በ20ኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ውሎ ጨዋታዎች በቀዳሚነት የተደረገው የአርባምንጭ ከተማ እና የፋሲል ከነማ ጨዋታ በአፄዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል ።
አርባምንጭ ከተማዎች በ19ኛው ሳምንት ባህርዳር ከተማን በረቱበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን በማድረግ አሸናፊ ፊዳን እና ኤሪክ ካፓይቶን በሀቢብ ከማል እና ፍቃዱ መኮንን ምትክ ፋሲል ከተማዎች ደግሞ በሳምንቱ ከአዲስ አበባ ከተማ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አንድ ለውጥ ብቻ በማድረግ አስቻለው ታመነን በያሬድ ባየህ ምትክ ጨዋታውን እንዲጀምር አድርገዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ፋሲል ከነማዎች ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት ወደ ፊት ለመድረስ ጥረቶችን በማድረግ የጀመሩት ሲሆን በአርባምንጭ ከተማ በኩል ደግሞ ፋሲል ከተማዎች ኳስን ከኋላ መስርተው እንዳይወጡ ጫን ብለው የተጫወቱ ሲሆን በተጨማሪም አፄዎቹ አልፈው ወደ ሜዳ ክፍላቸው በሚገቡ ጊዜ ተረጋግተው ኳሱን እንዳይዙ በማድረግ የተሳካላቸው ነበሩ ።
በጨዋታው የነበረው የመጀመሪያ ሙከራ 6ኛው ደቂቃ ላይ በአርባምንጭ ከተማ በኩል የተደረገ ሲሆን ሙና በቀለ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ፀጋዬ አበራ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብ የላከውን ኳስ ሳማኪ ሚካኤል ግብ ከመሆን አድኖታል ።
- ማሰታውቂያ -
በአዞዎቹ የመከላከል እንቅስቃሴ በቀላሉ የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ የተቸገሩት አፄዎቹ የተጋጣሚያውን ተጫዋቾች ወደ ራሳቸው ሜዳ በሚመጠቡት ጊዜ ኳሶች በረጅም ለፊት መስመር ተጫዋቾቻቸው በማድረስ የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ቢጥሩም ቀላል አልሆነላቸውም ነበር ።ከውሀ እረፍት መልስ 28ኛው ደቂቃ ላይ ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ቀኝ ካደላ ቦታ ላይ በቀጥታ ከቅጣት ምት ወደ ግብ የመታውን አስደናቂ ኳስ የአርባምንጭ ከተማው ግብ ጠባቂ ሳምሶን አሰፋ በድንቅ ብቃት አድኖታል ።
በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ አርባምንጭ ከተማዎች ቀድሞ ከነበረው በተወሰነ ወደ ፊት ለመድረስ ጥረቶችን ማድረግ የቻሉ ቢሆንም ከፀጋዬ አበራ ሙከራ ውጪ ሳማኪን የፈተነ የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል ። የመጀመሪያው አጋማሽም በሁለቱም በኩል ግብ ሳይቆጠርበት ተጠናቋል ።
የሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በፋሲል ከነማ በኩልም ሆነ በአርባምንጭ ከተማ በኩል ቶሎ ግብ ለማስቆጠር ፍላጎት ያሳዩበትን እንቅስቃሴ በማድረግ የጀመሩት ነበር ። አፄዎቹ በመስመሮች በኩል ለመጠቀም ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን አዞዎቹ በረጃጅም ኳሶች ወደ ፋሲል ከተማ የግብ ክልል ለመድረስ ሲጥሩ ቆይተዋል ።
የአጋማሹ ቀዳሚ ኢላማውን የጠበቀ የግብ መከራ በ53ኛው ደቂቃ ላይ የመዘገበ ሲሆን ኤሪክ ካፓይቶ ከሳጥን ውጪ ኳሱን አየር ላይ እንዳለ በቮሊ ወደ ግብ የመታው ኳስ በሳማኪ ተመልሷል ።
62ኛው ደቂቃ ላይ የአፄዎቹን ደጋፊዎች ጮቤ ያስረገጠ ግብ ተቆጥሯል ። ሽመክት ጉግሳ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ በዛብህ መለዮ አግኝቶ ለበረከት ደስታ ካቀበለው በኋላ በረከት መልሶ አመቻችቶ የሰጠውን ኳስ ለሳምሶን አሰፋ ለመመለስ ከባድ በሆነ ሁኔታ አክርሮ ወደ ግብ በመምታት ፋሲል ከነማን መሪ ያደረገ ግብ አስቆጠረ ።
ከግቡ መቆጠር ሶስት ደቂቃዎች በኋላ ከግቡ በርቀት ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት ሱራፌል ዳኛቸው ሳይታሰብ በቀጥታ ወደ ግብ የመታው አስገራሚ ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትሞ ወጥቷል ።
አዞዎቹ ቀስ በቀስ የአቻነቱን ግብ ፍለጋ ሜዳቸውን ለቀው በመውጣት የፋሲል ከነማን ተከላካዮች ለመፈተን የቻለለ ቢሆንን የጠራ የግብ ዕድል በመፍጠሩ ረገድ ውጤታማ መሆን አልቻሉም ነበር ። በአፄዎቹ በኩል የአርባምንጭ ከተማ በተለይም ረጃጅም ኳሶች በሟቋረጥ ላይ እና ጨዋታውን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረቶችን ማድረግ ችለዋል ።
በተደጋጋሚ ሲሰሩ የነበሩ ጥፋቶች ዳኛው የፊሽካቸውን ድምፅ ቶሎ ቶሎ እንዲያሰሙና ካርዶችንም እንዲመዙ ያስገደዳቸው ነበር ።
85ኛው ደቂቃ ላይ ሀቢብ ከማል ከቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብ የመታው ኳስ ሳማኪን ማለፍ የቻለ አልነበረም ።
በመጨረሻም ጨዋታው በአፄዎቹ የ 1 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል ።ውጤቱን ተከትሎ አርባምንጭ ከተማ በ26 ነጥብ በነበረበት 7ኛ ደረጃ ላይ ለመቆየት የተገደደ ሲሆን ሲሆን ፋሲል ከተነማ ደግሞ ነጥቡን 34 በማድረስ ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ማለት ችሏል ።
በ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ሚያዝያ 23 ( ዕሁድ ) አርባምንጭ ከተማ ወልቂጤ ከተማን ሲገጥም በማግስቱ ሚያዝያ 24 ( ሰኞ ) ምሸት 12 ሰዓት ጀምሮ ፋሲል ከተማ ከወላይታ ድቻ ጋር የሚጫወት ይሆናል ።