*….ሀዋሳ ካሉት 16 ዳኞች 8ቱ ከአዲስ አበባ መሆኑ
አነጋጋሪ ሆኗል….
*…… ድሬዳዋ ከነበሩት ዳኞች መሃል ሀዋሳ ያለው አንድ
ዳኛ ብቻ መሆኑም ትኩረት የሳበ ሆኟል…
*…… የሻሸመኔና የወልቂጤ ከተማ ቀሪ ጨዋታዎች
ትኩረት ይሰጠውም እየተባለ ነው…
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ያዋቀረው አዲሱ የብሄራዊ ዳኞች ኮሚቴ የዳኝነት ምደባ ላይ ጥያቄ እየተነሳ ነው።
በ23ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወሳኝ ጨዋታ የኢትዮጵያ ቡናና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ 2ለ2 በሆነ አቻ ውጤት ሲጠናቀቅ የተፈጠሩት የዳኝነት ስህተቶች ትኩረት ስቧል።
በጨዋታው ሳይመን ፒተር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሁለቱን ግቦች ሲያስቆጥር አማኑኤል ዮሀንስና የባንኩ ፈቱዱን ጀማል ራሱ ላይ ባስቆጠረው ግብ 2ለ2 ተለያይተዋል። ጨዋታውን ኢንተርናሽናል አርቢትር ማኑኤ ወ/ጻዲቅ ሲመራው ረዳቶቹ ኢንተርናሽያል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝና ፌዴራል ረዳት ዳኛ አማን ሞላ አራተኛ ዳኛ ፌዴራል ዳኛ ዮናስ ካሳሁን ሲሆኑ ኮሚሽነሩ ኮሚሽነር በላቸው ይታየው መሆናቸው ታውቋል።
- ማሰታውቂያ -
በጨዋታው ላይ ሁለቱም ቡድኖች በዳኝነት ውሳኔዎች የተበደሉ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና በአንተነህ አማካይት ያስቆጠረው ግብ ኦፍሳይድ ተብሎ ሲሻር የፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በእጅ የተነካ ኳስ ከፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውጪ ነው ተብሎ ቅጣት ምት መደረጉ የባንኩ ግብ ጠባቂ ፍሬው የቡናው አጥቂን በቦክስ የመታበትና ፍጹም ቅጣት ምት የተከለከለበት ውጤት ለዋጭ ስህተት የታየ ሲሆን በጭማሪ ሰአት ላይ የተቆጠረችውና ኢትዮጵያ ቡናን አቻ ያደረገችው የአንተነህ ግብ መስመሩን አላለፈችም ግቧ ልክ አይደለችም በሚል ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች አስተያየት ሰጥተውበታል። በዚህ ጨዋታ የጨዋታው ኮሚሽነር በላቸው ይታየው የሚያቀርበው ሪፖርት አጓጊ ሆኗል። በህጉ መሰረት ኮሚሽነሩ ተገቢ ሪፖርት ካቀረበ ዴኞቹ ላይ ርምጃ የሚወሰድ ሲሆን ሪፖርቱ በሰላም አልቋል የሚልና ከ8 ነጥብ በላይ ለዳኞቹ መሰጠቱን ካሳየ ደግሞ የውድድር ክፍሉ ኮሚሽነሩ ላይ የሚያስተላልፈው የቅጣት ሪፖርት ይጠበቃል። በዝምታ የሚታለፍ ከሆነ ደግሞ አወዳዳሪው አካል ላይ የፍትህ ማጓደል ጣት የሚቀሰር ይሆናል።
ከዚሁ ከዳኝነት ምደባ ጋር ተያይዞ በቀድሞ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሸዋንግዛው ተባባል የሚመራው የዳኞች ኮሚቴ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያደርግበት ወሳኝ ጊዜ ነው በሚል ባለሙያዎች እያሳሰቡ ነው። ለ23ኛ እና 24ኛ ሳምንት ጨዋታ ተመርጠው ወደ ሀዋሳ የተጓዙት ዳኞች 16 ሲሆኑ ከ16ቱ 8ቱ የአዲስ አበባ ዳኞች መሆናቸው ቅሬታ ፈጥሯል። በተለይ በተሰናበተው ኮሚቴ ተመርጠው በድሬዳዋ ከነበሩ ኢንተርናሽናል ዳኞች መሃል ሀዋሳ የተገኘው ኢንተርናሽናል አርቢትር በአምላክ ተሰማ ብቻ መሆኑ አዲሱን ኮሚቴ ምነካው አስብሏል።
ሊጉ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ እየተሻገረ ባለበት ለዋንጫና ላለለመውረድ የሚደረጉ ትግሎች የሁሉን የሰፖርት ቤተሰብ ልብ ወጥሮ በሚይዝበት በዚህ ወቅት ጥራትና ብቃት እንጂ ኮታና ማዳረስ የሚመስሉ የዳኞች ምደባ ላይ ጥያቄ የተነሳ ሲሆን ክለቦችም ቅሬታ እያሰሙ ነው በቅርብ ጊዜ ውስጥ ጠንክሮ የተሰማውን የመቻልን ጥያቄ ለአብነት ይጠቀሳል።
የኢትዮጵያ ቡናና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨዋታ በረዳትነት የመራው ይበቃል ደሳለኝ ከ3 ወራት ቅጣት በኋላ ምንም ጨዋታ ሳያጫውት የማች ፊትነሱ ሳይመለስ መመደቡ ኮሚቴው ዳኛውን አልተከላከለም አስበልቶታል ሲሉ የሙያ ባልደረቦቹ ቅሬታ ያሰማሉ። ኢንተርናሽናል አርቢትሮቹና አቅማቸውን ያስመሰከሩ ፌዴራል ዳኞችን በሙሉ ጤንነት ላይ እያሁ እነሱን ዘልለው አዲስ ዳኞችን መርጦ መውሰዱ የኮታና የማዳረስ ውሳኔ ነው እንዴ ሲሉ ስጋታቸውን የሚገልጹ ተበራክዋል።
በየክልሉ ያሉ ኢንተርናሽናል እና አቅማቸውን ያሳዩ ፌዴራል አርቢትሮች እያሉ አሳማኝ ባልሆነ መንገድ ካጫወቱ የቆዩ ዳኞች ከአዲስ አበባ ብቻ ተመርጧል ሲሉ ቅሬታቸውን የሚያሰሙ ዳኞች ብቅ እያሉም ነው። የእግርኳሱ ባለሙያዎች አዲሱ የዳኞች ኮሚቴን በቀጣይ ጨዋታ ላይ ጥንቃቄ እንዲወስድ ጠይቀዋል።
በተለይ ለዋንጫ እየተደረገ ባለው ፍልሚያና ላለመውረድ በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ በዳኝነት ስህተት የክለቦቹና የተጨዋቾቻቸው ልፋት ከንቱ እንዳይቀር ምደባው ላይ ጥንቃቄ እንዲደረግ ጠይቀዋል። ላለመውረድ እየተደረጀ ባለው ፍልሚያ 16ኛ ደረጃ ላይ ያለው አምበሪቾ ዱራሜ ከ14ኛው ክለብ ጋር ያለው የነጥብ ርቀት እየጨመረ መምጣቱና 17 ጊዜ የተሸነፈ ብቸኛ ክለብ በመሆኑ የመውረዱ ነገር ብዙዎችን ያስማማ ይመስላል። ነገር ግን በሻሸመኔ ከተማና በወልቂጤ ከተማ መሃል ሁለተኛ ወራጅ ክለብ ላለመሆን በሚደረገው ፍልሚያ ላይ የተሻለ የዳኝነት አፈጻጸም ያላቸው አርቢትሮች እንዲመደቡ ጠይቀዋል። ዳኝነቱ ካልተስተካከለ ሂደቱ ወደሌላ አቅጣጫ እንዳይወሰድ ያሰጋል የሚለው የስፖርት ቤተሰቡ ኮሚቴው በማንም ወገን እጁ ሳይጠመዘዝ በታማኝነት ውድድሩን እንዲመሩ ጠይቀዋል።