቲቪ መተላለፉ ለውጪ እድል በር ይከፍታልና ለዚህ ተዘጋጅታችኋል?

ዳንኤል፡- በደንብ ተዘጋጅተናል ትልቅም አድቫንቴጅ አለው እንደ ሀገር እንደተጨዋችና ታዳጊ ትልቅ እድል ይፈጥራል ማስታወቂያውን ስታየው ከጨርቅ ኳስ ወደ …………ነው ይላልና ትልቅ ለውጥ ያመጣል እንኳን ተጨዋቹ ወጌሻው በዲ.ኤስ.ቲቪ ለመታየት ብሎ ቦርጩን አጥፍቶ አሯሯጡን ለማስተላከል እየሰራ ነው /ሳቅ/ በግሌ ከእግዚአብሔር ጋር እድሉን ለማግኘት እጥራለሁ፡፡ ሠላሙን ያምጣልን እንጂ የሆነ ነገር አሳካለው ብዬ አምናለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የኮቪድ 19 አስከፊ 7 ወራትን እንዴት አሳለፍከው?

ዳንኤል፡- በጣም አሰልቺና አድካሚ ጊዜ ነበር፤አስፋልት ላይ ስንጫወት ነው የከረምነውኮ… በጣም ከባድ ጊዜ ነበር እግዜአብሔር ይመስገን ግን እንደፈራነው አልነበረም፡፡

ሀትሪክ፡- ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ በቦታህ ምርጡ ማነው?

ዳንኤል፡- በቦታዬ ምርጡ አሁን ለፋሲል ከተማ የፊረመው ይሁን እንዳሻው ሲጫወት ይመቸኛል የኮትዲቯር ብሔራዊ ቡድንን 2ለ1 በረታንበት ጨዋታ ልዩ ነበርና ምርጥ ነበርክ በርታ ብዬ አሞካሽቼዋለው ከውጪ ደግሞ የሪያል ማድሪዱ ቶኒ ክሩስ ይመቸኛል፡፡

ሀትሪክ፡-አሁን ለደረስኩበት ደረጃ እጁ አለበት ብለህ የምታሞግሰው አሰልጣኝ አለ?

ዳንኤል፡- አዎ በጣም ደግፎኛል አስተዋፅኦ አለው የምለው የመድን ድርጅት አሰልጣኝ የሆነ ፀጋዬ ወንድሙን ነው ከልጅነቴ ጀምሮ ያውቀኛል በአጋጣሚው ታናሽ ወንድሜ ትንሳኤ ደምሴ አቃቄ ቃሊቲ ነበር ለሱፐር ሊግ ክለብ ይጫወታል በደንብ ደግፎናል አሁን እንኳን ድሬዳዋ ከመግባቴ በፊት መድን ጋር ስዘጋጅ ነበር አሰልጣኙ ሁሌ ከጎኔ ስለሆነ አመሰግነዋለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- የማን.ዩናይትድ ደጋፊ ነህ…. ወደ ዩሮፓ ሊግ በመውረዳችሁ ምን ተሰማህ?

ዳንኤል፡- ተበሳጨሁ…ውሃ እየጠጣህ ስታበሽቀን ተናድጄ እያየሁህ ነበር /ሳቅ/ ለሊቱን ሙሉ ሆዴን ስቀጠቅጥ ነው ያደርኩት በተለይ በራሽፎርድ… እሱና ግሪንውድ እርስ በርስ ቢሰጣጡ የሚያገቡትን ማምከናችው አበሳጭቶኛል ዋጋ አስከፍለውናል በርግጥ እነርሱን ለመተቸት የምችልበት ሁኔታ ላይ አይደለሁም ግን የሚታይ ስህተት ፈፅመዋል… እኔ የማነፃፅራቸው ከነ ኔይማር ጋር ነው… ኔይማር ቢሆን እንዲህ ያደርግ ነበር…?…ይህንን ደግሞ አያደርግም እላለሁ እንጂ ዳንኤል ቢሆን ይህን ያደርጋል ወይም አያደርግም ማለት አልችልም… በውጤቱ ግን ተበሳጭቻለሁ፡፡

ሀትሪክ፡- ታዲያ ቁጣ ማብረጂያ ወተት ወይስ ውሃ?

ዳንኤል፡-/ሳቅ/ ጾም ላይ ስለሆንን ውሃዋን ለግቼዋለው የሆነ የተቃጠለ ነገር ግን ከውስጤ ይሸተኝ ነበር /ሳቅ/

ሀትሪክ፡ ሻምፒዮንስ ሊግ ላይ ማን ይንገስ?

ዳንኤል፡- ቢሳካላቸውና ዋንጫ ቢወስዱ የምለው ለፒ.ኤስ.ጂዎች ነው…ኔይማርን በጣም ስለምወደው ሲደሰቱ ማየት እፈልጋለው… ባሎን ዶርን ሁሉ ቢወስድ ደስ ይለኛል…በዚህ ሰዓት ማን.ዩናይትድን ከተውኩ ምርጫዬ ፒ.ኤስ.ጂ ነው፡፡

ሀትሪክ፡- የመጨረሻ ቃል…?

ዳንኤል፡- ቆሜ እንዳወራ ከችግሩ ተርፌ እንድመጣ ያደረገችኝን እመብርሃንን አመሰግናለሁ…ለኔ እንደደረሰች ለጓደኞቼ ደርሳ ከጉድ እንድታወጣቸው ነው የምፀልየው…አገራችንን ሠላም ታድርግልን ሠላም ይብዛልን…ለተሰጠኝ እድልም ሀትሪክን ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ስለ ኮቪድ 19
ያለው ሁኔታ ያስፈራል ሰው ሰርቶ መብላት አለበት አለበለዚያ አይኖርም ይሄ መርህ ከባድ በመሆኑ እግዚአብሔር ያመጣውን ልቀበል ብሎ ነው እየሰራ ያለው… በእርግጥ ሰውን እያሰነፈ ያለው የሚያገግ ሙት ሰዎች ብዛት ነው፡፡ በተጨማሪም ወጣት ላይ ችግር አያመጣም መባሉም ህብረተሰቡን አዘናግቷል፡፡ እናቴ ጋር መሄድ እየፈለኩ በበሽታው ምክንያት እየተሳቀክኩ ነው፡፡ ማክስ ማድረግ በሳኒታይዘር ማፅዳት የሚባለው መረሳቱ ነው ከባድ ነገር… ባረፍንበት ሆቴል አካባቢ ተማሪዎችን ሳይ ያስደነግጣል ማክስ ያላደረገ ይታሰራል የሚለው ቀርቶ ማክስ ያደረገ ይታሰራል የተባለ ይመስላል… ማክስ የሚያደርግ ሰው ማግኘት ብርቅ እየሆነ ነው አሁን ስለ ኮቪድ 19 ማውራት ከባድ ሆነኮ!

ስለ አባይ
እንደ ኢትዮጵያ በጣም ጨፍሬያለሁ በጣም ደስ ብሎኛል በራስ መቆም በራስ የራስን ነገር መወሰናችን ያደስታል የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ መገመት እችላለሁ በመጀመሪያ የውሃ ሙሌት ዜና ጨፍሬያለሁ ደስም ብሎኛል የግንባታውን ውጤት ለማየት ባልችል እንኳን ወደፊት የተሻለ ነገር ይመጣል ማለት ነው ብዬ ማሰቤ አስደስቶኛል… ህብረሰሰቡም በቦንድ ግዢ በ8100 A የግድቡን ግንባታ ማገዝ አለበት፤ በ8100 A ደጋግሜ ከመላኬ የተነሣ ኧረ በቃህ ተብያለሁ /ሳቅ/ የቦንዷን ነገር ወደፊት አጠናክረን መቀጠል አለብን፡፡

Editor at Hatricksport

Facebook

ዮሴፍ ከፈለኝ

Editor at Hatricksport