በ20ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ሀድያ ሆሳዕናን ከሀዋሳ ከተማ አገናኝቶ ሀድያ ሆሳዕና 3 – 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ደረጃውን ማሻሻል ችሏል ።
ሀድያ ሆሳዕናዎች በ19ኛው ሳምንት አዳማ ከተማን በረቱበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን በማድረግ ሀብታሙ ታደሰን እና ሳምሶን ጥላሁንን በባዬ ገዛኸኝ እና በእያሱ ታምሩ ምትክ ያሰለፉ ሲሆን በሀዋሳ ከተማ በኩል ደግሞ በሳምንቱ ወልቂጤ ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ ግቅ ጠባቂውን መሀመድ ሙንታሪ በሌላኛው የግብ ዘብ ዳግም ተፈራ ምትክ አሰልፈዋል ።ፈጥን ባለ እንቅስቃሴ የተጀመረው ጨዋታ በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ በሚደረጉ ጥረቶች የጀመረ ሲሆን በአንፃራዊነት ሀድያ ሆሳዕናዎች ከሀዋሳ ከተማ በተሻለ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ችለው ነበር ።
በሁለቱ መስመሮች ማጥቃትን ታሳቢ አድርገው የገቡት ሀድያ ሆሳዕናዎች የሀዋሳ ከተማን የኋላ ክፍል ጫና ውሰጥ መክተትም ችለው ነበር ።
በ14ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ጥላሁን ከማዕዘን ያሻገረውን ኳስ ሀብታሙ ታደሰ በግንባር በመግጨት ሀድያ ሆሳዕና መሪ ያደረገ ግብ አስቆጥሯል ።ቀድመው ግብ ያስተናገዱት ሀዋሳ ከተማዎች መልስ ለመስጠት 6 ያህል ደቂቃዎች ብቻ ነበር የፈጀባቸው ። በ20ኛው ደቂቃ ላይ መሀመድ ሙንታሪ በረጅም ያሻገረውን ኳስ በብሩክ በየነ ግንባር ተገጭቶ የደረሰውን ተባረክ ሔፋሞ ኳሱን ተቆጣጥሮ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት አስደናቂ ግብ አስቆጥሯል ።
- ማሰታውቂያ -
ከግቡ በኋላ ሀዋሳ ከተማዎች የሀድያ ሆሳዕናን የመስመር ላይ እንቅስቃሴ በመግታት የሚያገኟቸውን ኳሶች በፈጣን ወደ ተጋጣሚያቸውን የግብ ክልል በመላክ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ።በ35ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ታደሰ ከሳምሶን ጥላሁን ጋር አንድ ሁለት ቅብብል አድርጎ በሳጥኑ የቀኝ አቅጣጫ ይዞ የገባውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮት በግብ ጠባቂው በመሀመድ ሙንታሪ ሲመለስ በቅርብ የነበረው ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን በድጋሚ ኳሱን ወደ ግብ መምታት ቢችልም መሀመድ ሙንታሪ በድጋሚ መልሶ የማዕዘን ምት አድርጎታል ።
ሀድያ ሆሳዕናዎች መልሰው ጨዋታውን በመቆጣጠር ወደ ሀዋሳ ከተማ የግብ ክልል መድረስ የቻሉባቸወን አጋጣሚዎች መፍጠር ቢችሉም አጋጣሚዎቹን ወደ ግብ ሙከራ ለመቀየር አልቻሉም ።
ዳዊት ታደሰ በ45ኛው ደቂቃ ላይ ከርቀት ወደ ግብ የመታው ኳስ የአጋማሹ የመጨረሻ የግብ ሙከራ ሆኖ በ1 – 1 ውጤት ሁለቱ ክለቦች ወደ ዕረፍት አምርተዋል ።የሁለተኛውን አጋማሽ በተሻለ እንቅስቃሴ የጀመሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች በ53ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችለዋል ። ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን ከሀብታሙ ታደሰ የደረሰውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ በመምታት በመሀመድ ሙንታሪ መረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል ።
ከግቡ በኋላም በቀጣዩቹ ደቂቃዎች ላይ ሀድያ ሆሳዕናዎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረቶችን ማድረጋቸውን የቀጠሉ ሲሆን ሀዋሳ ከተማዎች ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመመለስ በረጃጅም እና ተሻጋሪ ኳሰች ወደ ሀድያ ሆሳዕና የግብ ክልል ለመድረስ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል ።በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም በኩል የነበረው ሀይል የቀላቀለ አጨዋወት ከባባድ ጥፋቶችን ሲያስመለክተን ነበር።
የሀድያ ሆሳዕናን የመከላከል አጥር ሰብረው ለመግባት የተቸገሩት ሀዋሳ ከተማዎች በ71ኛው ደቂቃ ላይ በኤፍሬም አሻሞ አማካኝነት ንፁህ ግብ አስቆጥረው የነበረ ቢሆንም የመስመር ዳኛው ከጨዋታ ውጪ ብለው ሽረውታል ።
በ77ኛው ደቂቃ ላይ ካሎንጂ ሞንዲያ ለግብ ጠባቂው መሀመድ ሙንታሪ የመለሰለትን ኳስ ግብ ጠባቂው መቆጣጠር ባለመቻሉ ሀዋሳ ከተማ ሶስተኛ ግብ አስተናግዷል ።ሀዋሳ ከተማ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ በቁጥር በዛ ብለው በሀድያ ሆሳዕና የሜዳ ክፍል በመገኘት ግብ ለማግኘት ያደርጉት የነበረው ጥረት ከፊት መስመሩ የዕለቱ ድክመት ጋር ተዳምሮ የሚነጠቋቸው ኳሶት ለመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ አድርገዋቸው ነበር ።
በዚህም 85ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረየሱስ ተክለብርሃን በግራ መስመር ገብቶ ለብርሃኑ በቀለ ብርሀኑ ጥሩ ኳስ አድርሶት የነበረ ቢሆንም የብርሀኑ ኳስ ሀይል ስላልነበረው መሀመድ ሙንታሪ በቀላሉ ይዞታል ።በ90+3 ደቂቃ ላይ ባዬ ገዛኸኝ ከቀኝ መስመር በቀጥታ ወደ ግብ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው መልሶት የማዕዘን ምት ሆኗል ።
በመጨረሻም ጨዋታው በሀድያ ሆሳዕና 3 – 1 አሸናፊነት ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ሀድያ ሆሳዕና ነጥቡን 28 በማድረስ ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ሲል ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ በ34 ነጥብ 3ኛ ደረጃን መያዝ ችሏል ።በ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሀድያ ሆሳዕና በመጪው ሚያዝያ 24 ( ሰኞ ) ቀን 9 ሰዓት ጀምሮ አዲስ አበባ ከተማን ሲገጥም ሚያዝያ 22 ( ቅዳሜ ) አመሻሽ 12 ሰዓት ጀምሮ ሀዋሳ ከተማ ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጋር የሚጫወት ይሆናል ።